ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ነቅታችሁ ኑሩ!
ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ነቅታችሁ ኑሩ!
“እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ።”—1 ተሰሎንቄ 5:6
1, 2. (ሀ) ፖምፔ እና ሄርኩላኒየም ምን ዓይነት ከተማዎች ነበሩ? (ለ) በፖምፔ እና በሄርኩላኒየም ከተማዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ችላ ያሉት የትኛውን የማስጠንቀቂያ ምልክት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በቬሱቪየስ ተራራ ሥር ፖምፔ እና ሄርኩላኒየም የሚባሉ ሁለት የበለጸጉ የሮማ ከተማዎች ይገኙ ነበር። እነዚህ ከተማዎች ሃብታም ሮማውያን የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው አመቺ ስፍራዎች ነበሩ። ቴአትር ቤቶቻቸው ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም የነበራቸው ሲሆን ፖምፔ ውስጥ የከተማውን ነዋሪ በሙሉ ሊይዝ የሚችል አንድ ግዙፍ አምፊቴአትር ነበር። በፖምፔ ላይ ጥናት የሚያደርጉ የመሬት ቆፋሪዎች 118 ቡና ቤቶችንና መሸታ ቤቶችን ያገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ቁማር መጫወቻ ወይም ዝሙት የሚፈጸምባቸው ቤቶች ነበሩ። በግድግዳዎች ላይ ከተሳሉት ሥዕሎችና በአካባቢው ከተገኙ የእጅ ጥበብ ሥራዎች መረዳት እንደሚቻለው በእነዚህ ከተማዎች ውስጥ ብልግናና ፍቅረ ነዋይ በእጅጉ ተስፋፍተው ነበር።
2 ነሐሴ 24, 79 እዘአ በቬሱቪየስ ተራራ ላይ እሳተ ገሞራ መፈንዳት ጀመረ። በእሳተ ገሞራ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ሳይንቲስቶች በመጀመሪያው ፍንዳታ ወቅት በሁለቱ ከተማዎች ላይ የዘነበው አነስተኛ መጠን ያለው የድንጋይ ቅላጭና አመድ ነዋሪዎቹ ከተማዎቹን ጥለው እንዳይወጡ የሚያግዳቸው እንዳልነበረ ያምናሉ። በእርግጥም ብዙዎቹ አካባቢውን ለቅቀው እንደወጡ ይታመናል። ሆኖም አደጋውን አቅልለው የተመለከቱ ወይም የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ችላ ያሉ ነዋሪዎች እዚያው ቀሩ። ከዚያም እኩለ ሌሊት ገደማ በሄርኩላኒየም ከተማ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የእሳተ ገሞራ ጋዝ፣ ጭቃና የድንጋይ ቅላጭ በመዝነቡ በከተማዋ ውስጥ የቀሩትን ነዋሪዎች በሙሉ ውጦ አስቀራቸው። ማለዳ ላይ በፖምፔ ከተማ ተመሳሳይ ነገር በመድረሱ በከተማይቱ ቀርተው የነበሩት ነዋሪዎች በሙሉ ለህልፈተ ሕይወት ተዳረጉ። የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ችላ ማለት የሚያስከትለው መዘዝ ምንኛ አሳዛኝ ነው!
