እምነትህ ምን ያህል ጠንካራ ነው?
እምነትህ ምን ያህል ጠንካራ ነው?
“በእምነታችሁ ቆማችኋል።”—2 ቆሮንቶስ 1:24
1, 2. እምነት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው? እምነታችንን ማጠናከር የምንችለውስ እንዴት ነው?
የይሖዋ አገልጋዮች እምነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያውቃሉ። እንዲያውም ‘ያለ እምነት አምላክን ደስ ማሰኘት አይቻልም።’ (ዕብራውያን 11:6) በመሆኑም መንፈስ ቅዱስንና የመንፈሱ ፍሬ የሆነውን እምነት ለማግኘት እንጸልያለን። (ሉቃስ 11:13፤ ገላትያ 5:22, 23) የአምልኮ ባልንጀሮቻችንን በእምነታቸው ብንመስላቸው የእኛም እምነት ሊጠናከር ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ ዕብራውያን 13:7
2 የአምላክ ቃል ለክርስቲያኖች በሙሉ የሚሰጠውን መመሪያ በጥብቅ ከተከተልን እምነታችን ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ይሆናል። በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብና ‘ታማኙ መጋቢ’ በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች እየታገዝን ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት በማጥናት እምነታችን እንዲያድግ ማድረግ እንችላለን። (ሉቃስ 12:42-44፤ ኢያሱ 1:7, 8) ዘወትር በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እርስ በርስ በእምነት መበረታታት እንችላለን። (ሮሜ 1:11, 12፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እንዲሁም አገልግሎት ወጥተን ለሌሎች ምሥራቹን ስንናገር እምነታችን ይጠናከራል።—መዝሙር 145:10-13፤ ሮሜ 10:11-15
3. እምነታችንን በማሳደግ ረገድ አፍቃሪ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን እርዳታ ይሰጡናል?
3 አፍቃሪ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርና ማበረታቻ በመስጠት እምነታችንን እንድንገነባ ይረዱናል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን . . . በእምነታችሁ ቆማችኋልና” በማለት የተናገረው የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት መንፈስ አላቸው። (2 ቆሮንቶስ 1:23, 24) የ1980 ትርጉም ደግሞ “እናንተ በእምነታችሁ የጸናችሁ ስለሆናችሁ፣ እናንተን ደስ እንዲላችሁ አብረናችሁ እንሠራለን” ይላል። ጻድቅ በእምነት ይኖራል። እርግጥ ነው፣ እምነት ማሳየትም ሆነ በአቋማችን በታማኝነት መጽናት ያለብን እኛው ራሳችን ነን። በዚህ ረገድ ‘እያንዳንዳችን የገዛ ራሳችንን ሸክም መሸከም አለብን።’—ገላትያ 3:11፤ 6:5
4. ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ስላሳዩት እምነት የያዙት ዘገባ እምነታችንን ለማጠናከር የሚረዳን እንዴት ነው?
4 ቅዱሳን ጽሑፎች እምነት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ የበርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዘዋል። እነዚህ ሰዎች ያከናወኗቸውን በርካታ አስደናቂ ተግባራት እናውቅ ይሆናል፤ ሆኖም ባሳለፉት ረዥም የሕይወት ዘመናቸው በየዕለቱ ያሳዩትን እምነትስ ምን ያህል እናውቃለን? ከእኛ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ሥር እያሉ ያሳዩትን እምነት መመርመራችን እምነታችንን ለማጠናከር ሊረዳን ይችላል።
እምነት ድፍረት ይሰጠናል
5. እምነት የአምላክን ቃል በድፍረት እንድናውጅ እንደሚያበረታን የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?
5 እምነት የአምላክን ቃል በድፍረት እንድናውጅ ያበረታናል። ሄኖክ አምላክ ያስተላለፈውን የጥፋት ፍርድ በድፍረት ተንብዮአል። “እነሆ፣ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፣ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል” ሲል ተናግሯል። (ይሁዳ 14, 15) አምላክ የለሽ የሆኑት የሄኖክ ጠላቶች ይህን የፍርድ መልእክት ሲሰሙ እሱን ለመግደል እንደፈለጉ አያጠራጥርም። ሆኖም መልእክቱን በእምነትና በድፍረት የተናገረ ሲሆን አምላክም የሞት ጣር ሳይደርስበት በሞት እንዲያንቀላፋ በማድረግ “ወስዶታል።” (ዘፍጥረት 5:24፤ ዕብራውያን 11:5) እንዲህ ዓይነት ተአምራዊ እርዳታ እናገኛለን ብለን ባንጠብቅም ይሖዋ ቃሉን በእምነትና በድፍረት ማወጅ እንድንችል ለምናቀርበው ጸሎት መልስ ይሰጠናል።—ሥራ 4:24-31
6. ኖኅ ከአምላክ እምነትና ድፍረት ማግኘቱ የረዳው እንዴት ነው?
