በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አምላክ ሆይ ይህ እንዲደርስብን ለምን ፈቀድህ?’

‘አምላክ ሆይ ይህ እንዲደርስብን ለምን ፈቀድህ?’

‘አምላክ ሆይ ይህ እንዲደርስብን ለምን ፈቀድህ?’

ሪካርዶ ከሚስቱ ከማሪያ ጋር ሆስፒታል ውስጥ ተቀምጦ የነበረበትን ዕለት ፈጽሞ አይረሳውም። a ሁለቱም የማሪያን የሕክምና ምርመራ ውጤት ለማንበብ ወኔው አልነበራቸውም። በመጨረሻ ሪካርዶ እንደ ምንም ብሎ ፖስታውን ከፈተውና በአብዛኛው በሕክምና ቃላት የተጻፈውን የምርምራ ውጤት በችኮላ ገረፍ ገረፍ እያደረጉ ማንበብ ጀመሩ። በወረቀቱ ላይ “ካንሰር” የሚለውን ቃል ሲመለከቱና ይህ ደግሞ ምን ዓይነት በሽታ እንደሆነ ሲያስቡት ሁለቱም ማልቀስ ጀመሩ።

ሪካርዶ “ሐኪሙ በጣም ደግ ሰው ነበር፤ የማሪያ ጤንነት አስጊ ሁኔታ ላይ መሆኑን ስላወቀ ትምክህታችንን በአምላክ ላይ መጣል እንዳለብን እየደጋገመ ይነግረን ነበር” በማለት ያስታውሳል።

ማሪያ የጨረር ሕክምና ከመጀመርዋ በፊት ዶክተሩ ቀኝ እግሯ ድንገተኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ አስተዋለ። ተጨማሪ ምርመራዎች ስታደርግ ካንሰሩ ወደ አንጎሏ መሰራጨቱ ተደረሰበት። የጨረር ሕክምናው ለአንድ ሳምንት ብቻ ከተሰጣት በኋላ እንዲቆም ተደረገ። ከዚያም ማሪያ ለሁለት ወር ያህል ራስዋን ስታ ከቆየች በኋላ አረፈች። ሪካርዶ የተሰማውን እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ከሥቃይዋ በመገላገሏ ደስ ቢለኝም እሷን በማጣቴ በጣም ስላዘንኩ ምነው እኔም ሞቼ ባረፍኩት ብዬ እስከ መመኘት ደርሼ ነበር። ብዙ ጊዜ እያለቀስኩ ‘ይህ ሁሉ እንዲደርስብኝ ለምን ፈቀድህ?’ በማለት አምላክን እጠይቅ ነበር።”

አሳዛኝ ሁኔታ ሲከሰት በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ

በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች ልክ እንደ ሪካርዶ በመከራ የተሞላ ሕይወት ለመኖር ተገድደዋል። አብዛኛውን ጊዜ መከራ የሚደርስባቸው ምኑም ውስጥ የሌሉበት ንጹሐን ሰዎች ናቸው። እስቲ የሰውን ዘር እንደ ቅጠል በማርገፍ ላይ ያሉ ማባሪያ የሌላቸው ጦርነቶች ያስከተሉትን ሰቆቃ አስብ። ወይም ደግሞ ተገደው የተደፈሩ፣ በትዳር ጓደኞቻቸው ወይም በወላጆቻቸው የሚደበደቡ፣ በሕፃንነታቸው በጾታ የተነወሩ እንዲሁም ሌላ ዓይነት ግፍ የተፈጸመባቸው በርካታ ሰዎች የሚሰማቸውን ስቃይ አስብ። በታሪክ ዘመናት በሙሉ ሰዎች አንዳቸው በሌላው ላይ የፈጸሙት ግፍና ያደረሱት መከራ ይህ ነው አይባልም። (መክብብ 4:1-3) በዚህ ላይ ደግሞ የተፈጥሮ አደጋ ሰለባዎች ወይም ስሜታዊ፣ አእምሯዊና አካላዊ ሕመም ያለባቸው ሰዎች የሚሰማቸው ስቃይም አለ። እንግዲያው ብዙዎች “በሰው ልጆች ላይ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስ አምላክ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?” ብለው መጠየቃቸው ብዙም ሊያስገርመን አይገባም።

ለሃይማኖት ያደሩ ሰዎችም እንኳን ይህ ነው የማይባል ስቃይና መከራ ይደርስባቸዋል። አንተም ‘አንድ አፍቃሪና ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ ሲደርስ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?’ ብለህ ሳታስብ አትቀርም። ለዚህ እንቆቅልሽ የሆነ ጥያቄ ትክክለኛና አሳማኝ መልስ ማግኘታችን የአእምሮ ሰላም እንዲኖረንና ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና እንዲጠናከር ለማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት እንችላለን። በሚቀጥለው ርዕስ ስር ያለውን ሐሳብ በማንበብ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶክተሩ ትምክህታችንን በአምላክ ላይ መጣል እንዳለብን እየደጋገመ ይነግረን ነበር