የአይሁድ ሥርዓት ፍጻሜ
3. የኢየሩሳሌምንና የሁለቱን ከተማዎች ጥፋት የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
3 የእነዚህ ሁለት ከተማዎች አስደንጋጭ ፍጻሜ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ኢየሩሳሌምን ድምጥማጧን ካጠፋው ጦርነት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። “በታሪክ ዘመናት በሙሉ በአሰቃቂነቱ አቻ ያልተገኘለት ይህ ከበባ” ከአንድ ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ አይሁዳውያን እልቂት ምክንያት እንደሆነ ይነገርለታል። ይሁን እንጂ በሁለቱ የሮማውያን ከተማዎች ላይ እንደሆነው ሁሉ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊትም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር።
4. ኢየሱስ የአይሁድ ሥርዓት ፍጻሜ መቅረቡን በተመለከተ ተከታዮቹን ለማስጠንቀቅ ምን ትንቢታዊ ምልክቶችን ተናግሯል? ይህ ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ከተማዋ መጥፋትና ከዚያ በፊት ስለሚፈጸሙ ክንውኖች ትንቢት ተናግሮ ነበር። ከእነዚህ ክንውኖች መካከል ጦርነት፣ ረሃብ፣ የምድር መናወጥና ዓመፅ ይገኙበታል። ሐሰተኛ ነቢያት እንደሚነሱ ሆኖም የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንደሚሰበክ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:4-7, 11-14) ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው በአሁኑ ጊዜ ቢሆንም በዚያን ዘመንም በተወሰነ መጠን ፍጻሜውን አግኝቷል። በይሁዳ ከባድ ረሃብ ተከስቶ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ። (ሥራ 11:28) ኢየሩሳሌም ከመጥፋትዋ ትንሽ ቀደም ብሎ በከተማዋ አቅራቢያ የምድር መናወጥ ተከስቶ እንደነበር አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ዘግቧል። የኢየሩሳሌም ጥፋት በተቃረበበት ወቅት የማያባራ ዓመፅ፣ በተለያዩ የአይሁድ የፖለቲካ አንጃዎች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት እንዲሁም አይሁዳውያንና አሕዛብ አብረው በሚኖሩባቸው በርካታ ከተማዎች ውስጥ እልቂት ተከስቶ ነበር። የሆነ ሆኖ የአምላክ መንግሥት ምሥራች “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” በመሰበክ ላይ ነበር።—ቆላስይስ 1:23
5, 6. (ሀ) በ66 እዘአ ፍጻሜውን ያገኘው የትኛው የኢየሱስ ትንቢት ነው? (ለ) ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ ስትጠፋ የሟቾቹ ቁጥር ከፍ እንዲል ያደረገው ምንድን ነው?
5 በመጨረሻም በ66 እዘአ አይሁዳውያን በሮም ላይ ዓመፁ። በሴስትየስ ጋለስ የተመራው ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ሲከብብ የኢየሱስ ተከታዮች “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ” በማለት ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ትዝ አላቸው። (ሉቃስ 21:20, 21) ኢየሩሳሌምን ለቅቀው መውጣት በሚገባቸው ወቅት ላይ እንደሚገኙ ገብቷቸዋል። ግን እንዴት አድርገው? በጋለስ የሚመራው ጦር ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደኋላ አፈገፈገ፤ ይህም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ትእዛዝ መሠረት ወደ ተራራ መሸሽ የሚችሉበትን መንገድ ከፈተላቸው።—ማቴዎስ 24:15, 16
6 ከአራት ዓመት በኋላ፣ የማለፍ በዓል በሚከበርበት ወቅት አካባቢ ጄኔራል ቲቶ የአይሁዳውያኑን ዓመፅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የሮማውያንን ሠራዊት እየመራ ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ። ወታደሮቹ ኢየሩሳሌምን ከብበው በዙሪያዋ “ቅጥር” በመሥራታቸው ማምለጥ የማይሞከር ነገር ሆነ። (ሉቃስ 19:43, 44) በአካባቢው የጦርነት ዳመና አጥልቶ የነበረ ቢሆንም በመላው የሮማ ግዛት የሚኖሩ እጅግ በርካታ አይሁዳውያን የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተዋል። በዚህ ጊዜ ማምለጥ በማይችሉበት ወጥመድ ውስጥ ገቡ። ጆሴፈስ እንደተናገረው ለሮማውያኑ ከበባ ሰለባ ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ በዓሉን ለማክበር ከኢየሩሳሌም ውጪ የመጡ ሰዎች ናቸው። a በመጨረሻ ኢየሩሳሌም ስትደመሰስ በሮማ ግዛት ውስጥ ከሚኖሩት አይሁዳውያን መካከል አንድ ሰባተኛ የሚያህሉት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ ሲደመሰሱ የአይሁድ ግዛትም ሆነ በሙሴ ሕግ ላይ የተመሠረተው ሃይማኖታዊ ሥርዓት አብሮ ጠፍቷል። b—ማርቆስ 13:1, 2
7. ታማኝ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት ማምለጥ የቻሉት ለምንድን ነው?
