በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሆን መጽናኛ

መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሆን መጽናኛ

መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሆን መጽናኛ

ሰዎች ይህ ሁሉ ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው አምላክ ለምን ዝም ብሎ ይመለከታል? የሚለው ጥያቄ ላለፉት መቶ ዘመናት በርካታ ፈላስፋዎችንና የሃይማኖት ምሁራንን ግራ ሲያጋባ ቆይቷል። አንዳንዶች አምላክ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ለዚህ ሁሉ መከራ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው እርሱ መሆን አለበት በማለት ይከራከራሉ። የክሌመንታይን ድርሳናት (The Clementine Homilies) የተባለው በሁለተኛው መቶ ዘመን የተጻፈው አዋልድ መጽሐፍ ደራሲ አምላክ ዓለምን በሁለቱም እጆቹ እየገዛ እንዳለ ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው አባባል አምላክ “ግራ እጁ” በሆነው በዲያብሎስ መከራና ሥቃይን የሚያመጣ ሲሆን “ቀኝ እጁ” በሆነው በኢየሱስ ደግሞ ሰዎችን ከመከራ ይታደጋቸዋል እንዲሁም ይባርካቸዋል።

ሌሎች ደግሞ አምላክ እርሱ ራሱ መከራ ባያመጣብንም እንኳ መከራ ሲደርስብን ዝም ብሎ ይመለከታል የሚለውን ሐሳብ መቀበል ስለሚከብዳቸው መከራ የሚባል ነገር ጨርሶ የለም ማለቱን መርጠዋል። ሜሪ ቤከር ኤዲ የተባሉ አንዲት ሴት “መከራ እንዲያው በሐሳባችን የፈጠርነውና ተጨባጭ መሠረት የሌለው ነገር ነው። ኃጢአት፣ ሕመምና ሞት ፈጽሞ እንደሌሉ ነገሮች አድርገን ብንቆጥራቸው ኖሮ አይኖሩም ነበር” በማለት ጽፈዋል።​—⁠ሳይንስ ኤንድ ሄልዝ ዊዝ ኪይ ቱ ዘ ስክሪፕቸርስ

ብዙዎች በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በተለይም ከአንደኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ እስካሁን የተፈጸሙትን አሳዛኝ ክስተቶች ሲመለከቱ አምላክ መከራን ማቆም ተስኖታል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ዴቪድ ውልፍ ሲልቨርማን የተባሉ አንድ አይሁዳዊ ምሁር “በእኔ አመለካከት ናዚዎች በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ያደረሱት እልቂት አምላክ ሁሉን ቻይ ነው የሚለውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርገዋል። እርሱ ደግ ሆኖ ሳለ በምድር ላይ ያለውን ክፋት እያየ ዝም ማለቱ ይህን ችግር ማስወገድ ቢሳነው ነው ማለት ይቀላል” ሲሉ ጽፈዋል።

ይሁን እንጂ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው አምላክ ነው፣ መከራን ማስቆም ተስኖታል ወይም መከራ እንዲያው በሐሳባችን የፈጠርነው ነገር ነው የሚሉት አመለካከቶች መከራ ለሚደርስባቸው የሰው ልጆች በምንም ዓይነት ማጽናኛ አይሆኑም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ አመለካከቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው ፍትሐዊ፣ ኃያል እና አሳቢ ከሆነው አምላክ ባሕርያት ፍጹም ተቃራኒ ናቸው። (ኢዮብ 34:10, 12፤ ኤርምያስ 32:17፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ታዲያ አምላክ መከራ ሲደርስብን እያየ እርምጃ ያልወሰደበትን ምክንያት በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሥቃይና መከራ የጀመረው እንዴት ነው?

አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ሥቃይና መከራ እንዲደርስባቸው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ጥንዶች ለአዳምና ለሔዋን ምንም እንከን የሌለበት አእምሮና አካል ሰጥቷቸው፣ ለመኖሪያ የሚሆን የተዋበ የአትክልት ሥፍራ አዘጋጅቶላቸው እንዲሁም ዓላማ ያለውና እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28, 31፤ 2:8) ይሁን እንጂ ደስታቸው ዘላቂ መሆኑ የተመካው የአምላክን የበላይ ገዥነት እንዲሁም መልካሙንና ክፉውን ለመወሰን ያለውን መብት አምነው በመቀበላቸው ላይ ነበር። ይህን መለኮታዊ ሥልጣን የሚወክል ‘መልካምንና ክፉን የሚያስታውቅ’ የተባለ አንድ ዛፍ ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አዳምና ሔዋን ከዛፉ እንዳይበሉ አምላክ የሰጣቸውን መመሪያ በማክበር ለአምላክ መገዛታቸውን ማሳየት ይችሉ ነበር። a

የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ። ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ የሚል ስያሜ ያገኘ አንድ ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር ሔዋንን አምላክን መታዘዝ ለእሷ እንደማይበጃት አሳመናት። እንደ እርሱ አባባል አምላክ ሔዋንን አንድ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ማለትም ነጻነቷን ብሎም መልካሙንና ክፉውን የመወሰን መብቷን ነፍጓታል። ሰይጣን ከዛፉ ብትበላ ‘ዓይኗ እንደሚከፈትና እንደ አምላክ መልካሙንና ክፉውን የምታውቅ እንደምትሆን’ ነገራት። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9) ራስዋን በራስዋ የማስተዳደር ነፃነት የማግኘት ጉጉት ያደረባት ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ በላች፤ አዳምም የእርሷን ፈለግ ተከተለ።

አዳምና ሔዋን አለመታዘዛቸው ያስከተለውን ውጤት የዚያኑ ቀን መመልከት ጀመሩ። መለኮታዊውን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው ለአምላክ ቢገዙ ኖሮ ያገኙት የነበረውን ጥበቃና በረከት አጡ። አምላክ ከገነት ያባረራቸው ሲሆን አዳምን እንዲህ አለው:- “ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ።” (ዘፍጥረት 3:17, 19) አዳምና ሔዋን ለኃጢአት፣ ለበሽታ፣ ለሥቃይ፣ ለእርጅናና ለሞት የተጋለጡ ሆኑ። መከራና ሥቃይ የሰው ልጅ ሕይወት ክፍል ሆነ።​—⁠ዘፍጥረት 5:29

ለጉዳዩ እልባት ማስገኘት

አንድ ሰው ‘አምላክ የአዳምንና የሔዋንን ኃጢአት እንዲሁ ቸል ብሎ ማለፍ አይችልም ነበር?’ በማለት ይጠይቅ ይሆናል። መልሱ አይችልም ነው። ምክንያቱም እንዲህ ቢያደርግ ሌሎች ለሥልጣኑ የሚኖራቸው አክብሮት ይበልጥ እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ምናልባት ሌሎችም ወደፊት እንዲያምፁ ሊያበረታታ ስለሚችል መከራው ከአሁኑ እጅግ የከፋ ይሆን ነበር። (መክብብ 8:11) በተጨማሪም ይህን ዓይነቱን ዓመፅ ችላ ብሎ ማለፉ አምላክን ራሱን የኃጢአት ተባባሪ ያደርገው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ የነበረው ሙሴ “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” በማለት ይገልጽልናል። (ዘዳግም 32:4) አምላክ ከራሱ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ አዳምና ሔዋን ማመፃቸው ያስከተለባቸውን መከራ እንዲቀምሱ አድርጓል።

አምላክ አዳምንና ሔዋንን የዓመፁ ዋነኛ ጠንሳሽ ከነበረው ከሰይጣን ጋር ወዲያውኑ ለምን አላጠፋቸውም? እንዲህ ማድረግ ይችል ነበር። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ አዳምና ሔዋን ለመከራና ለሞት የሚዳረጉ ልጆችን አይ​ወልዱም ነበር። ይሁን እንጂ ኃይሉን በዚህ መንገድ ቢያሳይ የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጡራኑ ላይ ያለው ሥልጣን ትክክለኛ መሆኑ ሳይረጋገጥ ይቀር ነበር። በተጨማሪም አዳምና ሔዋን ልጆች ሳያፈሩ መሞታቸው አምላክ ምድርን ፍጹም በሆኑ ዘሮቻቸው ለመሙላት የነበረው ዓላማ መክሸፉን ይጠቁም ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) “አምላክ እንደ ሰዎች አይደለም። . . . ቃል የገባውን ያደርጋል፤ የተናገረው ይፈጸማል።”​—⁠ዘኍልቍ 23:19ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን

አምላክ አቻ የሌለው ጥበቡን በመጠቀም ዓመፁ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል ፈቀደ። ዓመፀኞቹ ከአምላክ አመራር ስር ወጥቶ መኖር የሚያመጣቸውን ችግሮች መመልከት የሚችሉበት በቂ ጊዜ አግኝተዋል። የሰው ልጅ ታሪክ ሰዎች መለኮታዊ አመራር እንደሚያስፈልጋቸውና የአምላክ አገዛዝ ከሰይጣንም ሆነ ከሰው አገዛዝ በእጅጉ የላቀ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ አሳይቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አምላክ ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማው የሚፈጸምበትን መንገድ ለማመቻቸት አንዳንድ እርምጃዎችን ወሰደ። አንድ ‘ዘር’ ‘የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጥ’ እሱ የቆሰቆሰውን ዓመፅና በዚያ ምክንያት የመጣውን ጉዳት ለማስወገድ እንደሚመጣ ቃል ገባ።​—⁠ዘፍጥረት 3:15

ይህ ቃል የተገባለት ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። በ1 ዮሐንስ 3:​8 ላይ “የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ኢየሱስ ይህንን ያደረገው ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት የአዳምን ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት የሚያስፈልገውን ቤዛ በመክፈል ነው። (ዮሐንስ 1:29፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ከልብ እምነት የሚያሳድሩ ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመከራ እንደሚገላገሉ ቃል ተገብቶላቸዋል። (ዮሐንስ 3:16፤ ራእይ 7:17) ይህ የሚሆነው መቼ ነው?

ሥቃይና መከራ የሚያከትምበት ጊዜ

የሰው ልጆች የአምላክን ሥልጣን አንቀበልም ማለታቸው ይህ ነው ለማይባል ሥቃይና መከራ ዳርጓቸዋል። ታዲያ አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ እንዲያበቃ ለማድረግና ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ዳር ለማድረስ ሥልጣኑን ልዩ በሆነ መንገድ መጠቀሙ አግባብ ነው? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን’ ብለው እንዲጸልዩ ባስተማራቸው ጊዜ ይህን መለኮታዊ ዝግጅት ጠቅሶት ነበር።​—⁠ማቴዎስ 6:9, 10

ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲሞክሩ አምላክ የሰጣቸው የጊዜ ገደብ በቅርቡ ያበቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ንጉሥ ሆኖ በተሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው መንግሥት በ1914 በሰማይ ተቋቁሟል። b ይህ መንግሥት በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ይፈጫቸዋል፣ እንዲሁም ያጠፋቸዋል።​—⁠ዳንኤል 2:44

ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው አጭር አገልግሎት ወቅት መለኮታዊ አገዛዝ ዳግመኛ ሲቋቋም ለሰው ዘር የሚያመጣቸውን በረከቶች ለናሙና ያህል አሳይቷል። ኢየሱስ ለድሆችና አድልዎ ይደረግባቸው ለነበሩ የማኅበረሰቡ አባላት ከልብ ያዝን እንደነበር ከወንጌል ዘገባዎች መረዳት ይቻላል። የታመሙትን ፈውሷል፣ የተራቡትን መግቧል፣ ሙታንን አስነስቷል። ሌላው ቀርቶ የተፈጥሮ ኃይሎች እንኳን ይታዘዙለት ነበር። (ማቴዎስ 11:5፤ ማርቆስ 4:37-39፤ ሉቃስ 9:11-16) ኢየሱስ ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች ከቤዛዊ መሥዋዕቱ የማንጻት ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ምን ነገር ሊያከናውን እንደሚችል አስብ! መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በክርስቶስ አገዛዝ አማካኝነት ‘እንባዎችንም ሁሉ ከሰው ዘር ዓይኖች እንደሚያብስ፣ ሞትን፣ ኀዘንን፣ ጩኸትን ወይም ሥቃይን እንደሚያስወግድ’ ተስፋ ይሰጠናል።​—⁠ራእይ 21:4

ሥቃይና መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች የሚሆን ማጽናኛ

ሁሉን ቻይና አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ለእኛ እንደሚያስብልንና በቅርቡ የሰውን ዘር ከሥቃይና ከመከራ እንደሚገላግለው ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! አብዛኛውን ጊዜ አንድ በጠና የታመመ ሰው ጊዜያዊ ሥቃይ የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ ከሕመሙ ለዘለቄታው የሚፈውሰውን ሕክምና ለመቀበል ይስማማል። በተመሳሳይም አምላክ አሁን ያሉትን ሁኔታዎች በተመለከተ እያደረገ ያለው ነገር ዘላለማዊ በረከት እንደሚያስገኝልን ማወቃችን ምንም ዓይነት ጊዜያዊ ችግሮች ቢደርሱብንም ሊያጽናናን ይችላል።

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የጠቀስነው ሪካርዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሉት ተስፋዎች መጽናኛ ካገኙት ሰዎች መካከል አንዱ ነው። “ባለቤቴ ከሞተች በኋላ ራሴን ከሰዎች በጣም አገልል ነበር፤ እንዲህ ማድረጌ ግን ሐዘኔን ከማባባስ በስተቀር ባለቤቴን እንደማይመልሳት ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብኩ” በማለት ያስታውሳል። ይልቁንም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ መሳተፍ ቀጠለ። ሪካርዶ እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ፍቅራዊ ድጋፍ እንዳልተለየኝ ሲሰማኝና ትናንሽ በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳን ለጸሎቶቼ መልስ ሲሰጠኝ ስመለከት ወደ እርሱ ይበልጥ ቀረብኩ። በሕይወቴ ከገጠሙኝ መከራዎች ሁሉ የከፋውን ይህን ፈተና እንድቋቋም የረዳኝ አምላክ እንደሚወደኝ መገንዘቤ ነበር። ባለቤቴን ማጣቴ አሁንም ቢሆን በጣም ይሰማኛል፤ ሆኖም ይሖዋ እንዲደርስብን የሚፈቅደው ማንኛውም ነገር ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትልብን እንደማይችል ተገንዝቤአለሁ።”

እንደ ሪካርዶና በሚልዮን እንደሚቆጠሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ አንተም አሁን ያሉት የሰው ዘር ችግሮች ‘የማይታሰቡበትን፣ ወደ ልብም የማይመጡበትን’ ጊዜ ትናፍቃለህ? (ኢሳይያስ 65:17) “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ካደረግህ የአምላክ መንግሥት የምታመጣቸውን በረከቶች ማግኘት እንደምትችል እርግጠኛ ሁን።​—⁠ኢሳይያስ 55:6

ለዚህ እንዲረዳህ የአምላክን ቃል ማንበብንና ማጥናትን በሕይወትህ ውስጥ ዋነኛውን ቦታ ስጠው። ስለ አምላክና እርሱ ስለ ላከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በቂ እውቀት ለመቅሰም ጥረት አድርግ። ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተህ ለመኖር ጥረት በማድረግ ለሉዓላዊነቱ ለመገዛት ፈቃደኛ መሆንህን አሳይ። እንዲህ ማድረግህ ፈተናዎች እያሉም ደስተኛ ሆነህ እንድትቀጥል የሚረዳህ ሲሆን ወደፊት ደግሞ መከራ በማይኖርበት ዓለም ውስጥ ሕይወትን ለማጣጣም ያስችልሃል።​—⁠ዮሐንስ 17:3

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዘ ጀሩሳሌም ባይብል ዘፍጥረት 2:​17ን አስመልክቶ ባሰፈረው የግርጌ ማስታወሻ ላይ ‘መልካምንና ክፉን ማወቅ’ የሚለውን አባባል “ምን ነገር መልካም፣ ምን ነገር መጥፎ እንደሆነ የመወሰንና በዚያ መሠረት የመመራት ሥልጣን ማለትም የሰው ልጅ ፍጡር መሆኑን ለመቀበል አሻፈረኝ ብሎ ሙሉ በሙሉ በራስ ለመተዳደር ያደረገው ምርጫ” በማለት ይገልጸዋል። አክሎም “የመጀመሪያው ኃጢአት በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነበር” ይላል።

b ከ1914 ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በሚናገረው ሐሳብ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10, 11 ተመልከት።

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሥቃይንና መከራን ተቋቁመን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

“የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉት።” (1 ጴጥሮስ 5:7) በራሳችንም ሆነ በምንወደው ሰው ላይ መከራ ሲደርስ ግራ መጋባት፣ ብስጭትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማን ይችላል። ቢሆንም ይሖዋ የውስጥ ስሜታችንን እንደሚረዳልን እርግጠኛ ሁን። (ዘጸአት 3:7፤ ኢሳይያስ 63:9) በጥንት ጊዜ እንደነበሩት ታማኝ ሰዎች በውስጣችን የሚሰማንን ለይሖዋ ልንነግረውና ፍርሃታችንንና ጭንቀታችንን ልንገልጽለት እንችላለን። (ዘጸአት 5:22፤ ኢዮብ 10:1-3፤ ኤርምያስ 14:19፤ ዕንባቆም 1:13) በተአምራዊ መንገድ ከፊታችን የተጋረጠውን ፈተና ባያስወግድልንም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥበብና ጥንካሬ በመስጠት ጸሎታችንን ሊመልስልን ይችላል።​—⁠ያዕቆብ 1:5, 6

“መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቁጠር አትደነቁ።” (1 ጴጥሮስ 4:12 አ.መ.ት ) እዚህ ላይ ጴጥሮስ እየተናገረ የነበረው ስለ ስደት ቢሆንም ሐሳቡ በአንድ አማኝ ላይ ሊደርስ ለሚችለው ለማንኛውም መከራ ይሠራል። ሰዎች ይታረዛሉ፣ ይታመማሉ እንዲሁም የሚወዱትን ሰው በሞት ይነጠቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጊዜና እድል [አጋጣሚ፣ NW ]” በማንኛውም ሰው ላይ ችግር እንደሚያስከትሉ ይናገራል። (መክብብ 9:11) እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በጊዜያችን በጣም የተለመዱ ናቸው። ይህን መገንዘባችን የሚደርስብንን ማንኛውንም መከራና ሥቃይ ችለን ለመኖር ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 5:9) ይበልጥ ደግሞ “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸው” የሚለውን ማረጋገጫ ማስታወሳችን ልዩ የመጽናናት ምንጭ ይሆንልናል።​—⁠መዝሙር 34:15፤ ምሳሌ 15:3፤ 1 ጴጥሮስ 3:12

“በተስፋ ደስ ይበላችሁ።” (ሮሜ 12:12) በፊት የነበረንን ደስታ እያሰብን በመቆዘም ፋንታ አምላክ መከራና ሥቃይን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በገባው ተስፋ ላይ ማሰላሰል እንችላለን። (መክብብ 7:10) የራስ ቁር ራስን ከአደጋ እንደሚከላከል ሁሉ ይህ ከአምላክ ያገኘነው አስተማማኝ ተስፋም ከለላ ይሆንልናል። ተስፋ በሕይወታችን ውስጥ የሚደርስብንን ሥቃይ የሚያቀልልን ከመሆኑም በላይ ሥቃዩ በአእምሯችን፣ በስሜታችንና በመንፈሳዊ ጤንነታችን ላይ ዘላቂ ጉዳት እንዳያስከትልብን ይከላከልልናል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:8

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳምና ሔዋን በአምላክ አገዛዝ ላይ ዓመፁ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ሥቃይና መከራ የማይኖርበት ዓለም ለማምጣት ቃል ገብቷል