በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” ያደረጉት አስደሳች ስብሰባ

“ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” ያደረጉት አስደሳች ስብሰባ

“ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” ያደረጉት አስደሳች ስብሰባ

ዓለም በሥነ ምግባር፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ ቀውሶች እየታመሰ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን በዚህ ሁሉ አለመረጋጋት መሃል ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በሚል ጭብጥ የሦስት ቀናት የአውራጃ ስብሰባዎች አድርገው ነበር። ከግንቦት 2002 ጀምሮ እነዚህ ስብሰባዎች በዓለም ዙሪያ ተካሂደዋል።

ስብሰባዎቹ በእርግጥም አስደሳች ወቅቶች ነበሩ። እስቲ ይህንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሚያንጽ ፕሮግራም አጠር ባለ መልኩ እንከልስ።

የመጀመሪያው ቀን ኢየሱስ ባሳየው ቅንዓት ላይ ያተኮረ ነበር

የስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ጭብጥ “ጌታችን ኢየሱስ ያሳየውን የቅንዓት መንፈስ ኮርጁ” የሚል ነበር። (ዮሐንስ 2:17) “እናንት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አንድ ላይ በመሰብሰባችሁ ደስ ይበላችሁ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ልዩ መለያ የሆነው ደስታ ተካፋዮች እንዲሆኑ ከልብ የሚጋብዝ ነበር። (ዘዳግም 16:15) ይህን ንግግር ተከትሎ ቀናተኛ ከሆኑ የምሥራቹ ሰባኪዎች ጋር ቃለ ምልልስ ተደረገ።

“በይሖዋ ደስ ይበላችሁ” የሚለው ንግግር መዝሙር 37:1-11ን ቁጥር በቁጥር የሚያብራራ ነበር። ክፉዎች ያገኙትን የይምሰል ስኬት አይተን ‘እንዳንቀና’ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። ክፉዎች ስለ እኛ የተሳሳተ ነገር ቢናገሩም ጊዜው ሲደርስ ይሖዋ በእርግጥ ታማኝ ሕዝቦቹ እነማን እንደሆኑ ግልጽ ያደርጋል። “አመስጋኝ ሁኑ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ለአምላክ አመስጋኝነታችንን እንዴት ማሳየት እንደምንችል አብራርቷል። ሁሉም ክርስቲያኖች ለይሖዋ “የምሥጋናን መሥዋዕት” ማቅረብ አለባቸው። (ዕብራውያን 13:15) በይሖዋ አገልግሎት ላይ የምናውለው ጊዜ መጠን የተመካው ባለን የአመስጋኝነት መንፈስና በሁኔታዎቻችን ላይ እንደሆነ እሙን ነው።

የጭብጡ ቁልፍ ንግግር “የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በከፍተኛ ቅንዓት ያገለግላሉ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን ከሁሉ የላቀው የቅንዓት ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አጉልቷል። ሰማያዊው መንግሥት በ1914 ከተቋቋመ በኋላ እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ መንግሥቱ መቋቋም የሚናገረውን ምሥራች ለማወጅ ቅንዓት አስፈልጓቸዋል። ተናጋሪው በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ የተካሄደውን ስብሰባ ጠቀሰና “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ!” የሚለውን ታሪካዊ ጥሪ አስታወሰ። ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የነበራቸው ቅንዓት ስለ መንግሥቱ የሚናገሩትን ግሩም እውነቶች ለአሕዛብ ሁሉ እንዲያውጁ አነሳስቷቸዋል።

“ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለሆነ አትፍሩ” በሚል ርዕስ ከሰዓት በኋላ የቀረበው ንግግር የአምላክ ሕዝቦች የሰይጣን ዋነኛ ዒላማ መሆናቸውን ገለጸ። ይሁን እንጂ ተቃውሞ ቢያጋጥመንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው ስለሚገኙትና በጊዜያችን ስላሉት የእምነት ምሳሌዎች ማሰባችን መከራዎችንና ፈተናዎችን ያለ ፍርሃት በድፍረት መቋቋም እንድንችል ብርታት ይሰጠናል።​​—⁠⁠ኢሳይያስ 41:10