7 በ70 እዘአ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምን ለቅቀው ባይወጡ ኖሮ ከሞት ወይም ከምርኮ ማምለጥ ባልቻሉ ነበር። ይሁን እንጂ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢየሱስ ከ37 ዓመታት በፊት የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ በማክበር እርምጃ ወስደዋል። ከተማዋን ለቅቀው መውጣት ብቻ ሳይሆን ወደ ከተማዋ ተመልሰው አልገቡም።
ሐዋርያት የተናገሯቸው ወቅታዊ ማስጠንቀቂያዎች
8. ጴጥሮስ የምንን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጠውን የትኛውን ምክር አስታውሶስ ሊሆን ይችላል?
8 በዛሬውም ጊዜ ከዚህ በእጅጉ የሚልቅ ጥፋት እያንዣበበ ሲሆን በዚህም አማካኝነት አሁን ያለው ሥርዓት ይወገዳል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሩሳሌም ከመጥፋትዋ ከስድስት ዓመታት በፊት የሰጠው ምክር በተለይ በዚህ ዘመን የሚኖሩ ክርስቲያኖች ነቅተው እንዲኖሩ የሚያሳስብ ወቅታዊ ማስጠንቀቂያ ነው። ጴጥሮስ፣ ክርስቲያኖች ‘የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ’ ቸል እንዳይሉ ‘ቅን ልቡናቸውን’ ማነቃቃት እንደሚያስፈልግ ተሰምቶት ነበር። (2 ጴጥሮስ 3:1, 2) ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ክርስቲያኖች ነቅተው እንዲኖሩ ሲያበረታታ “ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ” በማለት ለሐዋርያቱ የተናገረውን ነገር አስታውሶ መሆን ይኖርበታል።—ማርቆስ 13:33
9. (ሀ) አንዳንዶች ምን ዓይነት አፍራሽ አመለካከት ያዳብራሉ? (ለ) በተለይ የተጠራጣሪነት አመለካከት አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ዛሬም አንዳንድ ዘባቾች “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው?” በማለት ያፌዛሉ። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ሁሉም ነገር እንዳለ እንደሚቀጥል እንጂ ለውጥ እንደማይኖር ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው በጥርጣሬ የተሞላ አመለካከት አደገኛ ነው። ጥርጣሬ የአምላክ ቀን በቅርብ እንደሚመጣ ያለንን እምነት ሊያዳክምብን ይችላል። ይህ ደግሞ ከልክ በላይ ለራሳችን ምኞት ወደማደር ሊመራን ይችላል። (ሉቃስ 21:34) ከዚህም በላይ ጴጥሮስ እንደተናገረው እነዚህ ዘባቾች በኖኅ ዘመን የነበረውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ጨርሶ ያጠፋ ጎርፍ ተከስቶ እንደነበረ ዘንግተዋል። በእርግጥም ይህ ጥፋት ሥር ነቀል ለውጥ አምጥቶ ነበር!—ዘፍጥረት 6:13, 17፤ 2 ጴጥሮስ 3:4-6
10. ጴጥሮስ መታገሥ ያቃታቸውን ሰዎች ያበረታታቸው ምን በማለት ነበር?
10 ጴጥሮስ፣ አምላክ ብዙውን ጊዜ ፈጥኖ እርምጃ የማይወስደው ለምን እንደሆነ እንዲያስታውሱ በመርዳት አንባቢዎቹ የትዕግሥትን ባሕርይ እንዲያዳብሩ አበረታቷቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ጴጥሮስ “በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን” መሆኑን ነገራቸው። (2 ጴጥሮስ 3:8) ይሖዋ ዘላለማዊ አምላክ ስለሆነ የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት እርምጃ የሚወስድበትን ትክክለኛ ጊዜ መምረጥ ይችላል። በመቀጠልም ጴጥሮስ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ ይሖዋ ፍላጎት እንዳለው ጠቀሰላቸው። አምላክ ፈጥኖ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ይጠፉ የነበሩ ሰዎች በመታገሡ ምክንያት ሊድኑ ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4፤ 2 ጴጥሮስ 3:9) ይሁን እንጂ ይሖዋ ይታገሣል ሲባል ፈጽሞ እርምጃ አይወስድም ማለት አይደለም። ጴጥሮስ ‘የይሖዋ ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል’ በማለት ተናግሯል።—2 ጴጥሮስ 3:10
11. በመንፈሳዊ ነቅተን እንድንኖር ምን ሊረዳን ይችላል? ይህስ የይሖዋን ቀን መምጣት ‘ሊያስቸኩል’ የሚችለው እንዴት ነው?
