ከአቅም በላይ የሚደረግ መዋጮ
ከአቅም በላይ የሚደረግ መዋጮ
“ለማኝ ትሉኝ ይሆናል፣ ሆኖም የምለምነው ለኢየሱስ ስለሆነ ቅር አልሰኝም።” አንድ የፕሮቴስታንት አገልጋይ የተናገሯቸው እነዚህ ቃላት ሃይማኖታዊ መዋጮን በተመለከተ እየተካሄደ ያለውን ውዝግብ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። በድርጅት መልክ የተዋቀሩ ሃይማኖቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ካላገኙ በቀር መንቀሳቀስ የሚችሉ አይመስልም። ለቀሳውስቱ ደመወዝ፣ ለቤተ መቅደሶች ግንባታና እድሳት እንዲሁም የወንጌል ዘመቻዎችን ለማካሄድ ገንዘብ ያስፈልጋል። ገንዘቡ የሚገኘው እንዴት ነው?
አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት በአሥራት መልክ ከሚሰበሰበው መዋጮ ነው። a ኖርማን ሮበርትሰን የተባሉት ወንጌላዊ እንዲህ ብለዋል:- “አምላክ ለምድራዊ መንግሥቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው በአሥራት አማካኝነት ነው። አሥራት ወንጌሉ እንዲሰበክ ለማድረግ አምላክ ያቋቋመው ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ነው።” እኚሁ ወንጌላዊ ተከታዮቻቸው የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲገልጹ እንዲህ በማለት አጥብቀው አሳስበዋቸዋል:- ‘አሥራት የምታወጡት አቅማችሁ ስለፈቀደላችሁ ብቻ መሆን የለበትም። ይህ ታዛዥ መሆናችሁን የምታሳዩበት ድርጊት ነው። አሥራት አለማውጣት የአምላክን ሕግ በቀጥታ እንደማፍረስና እንደማጭበርበር ይቆጠራል።’—ታይቲንግ —ጎድስ ፋይናንሻል ፕላን
መዋጮ ማድረግ የክርስትና አምልኮ ክፍል መሆን እንዳለበት ሳትስማማ አትቀርም። ሆኖም መዋጮ እንድታደርግ በተደጋጋሚ የሚደረግ ውትወታ የሚረብሽና ምናልባትም የሚያስመርር ሆኖብሃልን? ኢናስዩ ስትሪደ የተባሉት ብራዚላዊ የሃይማኖት ምሁር አብያተ ክርስቲያናት “የሃይማኖት ተቋሞቻቸው የገጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት” አሥራት መሰብሰብን እንደ አማራጭ አድርገው መውሰዳቸውን ያወገዙ ሲሆን እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት “ሕገ ወጥ፣ አግባብነት የጎደለው እንዲሁም ሃይማኖታዊ ቅሌት” ሲሉ ጠርተውታል። ይህ ሁኔታ የሚያስከትለውን ውጤት ሲናገሩም “ሥራ የሌላቸው ሰዎች፣ መበለቶች፣ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታ የሚጎድላቸው ሰዎች አምላክ እንደተዋቸውና ቤተሰቦቻቸውን አስርበውም ቢሆን ‘ለሰባኪው’ ከፍተኛ መዋጮ ማድረግ እንዳለባቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል” ብለዋል።
‘ምእመናኖቻቸው አሥራት እንዲያወጡ የሚያስገድዱ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳን ጽሑፎችን በትክክል ተግባራዊ እያደረጉ ነውን? ወይስ አንዳንድ ሃይማኖቶች አምላካዊ ቁጣ ይደርስባችኋል የሚል ማስፈራሪያ በመጠቀም መንጋውን እየበዘበዙ ነው? በእርግጥ አምላክ ከአቅማችን በላይ መዋጮ እንድናደርግ ይጠብቅብናልን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አሥራት የአንድ ሰው ጠቅላላ ገቢ አንድ አሥረኛ ነው።