በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ የማስተማር ችሎታ እንዲኖረን የሚረዳ የግል ጥናት

ጥሩ የማስተማር ችሎታ እንዲኖረን የሚረዳ የግል ጥናት

ጥሩ የማስተማር ችሎታ እንዲኖረን የሚረዳ የግል ጥናት

“ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር። ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ።”​1 ጢሞቴዎስ 4:​15, 16

1. ስለ ጊዜና ስለ ግል ጥናት ምን ለማለት ይቻላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 3:​1 ላይ “ለሁሉ ዘመን አለው” ይላል። ይህ አባባል በተለይ ለግል ጥናት ይሠራል። ብዙዎች አመቺ የሆነ ጊዜና ቦታ ካላገኙ መንፈሳዊ ነገር ማንበብም ሆነ ማጥናት ይከብዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል አድካሚ ሥራ ስትሠራ ውለህ እንዲሁም ከባድ እራት በልተህ በተለይ ደግሞ ቴሌቪዥን ፊት ለፊት የተመቻቸ ሶፋ ላይ ቁጭ ካልክ ማጥናት ያሰኝሃል? ይህ ለማጥናት እንደማይጋብዝ የታወቀ ነው። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ከምናደርገው ጥረት የተሻለ ጥቅም ማግኘት እንድንችል መቼና የት እንደምናጠና መምረጥ ይኖርብናል።

2. የግል ጥናት ለማድረግ ባብዛኛው ጥሩ የሚሆነው የትኛው ጊዜ ነው?

2 አንዳንዶች ማለዳ ንቁ ሆነው ሳለ ማጥናቱን የተሻለ ሆኖ ያገኙታል። ሌሎች ደግሞ በምሳ ሰዓት ላይ ያለቻቸውን አጭር የእረፍት ሰዓት ተጠቅመው ያጠናሉ። በሚከተሉት ምሳሌዎች ውስጥ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ ማግኘትን በተመለከተ የተጠቀሱትን ሐሳቦች ልብ በል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፣ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 143:​8) ነቢዩ ኢሳይያስም ጥናት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን እንደተገነዘበ ሲያሳይ እንዲህ ብሏል:- “የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፤ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፣ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል።” በየትኛውም ጊዜ ይሁን ዋናው ቁምነገር በምናጠናበትም ሆነ ከይሖዋ ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ አእምሮአችን በሚገባ ንቁ መሆን አለበት።​—⁠ኢሳይያስ 50:​4, 5፤ መዝሙር 5:​3፤ 88:​13

3. በደንብ ለማጥናት አመቺ የሆኑት ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

3 በደንብ ለማጥናት ከፈለግን ሌላው ልናስብበት የሚገባው ነገር የምንቀመጥበት ወንበር ወይም ሶፋ በጣም ምቹ መሆን የለበትም። የሚመች ሶፋ ላይ ተቀምጠን በንቃት ማጥናት አንችልም። በምናጠናበት ጊዜ አእምሮአችን ንቁ መሆን አለበት። አቀማመጣችን  በጣም የተመቻቸ ከሆነ ግን ውጤቱ ተቃራኒ ሊሆን ይችላል። ለማጥናትና ለማሰላሰል ጸጥታ መኖሩና ሐሳብን የሚከፋፍሉ ነገሮች አለመኖራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ራዲዮ ወይም ቴሌቪዥን ተከፍቶ እያለ ወይም ልጆች እየተንጫጩ ለማጥናት ብንሞክር ከጥናቱ ብዙ አንጠቀምም። ኢየሱስ ማሰላሰል በሚፈልግበት ጊዜ ፀጥ ወዳለ ቦታ ይሄድ ነበር። ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ ሆነን መጸለያችን አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግሯል።​—⁠ማቴዎስ 6:​6፤ 14:​13፤ ማርቆስ 6:​30-32

መልስ ለመስጠት የተዘጋጀን እንድንሆን የሚረዳ የግል ጥናት

4, 5. አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ጠቃሚ ሆኖ የምናገኘው እንዴት ነው?

