ሕይወቴን የለወጠ አጭር ማስታወሻ
የሕይወት ታሪክ
ሕይወቴን የለወጠ አጭር ማስታወሻ
አይሪን ሆከስተንባክ እንደተናገረችው
ሁኔታው የተፈጸመው በ1972 አንድ ማክሰኞ ምሽት ላይ ነው። በወቅቱ የ16 ዓመት ልጅ ስሆን ከወላጆቼ ጋር ሆኜ በኔዘርላንድ፣ ብራባንት ግዛት በምትገኘው በአይንትሆቨን ከተማ በተካሄደ አንድ ሃይማኖታዊ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። ጭንቅ ስላለኝ ባልመጣሁ ኖሮ የሚል ስሜት አደረብኝ። በዚህ ጊዜ ሁለት ወጣት ሴቶች “ውዷ አይሪን፣ ልንረዳሽ እንፈልጋለን” የሚል መልእክት የሰፈረበት ማስታወሻ ሰጡኝ። በወቅቱ ይህ አጭር መልእክት ሕይወቴን ምን ያህል እንደሚለውጠው እምብዛም አልተገነዘብኩም ነበር። ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጸመ ከመተረኬ በፊት ስለ ልጅነት ሕይወቴ ትንሽ ላጫውታችሁ።
የተወለድኩት በቤለቱንግ ደሴት ኢንዶኔዥያ ውስጥ ነው። በዚያ ሞቃታማ ደሴት እሰማቸው ከነበሩት ድምፆች መካከል አንዳንዶቹ አሁን ድረስ ትዝ ይሉኛል። ከእነዚህ መካከል የዘንባባ ዛፍ ቅጠሎች ንፋስ ወዲያና ወዲህ ሲያወዛውዛቸው የሚፈጥሩት ድምፅ፣ በአቅራቢያችን የሚገኘው ወንዝ ሲወርድ የሚያሰማው ድምፅ፣ የመንደራችን ልጆች ጫጫታ እንዲሁም በቤታችን ውስጥ የሚከፈተው ሙዚቃ ጥቂቶቹ ናቸው። በ1960፣ አራት ዓመት ሲሆነኝ ቤተሰባችን ከኢንዶኔዥያ ወደ ኔዘርላንድ ተዛወረ። ይህንን ረጅም ጉዞ ያደረግነው በመርከብ ሲሆን ይዣት የነበረችው በጣም የምወዳት አሻንጉሊት የምታሰማው ድምፅ አሁን ድረስ አይረሳኝም። ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ባደረብኝ ሕመም ምክንያት የመስማት ችሎታዬን አጣሁ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም ነገር መስማት አልቻልኩም። የቀረኝ ነገር ቢኖር ትዝታ ብቻ ነው።
የመስማት ችሎታ ሳይኖረኝ አደግሁ
ወላጆቼ ፍቅራዊ እንክብካቤ ያደርጉልኝ ስለነበር መጀመሪያ ላይ መስማት አለመቻሌ የሚያስከትለው ችግር ብዙም አልተሰማኝም። ልጅ ስለነበርኩ ለመስማት
እንዲረዳኝ የምጠቀምበትን ትልቅ መሣሪያ እንኳን ከመጫወቻ ለይቼ አላየውም ነበር፤ ለነገሩ መሣሪያውም ቢሆን ምንም ያህል አይረዳኝም ነበር። የጎረቤት ልጆች ከእኔ ጋር ማውራት ሲፈልጉ ሐሳባቸውን ሜዳው ላይ በጠመኔ ይጽፉልኛል፤ እኔም ድምፄን መስማት ባልችልም እንኳ መልስ እሰጣቸው ነበር።እያደግሁ ስሄድ ግን በአካባቢዬ ከሚገኙ ሰዎች የተለየ አንድ ችግር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። አንዳንዶች መስማት ስለማልችል እንደሚያሾፉብኝና ሌሎች ደግሞ ሊያቀርቡኝ እንደማይፈልጉ አስተዋልኩ። ብቸኝነት ይሰማኝ ጀመር። የመስማት ችሎታን ማጣት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ማስተዋል ስጀምርና እያደግሁ ስሄድ በአካባቢዬ ያለውን ዓለም ይበልጥ እየፈራሁት መጣሁ።
ወላጆቼ መስማት የተሳናቸው ልጆች በሚማሩበት ትምህርት ቤት ገብቼ እንድማር ሁኔታውን ለማመቻቸት ሲሉ በሊምበርግ ግዛት የሚገኘውን የመኖሪያ መንደር ለቅቀው በአይንትሆቨን ከተማ መኖር ጀመሩ። እዚያም አባቴ ሌላ ሥራ ሲይዝ ወንድሜና እህቶቼም አዲስ ትምህርት ቤት ገቡ። ለእኔ ብለው ላደረጓቸው እነዚህን ለመሳሰሉ ማስተካከያዎች ሁሉ ሳላመሰግናቸው አላልፍም። በትምህርት ቤት የድምፄን መጠን ከሁኔታዎች ጋር ማስተካከልና ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ መናገር ተማርሁ። ከዚህም በላይ አስተማሪዎቹ የምልክት ቋንቋ ባይጠቀሙም እንኳን አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ይህንን ቋንቋ አስተማሩኝ።
በብቸኝነት ስሜት ተውጦ መኖር
