ከምንጊዜውም የተሻለ ዘመን
ከምንጊዜውም የተሻለ ዘመን
ከባድና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙህ “የድሮውን ደግ ዘመን” ትናፍቃለህ? የምትናፍቅ ከሆነ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ልብ በል:- “ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።”—መክብብ 7:10
ሰሎሞን ይህን ምክር የሰጠው ለምን ነበር? ምክንያቱም ስላለፈው ዘመን ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ አሁን የገጠሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት እንደሚረዳ ስለሚያውቅ ነው። ምናለ “ደጉ ዘመን” ተመልሶ ቢመጣ የሚሉ ሰዎች በዚያን ጊዜም ቢሆን ችግሮች እንደነበሩና ሕይወት ሙሉ በሙሉ ከችግር ነጻ ሆኖ እንደማያውቅ ይዘነጋሉ። በድሮ ጊዜ አንዳንድ ነገሮች ከአሁኑ የተሻሉ ሊሆኑ ቢችሉም እንደ አሁኑ ጊዜ ሁሉ ያኔም አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደነበሩ አያጠያይቅም። ሰሎሞን እንደተናገረው ስላለፈው ዘመን ጥሩነት እያሰቡ መቆዘም ጥበብ አይሆንም፤ ምክንያቱም ያለፈውን ዘመን እንደገና መመለስ እንደማንችል የታወቀ ነው።
የድሮውን ዘመን ከልክ በላይ መናፈቅ በራሱ ጉዳት ሊኖረው ይችላል? አዎን፣ ከምንኖርበት ጊዜ ጋር ራሳችንን አስማምተን እንዳንኖር ወይም በጊዜያችን ላሉት አንዳንድ መልካም ሁኔታዎችና ወደፊት ለምናገኘው ተስፋ አድናቆት እንዳይኖረን የሚያደርገን ከሆነ ጉዳት አለው።
የዓለማችን ችግሮች እየተባባሱ የሚሄዱ ቢሆንም እንኳ ይህ የምንኖርበት ዘመን ከምንጊዜውም የተሻለ ነው። ለምን? ምክንያቱም አምላክ ምድርንና የመንግሥቱ ሰላማዊ አገዛዝ የሚያመጣቸውን በረከቶች በተመለከተ የገባው ተስፋ ፍጻሜውን ወደሚያገኝበት ጊዜ ይበልጥ እየተቃረብን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (ራእይ 21:4) በዚያን ጊዜ ሁኔታዎች ከአሁኑ በእጅጉ የተሻሉ ስለሚሆኑ “ደጉን ዘመን” የምንናፍቅበት ምንም ምክንያት አይኖርም።