የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
ጳውሎስ “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
ጳውሎስ የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ስለተቋቋመበት መንገድ ሲናገር እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር:- “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።” (1 ቆሮንቶስ 11:25, 26) አንዳንዶች እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ጊዜ ሁሉ” የሚለው ሐረግ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል በተደጋጋሚ ማለትም ብዙ ጊዜ ሊከበር እንደሚገባው ያሳያል የሚል አመለካከት አላቸው። በመሆኑም የሞቱን መታሰቢያ በዓመት አንድ ጊዜ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ያከብሩታል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንደዚያ ማለቱ ነበርን?
ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ካቋቋመ ወደ 2,000 ዓመት ሊሆነው ምንም ያህል አልቀረውም። በመሆኑም የመታሰቢያው በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንኳን እየተከበረ ከ33 እዘአ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተከብሯል ማለት ነው። ይሁን እንጂ በ1 ቆሮንቶስ 11:25, 26 ላይ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው የመታሰቢያው በዓል ምን ያህል ጊዜ መከበር እንዳለበት ሳይሆን እንዴት መከበር እንዳለበት ነው። ጳውሎስ እዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል “ብዙ ጊዜ” ወይም “በተደጋጋሚ” የሚል ትርጉም ያለውን ፖላኪስ ሳይሆን “እንደዚህ ባደረጋችሁ ቁጥር” የሚል ትርጓሜ ያለውን ኦሳኪስ የሚለውን ቃል ነው። ጳውሎስ ‘እንደዚህ ባደረጋችሁ ቁጥር የጌታን ሞት ትናገራላችሁ’ ማለቱ ነበር። a
ይህ ከሆነ ታዲያ የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል በዓመት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ መከበር ይኖርበታል? በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ማክበሩ ተገቢ ነው። መታሰቢያ በዓል እንደመሆኑ መጠን እንደሌሎች የመታሰቢያ በዓሎች ሁሉ በዓመት አንድ ጊዜ መከበር ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የሞተው አይሁዳውያን የማለፍን በዓል በሚያከብሩበት ዕለት ሲሆን ይህ በዓል የሚከበረው በዓመት አንድ ጊዜ ነበር። የማለፍ በዓል በተቋቋመበት ዕለት የቀረበው መሥዋዕት በግብፅ የነበሩ እስራኤላውያንን የበኩር ልጆች ሕይወት ከማትረፉም በላይ ለሕዝቡ ከባርነት ነጻ መውጣት መንገድ እንደጠረገላቸው ሁሉ የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞትም መንፈሳዊ እስራኤላውያን የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበት መንገድ ከፍቶላቸዋል። በመሆኑም ጳውሎስ ኢየሱስን “የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ” ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 5:7 አ.መ.ት ፤ ገላትያ 6:16) የኢየሱስ ሞት የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ከሚከበረው የአይሁዳውያን የማለፍ በዓል ጋር በዚህ መንገድ መዛመዱ ይህ በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሊከበር እንደሚገባ የሚጠቁም ተጨማሪ ማስረጃ ነው።
ከዚህም በላይ ጳውሎስ የኢየሱስን ሞት አይሁዳውያን በየዓመቱ ከሚያከብሩት ሌላ በዓል ይኸውም ከስርየት ቀን ጋር አዛምዶታል። ዕብራውያን 9:25, 26 እንዲህ ይላል:- “ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ [በስርየት ቀን] የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፣ [ኢየሱስ] ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ . . . አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” የኢየሱስ መሥዋዕት ዓመታዊውን የስርየት ቀን መሥዋዕት ስለተካው የሞቱ መታሰቢያ በዓል በዓመት አንድ ጊዜ መከበሩ ተገቢ ነው። የመታሰቢያውን በዓል በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ለማክበር የሚያስችል አንድም ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ የለም።
ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በሁለተኛው መቶ ዘመን በትንሿ እስያ የነበሩት ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በዓል “በአይሁዳውያን የመጀመሪያው ወር [ኒሳን] በአሥራ አራተኛው ቀን ላይ” የማክበር ልማድ እንደነበራቸው ታሪክ ጸሐፊው ጆን ሎውረንስ ፎን ሞስሃይም ዘግበዋል። በዓሉን በዓመት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ማክበር በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እየተለመደ የመጣው በኋለኞቹ ዓመታት ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1 ሳሙኤል 1:3, 7 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። እዚህ ላይ “ጊዜ ሁሉ” የሚለው አገላለጽ ሕልቃናና ሁለት ሚስቶቹ “በየዓመቱ” ወይም በዓመት አንድ ጊዜ ሴሎ ወደሚገኘው የመገናኛ ድንኳን ሲሄዱ የተፈጸመውን ሁኔታ ያመለክታል።