4 የተለያዩ ጽሑፎችን ተጠቅመን በተለይ ደግሞ አንድ ሰው በቅን ልቦና ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በማሰብ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ጥልቀት ያለው ምርምር ስናደርግ የግል ጥናቱን አርኪ ሆኖ እናገኘዋለን። (1 ጢሞቴዎስ 1:​4፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​23) ብዙ አዲስ ሰዎች ዛሬ በ261 ቋንቋዎች ተተርጉሞ የሚገኘውን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?  a የተባለውን ብሮሹር በማጥናት ላይ ናቸው? ብሮሹሩ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሲሆን አቀራረቡም በጣም ቀላልና ቀጥተኛ ነው። ሰዎች አምላክ ከእውነተኛው አምልኮ ምን እንደሚጠብቅ በቀላሉ እንዲገነዘቡ ይረዳል። ይሁን እንጂ ብሮሹሩ እያንዳንዱን ርዕሰ ጉዳይ በዝርዝር የሚዳስስ አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው እየተወያያችሁበት ስላለው ርዕስ ከበድ ያሉ ጥያቄዎችን ካነሳ መልስ ለመስጠት የሚያስችል ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

5 በሲዲ የተዘጋጁትን የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች በቋንቋቸው ማግኘት የሚችሉ ካሉ በኮምፒውተር አማካኝነት ብዙ መረጃ ማሰባሰብ ይችላሉ። ሆኖም ኮምፒውተር የሌላቸውስ? አንድ ሰው አምላክ ማን ነው? እና ኢየሱስ ማን ነበር? የሚሉትን የመሰሉ ጥያቄዎች ቢያነሳ እውቀታችንን ማስፋትና ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማየት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር ላይ ያሉትን ሁለት ርዕሶች እንደ ምሳሌ ወስደን እንመልከት።​—⁠ዘጸአት 5:​2፤ ሉቃስ 9:​18-20፤ 1 ጴጥሮስ 3:​15

አውነተኛው አምላክ ማን ነው?

6, 7. (ሀ) አምላክን በተመለከተ ምን ጥያቄ ይነሳል? (ለ) አንድ ቄስ በንግግራቸው ሳይጠቅሱት የቀሩት ትልቅ ነገር ምንድን ነው?

6 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር ትምህርት 2 “እውነተኛው አምላክ ማን ነው?” ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። አንድ ሰው እውነተኛውን አምላክ የማያውቀው ወይም ሕልውናውን የሚጠራጠር ከሆነ ሊያመልከው ስለማይችል ይህ ጥያቄ መነሳቱ አንገብጋቢ ነው። (ሮሜ 1:​19, 20፤ ዕብራውያን 11:​6) ይሁንና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ በተመለከተ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። (1 ቆሮንቶስ 8:​4-6) እያንዳንዱ ሃይማኖታዊ ፍልስፍና ስለ አምላክ ማንነት የየራሱን ማብራሪያ ይሰጣል። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት አምላክ ሥላሴ እንደሆነ አድርገው ነው። አንድ ታዋቂ የዩናይትድ ስቴትስ ቄስ “አምላክን ታውቁታላችሁን?” በሚል ርዕስ ንግግር ሰጥተው ነበር። ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ደጋግመው ቢጠቅሱም አንድም ጊዜ መለኮታዊውን ስም ሳያነሱ ቀርተዋል። እርግጥ የያዙትም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይሖዋ ወይም ያህዌህ ከሚለው ስም ይልቅ አሻሚ የሆነውንና የማንነት መለያ ሆኖ ሊያገለግል የማይችለውን “ጌታ” የሚለውን መግለጫ የሚጠቀም ነበር።

7 ቄሱ “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ እያንዳንዱም ወንድሙን:- እግዚአብሔርን [በዕብራይስጥ “ይሖዋን”] እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፣ ይላል እግዚአብሔር [በዕብራይስጥ ይሖዋ]” ብለው ከኤርምያስ 31:​33, 34 ላይ ሲያነብቡ አንድ ትልቅ ነገር ዘንግተዋል። ይዘውት የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም አይጠቀምም።​—⁠ዘጸአት 6:​3 የ1879 ትርጉም

8. የአምላክን ስም መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያረጋግጥልን ምሳሌ የትኛው ነው?

