በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስታ የሚያስገኝ ልግስና

ደስታ የሚያስገኝ ልግስና

ደስታ የሚያስገኝ ልግስና

በሰሜን ምሥራቅ ብራዚል በአንድ የድሆች መንደር ውስጥ የሚኖረው ዠኒቫው፣ ሚስቱንና ልጆቹን የሚያስተዳድረው የሆስፒታል የጥበቃ ሠራተኛ ሆኖ በሚያገኛት ከእጅ ወደ አፍ የሆነች ገቢ ነው። ዠኒቫው የራሱ ችግሮች ቢኖሩበትም አለማቋረጥ አሥራት ያወጣ ነበር። “አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቤ ይራብ ነበር። ሆኖም ማንኛውንም መሥዋዕት ከፍዬም ቢሆን ለአምላክ ከሁሉ የተሻለውን ለመስጠት ጥረት አደርግ ነበር” በማለት ያስታውሳል።

ዠኒቫው ከሥራ ከተባረረ በኋላም አሥራት ማውጣቱን አላቋረጠም። የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ ከፍ ያለ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ አምላክን እንዲፈትነው ይገፋፋው ነበር። እንደዚህ ካደረገ አምላክ ያለምንም ጥርጥር በረከቱን እንደሚያፈስስለት ነገረው። በመሆኑም ዠኒቫው ቤቱን ለመሸጥና ከዚያ የሚያገኘውን ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያኑ ለመስጠት ወሰነ።

ብዙ ቅን ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ልግስና ያደርጋሉ። አብያተ ክርስቲያናት አሥራት ማውጣት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ እንደሆነ ስለሚያስተምሩ በጣም ደሃ የሆኑ ብዙ ሰዎች በታዛዥነት አሥራት ያወጣሉ። በእርግጥ አሥራት ማውጣት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ነውን?

የሙሴ ሕግና አሥራት ማውጣት

ከ3, 500 ዓመታት በፊት ይሖዋ አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር 12 ነገዶች የሰጣቸው ሕግ አሥራት ማውጣትንም ይጨምር ነበር። ሕጉ ከምድሩ ምርትና ከዛፎቹ ፍሬ እንዲሁም ከመንጋው አሥራት እንዲያወጡና በመገናኛው ድንኳን ለሚያገለግሉት ሌዋውያን እንዲሰጧቸው ያዝዝ ነበር።​—⁠ዘሌዋውያን 27:30, 32፤ ዘኍልቁ 18:21, 24

ይሖዋ ሕጉ ‘ከባድ እንደማይሆንባቸው’ ለእስራኤላውያን ነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 30:11) አሥራት ማውጣትን ጨምሮ ትእዛዛቱን በታማኝነት እስከጠበቁ ድረስ የተትረፈረፈ ምርት እንደሚሰጣቸውም ቃል ገብቶላቸው ነበር። ከዚህም በላይ ለመጠባበቂያ ተብሎ በየዓመቱ የሚሰበሰብ ተጨማሪ አሥራት የነበረ ሲሆን ይህንንም ብሔሩ ለሃይማኖታዊ በዓላት አንድ ላይ በሚሰበሰብበት ጊዜ ይጠቀሙበት ነበር። ‘መጻተኛው፣ ድሀ አደጉና መበለቷም’ በዚህ ዝግጅት በመጠቀም መብላትና መጥገብ ይችሉ ነበር።​—⁠ዘዳግም 14:28, 29፤ 28:1, 2, 11-14

ሕጉ አሥራት አለማውጣት የሚያስከትለውን ቅጣት ባይገልጽም እያንዳንዱ እስራኤላዊ እውነተኛውን አምልኮ በዚህ መንገድ የመደገፍ ሥነ ምግባራዊ ግዴታ ነበረበት። እንዲያውም ይሖዋ በሚልክያስ ዘመን አሥራት የማውጣት ግዴታቸውን ቸል ያሉትን እስራኤላውያን ‘በአሥራትና በበኩራት ሰረቃችሁኝ’ በማለት ወቅሷቸዋል። (ሚልክያስ 3:8) አሥራት የማያወጡ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ወቀሳ ሊሰነዘርባቸው ይችላልን?