ቀጥሎ “የሚክያስ ትንቢት በይሖዋ ስም እንድንሄድ ብርታት ይሰጠናል” የሚል ጭብጥ ያለው ባለ ሦስት ክፍል ሲምፖዚየም ቀረበ። የመጀመሪያው ተናጋሪ ሚክያስ በኖረበት ወቅት የነበረውን የሥነ ምግባር ዝቅጠት፣ ሃይማኖታዊ ክህደትና ፍቅረ ነዋይን የማሳደድ ዝንባሌ በጊዜያችን ካለው ሁኔታ ጋር ካወዳደረ በኋላ “ታዛዥ ልብ እንዲኖረን ብንጥር፣ በቅዱስ አኗኗር ብንመላለስ፣ ሕይወታችን ለአምላክ ማደራችንን በሚያሳዩ ድርጊቶች እንዲሞላ ብናደርግ እንዲሁም የይሖዋ ቀን መምጣቱ እንደማይቀር ባንዘነጋ ስለወደፊቱ ጊዜ ያለን ተስፋ አስተማማኝ ይሆናል” በማለት ገለጸ።​​—⁠⁠2 ጴጥሮስ 3:11, 12

ሁለተኛው የሲምፖዚየሙ ተናጋሪ ሚክያስ በይሁዳ አለቆች ላይ ስለሰነዘረው ውግዘት ተናገረ። አለቆቹ አይዞህ ባይ የሌላቸውን ድሆች ይጨቁኑ ነበር። ሚክያስ እውነተኛው አምልኮ ድል የሚቀዳጅ መሆኑንም ተንብዮ ነበር። (ሚክያስ 4:1-5) እኛም የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በሚሰጠን ኃይል ይህንን የሚያነቃቃ የተስፋ መልእክት ለማወጅ ቆርጠናል። ይሁን እንጂ አካላዊ ሕመም ወይም ሌላ ችግር የምናደርገውን ተሳትፎ እንደገደበብን ቢሰማንስ? ሦስተኛው ተናጋሪ “ይሖዋ ከእኛ የሚፈልጋቸው ነገሮች ምክንያታዊና ሊደረስባቸው የሚችሉ” መሆናቸውን ተናገረ። ከዚያም ሚክያስ 6:​8 ላይ የሰፈረው “እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” የሚለው ሐሳብ የሚሠራባቸውን የተለያዩ ዘርፎች አብራራ።

የዓለም የሥነ ምግባር ዝቅጠት በክርስቲያኖች ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል “ልባችሁን በመጠበቅ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆናችሁ ኑሩ” በሚል ርዕስ ከቀረበው ንግግር ሁላችንም ጥቅም አግኝተናል። ለምሳሌ ያህል በሥነ ምግባር ንጹሕ መሆናችን ደስታ የሞላበት ትዳር ለመመሥረት እንድንችል ይረዳናል። ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን የጾታ ብልግና የመፈጸምን ሐሳብ ለአፍታም ቢሆን ወደ አእምሯችን ልናመጣው አይገባም።​​—⁠⁠1 ቆሮንቶስ 6:18

“ከመታለልም ሆነ ከማታለል ተጠበቁ” የሚለው ንግግር በከሃዲዎች የሚሰራጩትን የተጣመሙ እውነቶች፣ ከፊል እውነቶችና ዓይን ያወጡ ውሸቶች እንደ መርዝ አድርገን መመልከታችን የጥበብ እርምጃ እንደሆነ አብራርቷል። (ቆላስይስ 2:8) እንዲሁም ምንም የከፋ መዘዝ ሳይደርስብን የኃጢአት ፍላጎታችንን ማርካት እንደምንችል አድርገን በማሰብ ራሳችንን ማታለል የለብንም።

የመጀመሪያው ዕለት የመደምደሚያ ንግግር “እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልኩ” የሚል ነበር። የዓለም ሁኔታዎች ይበልጥ እየተባባሱ በሄዱ መጠን ይሖዋ በቅርቡ ጽድቅ የሰፈነበትን አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩት እነማን ናቸው? ይሖዋን የሚያመልኩ ብቻ ናቸው። ተናጋሪው እኛ፣ ልጆቻችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ለዚህ አዲስ ዓለም እንድንበቃ ለመርዳት እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ የተባለ አዲስ የማጥኛ መጽሐፍ መውጣቱን ገለጸ። ይህን መጽሐፍ በማግኘታችን ምንኛ ተደስተናል!

