በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ተግታችሁ ጠብቁ’!

‘ተግታችሁ ጠብቁ’!

‘ተግታችሁ ጠብቁ’!

“ለእናንተም የምነግራችሁን ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።”—⁠ማርቆስ 13:37

1, 2. (ሀ) አንድ ሰው ከደረሰበት ሁኔታ ንብረቱን ስለ መጠበቅ ምን ትምህርት አግኝቷል? (ለ) ኢየሱስ ስለ ሌባ ከተናገረው ምሳሌ ነቅቶ ስለመኖር ምን እንማራለን?

 ሁዋን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ንብረቶቹን ቤቱ ውስጥ አልጋው ሥር አስቀምጧቸው ነበር። በእርሱ እምነት ንብረቶቹን ማንም ሰው በማይጠረጥርበት ቦታ መሸሸጉ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሌሊት እርሱና ባለቤቱ ከባድ እንቅልፍ ወስዷቸው ሳለ ሌባ መኝታ ቤታቸው ገባ። ሌባው የት ቦታ መፈለግ እንዳለበት በሚገባ አውቆአል። ሁዋን አልጋው አጠገብ ባለው ጠረጴዛ መሳቢያ ውስጥ ያስቀመጠውን ገንዘብ ጨምሮ አልጋው ሥር የደበቃቸውን እነዚያን ውድ ንብረቶች በሙሉ ሌባው ዘርፎ ሄደ። በማግሥቱ ጠዋት ሁዋን መዘረፉን ተገነዘበ። ሁዋን እንቅልፍ የጣለው ሰው ንብረቶቹን መጠበቅ እንደማይችል ከዚህ አሳዛኝ ክስተት ፈጽሞ የማይረሳ ትምህርት አግኝቷል።

2 በመንፈሳዊ ሁኔታም ነገሩ ተመሳሳይ ነው። እንቅልፍ ከጣለን ተስፋችንንም ሆነ እምነታችንን መጠበቅ አንችልም። ጳውሎስ “እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ” የሚል ማሳሰቢያ የሰጠው በዚህ ምክንያት ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:​6) ኢየሱስ ነቅቶ መኖር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማስገንዘብ ስለ ሌባ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ለፍርድ ከመምጣቱ በፊት የሚከሰቱ ክንውኖችን ከገለጸ በኋላ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋል:- “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” (ማቴዎስ 24:42-44) ሌባ በዚህ ሰዓት እመጣለሁ ብሎ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ ማንም ሰው ባላሰበበት ሰዓት ላይ ለመምጣት ያስባል። በተመሳሳይም የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የሚመጣው ኢየሱስ እንደተናገረው ‘በማናስብበት ሰዓት’ ነው።

“ንቁ፤ በእምነት ጽኑ”

3. ኢየሱስ ከሠርግ የሚመለስ ጌታቸውን ስለሚጠባበቁ አገልጋዮች የተናገረው ምሳሌ ነቅቶ የመኖርን አስፈላጊነት በሚመለከት ምን ያስተምረናል?

3 በሉቃስ ወንጌል ውስጥ እንደተመዘገበው ኢየሱስ ክርስቲያኖችን ጌታቸው ከሠርግ የሚመለስበትን ጊዜ ከሚጠባበቁ ባሪያዎች ጋር አመሳስሏቸዋል። በሚመጣበት ጊዜ እርሱን ለመቀበል ዝግጁ ሆነው እንዲገኙ ነቅተው መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል። በተመሳሳይም ኢየሱስ ‘የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣል’ በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 12:40) ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች የምንኖርበትን ዘመን በሚመለከት ያላቸውን የጥድፊያ ስሜት ሊያጡ ይችላሉ። ይባስ ብሎም መጨረሻው በጣም ገና ነው የሚል አመለካከት ሊያድርባቸው ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያለው አመለካከት መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ በማለት ወደ ሥጋዊ ግቦች እንድናተኩር ሊያደርገን ይችላል። ይህ ደግሞ መንፈሳዊ እንቅልፍ እንዲጫጫነን ያደርጋል።​—⁠ሉቃስ 8:​14፤ 21:​34, 35