8 መዝሙር 8:​9 [NW ] የይሖዋን ስም መጠቀማችን ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሲጠቁም “አቤቱ ጌታችን ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ባለ ግርማ ነው” ይላል። እስቲ ይህንን “አቤቱ ጌታችን፣ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ እጅግ ተመሰገነ” ከሚለው ትርጉም ጋር አወዳድረው። (የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፤ በተጨማሪም ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል፣ ዘ ሆሊ ባይብል​—⁠ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን፣ ታናክ ​—⁠ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ የተባሉትን መጻሕፍት ተመልከት) ይሁንና በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት የምንችለው ቃሉ መንገዳችንን እንዲያበራልን ከፈቀድን ነው። ሆኖም የመለኮታዊውን ስም አስፈላጊነት በተመለከተ ለጥያቄዎቻችን መልስ የሚሰጠን የትኛው ጽሑፍ ነው?​—⁠ምሳሌ 2:​1-6

9. (ሀ) መለኮታዊውን ስም መጠቀም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማስረዳት የሚያግዘን ጽሑፍ የትኛው ነው? (ለ) ብዙ ተርጓሚዎች ለአምላክ ስም አክብሮት እንደሌላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

9 በ69 ቋንቋዎች ተተርጉሞ የሚገኘውን ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም የሚለውን ብሮሹር ልንጠቀም እንችላለን። b “የአምላክ ስም​—⁠ትርጉሙና አነባበቡ” (ገጽ 6-11) የሚለው ክፍል ቴትራግራማተን (በግሪክኛ “አራት ፊደላት” ማለት ነው) በመባል የሚታወቁት የዕብራይስጥ ፊደላት በጥንቱ የዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ 7, 000 ጊዜ ያክል ተጠቅሰው እንደሚገኙ ይገልጻል። ይሁንና ቀሳውስቱም ሆኑ የአይሁድ እምነትና የሕዝበ ክርስትና ተርጓሚዎች ስሙን ሆነ ብለው ከአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ አውጥተውታል። c ታዲያ አምላክን በስሙ ሊጠሩት ፈቃደኛ ካልሆኑ እንዴት እናውቀዋለን ብለው ሊናገሩና ከእርሱ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ሊመሠርቱ ይችላሉ? እውነተኛ ስሙ ዓላማው ምን እንደሆነና የእርሱን ማንነት ለመረዳት በር ይከፍታል። ደግሞስ እንደዚያ ባይሆን “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” የሚለው የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ምን ትርጉም ይኖረው ነበር?​—⁠ማቴዎስ 6:​9፤ ዮሐንስ 5:​43፤ 17:​6

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

10. ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የተሟላ መግለጫ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

10 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የሚለው ብሮሹር ትምህርት 3 “ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?” የሚል ርዕስ አለው። በስድስት አንቀጾች ውስጥ ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሕይወቱ አጀማመርና ወደ ምድር ስለመጣበት ዓላማ እጥር ምጥን ያለ መግለጫ ይሰጣል። ይሁን እንጂ ስለ ሕይወቱ የተሟላ ማብራሪያ ማግኘት ከፈለግህ ከወንጌል ዘገባዎቹ ውጭ በ111 ቋንቋዎች ተተርጉሞ ከሚገኘው እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ከተባለው መጽሐፍ የተሻለ ጽሑፍ አታገኝም።* ይህ መጽሐፍ በአራቱ ወንጌሎች ላይ ተመሥርቶ ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርቶች የጊዜ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ የተሟላ ዘገባ ያቀርባል። የመጽሐፉ 133 ምዕራፎች ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ይተርካሉ። ለየት ያለ አቀራረብ የምትመርጥ ከሆነ ደግሞ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 “ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚለውን ርዕስ ልትመለከት ትችላለህ።

11. (ሀ) ስለ ኢየሱስ ባላቸው እምነት የይሖዋ ምሥክሮችን ለየት የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? (ለ) የሥላሴ ትምህርት ትክክል እንዳልሆነ የሚያረጋግጡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? በዚህ ረገድስ የትኛው ጽሑፍ ጠቃሚ ሐሳቦች ይዟል?