ሁለተኛው ቀን በጎ ለማድረግ መቅናት አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጎላ ነበር

የስብሰባው ሁለተኛ ቀን “በጎ ለማድረግ የምትቀኑ ሁኑ” የሚል ጭብጥ ነበረው። (1 ጴጥሮስ 3:13) የመጀመሪያው ተናጋሪ የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ያብራራ ሲሆን የዕለቱን ጥቅስ አዘውትሮና ትርጉም ባለው መንገድ መመርመር ቅንዓታችንን እንደሚያሳድግልን ጎላ አድርጎ ገለጸ።

ከዚያም “አገልግሎታቸውን የሚያከብሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” የሚል ጭብጥ ያለው ሲምፖዚየም ቀረበ። የመጀመሪያው ክፍል በአምላክ ቃል በሚገባ መጠቀምን የሚያጎላ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) በመጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ መጠቀማችን በሰዎች ሕይወት ላይ ‘እንዲሠራ’ ያስችለዋል። (ዕብራውያን 4:12) የሰዎችን ትኩረት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መሳብና አሳማኝ በሆነ መንገድ ከእርሱ እየጠቀስን ማመራመር አለብን። የሲምፖዚየሙ ሁለተኛ ክፍል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በተደጋጋሚ ተመላልሶ መጠየቅ እንድናደርግላቸው የሚያሳስብ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 3:6) ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሳይዘገዩ ተመላልሶ ለመርዳት ዝግጅትና ድፍረት ያስፈልጋል። ሦስተኛው የሲምፖዚየሙ ክፍል በአገልግሎት ላይ የሚያጋጥመንን እያንዳንዱን ሰው ደቀ መዝሙር ሊሆን እንደሚችል አድርገን እንድንመለከተው የሚያሳስብ ሲሆን በመጀመሪያው ጉብኝታችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ግብዣ ማቅረብ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ሰዎችን መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ ሊሰጠን እንደሚችል ገልጿል።

የሚቀጥለው ንግግር ርዕስ “‘ሳናቋርጥ መጸለይ’ ያለብን ለምንድን ነው?” የሚል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በሁሉም የሕይወት ዘርፎች መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ ዘወር እንዲሉ አጥብቆ ያሳስባል። በግላችን ጸሎት የምናቀርብበት ጊዜ መመደብ አለብን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ ለልመናችን መልስ ከመስጠቱ በፊት ብዙ ጊዜ እንድንጸልይ ሊያደርግ ስለሚችል ሳናቋርጥ መጸለይ አለብን።​​—⁠⁠ያዕቆብ 4:8

“ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ያንጻል” የሚለው ንግግር የመናገር ችሎታችንን ራሳችንንና ሌሎችን ለማነጽ እንድንጠቀምበት አበረታቶናል። (ፊልጵስዩስ 4:8) የትዳር ጓደኛሞችና ልጆች በየቀኑ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ይኖርባቸዋል። ለዚህ እንዲረዳቸው ቤተሰቦች በቀን ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ አንድ ላይ ሆነው ለመመገብ ጥረት ማድረግ ያለባቸው ሲሆን ይህም የሚያንጹ መንፈሳዊ ውይይቶችን ለማድረግ ያስችላቸዋል።

የጠዋቱ ፕሮግራም የተጠናቀቀው “ራስን መወሰንና መጠመቅ መዳን የሚያስገኘው እንዴት ነው?” በሚለው አስደሳች ንግግር ነበር። የጥምቀት እጩዎቹ በቂ እውቀት የቀሰሙ፣ እምነት ያሳደሩ፣ ንስሐ የገቡ፣ ከክፉ ሥራቸው የተመለሱና ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ነበሩ። ተናጋሪው ከተጠመቁም በኋላ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም ቅንዓታቸውንና መልካም ምግባራቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧቸዋል።​​—⁠⁠ፊልጵስዩስ 2:15, 16