4. ተግተን እንድንጠብቅ የሚገፋፋን ምን ዓይነት ዝንባሌ መያዛችን ነው? ኢየሱስ ይህንን በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ ሌላም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አገልጋዮቹ ጌታቸው የሚመጣበትን ትክክለኛውን ሰዓት ባያውቁም በየትኛው ሌሊት እንደሚመጣ ያውቁ ነበር። ጌታችን ዛሬ ሌሊት አይመጣም ብለው አስበው ቢሆን ኖሮ ሌሊቱን ሙሉ ሲጠብቁ ማደር ይከብዳቸው ነበር። ሆኖም ጌታቸው የሚመጣበትን ትክክለኛውን ሌሊት ማወቃቸው ነቅተው እንዲጠብቁ ከፍተኛ ብርታት ሰጥቷቸዋል። በተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የምንኖረው በፍጻሜው ዘመን እንደሆነ ግልጽ ማስረጃዎች ይሰጡናል። ሆኖም መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛውን ቀንም ሆነ ሰዓት አይነግሩንም። (ማቴዎስ 24:​36) መጨረሻው መምጣቱ እንደማይቀር ማወቃችን ነቅተን እንድንኖር ይረዳናል። ሆኖም የይሖዋ ቀን በጣም እንደቀረበ እርግጠኞች ከሆንን ተግቶ ለመጠበቅ የሚያስችል ከፍተኛ ውስጣዊ ግፊት ይጨምርልናል።​—⁠ሶፎንያስ 1:14

5. ጳውሎስ “ንቁ” በማለት በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ነቅተን ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

5 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ንቁ፤ በእምነት ጽኑ” ሲል አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:​13 አ.መ.ት ) አዎን፣ ነቅተን መኖራችን በክርስቲያናዊ እምነት ጸንተን ከመቆማችን ጋር ከፍተኛ ተዛማጅነት አለው። ታዲያ ነቅተን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ጥልቀት ያለው የአምላክ ቃል እውቀት በመቅሰም ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​14, 15) ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበራችንና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን እምነታችንን ለማጠንከር ይረዳናል። የይሖዋን ቀን አቅርበን መመልከታችን የእምነታችን ዋነኛ ገጽታ ነው። ስለሆነም በዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ዋዜማ ላይ እንደምንኖር የሚያረጋግጡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን ከጊዜ ወደ ጊዜ መከለሳችን መጨረሻው መቅረቡን እንዳንዘነጋ ይረዳናል። a በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆኑ የዓለም ሁኔታዎችን በትኩረት መከታተላችን ጠቃሚ ነው። በጀርመን የሚኖር አንድ ወንድም “ስለ ጦርነት፣ የምድር መናወጥ፣ ስለ ዓመፅና ስለ ምድራችን መበከል የሚዘግቡ የቴሌቪዥን ዜናዎችን ባየሁ ቁጥር የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም እንደቀረበ ያለኝ እምነት ይጠናከራል” በማለት ጽፏል።

6. ኢየሱስ መንፈሳዊ ንቃት ቀስ በቀስ እየጠፋ ሊሄድ እንደሚችል በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