11 በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ኢየሱስን በተመለከተ የሚነሳው አወዛጋቢ ጥያቄ “የእግዚአብሔር ልጅ” ነው ወይስ “እግዚአብሔር ወልድ” የሚል ነው። በሌላ አባባል ጥያቄው ያለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ መማሪያ መጽሐፍ “የክርስትና እምነት ታላቅ ምሥጢር” ሲል በሚጠራው የሥላሴ ትምህርት ላይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በተለየ መልኩ ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ሳይሆን በእግዚአብሔር የተፈጠረ መሆኑን ያምናሉ። ይህ ርዕስ በ95 ቋንቋዎች ተተርጉሞ በሚገኘው በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? በሚለው ብሮሹር ውስጥ ግሩም በሆነ መንገድ ተብራርቷል። d ብሮሹሩ የሥላሴ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ እንዳልሆነ ለማስረዳት ከሚጠቅሳቸው በጣም ብዙ ጥቅሶች መካከል ማርቆስ 13:​32 እና 1 ቆሮንቶስ 15:​24, 28 ይገኙበታል።

12. ቀጥሎ ልንወያይበት የሚገባው ጥያቄ የትኛው ነው?

12 ስለ አምላክ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ከላይ የተወያየንባቸው ነጥቦች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማያውቁ ሰዎች ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት በማሰብ የግል ጥናት እንዴት ማድረግ እንደምንችል የሚያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው። (ዮሐንስ 17:​3) ይሁንና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ስለቆዩትስ ምን ለማለት ይቻላል? ለዓመታት ያካበቱት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ስላላቸው አሁን የይሖዋን ቃል በግላቸው ስለማጥናት ብዙ ሊጨነቁ አይገባም ማለት ነውን?

‘መጠንቀቅ’ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

13. አንዳንዶች የግል ጥናትን በተመለከተ ምን የተሳሳተ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል?

13 ለብዙ ዓመታት በጉባኤ ውስጥ የቆዩ አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክር በሆኑባቸው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ባገኙት እውቀት ብቻ ረክተው የመኖር ልማድ ሊያዳብሩ ይችላሉ። “እኔ እንደ አዳዲሶቹ ያን ያህል ማጥናት አያስፈልገኝም። ደግሞም ባለፉት ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ ሌሎች ጽሑፎችን ብዙ ጊዜ አንብቤያለሁ” ብሎ ማሰቡ ቀላል ነው። ይህ ግን “ባለፉት ዘመናት የበላሁት ምግብ በጣም ብዙ ስለሆነ አሁን ስለ አመጋገቤ ብዙም ማሰብ አያስፈልገኝም” እንደ ማለት ይቆጠራል። ሆኖም ሰውነታችን ጤነኛና ብርቱ እንዲሆን ከተፈለገ በደንብ የተዘጋጀና ለሰውነት ገንቢ የሆነ ምግብ ዘወትር ማግኘት እንደሚያስፈልገው እናውቃለን። መንፈሳዊ ጤንነታችንንና ኃይላችንን በተመለከተ ደግሞ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!​—⁠ዕብራውያን 5:​12-14

14. ለራሳችን መጠንቀቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

14 እንግዲያው ለረጅም ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ስንማር የቆየንም እንሁን አዲሶች ሁላችንም ጳውሎስ በወቅቱ የጎለመሰ ክርስቲያን ለነበረው ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ልብ ልንል ይገባል:- “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።” (1 ጢሞቴዎስ 4:​15, 16) የጳውሎስን ምክር ልብ ልንለው የሚገባው ለምንድን ነው? ጳውሎስ “የዲያብሎስን ሽንገላ [የተንኰል ሥራ]” መቋቋም እንዳለብንና “በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር” ውጊያ እንዳለብን መናገሩን አትዘንጋ። ሐዋርያው ጴጥሮስም ዲያብሎስ “የሚውጠውን ፈልጎ” እንደሚዞር ተናግሯል። ‘ከሚውጠው’ አንዱ ደግሞ እኛ ልንሆን እንችላለን። ምናልባት ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት አለመስጠታችን አመቺ ቀዳዳ ሊከፍትለት ይችላል።​—⁠ኤፌሶን 6:​11, 12፤ 1 ጴጥሮስ 5:​8

15. መንፈሳዊ መከላከያችን ምንድን ነው? በየጊዜው ልናድሰው የምንችለውስ እንዴት ነው?