ከሰዓት በኋላ በቀረበው “ልካችሁን የምታውቁ ሁኑ፤ ቀና ዓይን ይኑራችሁ” በሚለው ንግግር ላይ ሁለት ዓቢይ ነጥቦች ጎላ ተደርገው ተገልጸዋል። ልክን ማወቅ ስለ አቅማችን ውስንነትና በአምላክ ፊት ስላለን ቦታ ትክክለኛ አመለካከት መያዝ ማለት ነው። ልክን ማወቅ ዓይናችን “ቀና” እንዲሆን ማለትም ትኩረታችን በቁሳዊ ነገሮች ላይ ሳይሆን በአምላክ መንግሥት ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን ይረዳናል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስለሚያሟላልን የምንጨነቅበት ምክንያት አይኖርም።​​—⁠⁠ማቴዎስ 6:22-24, 33, 34

የሚቀጥለው ተናጋሪ “መከራ ሲደርስባችሁ በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ይኑራችሁ” በሚል ርዕስ ትምክህታችንን በይሖዋ ላይ መጣል ያለብን ለምን እንደሆነ አብራራ። ያለብንን የግል ድካምና የኑሮ ወይም የጤና ችግር መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጠን እንለምነው፤ እንዲሁም ሌሎች እንዲረዱን እንጠይቅ። በፍርሃት ከመሸበር ወይም ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ቃሉን በማንበብ በአምላክ ላይ ያለንን ትምክህት ማጠናከር አለብን።​​—⁠⁠ሮሜ 8:35-39

የአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ሲምፖዚየም “የእምነታችን ጥንካሬ በተለያዩ መከራዎች ይፈተናል” የሚል ጭብጥ ነበረው። የመጀመሪያው ክፍል ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ስደት እንደሚያጋጥማቸው አስታወሰን። ስደት ለሌሎች ምሥክርነት ይሰጣል፣ እምነታችንን ያጠነክረዋል፤ እንዲሁም ለአምላክ ያለንን ታማኝነት ለማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል። ሕይወታችንን አደጋ ላይ መጣል ባንፈልግም ከስደት ለማምለጥ ብለን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ዘዴዎችን ፈጽሞ አንጠቀምም።​​—⁠⁠1 ጴጥሮስ 3:16

ሁለተኛው የሲምፖዚየሙ ተናጋሪ የገለልተኝነት አቋምን ለሚመለከቱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጠ። የጥንት ክርስቲያኖች ፀረ ጦርነት አቋም ባያራምዱም በዋነኛነት ታማኝ መሆን ያለባቸው ለአምላክ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከዓለም አይደላችሁም’ የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት በጥብቅ ይከተላሉ። (ዮሐንስ 15:19) የገለልተኝነት አቋማችንን በተመለከተ ፈተናዎች በድንገት ሊያጋጥሙን ስለሚችሉ ቤተሰቦች ጊዜ መድበው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የያዘውን መመሪያ መከለሳቸው አስፈላጊ ነው። ሦስተኛው የሲምፖዚየሙ ተናጋሪ እንደጠቆመው ሰይጣን በእኛ ላይ ጥቃት የሚሰነዝርበት ዋነኛ ዓላማ እኛን ቃል በቃል ለመግደል ሳይሆን ታማኝነታችንን እንድናጎድል ለማድረግ ነው። ከሌሎች የሚሰነዘርብንን ነቀፌታ፣ የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም የሚደረግብንን ተጽዕኖ፣ ያለብንን ስሜታዊ ስቃይና አካላዊ ሕመም በጽናት በመወጣት ይሖዋን እናስከብራለን።

የዕለቱ ፕሮግራም የተደመደመው “ወደ ይሖዋ ቅረቡ” በሚል ልብ የሚነካ ግብዣ ነበር። የይሖዋን ዋና ዋና ባሕርያት በሚገባ መረዳታችን ወደ እርሱ እንድንቀርብ ያደርገናል። ሕዝቡን በተለይም በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ገደብ የለሽ ኃይሉን ይጠቀማል። ፍትሑ ርኅራሄ የጎደለው ባሕርይ ሳይሆን ጽድቅን ለሚያደርግ ሁሉ ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኝበትን መንገድ እንዲያመቻች ይገፋፋዋል። የአምላክ ጥበብ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጽፍ በግልጽ ታይቷል። ከሁሉም ይበልጥ የሚማርከው ባሕርይው ፍቅሩ ሲሆን የሰው ዘር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን የሚያገኝበትን ዝግጅት እንዲያደርግ አነሳስቶታል። (ዮሐንስ 3:16) ተናጋሪው ይሖዋን የቅርብ ወዳጅህ አድርገው የተባለ ማራኪ አንድ አዲስ መጽሐፍ መውጣቱን በማስታወቅ ንግግሩን ደመደመ።