6 በማርቆስ ምዕራፍ 13 ላይ ኢየሱስ ተከታዮቹ ነቅተው እንዲኖሩ ለማሳሰብ የተናገረውን ሌላ ታሪክ እናገኛለን። ኢየሱስ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተከታዮቹን ሁኔታ ወደ ሩቅ አገር የሄደውን የጌታውን መምጣት ከሚጠባበቅ በረኛ ጋር በማወዳደር ተናግሯል። በረኛው ጌታው የሚመለስበትን ሰዓት ስለማያውቅ ያለው አማራጭ ተግቶ መጠበቅ ብቻ ነው። ጌታው ሌሊቱ ካሉት አራት ክፍሎች መካከል በአንደኛው ላይ ሊመጣ እንደሚችል ኢየሱስ ተናግሯል። አራተኛው ክፍል ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት እስከ ማለዳ ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። በረኛው ኃይለኛ እንቅልፍ የሚጫጫነው በተለይ በዚህኛው ክፍለ ጊዜ ነው። ወታደሮች አንድን ጠላት በተዘናጋበት ሰዓት ላይ ለመያዝ ጎሕ ከመቅደዱ በፊት ያለውን ጊዜ እንደሚመርጡ ይነገራል። በተመሳሳይም በዙሪያችን ያለው ዓለም በመንፈሳዊ ሁኔታ ጭልጥ ባለ እንቅልፍ ላይ በሚገኝበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን ላይ ነቅቶ መኖር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። (ሮሜ 13:​11, 12) ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ “ተጠንቀቁ፤ ትጉ . . . ስለዚህ ትጉ። ለእናንተም የምነግራችሁን ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ” በማለት በተደጋጋሚ ያሳሰበው በዚህ ምክንያት ነው።​—⁠ማርቆስ 13:32-37

7. ነቅቶ መኖርን በሚመለከት ምን አደጋ ተደቅኖብናል? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት በተደጋጋሚ ምን ዓይነት ማበረታቻ ይሰጣል?

7 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅትና ከትንሣኤው በኋላ ነቅቶ የመኖርን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ተናግሯል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሚናገርባቸው በአብዛኞቹ ቦታዎች ላይ ነቅተን እንድንኖር ወይም ተግተን እንድንጠብቅ የሚያሳስብ ማስጠንቀቂያ እናገኛለን። b (ሉቃስ 12:​38, 40፤ ራእይ 3:​2፤ 16:​14-16) በመንፈሳዊ ማሸለብ በጣም አደገኛ መሆኑ ግልጽ ነው። ሁላችንም ብንሆን እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ልብ ማለት ይኖርብናል!​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​2, 6

ነቅተው መጠበቅ ያቃታቸው ሦስት ሐዋርያት

8. ሦስቱ የኢየሱስ ሐዋርያት ጌቴሴማኒ በተባለው የአትክልት ቦታ ምን ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ?

8 ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ምሳሌ እንደምንገነዘበው ነቅቶ ለመኖር እንዲሁ ቅን ፍላጎት ብቻውን አይበቃም። እነዚህ ሦስት ሐዋርያት ኢየሱስን በታማኝነት የተከተሉና ለእርሱ ጥልቅ ፍቅር ያላቸው መንፈሳዊ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ኒሳን 14, 33 እዘአ ሌሊት ላይ ነቅተው መጠበቅ አቃታቸው። እነዚህ ሦስት ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር በባለ ደርብ ክፍል ውስጥ የማለፍን በዓል ካከበሩ በኋላ አብረውት ጌቴሴማኒ ወደሚባል የአትክልት ስፍራ ሄዱ። እዚያ ሲደርሱ ኢየሱስ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው። (ማቴዎስ 26:38) ኢየሱስ በሰማይ ወደሚኖረው አባቱ ሦስት ጊዜ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረበ። የሚያሳዝነው ሦስቱንም ጊዜ ተመልሶ መጥቶ ሲያያቸው ተኝተው አገኛቸው።​—⁠ማቴዎስ 26:​40, 43, 45

9. ሐዋርያቱ በእንቅልፍ የተሸነፉበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

9 እነዚህ ታማኝ ሰዎች በዚያ ምሽት ኢየሱስ በነገራቸው መሠረት ነቅተው መጠበቅ ሳይችሉ የቀሩት ለምን ነበር? አንደኛው ምክንያት አካላዊ ድካም ተጫጭኗቸው ስለነበረ ነው። በጣም በመምሸቱ ምናልባትም እኩለ ሌሊት በማለፉ “ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው” ነበር። (ማቴዎስ 26:​43) ይሁንና ኢየሱስ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” አላቸው።​—⁠ማቴዎስ 26:41

10, 11. (ሀ) ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ እያለ በጣም ደክሞት የነበረ ቢሆንም እንዲተጋ የረዳው ምንድን ነው? (ለ) ሦስቱ ሐዋርያት ከደረሰባቸው ሁኔታ ምን ልንማር እንችላለን?