እያደግሁ ስመጣ ወላጆቼ ከእኔ ጋር ለመግባባት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ የነበረ ቢሆንም ለእኔ ግልጽ የማይሆኑልኝ በርካታ ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ወላጆቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያጠኑ አላወቅሁም ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ቤተሰባችን ብዙ ሰዎች ወደተሰበሰቡበት ቦታ እንደሄደ አስታውሳለሁ። ሁሉም ፊት ለፊታቸውን ይመለከቱ እንዲሁም አልፎ አልፎ ያጨበጭቡ ነበር፤ በመሃል ደግሞ ተነስተው ይቆማሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ለምን እንደዚህ እንደሚያደርጉ አይገባኝም ነበር። በዚያን ዕለት የተገኘሁት በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንደነበር የገባኝ ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው። ወላጆቼ በአይንትሆቨን ከተማ ወደሚገኝ አነስ ያለ አዳራሽም ይወስዱኝ ነበር። እዚያ የማያቸው ሰዎች ሁሉ ደጎች በመሆናቸውና ወላጆቼም እዚያ ሲሄዱ ደስ እንደሚላቸው ስለሚሰማኝ እዚያ መሄዳችንን አልጠላውም፤ ሆኖም አዘውትረን ወደዚያ ቦታ ለምን እንደምንሄድ አይገባኝም ነበር። አሁን ግን ይህ አዳራሽ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ እንደሆነ አውቄያለሁ።
የሚያሳዝነው ግን በስብሰባው ላይ ምን ትምህርት እየቀረበ እንዳለ በጽሑፍ የሚገልጽልኝ ሰው አልነበረም። ይህ ሊሆን የቻለው በስብሰባው ላይ የነበሩት ሰዎች እኔን የመርዳት ፍላጎት ቢኖራቸውም መስማት ስለማልችል እንዴት እንደሚረዱኝ ግራ ገብቷቸው ስለነበረ ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ብቸኝነት ስለሚሰማኝ ‘እዚህ ከምመጣ ይልቅ ትምህርት ቤት ብሆን ይሻለኝ ነበር’ ብዬ አስብ ነበር። ሆኖም ልክ ይህንን እያሰብሁ ሳለ ሁለት ወጣት ሴቶች በብጣሽ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ጫር ጫር አድርገው ሰጡኝ። በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ይህንን መልእክት ነበር። አጭር መልእክት የሰፈረበት ይህ ማስታወሻ ከብቸኝነት ሕይወቴ የሚገላግለኝ ውድ ዝምድና ለመመሥረት መንገድ ይከፍትልኛል ብዬ ጨርሶ አላሰብኩም ነበር።
ውድ የሆነ ዝምድና መመሥረት
ማስታወሻውን ጽፈው የሰጡኝ ኮሌትና ሄርሜን በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ነበሩ። ቆየት ብሎ እንደተገነዘብኩት እነዚህ ወጣቶች እኔ ወደምሰበሰብበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የመጡት የዘወትር አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነው ነበር። ምንም እንኳን ኮሌትና ሄርሜን የምልክት ቋንቋ ባይችሉም ከከንፈራቸው እንቅስቃሴ ምን እንዳሉ ስለምረዳ በደንብ እንግባባ ነበር።
ኮሌትና ሄርሜን እኔን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት መጠየቃቸው ወላጆቼን አስደሰታቸው፤ እነዚህ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን ከማስጠናትም አልፈው በሌሎች በብዙ መንገዶች ረድተውኛል። በመንግሥት አዳራሽ
በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ምን ትምህርት እየቀረበ እንዳለ በጽሑፍ ይገልጹልኛል እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ከሌሎች ጋር እንድቀራረብ ለማድረግ ይጥሩ ነበር። በስብከቱ ሥራ የምጠቀምባቸውን መግቢያዎች ያለማምዱኛል እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ሲሰጠኝ ያዘጋጁኝ ነበር። ይታያችሁ፣ መስማት በሚችሉ ሰዎች ፊት ቀርቤ ክፍል ለማቅረብ እንኳን ድፍረት አገኘሁ!ከዚህም በላይ ኮሌትና ሄርሜን ልተማመንባቸው የምችል ጓደኞች እንደሆኑ እንዲሰማኝ አድርገውኛል። ታጋሾች ከመሆናቸውም በላይ ጥሩ አዳማጮች ናቸው። በምሠራቸው ስህተቶች የምንስቅባቸው ጊዜያት ቢኖሩም አሹፈውብኝ ወይም አብሬያቸው በመሆኔ ተሸማቅቀው አያውቁም። ስሜቴን ለመረዳት የሚጥሩ ሲሆን ከእነርሱ እኩል እንደሆንኩ አድርገው ይመለከቱኝ ነበር። እነዚህ ደግ ሴቶች ውድ የሆነ ስጦታ ማለትም ፍቅራቸውንና ወዳጅነታቸውን ሰጥተውኛል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላካችን ይሖዋን ልተማመንበት የምችል ወዳጅ መሆኑን እንድገነዘብ አድርገውኛል። ይሖዋ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ተቀምጬ እያለሁ ይመለከተኝ እንደነበረና መስማት አለመቻሌ ያስከተለብኝን ችግሮች እንደተረዳልኝ ነገሩኝ። ሦስታችንም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ጓደኛሞች እንድንሆን ስላስቻለን በጣም አመስጋኝ ነኝ! ይሖዋ ያደረገልኝ እንክብካቤ በጥልቅ ስለነካኝና ለእርሱ ባለኝ ፍቅር በመነሳሳት ሐምሌ 1975 ራሴን ለእርሱ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።