6 ኖኅ “ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ።” (ዕብራውያን 11:7፤ ዘፍጥረት 6:13-22) ከዚህም በላይ ኖኅ በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች የአምላክን ማስጠንቀቂያ በድፍረት ያወጀ ‘የጽድቅ ሰባኪ’ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) ይህ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ስናሳያቸው አንዳንዶች እንደሚያፌዙብን ሁሉ ኖኅ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ሲነግራቸው አፊዘውበት መሆን እንዳለበት የተረጋገጠ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:3-12) ይሁን እንጂ አምላክ እምነትና ድፍረት ስለሚሰጠን እንደ ሄኖክና ኖኅ እኛም የጥፋት መልእክቱን ማድረስ እንችላለን።
እምነት ትዕግሥተኞች ያደርገናል
7. አብርሃምና ሌሎች እምነትና ትዕግሥት ያሳዩት እንዴት ነበር?
7 በተለይ የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ስንጠባበቅ እምነትና ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልገናል። ‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል ከሚወርሱት’ መካከል ፈሪሃ አምላክ የነበረው አብርሃም ይገኝበታል። (ዕብራውያን 6:11, 12) ለኑሮ ምቹ የነበረችውን ዑርን ለቅቆ አምላክ ቃል በገባለት ምድር መጻተኛ ሆኖ የኖረው በእምነት ነበር። ይስሐቅና ያዕቆብ የዚሁ የተስፋ ቃል ወራሾች ነበሩ። ይሁን እንጂ “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙም።” “የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር [በእምነት] ይናፍቃሉ።” ከዚህም የተነሳ አምላክ “ከተማን አዘጋጅቶላቸዋል።” (ዕብራውያን 11:8-16) አዎን፣ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ እንዲሁም ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሚስቶቻቸው የአምላክን ሰማያዊ መንግሥት በትዕግሥት ተጠባብቀዋል። በዚያ መንግሥት ሥር በምድር ላይ ለመኖር ከሞት ይነሣሉ።
8. አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ትዕግሥትና እምነት ያሳዩት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነው?
8 አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ እምነታቸውን እስከ መጨረሻ ጠብቀዋል። ተስፋይቱን ምድር አልወረሱም፤ እንዲሁም በአብርሃም ዘር የምድር አሕዛብ ራሳቸውን ሲባርኩ አልተመለከቱም። (ዘፍጥረት 15:5-7፤ 22:15-18) ‘እግዚአብሔር የሠራት ከተማ’ የምትመሠረተው ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ እምነትና ትዕግሥት አሳይተዋል። በአሁኑ ጊዜ መሲሐዊው መንግሥት በሰማይ የተቋቋመ በመሆኑ እኛም እምነትና ትዕግሥት ማሳየት ይኖርብናል።—መዝሙር 42:5, 11፤ 43:5
እምነት የላቁ ግቦች እንድናወጣ ያስችለናል
9. እምነት ምን ዓይነት ግቦችን እንድናወጣ ይረዳናል?
9 ታማኞቹ የእምነት አባቶች እጅግ የላቁ ግቦች ስለነበሯቸው ወራዳ የሆነውን የከነዓናውያንን አኗኗር ፈጽሞ አልተከተሉም። በተመሳሳይ እምነት በክፉው በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ዓለም እንዳይውጠን መቋቋም የምንችልባቸውን መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ ያስችለናል።—1 ዮሐንስ 2:15-17፤ 5:19
10. ዮሴፍ በዓለም ታዋቂ ከመሆን ይልቅ እጅግ የላቀ ግብ እንደተከታተለ እንዴት እናውቃለን?