ሦስተኛው ቀን መልካም ለማድረግ እንድንቀና አበረታቶናል

የአውራጃ ስብሰባው ሦስተኛ ቀን ጭብጥ “መልካሙን ለማድረግ የሚቀና ሕዝብ” የሚል ነበር። (ቲቶ 2:14) የጠዋቱ ፕሮግራም አንድ ቤተሰብ በዕለቱ ጥቅስ ላይ ሲወያይ በሚያሳይ ክፍል ጀመረ። ከዚያ በመቀጠል “የምትመኩት በይሖዋ ላይ ነውን?” የሚል ንግግር ቀረበ። መንግሥታት በራሳቸው ጥበብና ጥንካሬ በመመካት ትምክህታቸውን በውሸት ተስፋ ላይ አድርገዋል። የአምላክ አገልጋዮች ግን መከራ ቢያጋጥማቸውም እንኳን በድፍረትና በደስታ ትምክህታቸውን በይሖዋ ላይ ይጥላሉ።​​—⁠⁠መዝሙር 46:1-3, 7-11

“ወጣቶች​​—⁠⁠ከይሖዋ ድርጅት በምታገኙት እገዛ ለሕይወታችሁ ዕቅድ አውጡ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር አንድ ወጣት ሕይወቱን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ሊጠቀምበት የሚችለው እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ነበር። ሃብት፣ ንብረትና ዝናን በማሳደድ ሕይወትን በተሻለ መንገድ መጠቀም አይቻልም። ወጣቶች ገና በለጋነታቸው እርሱን እንዲያስቡት አምላክ በፍቅር ያሳስባቸዋል። ተናጋሪው በወጣትነታቸው ክርስቲያናዊ አገልግሎትን ግባቸው ካደረጉ አንዳንድ ወጣቶች ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገ ሲሆን እንዲህ በማድረጋቸው ያገኙትን ደስታ ለመመልከት ችለናል። እንዲሁም ወጣት ምሥክሮች የይሖዋን ድርጅት ለዘላለም የሙጥኝ ብለው ለመዝለቅ የሚያስችላቸውን መሠረት እንዲጥሉ ለመርዳት ተብሎ የተዘጋጀው ወጣቶች​​⁠⁠በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አቅዳችኋል? የተባለው አዲስ ትራክት መውጣቱ ምንኛ ጠቃሚ ነበር!

ቀጥሎ “በአስቸጋሪ ጊዜያትም ጸንታችሁ ቁሙ” የተባለው የሚመስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማ ቀረበ። ድራማው ኤርምያስ ከልጅነቱ ጊዜ አንስቶ ኢየሩሳሌም እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ ያሳለፈውን ረጅም የነቢይነት ሕይወት የሚተርክ ነበር። ኤርምያስ ለተልዕኮው ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር። ቢሆንም ተቃውሞ እያለም እንኳን የተሰጠውን ተልዕኮ የተወጣ ሲሆን ይሖዋም ከመከራ አድኖታል።​​—⁠⁠ኤርምያስ 1:8, 18, 19

ድራማውን ተከትሎ “የአምላክን ቃል እንደ ኤርምያስ በድፍረት አውጁ” የሚል ንግግር ቀረበ። በዛሬው ጊዜ ያሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አብዛኛውን ጊዜ የሐሰትና የተንኮል ፕሮፓጋንዳ ዒላማዎች ናቸው። (መዝሙር 109:1-3) ይሁን እንጂ እኛም እንደ ኤርምያስ በይሖዋ ቃል በመደሰት የሚሰነዘርብንን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነቀፋ መቋቋም እንችላለን። ደግሞም ከእኛ ጋር የሚዋጉ እንደማያሸንፉ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ነን።

