በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፊትና አሁን—የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

በፊትና አሁን—የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል”

በፊትና አሁን—የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ቶኒ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለ ሥርዓት አልበኛና ጠበኛ ልጅ ከመሆኑም በላይ በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ውስጥ በጣም መጥፎ ከሚባሉት አካባቢዎች አይታጣም ነበር። አንዳንዶቹ ጓደኞቹ ዱርዬዎች የነበሩ ሲሆን እነርሱም አብዛኛውን ጊዜ ቤት ሰብረው ይዘርፉ፣ ቡድን ለይተው ይደባደቡ እንዲሁም መሣሪያ እየተታኮሱ ይፋለሙ ነበር።

ቶኒ ሲጋራ ማጨስ የጀመረው ገና በዘጠኝ ዓመቱ ነው። አሥራ አራት ዓመት ሲሆነው አዘውትሮ ማሪዋና ይወስድ የነበረ ሲሆን ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር ይከተል ነበር። በ16 ዓመቱ ሄሮይን የተባለው አደገኛ ዕፅ ሱሰኛ ሆነ። በዚህም ምክንያት ቶኒ ኮኬይንና ኤል ኤስ ዲ የተባሉትን አደገኛ ዕፆች ጨምሮ “ሱሴን ሊያረካልኝ የሚችል ማንኛውንም ነገር እወስድ ነበር” በማለት ይናገራል። ከዚያም በመጥፎ ምግባራቸው ከታወቁ ሁለት የወንጀለኛ ቡድኖች ጋር በመሆን አደገኛ ዕፅ ማዘዋወር ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ በምሥራቃዊ አውስትራሊያ ጠረፍ ታዋቂ ከሆኑት የዕፅ ነጋዴዎች መካከል አንዱ ሆነ።

ቶኒ የሄሮይንና የማሪዋና ሱሱን ለማርካት በየዕለቱ ከ160 እስከ 320 የአሜሪካ ዶላር ያወጣ ነበር። ከዚህ የከፋው ግን አኗኗሩ በቤተሰቡ ላይ ያስከተለው መዘዝ ነበር። “በቤታችን ውስጥ ያስቀመጥነውን ዕፅና ገንዘብ የሚፈልጉ ወንጀለኞች በተደጋጋሚ ጊዜያት በእኔና በባለቤቴ ላይ ሽጉጥና ጩቤ መዝዘውብናል” ይላል። ቶኒ ሦስት ጊዜ ከታሰረ በኋላ የሕይወቱ መጨረሻ ምን እንደሚሆን ለማሰብ ተገደደ።

ቶኒ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ የነበረ ቢሆንም እንኳን ኃጢአተኞችን በሲኦል ውስጥ ለዘላለም እንደሚያቃጥል የሚነገርለትን አምላክ መቅረብ አልፈለገም። ሆኖም ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቱ መጥተው ሲያነጋግሩትና አምላክ እንዲህ ያለ ድርጊት እንደማይፈጽም ሲማር በጣም ተገረመ። እንዲያውም ሕይወቱን ማስተካከልና የአምላክን በረከቶች ማግኘት እንደሚችል ሲያውቅ ደስ አለው። “በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና” የሚሉት የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት ቶኒን ማረኩት። (ማርቆስ 10:27) በተለይ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚለው የሚያበረታታ ግብዣ ቶኒን በእጅጉ ነካው።​​—⁠⁠ያዕቆብ 4:8

አሁን ቶኒ ሕይወቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ጋር አስማምቶ የመኖር ፈታኝ ሁኔታ ገጠመው። እንዲህ ይላል:- “በመጀመሪያ ሲጋራ ማጨስ አቆምኩ፤ ከዚህ በፊት ይህንን ልማድ ለመተው ተደጋጋሚ ሙከራ ባደርግም ፈጽሞ አልተሳካልኝም ነበር። ሆኖም ከይሖዋ ባገኘሁት ኃይል ላለፉት 15 ዓመታት አብሮኝ ከቆየው ከሄሮይንና ከማሪዋና ሱስ መላቀቅ ችያለሁ። እነዚህን ልማዶች ፈጽሞ ማሸነፍ የምችል አይመስለኝም ነበር።”

አሁን ቶኒና ባለቤቱ አምላክ ሰዎችን በሲኦል ውስጥ ለዘላለም ያቃጥላል በሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት አይረበሹም፤ ከዚያ ይልቅ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አግኝተዋል። (መዝሙር 37:10, 11፤ ምሳሌ 2:21) ቶኒ “ሕይወቴን ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር አስማምቼ ለመኖር ረዘም ያለ ጊዜና ከፍተኛ ጥረት የጠየቀብኝ ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ ተሳክቶልኛል” በማለት ተናግሯል።

በእርግጥም የቀድሞው የዕፅ ሱሰኛ አኗኗሩን ለውጦ ክርስቲያን መሆን ችሏል። እሱና ባለቤቱ ጊዜያቸውንና ንብረታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዓታት ያሳልፋሉ። ከዚህም በላይ ሁለት ልጆቻቸውን በአምላካዊ ጎዳና ለማሳደግ ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ አስገራሚ ለውጥ ሊገኝ የቻለው የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን የመለወጥ ድንቅ ኃይል ስላለው ነው። በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።”​​—⁠⁠ዕብራውያን 4:12 አ.መ.ት 

እንደዚህ የመሰሉ አበረታች ተሞክሮዎች እያሉም እንኳን አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ቤተሰብን እንደሚያፈርስና የወጣቶችን መልካም ሥነ ምግባር እንደሚያበላሽ በመናገር መሠረተ ቢስ ክስ ይሰነዝራሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የቶኒ ተሞክሮ ይህንን አባባል ውድቅ የሚያደርግ ነው።

እንደ ቶኒ ሁሉ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ከአደገኛ ሱሶች መላቀቅ ችለዋል። እንዴት? በአምላክና በቃሉ ላይ በመታመንና አሳቢ የሆኑ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው በሚያደርጉላቸው ድጋፍ በመታገዝ ነው። ቶኒ እንዲህ በማለት በደስታ ስሜት ይናገራል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ለልጆቼ ጥበቃ እንደሆኑላቸው ተመልክቻለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ትዳሬን ታድጎልኛል። ጎረቤቶቼም ስለማይፈሩኝ አሁን የሰላም እንቅልፍ ይተኛሉ።”

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ከይሖዋ ባገኘሁት ኃይል ለ15 ዓመታት አብሮኝ ከቆየው የዕፅ ሱስ መላቀቅ ችያለሁ ’

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብዙ የዕፅ ሱሰኞች ከዚህ አደገኛ ልማድ እንዲላቀቁ ረድተዋቸዋል። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-

“በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) ዕፅ መውሰድ የአምላክን ሕግ ይጻረራል።

“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።” (ምሳሌ 9:10) ብዙዎች ስለ ይሖዋና ስለ መንገዶቹ ባገኙት ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አምላካዊ ፍርሃት ማዳበራቸው ከዕፅ ሱሰኝነት እንዲላቀቁ ረድቷቸዋል።

“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” (ምሳሌ 3:5, 6) በአምላክ ላይ መታመን ጎጂ ልማዶችን ለማሸነፍ ያስችላል።