ጽናቷ ክሷታል
ጽናቷ ክሷታል
ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች የሚወዱት ሰው ስለ አምላክ ዓላማዎች ተምሮ ደስ ብሎት እንዲኖር ይፈልጋሉ። አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ ሲወስን ሌሎች ወጣትም ሆኑ አረጋውያን በመልካም አኗኗራቸው ግለሰቡ እንዲህ ያለውን ጥበብ የተሞላበት እርምጃ እንዲወስድ ረድተውት ሊሆን ይችላል። ኬአሪም የተባለች በሜክሲኮ የምትኖር አንዲት በአሥራዎቹ እድሜ የምትገኝ ልጃገረድ ሁኔታም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የልዩ ስብሰባ ቀን የሚከተለውን ማስታወሻ ለወንድሞች ሰጠቻቸው:-
“ደስታዬን ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ። ለምን እንደዚህ እንደምል ልንገራችሁ። የዛሬ 18 ዓመት ገና እኔ ከመወለዴ በፊት ወላጆቼ እውነትን ሰሙ። እናቴ በኋላም እኔና ወንድሜ በእውነት መንገድ መጓዝ ጀመርን። ሦስታችንም አንድ ላይ ሆነን አባታችን በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምር ወደ ይሖዋ እንጸልይ ነበር። የዛሬው ዕለት ለእኛ ልዩ ቀን ነው። ምክንያቱም ከ18 ዓመታት በኋላ አባቴ ዛሬ ይጠመቃል። ለዓመታት በጉጉት ስንጠባበቀው የነበረው ይህ ቀን ከመድረሱ በፊት ይሖዋ መጨረሻውን ባለማምጣቱ አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ፣ አመሰግንሃለሁ!”
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የዚች ወጣት ልጃገረድ ቤተሰብ በ1 ጴጥሮስ 3:1, 2 ላይ “እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን መሠረታዊ ሥርዓት እንደሠሩበት ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲሁም ወጣቷ ኬአሪም በዘዳግም 5:16 ላይ ያሉትን “እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር” የሚሉትን ቃላት በሥራ ላይ አውላ መሆን አለበት። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላቸውና ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቃቸው ለኬአሪምና ለቤተሰቧ በእርግጥም በረከት አምጥቶላቸዋል።