“የዚህ ዓለም መልክ እየተለወጠ ነው” በሚል ርዕስ የቀረበው የሕዝብ ንግግር በእርግጥም ወቅታዊ ነበር። የምንኖርበት ጊዜ በጣም አስገራሚ ለውጦች የታዩበት ወቅት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሁኔታዎች ጨምሮ “ሰላምና ደህንነት” የሚለው ልፈፋ አስፈሪ ወደሆነው የአምላክ የፍርድ ቀን እንደሚያደርሰን ይናገራል። (1 ተሰሎንቄ 5:3) ይህ የአምላክ የፍርድ ቀን ጦርነትን፣ ወንጀልን፣ ዓመፅን አልፎ ተርፎም በሽታን በማስወገድ አስደናቂ ለውጦች ያደርጋል። እንግዲያው ይህ ወቅት በዚህ ሥርዓት የምንታመንበት ጊዜ ሳይሆን ለአምላክ ያደርን ሆነንና የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ጠብቀን የምንኖርበት ጊዜ ነው።

የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ፍሬ ሐሳቦች ከቀረቡ በኋላ “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን መልካም ሥራ ይብዛላችሁ” በሚል ርዕስ የስብሰባው የመጨረሻ ንግግር ቀረበ። ተናጋሪው የስብሰባው ፕሮግራም እንዴት በመንፈሳዊ እንዳነቃቃንና ትምክህታችንን በይሖዋ ላይ እንድንጥል እንዳበረታታን ገለጸ። ንግግሩን ሲደመድም ንጹሕ፣ አፍቃሪና ቀናተኛ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች እንድንሆን አበረታታን።​​—⁠⁠1 ጴጥሮስ 2:12

“ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በተሰኘው የአውራጃ ስበስባ ላይ የቀረቡልንን መንፈሳዊ በረከቶች ተቋድሰን ወደ ቤታችን ስንመለስ በነህምያ ዘመን የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች የተሰማቸው ዓይነት ከፍተኛ የደስታ ስሜት እንደተሰማን አያጠራጥርም። (ነህምያ 8:12) ይህ መንፈስ የሚያነቃቃ የአውራጃ ስብሰባ በደስታ እንድትሞላና ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆነህ በቁርጠኝነት ወደፊት እንድትገፋ አላነሳሳህም?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አዲስ የማጥኛ መጽሐፍ!

የአውራጃ ስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ከመደምደሙ በፊት እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ (በእንግሊዝኛ) የተባለው አዲስ መጽሐፍ እንደወጣ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲነገር በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ተደስተው ነበር። መጽሐፉ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አጥንተው የጨረሱትን ለማስጠናት የተዘጋጀ ሲሆን “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎችንም እምነት የሚያጠናክር እንደሚሆን አያጠራጥርም።​​—⁠⁠ሥራ 13:48

[ምንጭ]

በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያለው ስዕል:- U.S. Navy photo

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ወደ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ የተደረገ ዝግጅት

በአውራጃ ስብሰባው ሁለተኛ ቀን የመጨረሻው ተናጋሪ ይሖዋን የቅርብ ወዳጅህ አድርገው (በእንግሊዝኛ) የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ መውጣቱን አስታውቆ ነበር። መጽሐፉ አራት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል የይሖዋን ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም ኃይሉን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ፍቅሩን አንድ በአንድ የሚያብራሩ ናቸው። እያንዳንዱ የመጽሐፉ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ባሕርያት ጉልህ በሆነ ሁኔታ እንዴት እንዳንጸባረቀ የሚያሳይ አንድ ምዕራፍ አለው። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ እኛም ሆንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ከይሖዋ አምላክ ጋር ጠንካራና የቅርብ ዝምድና እንድንመሠርት ለመርዳት ነው።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለወጣቶች የሚሆን መንፈሳዊ መመሪያ

በአውራጃ ስብሰባው ሦስተኛ ቀን ወጣቶች —⁠⁠በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል? የሚል ርዕስ ያለው አንድ ልዩ ትራክት ወጥቶ ነበር። ወጣት ምሥክሮች የወደፊት ሕይወታቸውን በሚመለከት ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርጉ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀው ይህ አዲስ ትራክት ይሖዋን ለዘላለም የማገልገል ግብ እንዲኖራቸው የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይሰጣል።