በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን ምሥክር ሆኖ ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ የሚናገረው ሁሉ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ እጁን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመጫን መሐላ መፈጸሙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተቀባይነት ያለው ድርጊት ነውን?

በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። (ገላትያ 6:5) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ችሎት ፊት ቀርበን የምንናገረው ሁሉ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ መሐላ መፈጸምን አይከለክልም።

መሐላ መፈጸም ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሲሰራበት የቆየ ልማድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ጊዜ ግሪካውያን መሐላ ሲፈጽሙ እጃቸውን ወደ ሰማይ ያነሱ ወይም መሠዊያ ላይ ይጭኑ ነበር። አንድ ሮማዊ መሐላ ሲፈጽም በእጁ ድንጋይ ከያዘ በኋላ “ውሸት ከተናገርኩ ጁፒተር [የተባለው አምላክ] ከተማይቱን በሚያድንበት ጊዜ እኔን ልክ እንደዚህ ድንጋይ ከበረከቱ አሽቀንጥሮ ይጣለኝ” በማለት ይምል ነበር።​​—⁠⁠በጆን ማክሊንቶክ እና በጀምስ ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፔዲያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል፣ ኤንድ ኤክሌሲያስቲካል ሊትሬቸር ጥራዝ 7 ገጽ 260።

እንደዚህ ዓይነቱ ልማድ ሰዎች የሚመለከታቸውና ለድርጊቶቻቸውም ተጠያቂ የሚያደርጋቸው መለኮታዊ ኃይል መኖሩን እንደሚያምኑ ያሳያል። በጥንት ጊዜያት የነበሩ የይሖዋ አምላኪዎች ይሖዋ የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን እንደሚመለከት ተገንዝበው ነበር። (ምሳሌ 5:21፤ 15:3) መሐላ በሚፈጽሙበት ጊዜ ልክ በይሖዋ ፊት እንደሚምሉ ወይም እሱን እንደ ምሥክር አድርገው እንደማሉ ይናገሩ ነበር። ቦዔዝ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን እና ሴዴቅያስ እንደዚህ አድርገዋል። (ሩት 3:13፤ 2 ሳሙኤል 3:35፤ 1 ነገሥት 2:23, 24፤ ኤርምያስ 38:16) የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች መሐላ እንዲፈጽሙ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎችም ተቀብለዋል። በዚህ ረገድ አብርሃምና ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጉትን መመልከት ይቻላል።​​—⁠⁠ዘፍጥረት 21:22-24፤ ማቴዎስ 26:63, 64

ይሖዋን እንደ ምሥክር አድርጎ የሚምል ሰው አንዳንድ ጊዜ እጅን እንደማንሳት ያለ አንድ ዓይነት የሰውነት እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር። አብራም (አብርሃም) ለሰዶም ንጉሥ “ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 14:22) ነቢዩ ዳንኤልን ያነጋገረው መልአክ ‘ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሏል።’ (ዳንኤል 12:7) አምላክ ራሱ በምሳሌያዊ አነጋገር ለመሐላ እጁን እንዳነሳ ተገልጿል።​​—⁠⁠ዘዳግም 32:40፤ ኢሳይያስ 62:8, 9

ቅዱሳን ጽሑፎች መሐላ መፈጸምን አያወግዙም። ይህ ማለት ግን አንድ ክርስቲያን አንድ ነገር በተናገረ ቁጥር የተናገረው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ መማል ይገባዋል ማለት አይደለም። ኢየሱስ “ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን” ብሏል። (ማቴዎስ 5:33-37) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥቷል። ያዕቆብ “አትማሉ” ብሎ ሲናገር በሆነ ባልሆነው የመማልን ልማድ ማውገዙ ነበር። (ያዕቆብ 5:12) ሆኖም ኢየሱስም ሆነ ያዕቆብ ፍርድ ቤት ቀርበን የምንሰጠው ቃል እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ መሐላ መፈጸም ስህተት ነው አላሉም።

እንግዲያው አንድ ክርስቲያን ፍርድ ቤት ቀርቦ የሚሰጠው የምሥክርነት ቃል ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ መሐላ እንዲፈጽም ቢጠየቅ ምን ማድረግ ይኖርበታል? መሐላውን መፈጸም እንደሚችል ሆኖ ሊሰማው ይችላል። ካልሆነም ደግሞ የሚሰጠው ምሥክርነት ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላ መግለጫ እንዲጠቀም ይፈቀድለት ይሆናል።​​—⁠⁠ገላትያ 1:20

አንድ ክርስቲያን መሐላ በሚፈጽምበት ወቅት እጁን እንዲያነሳ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲጭን ፍርድ ቤቱ የሚያዝዝ ከሆነ ለመታዘዝ ሊመርጥ ይችላል። መሐላ ሲፈጽሙ እጅ እንደማንሳት ያለ አንድ ዓይነት የሰውነት እንቅስቃሴ ያደረጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ምሳሌዎችን ያስታውስ ይሆናል። አንድ ክርስቲያን መሐላ በሚፈጽምበት ጊዜ ይበልጥ ሊያሳስበው የሚገባው አንድ ዓይነት የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረጉ ሳይሆን እውነቱን ለመናገር መሐላውን የፈጸመው በአምላክ ፊት መሆኑ ነው። በዚህ መንገድ የሚፈጸም መሐላ ከፍ ተደርጎ ሊታይ ይገባዋል። አንድ ክርስቲያን መሐላ ፈጽሞ የቀረበለትን ጥያቄ መመለስ እንደሚችል ሆኖ ከተሰማው እውነቱን ለመናገር ራሱን ግዴታ ውስጥ እንዳስገባ ማስታወስ ይኖርበታል። ክርስቲያኖች መሐላ ፈጸሙም አልፈጸሙ ሁልጊዜ እውነቱን መናገር እንዳለባቸው ያውቃሉ።