10 በመለኮታዊ አመራር አማካኝነት የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በግብፅ የምግብ አስተዳዳሪ ሆኖ አገልግሏል። ሆኖም በዚህ ዓለም ላይ ታላቅ ሰው የመሆን ግብ አልነበረውም። ዮሴፍ፣ ይሖዋ የሰጠው የተስፋ ቃል እንደሚፈጸም እምነት ስለነበረው የ110 ዓመት ሰው እያለ ወንድሞቹን “እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጐብኘትን ይጐበኛችኋል፣ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል” አላቸው። ዮሴፍ ተስፋይቱ ምድር እንዲቀበር ጠይቋል። ከሞተ በኋላ በሽቱ አሽተው ግብፅ ውስጥ በሣጥን አኖሩት። ሆኖም እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲወጡ ነቢዩ ሙሴ የዮሴፍ አጥንት በተስፋይቱ ምድር እንዲቀበር ወሰደው። (ዘፍጥረት 50:22-26፤ ዘጸአት 13:19) የዮሴፍ ዓይነት እምነት መያዛችን በዓለም ከሚገኝ እውቅና ይልቅ የላቁ ግቦችን እንድንከታተል ሊያነሳሳን ይገባል።—1 ቆሮንቶስ 7:29-31
11. ሙሴ መንፈሳዊ ግብ እንዳለው ያሳየው በምን መንገድ ነው?
11 ሙሴ በጣም የተማረ የግብፅ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል በመሆን ‘ለጊዜው በኃጢአት ከሚያገኘው ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መርጧል።’ (ዕብራውያን 11:23-26፤ ሥራ 7:20-22) ይህም ዓለማዊ ክብርንና ከሞተ በኋላ ባጌጠ የሬሳ ሣጥን ግብፅ ውስጥ በአንድ እውቅና ባተረፈ ቦታ በታላቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት የመቀበር አጋጣሚውን መሥዋዕት እንዲያደርግ ጠይቆበታል። ሆኖም መሥዋዕት ያደረገው ነገር “የእግዚአብሔር ሰው፣” የቃል ኪዳኑ መካከለኛ፣ የይሖዋ ነቢይና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በመሆን ካገኘው መብት ጋር ሲነጻጸር ፋይዳው ምን ያህል ነው? (ዕዝራ 3:2) ምኞትህ በሥራው ዓለም ከፍተኛ እድገት ማግኘት ነው? ወይስ እምነትህ እጅግ የላቀ መንፈሳዊ ግብ እንድታወጣ አስችሎሃል?
እምነት ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል
12. እምነት ረዓብ አኗኗሯን እንድትለውጥ የረዳት እንዴት ነው?
12 እምነት ሰዎች የላቁ ግቦች እንዲያወጡ ከማስቻሉም በተጨማሪ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲመሩም ይረዳቸዋል። ኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ረዓብ የግልሙትና ኑሮዋ ሕይወቷን ትርጉም የለሽ አድርጎባት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ እምነት ማሳየቷ ታላቅ ወሮታ እንድታገኝ አስችሏታል! ‘እስራኤላውያኑን መልእክተኞች ተቀብላ በማስተናገድና’ ከከነዓናውያን ጠላቶቻቸው በዘዴ ማምለጥ እንዲችሉ ‘በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ [በእምነት] ሥራ ጸድቃለች።’ (ያዕቆብ 2:24-26) በተጨማሪም እውነተኛው አምላክ ይሖዋ መሆኑን ተቀብላ የግልሙትና ሕይወቷን በመተው እምነት አሳይታለች። (ኢያሱ 2:9-11፤ ዕብራውያን 11:30, 31) ያገባችው ሰው አማኝ ያልሆነ ከነዓናዊ ሳይሆን የይሖዋ አገልጋይ ነበር። (ዘዳግም 7:3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 7:39) ረዓብ የመሲሑ ቅድመ አያት የመሆን ታላቅ መብት አግኝታለች። (1 ዜና መዋዕል 2:3-15፤ ሩት 4:20-22፤ ማቴዎስ 1:5, 6 አ.መ.ት ) ሥነ ምግባር የጎደለውን ሕይወት እርግፍ አድርገው እንደተዉ ሌሎች ሰዎች እርሷም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ከሞት የመነሳት ተጨማሪ ወሮታ ታገኛለች።
13. ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ የፈጸማቸው ኃጢአቶች ምንድን ናቸው? ሆኖም ምን ዓይነት ዝንባሌ አሳይቷል?
