ታስታውሳለህን?
ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃቸዋልን? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-
• “የማመዛዘን ችሎታ” ሊጠብቅህ የሚችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 1:4)
የማመዛዘን ችሎታ ለመንፈሳዊ አደጋዎች ንቁ እንድንሆን የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ በሥራ ቦታ ከሚያጋጥመን የጾታ ፈተና መራቅን የመሳሰሉ የጥበብ እርምጃዎች ለመውሰድ ያነሳሳናል። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ፍጹማን አለመሆናቸውን እንድንገነዘብ የሚረዳን ሲሆን ይህም ሌሎች ሲያስቀይሙን በችኮላ ተገቢ ያልሆነ እርምጃ እንዳንወስድ ይጠብቀናል። በተጨማሪም መንፈሳዊ አቅጣጫችንን እንድንስት የሚያደርገንን ቁሳዊ ነገሮችን የማሳደድ ዝንባሌ መቋቋም ያስችለናል።—8/15 ገጽ 21-4
• አንድ ሰው ጥሩ ጎረቤት መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ጥሩ ጎረቤት መሆን የምንችልባቸው ሁለት መንገዶች ለጋስ ሰጪና አድናቂ ተቀባይ መሆን ናቸው። አንድ ዓይነት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ጥሩ ጎረቤት መሆን ጠቃሚ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ ክፋትን ለማስወገድ በቅርቡ የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ ለሰዎች ማስጠንቀቂያ በመናገር ጥሩ ጎረቤቶች ለመሆን ይጥራሉ።—9/1 ገጽ 4-7
• በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እውነተኛዎቹ ቅዱሳን እነማን ናቸው? የሰውን ዘር የሚረዱትስ እንዴት ነው?
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በሙሉ እውነተኛ ቅዱሳን ሲሆኑ ይህን መብት ያገኙት ከሰዎች ወይም ከሃይማኖታዊ ድርጅቶች ሳይሆን ከአምላክ ነበር። (ሮሜ 1:7) ቅዱሳን ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ካረጉ በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩትን ታማኞች በመባረኩ ሥራ ከክርስቶስ ጋር ተባብረው ይሠራሉ። (ኤፌሶን 1:18-21)—9/15 ገጽ 5-7
• ክርስቲያኖች በጥንቷ ግሪክ ይካሄዱ ስለነበሩት የአትሌቲክስ ውድድሮች ማወቃቸው ሊጠቅማቸው የሚችለው እንዴት ነው?
የጳውሎስና የጴጥሮስ ደብዳቤዎች በጥንት ጊዜ ይካሄዱ በነበሩት የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የተመሠረቱ ምሳሌዎችን ወይም ስለ ውድድሮቹ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ይዘዋል። (1 ቆሮንቶስ 9:26፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:7፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:5፤ 1 ጴጥሮስ 5:10) አንድ የጥንት አትሌት ጥሩ ስልጠና ማግኘቱ፣ ራሱን መግዛቱና በሚገባ የታሰበበት ጥረት ማድረጉ የግድ አስፈላጊ ነበር። ይኸው ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ለሚያደርጓቸው መንፈሳዊ ጥረቶችም ይሠራል።—10/1 ገጽ 28-31
• ልጆችን በውጭ አገር ማሳደግ ምን ችግሮች አሉት? ምንስ በረከቶች ያስገኛል?
ብዙ ልጆች ከወላጆቻቸው በተሻለ ፍጥነት አዲስ ቋንቋ የሚማሩ መሆናቸው ወላጆች የልጆቻቸውን አስተሳሰብና ድርጊት ለመረዳት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። ከዚህም በላይ ልጆች በወላጆቻቸው ቋንቋ የሚቀርቡላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በቀላሉ አይረዱ ይሆናል። ቢሆንም ወላጆች የራሳቸውን ቋንቋ ለልጆቻቸው በማስተማር የቤተሰብ ትስስራቸውን ማጠናከር ይችላሉ። ይህም ልጆቹ ሁለት ቋንቋዎችን እንዲያውቁና ከሁለት ዓይነት ባሕሎች ጋር እንዲላመዱ ያስችላቸዋል።—10/15 ገጽ 22-6
• ይቅርታ መጠየቅን መማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አብዛኛውን ጊዜ ከልብ ይቅርታ በመጠየቅ የሻከረ ግንኙነትን ማደስ ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይቅርታ መጠየቅ ምን ያህል ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ይዟል። (1 ሳሙኤል 25:2-35፤ ሥራ 23:1-5) ብዙውን ጊዜ በሁለት ግለሰቦች መካከል አለመግባባት ሲነሳ በሁለቱም ወገን ጥፋት ይኖራል። ስለዚህ ሁለቱም ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ መጠየቃቸው አስፈላጊ ነው።—11/1 ገጽ 4-7
• በአነስተኛ ገንዘብም እንኳ ቢሆን ቁማር መጫወት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
ቁማር መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘውን የራስ ወዳድነት፣ የፉክክርና የስግብግብነት መንፈስ ያበረታታል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አብዛኞቹ የቁማር ሱሰኞች ቁማር መጫወት የጀመሩት ገና በለጋ እድሜያቸው በአነስተኛ ገንዘብ በመወራረድ ነው።—11/1 ገጽ 31
• ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉት በግሪክኛ ቋንቋ ሆኖ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ግሪክኛ መተርጎም ለምን አስፈለገ? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
በጊዜያችን ያለው ግሪክኛ የሴፕቱጀንት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ከተጻፉበት ግሪክኛ በእጅጉ የተለየ ነው። ባለፉት መቶ ዘመናት ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከፊሉን በጊዜያችን ሰዎች ወደሚጠቀሙበት ግሪክኛ ለመተርጎም በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል። ባሁኑ ጊዜ ማንኛውም ግሪካዊ በቀላሉ ሊረዳቸው የሚችላቸው ሙሉውን ወይም ከፊሉን መጽሐፍ ቅዱስ የያዙ 30 የሚያህሉ ትርጉሞች ያሉ ሲሆን በ1997 ታትሞ የወጣው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ከእነዚህ አንዱ ነው።—11/15 ገጽ 26-9
• ክርስቲያኖች አሥራት እንዲያወጡ የማይጠበቅባቸው ለምንድን ነው?
ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር በተሰጠው ሕግ አሥራት የሌዊን ነገድና የተቸገሩ ሰዎችን ለመደገፍ የሚያስችል ዝግጅት ነበር። (ዘሌዋውያን 27:30፤ ዘዳግም 14:28, 29) የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ሕጉንና አሥራት የማውጣት ግዴታን አስቀርቷል። (ኤፌሶን 2:13-15) በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንደ ገቢው መጠን እና ልቡ እንዳነሳሳው የመስጠት ልማድ ነበረው። (2 ቆሮንቶስ 9:5, 7)—12/1 ገጽ 4-6
• ራእይ 20:8 ሰይጣን በመጨረሻው ፈተና ላይ የሚያስታቸው ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ይጠቁማል?
ጥቅሱ ሰይጣን የሚያስታቸው ሰዎች “እንደ ባሕር አሸዋ” እንደሆኑ ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ መግለጫ አብዛኛውን ጊዜ ከብዛት ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው መልኩ ያልተወሰነ ቁጥርን ብቻ ለማመልከት ያገለግላል። “በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” ይበዛል የተባለለት የአብርሃም ዘር ከኢየሱስ ሌላ 144, 000 የሚያህሉ ሰዎችን የሚያቅፍ ሆኖ ተገኝቷል። (ዘፍጥረት 22:17፤ ራእይ 14:1-4)—12/1 ገጽ 29