10 ታሪካዊ በሆነው በዚያ ምሽት ኢየሱስም ደክሞት ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ሊያዝ ጥቂት ሰዓታት ብቻ በቀሩበት በዚያ ወቅት እንቅልፍ እንዲያሸንፈው ከመፍቀድ ይልቅ ጊዜውን ከልብ የመነጨ ጸሎት ለማቅረብ ተጠቅሞበታል። ከጥቂት ቀናት በፊት ተከታዮቹን “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ” በማለት እንዲጸልዩ አበረታቷቸው ነበር። (ሉቃስ 21:36፤ ኤፌሶን 6:18) ኢየሱስ ጸሎትን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር የምንታዘዝና ምሳሌውን የምንኮርጅ ከሆነ ለይሖዋ የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ልመና በመንፈሳዊ ነቅተን እንድንኖር ይረዳናል።

11 እርግጥ ነው፣ በወቅቱ ደቀ መዛሙርቱ አይገንዘቡት እንጂ ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተይዞ ሞት እንደሚፈረድበት ያውቅ ነበር። ፈተናው የሚቋጨው ስቃይ በተሞላበት መንገድ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ነው። ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ጠቅሶ ሐዋርያቱን አስጠንቅቋቸው የነበረ ቢሆንም የሚናገረው አልገባቸውም። በመሆኑም እርሱ ተግቶ በሚጸልይበት ጊዜ እነርሱ ተኝተው ነበር። (ማርቆስ 14:​27-31፤ ሉቃስ 22:​15-18) እንደ ሐዋርያቱ ሁሉ የእኛም ሥጋ ደካማ ከመሆኑም በላይ ገና ያልተረዳናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በመሆኑም የምንኖርበትን ዘመን አጣዳፊነት የማንረዳ ከሆነ መንፈሳዊ እንቅልፍ ሊያሸንፈን ይችላል። ንቁ መሆን የምንችለው ተግተን የምንጠብቅ ከሆነ ብቻ ነው።

በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ባሕርያት

12. ጳውሎስ በመጠን ከመኖር ጋር አያይዞ የጠቀሳቸው ሦስት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

12 የጥድፊያ ስሜታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ጸሎት ያለውን ወሳኝ ቦታና የይሖዋን ቀን ቅርብ አድርገን የመመልከትን አስፈላጊነት ቀደም ብለን ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ ጳውሎስ “ከቀን ስለ ሆንን፣ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር” በማለት ልናዳብራቸው የሚገቡ ሌሎች ሦስት ባሕርያትን ገልጾልናል። (1 ተሰሎንቄ 5:​8) በመንፈሳዊ ነቅተን እንድንኖር በማስቻል ረገድ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና በአጭሩ እንመልከት።

13. ነቅተን በመኖር ረገድ እምነት የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?

13 ይሖዋ እንዳለና ‘ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ’ ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል። (ዕብራውያን 11:​6) ኢየሱስ መጨረሻውን አስመልክቶ የተናገረውና በአንደኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው ትንቢት በዘመናችን በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ማግኘቱ እምነታችንን ያጠነክርልናል። እንዲህ ያለው እምነት ‘ትንቢታዊው ራእይ በእርግጥ እንደሚመጣና እንደማይዘገይ’ በመተማመን የይሖዋን ቀን በጉጉት እንድንጠባበቅ ያደርገናል።​—⁠ዕንባቆም 2:​3

14. ነቅተን መኖር እንድንችል ተስፋ በጣም አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው እንዴት ነው?