13 ረዓብ የግልሙትና ሕይወት ከተወች በኋላ ቀና መንገድ እንደተከተለች ግልጽ ነው። ሆኖም ሕይወታቸውን ለአምላክ ከወሰኑ በርካታ ዓመታት ያስቆጠሩ አንዳንድ ግለሰቦች ከባድ ኃጢአት ፈጽመዋል። ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ዝሙት ከፈጸመና ባልዋ በጦር ሜዳ እንዲገደል ካደረገ በኋላ ሴቲቱን ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት። (2 ሳሙኤል 11:1-27) ዳዊት በጥልቅ ሐዘን ንስሐ ከገባ በኋላ ይሖዋን “ቅዱስ መንፈስህን ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” በማለት ተማጸነ። አምላክም መንፈሱን አልወሰደበትም። ይሖዋ መሐሪ እንደሆነና በኃጢአት ምክንያት “የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ” እንደማይንቅ ዳዊት እምነት ነበረው። (መዝሙር 51:11, 17፤ ) ዳዊትና ቤርሳቤህ ባሳዩት እምነት የተነሳ የመሲሑ ቅድመ አያቶች የመሆን መብት አግኝተዋል።— 103:10-141 ዜና መዋዕል 3:5፤ ማቴዎስ 1:6, 16፤ ሉቃስ 3:23, 31
አምላክ የአገልጋዮቹን እምነት ያጠናክራል
14. ጌዴዎን ምን ዓይነት ማረጋገጫ አገኘ? እምነታችንን በተመለከተ ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
14 በእምነት የምንመላለስ ብንሆንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለን ማረጋገጫ ማግኘት እንፈልግ ይሆናል። “በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ” ከተባለላቸው አንዱ የሆነው መስፍኑ ጌዴዎን እንዲህ ያለ ማረጋገጫ ማግኘት ፈልጎ ነበር። (ዕብራውያን 11:32, 33) ምድያማውያንና ግብረአበሮቻቸው እስራኤልን በወረሩ ጊዜ የአምላክ መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ። ይሖዋ ከእርሱ ጋር ለመሆኑ ማረጋገጫ ለማግኘት የተባዘተ የበግ ጠጉር ሌሊቱን አውድማ ላይ በማኖር ምልክት ለማየት ፈለገ። በመጀመሪያው ምልክት መሬቱ ደረቅ ሆኖ በጠጉሩ ላይ ጠል ሆነ። በሁለተኛው ምልክት ላይ ደግሞ ጠጉሩ ደረቅ ሆኖ መሬቱ ጠል ያዘ። በባሕሪው ጠንቃቃ የሆነው ጌዴዎን ከእነዚህ ማረጋገጫዎች ባገኘው ብርታት በእምነት እርምጃ በመውሰድ የእስራኤልን ጠላቶች ድል አድርጓል። (መሳፍንት 6:33-40፤ 7:19-25) አንድ ከባድ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ማረጋገጫ ማግኘት ብንፈልግ ይህ እምነት እንደጎደለን የሚያሳይ ድርጊት አይደለም። ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ብንመረምር እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለማግኘት ብንጸልይ በእርግጥ እምነት እንዳለን እናሳያለን።—ሮሜ 8:26, 27
15. ባርቅ ባሳየው እምነት ላይ ማሰላሰላችን እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?