11 ጴጥሮስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ምሳሌ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ሌባ መያዝ እንዲህ ቀላል አይደለም። እንቅልፍ ወሰድ መለስ ከሚያደርገው ዘብ ጠባቂ ይልቅ ሌሊቱን ሙሉ ነቅቶ የሚጠብቅ ሰው ሌባ መምጣቱን ሊያውቅ እንደሚችል የታወቀ ነው። አንድ ዘብ ጠባቂ ነቅቶ እንዲጠብቅ ምን ሊረዳው ይችላል? ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ ወዲያ ወዲህ መንቀሳቀሱ ንቁ እንዲሆን ይረዳዋል። በተመሳሳይም፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ነቅተን እንድንኖር ይረዳናል። ስለሆነም ጴጥሮስ “በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል” መመላለስ እንደሚኖርብን አሳስቦናል። (2 ጴጥሮስ 3:11) ይህን ዓይነት አኗኗር መከተላችን ‘የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እንድናስቸኩል’ ይረዳናል። የይሖዋን ፕሮግራም መለወጥ እንደማንችል የታወቀ ነው። መጨረሻው እርሱ በወሰነው ቀን መምጣቱ አይቀርም። ሆኖም በእርሱ አገልግሎት የተጠመድን ከሆነ ይህ ቀን በፍጥነት የደረሰ ሆኖ ይሰማናል።—1 ቆሮንቶስ 15:58
12. በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ትዕግሥት መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
12 ስለሆነም የይሖዋ ቀን እንደዘገየ የሚሰማው ሰው ጴጥሮስ ይሖዋ የቀጠረውን ቀን በትዕግሥት እንድንጠባበቅ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርግ ማበረታቻ ቀርቦለታል። እርግጥ ነው፣ አምላክ በመታገሡ ምክንያት ያገኘነውን ተጨማሪ ጊዜ በጥበብ ልንጠቀምበት ይገባል። ለምሳሌ ያህል ጊዜውን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማፍራት እንዲሁም በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ምሥራቹን ለመንገር ልንጠቀምበት እንችላለን። ነቅተን የምንኖር ከሆነ ይሖዋ በዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ላይ ‘ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ በሰላም’ ያገኘናል። (2 ጴጥሮስ 3:14, 15) ይህ እንዴት ያለ በረከት ያስገኝልናል!
13. ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሰጣቸው የትኛው ምክር ዛሬም ይሠራል?
13 ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ነቅቶ የመኖርን አስፈላጊነት ተናግሯል። “እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ” በማለት ምክር ሰጥቷል። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 6) ይህ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ በተቃረበበት በዚህ ጊዜ ምክሩ ምንኛ አስፈላጊ ነው! የይሖዋ አምላኪዎች ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ምንም ፍላጎት በሌለው ዓለም ውስጥ ይኖራሉ፤ ይህም ተጽእኖ ሊያሳድርባቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። ስለሆነም ጳውሎስ “የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር” በማለት መክሯል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) የአምላክን ቃል ዘወትር በማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ዘወትር በመሰብሰብ የጳውሎስን ምክር መከተልና ነቅተን መኖር እንችላለን።—ማቴዎስ 16:1-3
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ነቅተው እየኖሩ ነው
14. ጴጥሮስ ነቅተን እንድንኖር የሰጠውን ምክር ብዙ ሰዎች እየተከተሉ መሆናቸውን የሚያሳየው የትኛው አኃዛዊ መረጃ ነው?