እስኪ ጉዳዩን በጥሞና ለመመርመር እንሞክር። አብዛኛውን ጊዜ የአንድ አገር ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑት በዚያው አገር ውስጥ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በብሪታንያ አሽከርካሪዎች በግራ በኩል እንዲያሽከረክሩ የሚያዝዘው ሕግ ፈረንሳይ ውስጥ ባሉ አሽከርካሪዎች ላይ አይሠራም። በተመሳሳይም አሥራት እንዲወጣ የሚያዝዘው ሕግ አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር ብቻ የገባው ልዩ ቃል ኪዳን ክፍል ነው። (ዘጸአት 19:3-8፤ መዝሙር 147:19, 20) በመሆኑም ለዚያ ሕግ ተገዢ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው እስራኤላውያን ብቻ ነበሩ።

ከዚህም በላይ አምላክ የማይለወጥ መሆኑ እሙን ቢሆንም ሕግጋቱ ግን አንዳንድ ጊዜ ሊለወጡ ይችላሉ። (ሚልክያስ 3:6) መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገረው ኢየሱስ በ33 እዘአ መሥዋዕታዊ ሞት ሲሞት ‘አሥራት የማውጣትን ትእዛዝ’ ጨምሮ ሕጉን ‘ደምስሶታል’ ወይም ‘አስወግዶታል።’​—⁠ቆላስይስ 2:13, 14፤ ኤፌሶን 2:13-15፤ ዕብራውያን 7:5, 18

ክርስቲያናዊ ልግስና

ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ ቢሆን እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ መዋጮ ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ ምስክሮቹ’ እንዲሆኑ ትልቅ ተልዕኮ ሰጥቷቸው ነበር። (ሥራ 1:8) የአማኞች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን ጉባኤዎችን የሚጎበኙና የሚያበረታቱ ተጨማሪ ክርስቲያን አስተማሪዎችና የበላይ ተመልካቾችም አስፈለጉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መበለቶች፣ ወላጆች የሌሏቸው ልጆችና ሌሎች የተቸገሩ ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን ወጪዎች የሚሸፍኑት እንዴት ነበር?

በ55 እዘአ ገደማ በአውሮፓና በትንሿ እስያ የሚገኙ ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች በይሁዳ ያለው ጉባኤ ችግር ላይ በመውደቁ እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ለቅዱሳን የተደረገው ይህ መዋጮ’ እንዴት እንደ ተሰበሰበ ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 16:1) ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ልግስናን በተመለከተ የሰጠውን ሐሳብ ስትመለከት ትገረም ይሆናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልደረቦቹን በመደለል መዋጮ እንዲያደርጉ ለማነሳሳት አልሞከረም። እንዲያውም “መከራ” እና ‘ከፍተኛ ድህነት’ የነበረባቸው የመቄዶንያ ክርስቲያኖች ‘ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት ለማድረግ በብዙ ልመና ጳውሎስን መለመን’ አስፈልጓቸው ነበር።​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:1-4

እውነት ነው፣ ጳውሎስ ይበልጥ ባለጸጋ የሆኑት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጋስ የሆኑትን የመቄዶንያ ወንድሞቻቸውን ምሳሌ እንዲኮርጁ አበረታቷቸዋል። ያም ሆኖ ግን አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳለው ‘ትእዛዝ ከማውጣት ይልቅ ጥያቄ ወይም ሐሳብ ማቅረብ፣ ማበረታታት ወይም ልመና ማቅረብ መርጧል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መዋጮ እንዲያደርጉ ተገድደው ቢሆን ኖሮ ከልባቸው ተነሳስተው በፈቃደኝነት መንፈስ አይሰጡም ነበር።’ ጳውሎስ ‘እግዚአብሔር የሚወደው በደስታ’ እንጂ “በኀዘን ወይም በግድ” የሚሰጠውን እንዳልሆነ ያውቅ ነበር።​—⁠2 ቆሮንቶስ 9:7

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የነበራቸው እምነትና እውቀት ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ካላቸው እውነተኛ ፍቅር ጋር ተዳምሮ ከልባቸው እንዲሰጡ ሊገፋፋቸው ይገባ ነበር።​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:7, 8

“በልቡ እንዳሰበ”

ጳውሎስ የተወሰነ መጠን ያለው መዋጮ እንዲያደርጉ ከመደንገግ ይልቅ “ከእናንተ እያንዳንዱ እንደ ገቢው መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን [“የተወሰነ ገንዘብ፣” NIV ] እየለየ ያስቀምጥ” የሚል ሐሳብ አቅርቦላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:2 አ.መ.ት ) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እቅድ በማውጣት የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየጊዜው ካስቀመጡ ጳውሎስ ሲመጣ ቅር እያላቸው ወይም በስሜታዊነት ተገፋፍተው ለመስጠት አይገደዱም። እያንዳንዱ ክርስቲያን ምን ያህል እንደሚሰጥ የሚወስነው ራሱ በመሆኑ የሚሰጠው “በልቡ እንዳሰበ” ነበር።​—⁠2 ቆሮንቶስ 9:5, 7

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በበረከት ለማጨድ በበረከት መዝራት ነበረባቸው። ከአቅማቸው በላይ የሆነ መዋጮ እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ምክር ተሰጥቷቸው አያውቅም። ጳውሎስ ‘ለእናንተም መከራ እንዲሆን ብዬ አይደለም’ ብሏቸዋል። ልግስና “እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 8:12, 13፤ 9:6) ሐዋርያው ቆየት ብሎ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ነገር ግን . . . ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ጳውሎስ ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት የሚጻረር መዋጮ እንዲደረግ አላበረታታም።

ጳውሎስ በበላይነት ያስተባበረው ተቸግረው ለነበሩ ‘ቅዱሳን የሚደረገውን መዋጮ’ እንደሆነ ልብ  ማለት ያስፈልጋል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጳውሎስም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት ለሚያከናውኑት አገልግሎት የሚውል የገንዘብ መዋጮ እንዳሰባሰቡ ወይም አሥራት እንደተቀበሉ የሚናገር ሐሳብ አናገኝም። (ሥራ 3:6) ጳውሎስ ጉባኤዎች የላኩለትን ስጦታ በአመስጋኝነት ይቀበል የነበረ ቢሆንም በወንድሞቹ ላይ “ሸክም” ከመሆን ተቆጥቧል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:9 አ.መ.ት ፤ ፊልጵስዩስ 4:15-18

ዛሬ በፈቃደኝነት የሚደረግ ልግስና

በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች አሥራት ከማውጣት ይልቅ በፈቃደኝነት ልግስና ያደርጉ ነበር። ዛሬም ይህ አሠራር የምሥራቹን ስብከት ለመደገፍና የተቸገሩ ክርስቲያኖችን ለመርዳት ያስችል እንደሆነ ለማወቅ ትፈልግ ይሆናል።

በ1879 የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ‘ሰዎች እርዳታ እንዲሰጧቸው ፈጽሞ እንደማይለምኑ’ በግልጽ ተናግረው ነበር። ይህ ውሳኔ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማሰራጨት የሚያደርጉትን ጥረት አደናቅፎባቸው ይሆን?

የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ወቅት በ235 አገሮች መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ ክርስቲያናዊ መጽሐፎችንና ሌሎች ጽሑፎችን ያሰራጫሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የሚሰጠው መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት በመጀመሪያ መታተም ሲጀምር በአንድ ቋንቋና በ6,000 ቅጂዎች የሚዘጋጅ ወርሃዊ መጽሔት ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ይህ መጽሔት በወር ሁለት ጊዜ ከ24, 000, 000 በሚበልጡ ቅጂዎችና በ146 ቋንቋዎች ይታተማል። ምሥክሮቹ በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑትን መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ ለማደራጀት በ110 አገሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ገንብተዋል ወይም ለቅርንጫፍ ቢሮ የሚሆኑ ሕንፃዎችን ገዝተዋል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለመማር የሚፈልጉ ሰዎችን ለማስተናገድ በየአካባቢው በሺዎች የሚቆጠሩ የመሰብሰቢያ ቦታዎችንና ትላልቅ የስብሰባ አዳራሾችን ገንብተዋል።

የሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች የእምነት አጋሮቻቸውን ሰብዓዊ ፍላጎትም ቸል አይሉም። ወንድሞቻቸው በጦርነት፣ በምድር መናወጥ፣ በድርቅ ወይም በአውሎ ንፋስ ምክንያት ችግር ላይ ሲወድቁ የሕክምና ቁሳቁሶች፣ ምግብ፣ ልብስና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን በማቅረብ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣሉ። እነዚህ ወጪዎች የሚሸፈኑት ግለሰብ ክርስቲያኖችና ጉባኤዎች በፈቃደኝነት በሚያደርጉት ልግስና ነው።

በፈቃደኝነት የሚደረግ ልግስና ውጤታማ ከመሆኑም በላይ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው እንደ ዠኒቫው ላሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ሸክሙን ያቀልላቸዋል። የሚያስደስተው ዠኒቫው ቤቱን ከመሸጡ በፊት ማሪያ የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወደ ቤቱ ትሄዳለች። ዠኒቫው “ከእርስዋ ጋር ያደረግሁት ውይይት ቤተሰቤን ከብዙ ችግሮች ጠብቆታል” በማለት ተናግሯል።

ዠኒቫው የጌታ ሥራ በአሥራት ላይ የተመካ እንዳልሆነ ተገነዘበ። እንዲያውም ክርስቲያኖች አሥራት የማውጣት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ እንደሌለባቸው ከዚህ ይልቅ የአቅማቸውን ያህል በልግስና ቢሰጡ እንደሚባረኩ ተረዳ።

ዠኒቫው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ልግስና ማድረጉ እውነተኛ ደስታ አስገኝቶለታል። እንዲህ በማለት ደስታውን ይገልጻል:- “የምሰጠው 10 በመቶ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ሆኖም በማደርገው መዋጮ ደስተኛ ነኝ፤ ይሖዋም እንደሚደሰት እርግጠኛ ነኝ።”

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የቀድሞዎቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አሥራት ማውጣት እንደሚያስፈልግ አስተምረዋልን?

“በመካከላችን ያሉት ባለጸጋዎች የተቸገሩትን ይረዷቸዋል። . . . ባለጸጋ የሆኑት በፈቃደኝነት ያሰቡትን ያህል ይሰጣሉ።”​—በሰማዕቱ ጀስቲን የተዘጋጀው ዘ ፈርስት አፖሎጂ፣ 150 እዘአ ገደማ

“አይሁዳውያን የንብረቶቻቸው አንድ አሥረኛ ለአምላክ የተወሰነ ነበር፤ ነጻ የወጡት ክርስቲያኖች ግን ያላትን ሁሉ በአምላክ መዝገብ ውስጥ እንደጣለችው ደሃ መበለት . . . ያላቸውን ሁሉ ለጌታ ዓላማ ያውላሉ።”​—አይሪኒየስ፣ በ180 እዘአ ገደማ ያዘጋጀው አጌነስት ሄረሲስ

“የመዋጮ መሰብሰቢያ ሳጥን ቢኖረንም መዋጮ የምናደርገው መዳን ያስገኝልናል ብለን አይደለም። እያንዳንዱ ሰው መስጠት ከፈለገ በየወሩ በሳጥኑ ውስጥ አነስ ያለ መዋጮ ይከትታል፤ ይህንን የሚያደርገው ግን የመስጠት ፍላጎቱና አቅሙ ካለው ብቻ ነው፣ ሁሉም ነገር የሚደረገው በፈቃደኝነት እንጂ በግዴታ አይደለም።”​—ተርቱሊያን በ197 እዘአ ገደማ ያዘጋጀው አፖሎጂ

“ቤተ ክርስቲያኗ እየሰፋችና የተለያዩ ተቋሞች እየተከፈቱ ሲሄዱ ቀሳውስቱ በተገቢው መንገድ ቋሚ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችላቸው ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ሆነ። በጥንቱ ሕግ ውስጥ የነበረው አሥራት የማውጣት ሥርዓት ሥራ ላይ እንዲውል ተደረገ። . . . በዚህ ጉዳይ ላይ የተላለፈው የመጀመሪያው ውሳኔ በ567 በቱር የተሰበሰቡት ጳጳሳት ባዘጋጁት ደብዳቤና በ585 የተደረገው የማኮን ጉባኤ በደነገጋቸው [ቀኖናዎች] ላይ ሰፍሮ እንደሚገኝ ይታመናል።”​—ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ

[ምንጭ]

ከላይ በስተግራ ያለው ሳንቲም:- Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፈቃደኝነት የሚደረግ ልግስና ደስታ ያስገኛል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፈቃደኝነት የሚደረጉ መዋጮዎች የስብከቱን ሥራ፣ በድንገተኛ አደጋዎች ወቅት የሚደረገውን የእርዳታ ዝግጅትና የመሰብሰቢያ ቦታዎችን ግንባታ በገንዘብ ለመደገፍ ያስችላሉ