15 መስፍኑ ባርቅ በማበረታቻ መልክ ባገኘው ማረጋገጫ እምነቱ ተጠናክሯል። የከነዓኑ ንጉሥ ኢያቢስ ከሚያደርስባቸው ጭቆና እስራኤላውያንን ነፃ ለማውጣት እርምጃ እንዲወስድ ነቢይቱ ዲቦራ አደፋፍራዋለች። ባርቅ በእምነትና መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው ባገኘው ማረጋገጫ በቂ ትጥቅ የሌላቸውን 10, 000 ሰዎች ይዞ በሲሣራ የሚመራውንና በከፍተኛ የጦር ኃይል የተጠናከረውን የኢያቢስን ሠራዊት ድል አድርጓል። ይህ ድል ዲቦራና ባርቅ በተቀኙት መዝሙር በከፍተኛ ስሜት ተከብሯል። (መሳፍንት 4:1–5:31) ባርቅ በአምላክ የተሾመ የእስራኤል መሪ እንደመሆኑ ዲቦራ በሰጠችው ማበረታቻ እርምጃ በመውሰዱ በእምነት “የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ” ከተባለላቸው የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ለመሆን በቅቷል። (ዕብራውያን 11:34) ለይሖዋ ከምናቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተሰጠንን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ብቃት እንደሌለን ሆኖ ከተሰማን ባርቅ በእምነት ተነሳስቶ እርምጃ በመውሰዱ አምላክ እንዴት እንደባረከው ቆም ብለን ማሰባችን ለተግባር ሊያነሳሳን ይችላል።
እምነት ሰላም ለማስፈን ይረዳል
16. አብርሃም ሰላምን በመከታተል ረገድ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
16 እምነት ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ከባድ ኃላፊነቶችን ለመወጣት እንደሚረዳን ሁሉ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረንም ይረዳናል። በእረኞቻቸው መካከል ጠብ በመነሳቱ ምክንያት ለመለያየት በተገደዱበት ጊዜ አረጋዊው አብርሃም በዕድሜ ታናሹ የሆነው የወንድሙ ልጅ ሎጥ የተሻለውን የግጦሽ መሬት እንዲመርጥ ቅድሚያ ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 13:7-12) አብርሃም ይህን ችግር መፍታት እንዲችሉ አምላክ እንዲረዳቸው በእምነት ጸልዮ መሆን አለበት። የራሱን ፍላጎት ከማስቀደም ይልቅ ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ ፈትቷል። ከክርስቲያን ወንድማችን ጋር ብንጋጭ አብርሃም ያሳየውን ፍቅራዊ አሳቢነት በማስታወስ በእምነት እንጸልይ እንዲሁም ‘ሰላምን እንሻ።’—1 ጴጥሮስ 3:10-12
17. በጳውሎስ፣ በበርናባስና በማርቆስ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ተፈትቷል ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?
17 ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በእምነት ተግባራዊ ማድረግ ሰላም ለማስፈን እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እንመልከት። ጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ሊጀምር ሲል በቆጵሮስና በትንሹ እስያ የሚገኙትን ጉባኤዎች ተመልሰው እንዲጎበኙ ለበርናባስ ሐሳብ አቀረበለት። በርናባስ በጳውሎስ ሐሳብ ቢስማማም የአክስቱ ልጅ የሆነው ማርቆስ አብሯቸው እንዲመጣ ፈለገ። ማርቆስ ጵንፍልያ ላይ ትቷቸው ተመልሶ ስለነበር ጳውሎስ በሐሳቡ ሳይስማማ ቀረ። ይህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ በመካከላቸው ‘መከፋፋትን’ ፈጠረ። በርናባስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ሲያመራ ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን የጉዞ ጓደኛው አድርጎ በመምረጥ “አብያተ ክርስቲያናትንም እያጸና በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር።” (ሥራ 15:36-41) ከጊዜ በኋላ ማርቆስ ከጳውሎስ ጋር ሮም እንደነበረ መጠቀሱና ሐዋርያው ስለ እርሱ መልካም ቃል መናገሩ በመካከላቸው የተፈጠረው አለመግባባት ተፈትቶ እንደነበር ያሳያል። (ቆላስይስ 4:10፤ ፊልሞና 23, 24) ጳውሎስ በ65 እዘአ ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት ጢሞቴዎስን “ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው” ብሎት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:11) ጳውሎስ ከበርናባስና ከማርቆስ ጋር ያለውን ግንኙነት በማስመልከት በእምነት ተደጋጋሚ ጸሎት አቅርቦ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ይህም “የእግዚአብሔር ሰላም” የሚያመጣውን የአእምሮ ሰላም አስገኝቶለታል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
18. ኤዎድያንና ሲንጤኪን በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስወገድ ምን አድርገው መሆን አለበት?
18 እርግጥ ነው፣ ፍጹማን ባለመሆናችን “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን።” (ያዕቆብ 3:2) በጳውሎስ ዘመን በሁለት ክርስቲያን ሴቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበር ጳውሎስ እነርሱን በተመለከተ “በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ . . . እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ . . . በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:1-3) እነዚህ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች በማቴዎስ 5:23, 24 ላይ ተመዝግበው እንደሚገኙት ያሉትን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ በመካከላቸው የተፈጠረውን ቅራኔ ፈትተው እንደሚሆን አያጠራጥርም። ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በእምነት ተግባራዊ ማድረግ በዛሬውም ጊዜ ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
እምነት እንድንጸና ያስችለናል
19. ይስሐቅና ርብቃ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር? ይህስ እምነታቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋልን?
19 እምነት ካለን ችግሮችን በጽናት ማሳለፍም እንችላለን። አንድ የተጠመቀ የቤተሰባችን አባል የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ አማኝ ያልሆነ ሰው በማግባቱ ምክንያት አዝነን ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ይስሐቅና ርብቃ ልጃቸው ዔሳው ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሴቶች በማግባቱ በጣም አዝነው ነበር። ኬጢያዊያን ሚስቶቹ ‘ልባቸውን ያሳዝኑ’ ስለነበር ርብቃ “ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?” በማለት ምሬቷን እስከመግለጽ ደርሳ ነበር። (ዘፍጥረት 26:34, 35፤ 27:46) ሆኖም ይህ ፈታኝ ሁኔታ ይስሐቅና ርብቃ እምነታቸውን እንዲያጡ አላደረጋቸውም። እኛም ልንገፋው የማንችለው አስቸጋሪ ሁኔታ በሚገጥመን ጊዜ ጠንካራ እምነት እናሳይ።
20. ኑኃሚንና ሩት ካሳዩት እምነት ምን ትምህርት እናገኛለን?
20 በዕድሜ የገፋችው መበለቲቱ ኑኃሚን አይሁዳዊት ስትሆን የመሲሑ ቅድመ አያት የሚሆኑ ወንዶች ልጆች በአይሁድ ከሚገኙ ሴቶች ሊወለዱ እንደሚችሉ ታውቅ ነበር። የእርሷ ወንዶች ልጆች ልጅ ሳይወልዱ በመሞታቸውና እርሷም የመውለጃ ዕድሜዋ በማለፉ ምክንያት ቤተሰቧ የመሲሑ ቅድመ አያት የመሆን ዕድሉ በጣም የመነመነ ነበር። ሆኖም መበለት የሆነችው ምራቷ ሩት በዕድሜ የገፋውን ቦዔዝን አግብታ ወንድ ልጅ በመውለዷ የመሲሑ የኢየሱስ ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች! (ዘፍጥረት 49:10, 33፤ ሩት 1:3-5፤ 4:13-22፤ ማቴዎስ 1:1, 5) ኑኃሚንና ሩት በአስቸጋሪ ሁኔታ ሥር እምነታቸውን ጠብቀው መኖራቸው ደስታ አስገኝቶላቸዋል። እኛም መከራ ሲያጋጥመን እምነታችንን ጠብቀን መኖራችን ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል።
21. እምነት ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን አለበት?
21 ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ማወቅ ባንችልም እንኳ ማንኛውንም ፈታኝ ሁኔታ በእምነት መወጣት እንችላለን። እምነት ደፋርና ትዕግሥተኞች እንድንሆን ይረዳናል። ላቅ ያሉ ግቦች እንድናወጣና አስደሳች ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል። እምነት ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረንና መከራን ተቋቁመን እንድናልፍ ይረዳናል። በመሆኑም “ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ” መካከል እንሁን። (ዕብራውያን 10:39) አፍቃሪ አምላካችን ይሖዋ በሚሰጠን ብርታት በመታገዝ ለእርሱ ክብር ጠንካራ እምነት ማሳየታችንን እንቀጥል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• እምነት ድፍረት እንደሚሰጠን የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለን?
• እምነት ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
• እምነት ሰላም የሚያሰፍነው እንዴት ነው?
• እምነት መከራን በጽናት ተቋቁመን እንድንኖር እንደሚረዳን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እምነት ኖኅና ሄኖክ የይሖዋን መልእክት በድፍረት እንዲያውጁ ረድቷቸዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሙሴ ዓይነት እምነት ማዳበራችን መንፈሳዊ ግቦችን እንድንከታተል ይገፋፋናል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባርቅ፣ ዲቦራና ጌዴዎን መለኮታዊ ድጋፍ እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ማግኘታቸው እምነታቸውን አጠናክሮላቸዋል