14 በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በዚህ ማበረታቻ መሠረት በዛሬው ጊዜ ነቅተው የሚኖሩ ሰዎች አሉ? እንዴታ። በ2002 የአገልግሎት ዓመት 6, 304, 645 የሚያህል ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ተመዝግቧል። ይህም በ2001 ላይ የ3.1 በመቶ ጭማሪ መገኘቱን የሚጠቁም ነው። እነዚህ አስፋፊዎች ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በመናገር 1, 202, 381, 302 ሰዓት ማሳለፋቸው በመንፈሳዊ ነቅተው ለመኖራቸው ተጨባጭ ማስረጃ ነው። እነዚህ አስፋፊዎች እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ ላይ የሚካፈሉት ሲመቻቸው ብቻ አይደለም። በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ሥራ ነው። በኤል ሳልቫዶር የሚኖሩትን ኤድዋርዶን እና ናኦሚን እንደ ምሳሌ መመልከታችን ከእነዚህ አስፋፊዎች መካከል ብዙዎቹ ያላቸውን ዝንባሌ እንድንገነዘብ ይረዳናል።
15. ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊ ነቅተው እንደሚኖሩ የሚያሳየው ከኤል ሳልቫዶር የተገኘው የትኛው ተሞክሮ ነው?
15 ከጥቂት ዓመታት በፊት ኤድዋርዶ እና ናኦሚ “የዚች ዓለም መልክ አላፊ [“ተለዋዋጭ፣” NW ] ነውና” ሲል ጳውሎስ የሰጠውን ማሳሰቢያ በጥሞና አሰቡበት። (1 ቆሮንቶስ 7:31) አኗኗራቸውን ቀላል አደረጉና የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ጊዜው እያለፈ ሲሄድ የተለያዩ በረከቶችን ከማግኘታቸውም በላይ በወረዳና በአውራጃ ሥራ ላይ የማገልገል መብት እስከማግኘት ደርሰዋል። ኤድዋርዶ እና ናኦሚ አንዳንድ ከባድ ችግሮች አጋጥሟቸው የነበረ ቢሆንም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ሲሉ ቁሳዊ ጥቅማቸውን መሥዋዕት ለማድረግ በመወሰናቸው ተቆጭተው አያውቁም። በኤል ሳልቫዶር ያሉትን 2, 454 አቅኚዎች ጨምሮ 29, 269 ከሚያህሉ አስፋፊዎች መካከል አብዛኞቹ ተመሳሳይ የሆነ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ አሳይተዋል። በዚህች አገር ውስጥ ባለፈው ዓመት 2 በመቶ ጭማሪ የተገኘበት አንደኛው ምክንያት ይህ ነው።
16. በኮት ዲቩዋር የሚኖር አንድ ወጣት ወንድም ምን ዓይነት ዝንባሌ አሳይቷል?
16 በኮት ዲቩዋር የሚኖር አንድ ወጣት ክርስቲያንም ተመሳሳይ ዝንባሌ አሳይቷል። ይህ ወጣት ለቅርንጫፍ ቢሮው እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በጉባኤ አገልጋይነት በማገልገል ላይ እገኛለሁ። ይሁንና እኔ ራሴ ምሳሌ ሳልሆን ወንድሞች አቅኚዎች እንዲሆኑ መምከሩ በጣም ከበደኝ። በመሆኑም ጥሩ ደመወዝ ያስገኝልኝ የነበረውን ሥራዬን ትቼ የራሴን ሥራ ጀመርኩኝ፤ ይህም ለአገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ እንዳገኝ አስችሎኛል።” ይህ ወጣት ወንድም 6, 701 አስፋፊዎች ባሉባትና ባለፈው ዓመት የ5 በመቶ ጭማሪ ባደረገችው በኮት ዲቩዋር ከሚያገለግሉት 983 አቅኚዎች መካከል አንዱ ነው።
17. በቤልጅየም የምትኖር አንዲት ወጣት ምሥክር ሰዎች ያላቸውን ጭፍን ጥላቻ ፈርታ ዝም ያላለችው እንዴት ነው?
