በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እጃችሁን አጽኑ

እጃችሁን አጽኑ

እጃችሁን አጽኑ

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅ የሚለው ቃል ከ1, 800 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። ከእጅ ጋር የተያያዙ በርካታ ፈሊጣዊ አነጋገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ንጹሕ እጅ ክፋት አለመሥራትን ያመለክታል። (2 ሳሙኤል 22:​21፤ መዝሙር 24:​3, 4) እጅ መክፈት ለሌሎች ልግስና ማሳየት ማለት ነው። (ዘዳግም 15:​11፤ መዝሙር 145:​16) ሕይወቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሰው ነፍሱን በእጁ እንደጣለ ተደርጎ ይገለጻል። (1 ሳሙኤል 19:​5) እጅን ማላላት ተስፋ መቁረጥን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (2 ዜና መዋዕል 15:​7) እንዲሁም እጅን ማጽናት በአጭር ታጥቆ ለሥራ መነሳትን ያመለክታል።​—⁠1 ሳሙኤል 23:​16

በዛሬው ጊዜ እጃችንን ማጽናታችን አጣዳፊ ጉዳይ ነው። የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲሰማን የያዝነውን እርግፍ አድርገን መተው ወይም እጃችንን ማላላት ይቀናናል። ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲያቋርጡ፣ ባሎች ቤተሰባቸውን፣ እናቶች ደግሞ ልጆቻቸውን ጥለው ሲሄዱ መመልከት የተለመደ ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት መወጣት እንድንችል እጃችንን ማጽናት ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:​13) እንዲህ በማድረግ የይሖዋን ልብ እናስደስታለን።​—⁠ምሳሌ 27:​11

እጃችንን ማጽናት የምንችልበት መንገድ

በዕዝራ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ አድሰው ለመጨረስ እጃቸውን ማጽናት አስፈልጓቸው ነበር። እንዲህ ማድረግ የቻሉት እንዴት ነበር? ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፣ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።” (ዕዝራ 6:22) ይሖዋ ሕዝቦቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ‘የአሦር ንጉሥ’ እንዲፈቅድላቸው ያነሳሳውና የጀመሩትን ሥራ ማጠናቀቅ እንዲችሉ ውስጣዊ ግፊት ያሳደረባቸው በመንፈሱ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ከጊዜ በኋላ የኢየሩሳሌም ግንብ መጠገን ባስፈለገው ጊዜ ነህምያ ወንድሞቹ ለሥራው እንዲንቀሳቀሱ እጃቸውን አጽንቷል። እንዲህ የሚል እናነብባለን:- “የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነች፣ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም:- እንነሣና እንሥራ አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ።” ነህምያና አይሁዳውያን ወገኖቹ እጃቸውን አበርትተው የኢየሩሳሌምን ግንብ በ52 ቀናት ውስጥ አድሰው ጨረሱ!​—⁠ነህምያ 2:18፤ 6:9, 15

በተመሳሳይም ይሖዋ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ እንድንችል እጃችንን ያበረታልናል። (ማቴዎስ 24:​14) ይህንንም የሚያደርገው ‘ፈቃዱን እንድናደርግ በመልካም ነገር ሁሉ በማስታጠቅ ነው።’ (ዕብራውያን 13:​21 አ.መ.ት ) ከሁሉ የላቀ ጥራት ያላቸውን መሣሪያዎች ሰጥቶናል። በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን ለሰዎች ለማዳረስ የሚረዱን መጽሐፍ ቅዱስ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ብሮሹሮች፣ ትራክቶች እንዲሁም የቴፕና የቪዲዮ ክሮች አሉን። እንዲያውም ጽሑፎቻችን ከ380 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ በእነዚህ ግሩም መሣሪያዎች ተጠቅመን አገልግሎታችንን መፈጸም እንድንችል በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች አማካኝነት መለኮታዊ ትምህርትና ሥልጠና ይሰጠናል።

ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች እጃችንን የሚያጸናልን ቢሆንም እንኳ እኛም የበኩላችንን ጥረት እንድናደርግ ይጠብቅብናል። ከሶርያውያን ወራሪዎች ጋር የሚያደርገውን ውጊያ በተመለከተ እርዳታ ለመጠየቅ ለመጣው ለንጉሥ ዮአስ ነቢዩ ኤልሳዕ ምን እንዳለው አስታውስ። ኤልሳዕ ፍላጻዎችን ወስዶ ምድሩን እንዲመታ ለንጉሡ ነገረው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ። የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ:- አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ አለ።” (2 ነገሥት 13:18, 19) ዮአስ በቂ ቅንዓት ሳያሳይ በመቅረቱ ከሶርያውያን ጋር በሚያደርገው ውጊያ የሚያገኘው ድል የተሟላ አይሆንም።

ይሖዋ እንድንሠራው የሰጠንን ሥራ ዳር ማድረስ ከፈለግን ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት በእኛም ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። ከፊታችን ስለተደቀኑብን መሰናክሎች ወይም የተሰጠን ሥራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እያሰቡ ከመጨነቅ ይልቅ ሥራችንን በቅንዓትና በሙሉ ልብ ማከናወን ይኖርብናል። እጃችንን ማጽናትና እርዳታ ለማግኘት በይሖዋ መታመን ይኖርብናል።​—⁠ኢሳይያስ 35:​3, 4

ይሖዋ እጃችንን ያጸናልናል

ይሖዋ ፈቃዱን መፈጸም እንድንችል እኛን ከመርዳትና እጃችንን ከማጽናት ወደኋላ አይልም። እርግጥ ነው፣ አምላክ በተአምር ሁሉንም ነገር ያደርግልናል ማለት አይደለም። የራሳችንን ድርሻ እንድንወጣ ይጠብቅብናል። ይህም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንድናነብ፣ አዘውትረን ለስብሰባዎች እንድንዘጋጅና እዚያም እንድንገኝ፣ በተቻለ መጠን በአገልግሎት አዘውትረን እንድንሳተፍና ሳናቋርጥ ወደ እሱ እንድንጸልይ ይፈልግብናል። አጋጣሚው እያለን በታማኝነትና በትጋት ድርሻችንን ከተወጣን ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር ማድረግ እንድንችል ብርታት ይሰጠናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​13

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሚስቱንና እናቱን በሞት ያጣውን የአንድ ክርስቲያን ሁኔታ ተመልከት። ገና ከሐዘኑ ሳያገግም ምራቱ ባሏንና የክርስትናን ጎዳና ጥላ ሄደች። ይህ ወንድም “የሚደርስብን የፈተና ዓይነት፣ ጊዜውም ሆነ ብዛቱ በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ አለመሆኑን ተምሬአለሁ” ሲል ተናግሯል። ወደፊት መጓዙን እንዲቀጥል ብርታት ያገኘው እንዴት ነው? “ጸሎትና የግል ጥናት ፈተናዎቹን መወጣት እንድችል ረድተውኛል። እንዲሁም መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ የሰጡኝ ድጋፍ ከፍተኛ ማጽናኛ ሆኖልኛል። ከሁሉም በላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከመከሰታቸው በፊት ከይሖዋ ጋር ጥሩ የግል ዝምድና መመሥረት ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ።”

በሕይወታችን ላይ ምንም ዓይነት ሁኔታዎች ያጋጥሙን ትምክህታችንን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ለመጣልና እጃችንን ለማጽናት ባዘጋጃቸው መሣሪያዎች በጥሩ ሁኔታ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ከሁሉ የላቀ ጥራት ያለው አገልግሎት ለይሖዋ ማቅረብ የምንችል ከመሆኑም በላይ ለውድ ስሙ ውዳሴና ክብር እናመጣለን።​—⁠ዕብራውያን 13:​15

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮአስ ከፍተኛ ቅንዓት ሳያሳይ በመቅረቱ ከሶርያ ጋር ባደርገው ውጊያ የተሟላ ድል አላገኘም