ከባለቤቴ ጋር ጉባኤዎችን መጎብኘት
ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ከበርካታ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጋር ተዋወቅሁ። ከአንድ ወንድም ጋር የተለየ ወዳጅነት ስለነበረን በ1980 ተጋባን። ብዙም ሳይቆይ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከዚያም በ1994 ከባለቤቴ ከሃሪ ጋር የምልክት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን እንድንረዳ ልዩ አቅኚዎች ሆነን ተመደብን። በቀጣዩ ዓመት መስማት የሚችለው ባለቤቴ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የተለያዩ ጉባኤዎችን እንዲጎበኝ ሲመደብ አብሬው መጓዙ ፈታኝ ሆኖብኝ ነበር።
ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት አንድ ዘዴ ፈጠርኩ። አንድን ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንጎበኝ ቶሎ ብዬ የቻልኩትን ያህል ብዙ ወንድሞችንና እህቶችን ቀርቤ ሰላም በማለት እተዋወቃቸዋለሁ። ከዚያም መስማት እንደማልችል እነግራቸውና ከእኔ ጋር በሚያወሩበት ጊዜ ፊት ለፊት እያዩኝና ረጋ ብለው እንዲናገሩ እጠይቃቸዋለሁ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይም ወዲያው ተሳትፎ ማድረግ እጀምራለሁ። እንዲሁም በዚያ ሳምንት በሚደረጉት የጉባኤና የመስክ አገልግሎት ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን ትምህርት በጽሑፍ ሊገልጽልኝ የሚችል ፈቃደኛ ሰው እንዳለ እጠይቃቸዋለሁ።
በዚህ መንገድ ወንድሞችንና እህቶችን ቶሎ ስለቀረብኳቸው አንዳንድ ጊዜ መስማት የማልችል መሆኔን ይረሱትና አስቂኝ የሆኑ አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ። ለምሳሌ
ያህል መንገድ ላይ ሲያዩኝ እኔን ሰላም ለማለት የመኪናቸውን ጥሩንባ አሰምተው እንደነበረ ይነግሩኛል፤ መስማት ስለማልችል ምንም ምላሽ ሳልሰጣቸው እቀራለሁ። አንዳንድ ጊዜ እኔ ራሴም የአቅም ገደብ እንዳለብኝ እረሳዋለሁ። ለባለቤቴ ምስጢር የሆነ ነገር በጆሮው ሹክ ስለው ድንገት ፊቱ ሲቀላ እመለከታለሁ፤ ለካስ እኔ “በሹክሹክታ የተናገርኩ” ይመስለኛል እንጂ ድምፄ ለሌሎችም ይሰማል።ልጆችም ባልተጠበቁ መንገዶች እርዳታ አድርገውልኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኘነው አንድ ጉባኤ ውስጥ አንድ የዘጠኝ ዓመት ልጅ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ያሉት አንዳንዶች እኔን ለማነጋገር እምብዛም እንዳልደፈሩ ይመለከትና አንድ ነገር ለማድረግ ይወስናል። ወደ እኔ መጥቶ እጄን ይዞ እየጎተተ ወደ መሃል ከወሰደኝ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከአይሪን ጋር ላስተዋውቃችሁ፣ መስማት የማትችል እህት ናት!” አላቸው። በአዳራሹ ውስጥ የነበሩት ወደ እኔ መጡና ተዋወቁኝ።
ከባለቤቴ ጋር በወረዳ ሥራ መካፈሌ ብዙ ጓደኞች እንዳፈራ ረድቶኛል። የዛሬው ሕይወቴ ብቸኛ እንደሆንኩ ይሰማኝ ከነበረበት ጊዜ ጋር ሲወዳደር ምንኛ የተለየ ነው! ኮሌትና ሄርሜን ያንን አጭር ማስታወሻ ከሰጡኝ ዕለት ጀምሮ ወዳጅነት ያለውን ኃይል ከመገንዘቤም በላይ ውድ የሆኑ ጓደኞች ማግኘት ችያለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ከማንም ይበልጥ ውድ ወዳጅ የሆነውን ይሖዋን ማወቅ ችያለሁ። (ሮሜ 8:38, 39) ያ አጭር ማስታወሻ ሕይወቴን በእጅጉ ለውጦታል!
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምወዳት አሻንጉሊት ድምፅ አሁን ድረስ አይረሳኝም
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አገልግሎት ላይ ሆኜ እንዲሁም ከባለቤቴ ከሃሪ ጋር