17 በቤልጅየም የሚኖሩ 24, 961 የመንግሥቱ አስፋፊዎች አሁንም ድረስ መሠረተ ቢስ ጥላቻና አድልዎ ይፈጸምባቸዋል። ሆኖም ይህ ለፍርሃት እጃቸውን በመስጠት አገልግሎታቸውን በቅንዓት ከማከናወን ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም። የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንዲት የ16 ዓመት ወጣት ክፍል ውስጥ በግብረ ገብ ክፍለ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መናፍቃን እንደሆኑ ሲነገር ሰማች። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት በትክክል ምን ዓይነት እንደሆነ ለመግለጽ እንዲፈቀድላት ጠየቀች። የይሖዋ ምሥክሮች —ከስሙ በስተጀርባ ያለ ድርጅት የተባለውን የቪዲዮ ካሴትና የይሖዋ ምሥክሮች —እነማን ናቸው? (እንግሊዝኛ) የተባለውን ብሮሹር ተጠቅማ የይሖዋ ምሥክሮችን ትክክለኛ ማንነት አስረዳች። የሰጠችው ማብራሪያ ከፍተኛ አድናቆትና ተቀባይነት በማግኘቱ በቀጣዩ ሳምንት ውስጥ ለተማሪዎቹ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት ብቻ የሚመለከት ፈተና ተሰጣቸው።
18. በአርጀንቲና እና በሞዛምቢክ የሚገኙ አስፋፊዎች የኢኮኖሚ ችግር ይሖዋን ከማገልገል እንዳላገዳቸው የሚያሳይ ምን ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል?
18 ብዙ ክርስቲያኖች በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ከባድ ችግሮችን መጋፈጥ ግድ ሆኖባቸዋል። ይሁንና ይሖዋን ከማገልገል እንዲያግዳቸው አይፈቅዱም። በመገናኛ ብዙሃን በሰፊው እንደተገለጸው አርጀንቲና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ቢያጋጥማትም ባለፈው ዓመት 126, 709 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት አድርጋለች። ሞዛምቢክ ውስጥ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ድህነት አለ። ሆኖም በዚህች አገር ውስጥ የ4 በመቶ ጭማሪ በመገኘቱ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ላይ የተካፈሉት አስፋፊዎች ቁጥር 37, 563 እንደደረሰ ተገልጿል። በአልባኒያ ውስጥ ብዙ ሰዎች ኑሮ በእጅጉ ከብዷቸዋል። ሆኖም በዚች አገር ውስጥ 12 በመቶ የሆነ ግሩም ጭማሪ በመገኘቱ ከፍተኛው የአስፋፊዎች ቁጥር 2, 708 ሆኗል። የይሖዋ አገልጋዮች መንግሥቱን እስካስቀደሙ ድረስ ምንም ዓይነት ችግር መንፈሱን ሊያግድ እንደማይችል ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል።—ማቴዎስ 6:33
19. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ብዙ በግ መሰል ሰዎች እንዳሉ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ከዓመታዊው ሪፖርት ውስጥ የይሖዋ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ነቅተው በመኖር ላይ መሆናቸውን የሚያሳየው አንዳንድ ገጽታ ምንድን ነው? (ከገጽ 12-15 ያለውን ሰንጠረዥ ተመልከት)
19 ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ በእያንዳንዱ ወር በአማካይ 5, 309, 289 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዳሉ ሪፖርት መደረጉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ብዙ በግ መሰል ሰዎች እንዳሉ የሚጠቁም ነው። በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከተገኙት 15, 597, 746 ተሰብሳቢዎች ውስጥ አብዛኞቹ ይሖዋን የሚያገለግሉ አይደሉም። እነዚህ ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ያላቸውን እውቀት ይበልጥ እንዲያሳድጉ ምኞታችን ነው። ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመንፈስ ቅዱስ ከተቀቡት ወንድሞቻቸው ጋር ‘ሌሊትና ቀን በመቅደሱ’ የሚያቀርቡት አገልግሎት እያስመዘገበ ያለው ውጤት በጣም የሚያስደስት ነው።—ራእይ 7:9, 15፤ ዮሐንስ 10:16
ከሎጥ የምናገኘው ትምህርት
20. ከሎጥና ከሚስቱ ሁኔታ ምን እንማራለን?