15 ታዲያ መከላከያችን ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “በክፉው ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ” በማለት ያሳስበናል። (ኤፌሶን 6:13) ይህ መንፈሳዊ የጦር ዕቃ በጥሩ ሁኔታ የሚያገለግለው በመጀመሪያው ይዞታው እንዳለ ሲቆይ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ሲታደስ ነው። እንግዲያው የተሟላ የሚባለው የአምላክ የጦር ዕቃ ከአምላክ ቃል በየጊዜው የሚገኙትን አዳዲስ ትምህርቶች መቅሰምን ይጨምራል። ይህም ይሖዋ በቃሉ እንዲሁም በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት በየጊዜው ከሚያቀርብልን እውነት ጋር በሚገባ የመተዋወቁን አስፈላጊነት የሚጠቁም ነው። መንፈሳዊ የጦር ዕቃችንን ለማደስ አዘውትረን የአምላክን ቃልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማጥናታችን ወሳኝ ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​45-47፤ ኤፌሶን 6:​14, 15

16. ‘የእምነት ጋሻችን’ በጥሩ ይዞታ ላይ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ጳውሎስ የሰይጣንን የሚንበለበሉ ፍላጻዎች (የሐሰት ክሶችና የከሃዲዎች ትምህርት) ለመከላከል ብሎም ለማምከን የሚረዳን “የእምነት ጋሻ” ወሳኝ የመከላከያ ትጥቅ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ኤፌሶን 6:16) እንግዲያው የእምነት ጋሻችን ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነና ለማደስና ለማጠናከር ምን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባን መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል እንደሚከተለው እያልክ ልትጠይቅ ትችላለህ:- ‘በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት ለሚካሄደው ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምዘጋጀው እንዴት ነው? በስብሰባው ወቅት በደንብ የታሰበባቸው መልሶች በመስጠት ሌሎችን “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ” ለማነቃቃት እንድችል በቂ ዝግጅት አድርጌአለሁን? ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሰውን ጥቅሶች እያወጣሁ አነብባለሁን? በስብሰባዎች ላይ ከልቤ ተሳትፎ በማድረግ ለሌሎች የብርታት ምንጭ እሆናለሁን?’ የሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ ጠንካራ ስለሆነ የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንድንችል በሚገባ ማዋሃድ ይኖርብናል።​—⁠ዕብራውያን 5:​14፤ 10:​24

17. (ሀ) ሰይጣን መንፈሳዊነታችንን ለማዳከም በሚያደርገው ጥረት ምን መርዝ ይጠቀማል? (ለ) ለሰይጣን መርዝ ማርከሻው ምንድን ነው?

17 ሰይጣን የኃጢአተኛ ሥጋችንን ድክመት ስለሚያውቅ የሚጠቀምባቸው የሽንገላ ዘዴዎች መሠሪ ናቸው። መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው መንገዶች አንዱ ወሲባዊ ምስሎች በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔት፣ በቪዲዮ እንዲሁም በጽሑፎች ላይ በብዛት እንዲወጡ ማድረግ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህ መርዝ በደካማ ጎናቸው እንዲገባ በመፍቀዳቸው በጉባኤ ውስጥ መብታቸውን አጥተዋል አልፎ ተርፎም ለከፋ መዘዝ ተዳርገዋል። (ኤፌሶን 4:​17-19) ለሰይጣን መንፈሳዊ መርዝ ማርከሻው ምንድን ነው? አዘውትረን የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጋችንን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችንን እንዲሁም የአምላክን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበሳችንን ችላ አለማለት ነው። እነዚህ ነገሮች መልካምና ክፉ የሆነውን መለየት እንድንችልና አምላክ የሚጠላውን እንድንጠላ ይረዱናል።​—⁠መዝሙር 97:​10፤ ሮሜ 12:​9

18. በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ “የመንፈስ ሰይፍ” ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

18 አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት ልማዳችንን ካጠናከርን ከአምላክ ቃል ባገኘነው ትክክለኛ እውቀት የሚሰነዘርብንን ጥቃት መከላከል ብቻ ሳይሆን ‘የመንፈስ ሰይፍ በተባለው የአምላክ ቃል’ በተሳካ መንገድ ማጥቃትም እንችላለን። የአምላክ ቃል “ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ኤፌሶን 6:​17፤ ዕብራውያን 4:​12) ይህን “ሰይፍ” በመጠቀም ረገድ ጥሩ ችሎታ ካዳበርን ፈታኝ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ጉዳት የሌለው አልፎ ተርፎም ማራኪ መስሎ የሚታየውን ነገር በመበጣጠስ የሰይጣን ገዳይ ወጥመድ መሆኑን ማጋለጥ እንችላለን። ያከማቸነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ክፉ የሆነውን ነገር በማስወገድ መልካም የሆነውን እንድናደርግ ይረዳናል። በመሆኑም ሁላችንም ‘ሰይፌ የተሳለ ነው ወይስ ዝገት የበላው? የማጥቃት ኃይሌን የሚያጠናክሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማስታወስ እቸገራለሁን?’ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በግል የማጥናት ልማዳችንን አጥብቀን በመከተል ዲያብሎስን እንቋቋም።​—⁠ኤፌሶን 4:​22-24

19. በግል ጥናታችን የምንተጋ ከሆነ ምን ጥቅሞች ልናገኝ እንችላለን?

19 ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፋቸውን እነዚህን ቃላት ልብ ካልናቸው መንፈሳዊነታችንን ልናጠናክር እንዲሁም በአገልግሎታችን ይበልጥ ፍሬያማ ልንሆን እንችላለን። መንፈሳዊ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ለጉባኤው ትልቅ በረከት ሊሆኑ ይችላሉ። ሁላችንም ብንሆን ሳንናወጥ በእምነት ጸንተን ልንኖር እንችላለን።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17፤ ማቴዎስ 7:​24-27

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንድ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለውን ብሮሹር ካጠና በኋላ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ማጥናቱ አይቀርም። ሁለቱም የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁዋቸው ጽሑፎች ናቸው። እዚህ ላይ የቀረቡት ምክሮች ለመንፈሳዊ እድገት እንቅፋት የሚሆኑትን ነገሮች ለማስወገድ ይረዳሉ።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ በቋንቋቸው የሚያገኙ ጥራዝ 2 ላይ “ይሖዋ” የሚለውን ርዕስ መመልከት ይችላሉ።

c በርካታ የስፓንኛና የካታሎን ትርጉሞች አራቱን የዕብራይስጥ ፊደላት “ዮቬ፣” “ያሃቬ፣” “ጆቬ፣” እና “ካሆቬ” ብለው በመተርጎም ረገድ እንደ አብነት ይጠቀሳሉ።

d በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ታስታውሳለህን?

• ትርጉም ያለው የግል ጥናት ለማድረግ የሚያስፈልጉት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

• ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክን ስም በተመለከተ ምን ስህተት ይሠራሉ?

• የሥላሴ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደሌለው ለማረጋገጥ የትኞቹን ጥቅሶች ትጠቀማለህ?

• ለብዙ ዓመታት በክርስትና ጎዳና ስንመላለስ የቆየን ብንሆንም እንኳ ራሳችንን ከሰይጣን ሽንገላ ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትርጉም ያለው የግል ጥናት ለማድረግ የሚረብሽ ነገር የሌለበት አመቺ መቼት ሊኖር ይገባል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ሰይፍህ ’ የተሳለ ነው ወይስ ዝገት የበላው?