14 ተስፋ አምላክ ቃል የገባልን አንዳንድ ነገሮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ ስንጠባበቅ የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ችግሮች በጽናት እንድንቋቋም “እንደ ነፍስ መልሕቅ” ሆኖ ያገለግለናል። (ዕብራውያን 6:18, 19) አሁን በ90ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙትና ከተጠመቁ ከ70 ዓመታት በላይ የሆናቸው ማርጋሬት የተባሉ አንዲት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያን የተሰማቸውን እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ባለቤቴ በ1963 በካንሰር በሽታ ሲሞት መጨረሻው ቶሎ በመጣ የሚል ስሜት አድሮብኝ ነበር። አሁን ግን ለራሴ ጥቅም ብቻ አስብ እንደነበረ ተገንዝቤአለሁ። በዚያ ወቅት የስብከቱ ሥራ በዓለም ዙሪያ ምን ያህል ሊስፋፋ እንደሚችል የምናውቀው ነገር አልነበረም። አሁንም እንኳን ምሥራቹ ገና በደንብ ያልተዳረሰባቸው ቦታዎች አሉ። በመሆኑም ይሖዋ ትዕግሥት በማሳየቱ ደስተኛ ነኝ።” ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን ያደርጋል፤ ተስፋውም አያሳፍርም’ በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል።​—⁠ሮሜ 5:3-5

15. መጨረሻውን ለረጅም ጊዜ የጠበቅን ሆኖ ቢሰማንም እንኳን ፍቅር ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?

15 ክርስቲያናዊው ፍቅር ለምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ዋነኛው ግፊት በመሆኑ ጎልቶ የሚታይ ባሕርይ ነው ለማለት ይቻላል። ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መቼም ይሁን መች እርሱን የምናገለግለው ስለምንወደው ነው። አንድን ክልል ምንም ያህል ደጋግመን ብንሸፍን እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለረጅም ዓመታት እንድንሰብክ የአምላክ ፈቃድ ቢሆንም እንኳ ለሰዎች ያለን ፍቅር ምንጊዜም ይህን ከማድረግ ወደኋላ እንዳንል ይገፋፋናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” (1 ቆሮንቶስ 13:​13) ፍቅር እንድንጸናና ነቅተን እንድንጠብቅ ይረዳናል። “[ፍቅር] ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​7, 8

“ያለህን አጽንተህ ያዝ”

16. እጃችንን ከማላላት ይልቅ ምን ዓይነት ዝንባሌ ማዳበር ይኖርብናል?

16 የዓለም ሁኔታ በመጨረሻው ቀን ማብቂያ ላይ እንደምንኖር ዘወትር በሚያስታውሰን በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ እንገኛለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ጊዜው እጃችንን የምናላላበት ሳይሆን ‘ያለንን አጽንተን የምንይዝበት’ ወቅት ነው። (ራእይ 3:​11) ‘ተግተን በመጸለይ’ እንዲሁም እምነት፣ ተስፋና ፍቅር በማዳበር ከፊታችን ለሚጠብቀን የፈተና ሰዓት ዝግጁዎች ሆነን እንጠብቃለን። (1 ጴጥሮስ 4:​7) የጌታ ሥራ የበዛልን ነን። ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በሚያንጸባርቁ ሥራዎች መጠመዳችን ነቅተን እንድንኖር ይረዳናል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​11

17. (ሀ) ተስፋ ሳንቆርጥ በትዕግሥት መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው? (በገጽ 21 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ምን በረከት ያገኛሉ?

17 ኤርምያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ . . .። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው። ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።” (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:24-26) አንዳንዶቻችን ፍጻሜውን የጠበቅነው ለአጭር ጊዜ ነው። ሌሎች ደግሞ የይሖዋን ማዳን ለረጅም ዓመታት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ረጅም መስሎ የሚታየው ይህ ጊዜ ወደፊት ከሚጠብቀን የዘላለም ሕይወት ጋር ሲነጻጸር ምንኛ አጭር ነው! (2 ቆሮንቶስ 4:​16-18) ይሖዋ የቀጠረውን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅን አስፈላጊ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበርና ሌሎች በይሖዋ ትዕግሥት ተጠቅመው እውነትን እንዲቀበሉ መርዳት እንችላለን። እንግዲያው ሁላችንም ተግተን መጠባበቃችንን እንቀጥል። የይሖዋን ምሳሌ በመኮረጅ በትዕግሥት የምንጠባበቅና እርሱ ለሰጠን ተስፋ የምናመሰግን እንሁን። እንዲሁም በታማኝነት ነቅተን ስንጠባበቅ የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ “ምድርንም ትወርስ ዘንድ [ይሖዋ] ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ” የሚለው ትንቢታዊ ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ የማየት አጋጣሚ ይኖረናል።​—⁠መዝሙር 37:34