20 እርግጥ ነው፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም አንዳንድ ጊዜ የጥድፊያ ስሜታቸው ሊቀዘቅዝባቸው ይችላል። የአብርሃም የወንድሙ ልጅ የነበረውን ሎጥን እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። ሁለት መላእክት አምላክ ሰዶምንና ገሞራን ሊያጠፋ መሆኑን ነገሩት። ሎጥ ‘በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ ተገፍቶ’ ስለነበር እንደሚጠፉ መስማቱ አላስደነቀውም። (2 ጴጥሮስ 2:7) ይሁንና ሁለቱ መላእክት ሎጥ በፍጥነት ሰዶምን ለቅቆ እንዲወጣ ቢነግሩትም ‘ዘገየ።’ ከዚህም የተነሳ ሁለቱ መላእክት የሎጥንና የቤተሰቡን እጅ ይዘው ከከተማው ማውጣት ግድ ሆኖባቸው ነበር። በኋላም የሎጥ ሚስት ሁለቱ መላእክት ወደኋላ እንዳይመለከቱ የሰጡትን ትእዛዝ ሳትጠብቅ ቀረች። ትእዛዙን ችላ ማለቷ ሕይወቷን አሳጥቷታል። (ዘፍጥረት 19:14-17, 26) ኢየሱስ “የሎጥን ሚስት አስቧት” በማለት አስጠንቅቋል።—ሉቃስ 17:32
21. ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ነቅተን መኖር የሚኖርብን ለምንድን ነው?
21 በመግቢያችን ላይ በተጠቀሱት በፖምፔ እና በሄርኩላኒየም የደረሰው የተፈጥሮ አደጋ፣ ከኢየሩሳሌም መጥፋት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙት ክስተቶች እንዲሁም በኖኅ ዘመን የደረሰው የጥፋት ውኃና የሎጥ ታሪክ ማስጠንቀቂያ ማዳመጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምሩናል። የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ስለ መጨረሻው ዘመን የተነገሩት ምልክቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን እንገነዘባለን። (ማቴዎስ 24:3) ከሐሰት ሃይማኖት ወጥተናል። (ራእይ 18:4) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ‘የይሖዋን ቀን መምጣት ማስቸኮል’ ይኖርብናል። (2 ጴጥሮስ 3:12) አዎን፣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ነቅተን መኖር በሚገባን ጊዜ ውስጥ እንገኛለን! ነቅተን ለመኖር ልንወስዳቸው የሚገቡን እርምጃዎችና ልናዳብራቸው የሚያስፈልጉን ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም ከ120, 000 በላይ ነዋሪዎች ነበራት ማለት አይቻልም። ዩሴቢየስ በ70 እዘአ 300, 000 ነዋሪዎች የማለፍን በዓል ለማክበር ከይሁዳ አውራጃ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተዋል የሚል ግምት አለው። የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል የተቀሩት የመጡት ከሌሎች የሮማ ግዛቶች መሆን ይኖርበታል።
b እርግጥ ነው፣ የሙሴ ሕግ በይሖዋ ዘንድ በ33 እዘአ በአዲሱ ቃል ኪዳን ተተክቷል።—ኤፌሶን 2:15
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በከተማይቱ ላይ ከደረሰው ጥፋት እንዲያመልጡ ያስቻላቸው የትኛው ሁኔታ ነበር?
• ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፏቸው ደብዳቤዎች ላይ የሚገኘው ምክር ነቅተን እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው?
• በዛሬው ጊዜ ነቅተው በመኖር ላይ እንዳሉ ያስመሰከሩት እነማን ናቸው?
• ስለ ሎጥና ስለ ሚስቱ ከሚናገረው ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[ከገጽ 12-15 የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የ2002 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት
(መጽሔቱን ተመልከት)
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ66 እዘአ በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ታዝዘዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳቸው ነቅቶ ለመኖር ይረዳቸዋል