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በጥር 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 12-13 ላይ የወጡትን “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ እንደምንኖር የሚጠቁሙ ስድስት ማስረጃዎችን እንደገና መከለሱ ጠቃሚ ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1

b ደብሊው ኢ ቫይን የተባሉ አንድ የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ “ተግታችሁ ጠብቁ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ግስ ቃል በቃል ሲተረጎም ‘እንቅልፍን ማባረር’ ማለት እንደሆነ ከገለጹ በኋላ ቃሉ “መንቃትን ብቻ ሳይሆን አንድን ነገር በንቃት መጠባበቅን ያመለክታል” በማለት ተናግረዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እንደቀረበ ያለንን ትምክህት ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?

• ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ካጋጠማቸው ሁኔታ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?

• በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር ሊረዱን የሚችሉ ሦስት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

• የምንኖረው ‘ያለንን አጽንተን መያዝ’ በሚያስፈልገን ጊዜ ውስጥ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘የሚታገሥ ደስተኛ ነው።’​—ዳንኤል 12:​12

አንድ ዘብ ጠባቂ የሚጠብቀውን ግቢ ሌባ ሊዘርፍ እንዳሰበ ጠረጠረ እንበል። ዘብ ጠባቂው ለዓይን ያዝ ከሚያደርግበት ጊዜ አንስቶ የሌባውን መምጣት የሚጠቁም ድምፅ ለመስማት በንቃት መከታተል ይጀምራል። ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ ጆሮውን አቁሞና ዓይኑን ተክሎ አካባቢውን ይከታተላል። ዘብ ጠባቂው የቅጠል ኮሽታ በሰማ ቁጥር ሌባው የመጣ መስሎት ደንገጥ ማለቱ እንደማይቀር መገመት አያዳግትም።​—⁠ሉቃስ 12:​39, 40

“የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ” ነቅተው የሚጠባበቁ ክርስቲያኖች ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:​7) ሐዋርያት ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‘የእስራኤልን መንግሥት መልሶ’ የሚያቋቁም መስሏቸው ነበር። (ሥራ 1:​6) ከብዙ ዓመታት በኋላም ኢየሱስ ዳግም የሚገኝበት ጊዜ ገና ወደፊት እንደሆነ በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ማስታወስ አስፈልጎ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:​3, 8) ያም ሆኖ ግን የይሖዋን ቀን በተመለከተ የነበራቸው አንዳንድ የተሳሳተ ግምት የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ እንዲተዉ አላደረጋቸውም።​—⁠ማቴዎስ 7:​13

በዘመናችን የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የዘገየ መስሎ መታየቱ ተስፋ ቆርጠን ተግተን መጠባበቃችንን እንድናቆም ሊያደርገን አይገባም። ተግቶ የሚጠባበቅ አንድ ዘብ ጠባቂ የተለያዩ ድምፆችን ሰምቶ ሌባ የመጣ መስሎት የሚታለልባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም በዚህ ተዘናግቶ ተግቶ ከመጠበቅ ወደኋላ ማለት የለበትም! ምክንያቱም ይህ ግዴታው ነው። ክርስቲያኖችም መዘናጋት የለባቸውም።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ቀን መቅረቡን ከልብ ታምናለህ?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉባኤ ስብሰባዎች፣ ጸሎትና ጥሩ የጥናት ልማድ ተግተን እንድንጠብቅ ይረዱናል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ እህት ማርጋሬት እኛም በትዕግሥትና በንቃት ተግተን እንጠባበቅ