በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ጥሩ ሰው በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኛል’

‘ጥሩ ሰው በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኛል’

ጥሩ ሰው በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኛል’

የሕይወት ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነው። (መዝሙር 36:​9) አዎን፣ “በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።” (ሥራ 17:28) ይሖዋ አምላክ ከእርሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለሚመሠርቱ ሰዎች በረከት እንደሚያወርድላቸው ማወቃችን ልባችን በከፍተኛ አድናቆት እንዲሞላ አያደርግም? እንዴታ! “የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ . . . የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6:​23) እንግዲያው የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት መጣራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

መዝሙራዊው ‘አምላክ ሞገስን ይሰጣል’ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝሙር 84:​11) ሆኖም አምላክ ሞገሱን የሚሰጠው ለእነማን ነው? በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለሌሎች ጥሩ ስሜት የሚያሳዩት በትምህርት ደረጃ፣ በሃብት፣ በቆዳ ቀለም፣ በዘርና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ነገሮችን መሠረት በማድረግ ነው። አምላክስ ሞገሱን የሚያሳየው ለእነማን ነው? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን “ደኅና [“ጥሩ፣” NW ] ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል፤ ተንኰለኛውን ሰው ግን ይቀሥፈዋል” በማለት መልስ ይሰጠናል።​​—⁠⁠ምሳሌ 12:2

በግልጽ ማየት እንደምንችለው ይሖዋ በጥሩ ወይም በበጎ ሰው ደስ ይሰኛል። የአንድ ጥሩ ሰው በጎነት ራስን መገሠጽን፣ ከአድልዎ ነጻ መሆንን፣ ትሕትናን፣ ርኅራኄንና ጠንቃቃነትን ያጠቃልላል። እንዲህ ያለ ሰው አሳቡ ጽድቅ፤ ከአፉ የሚወጡት ቃላት የሚያበረታቱ፤ ድርጊቱ ትክክልና ሌሎችን የሚጠቅም ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ 12ኛ ምዕራፍ የመጀመሪያ ክፍል በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጥሩነትን እንዴት ማንጸባረቅ እንደምንችል የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ይህንን ባሕርይ ማንጸባረቃችን ምን ጥቅሞች እንደሚያስገኝልን ይገልጽልናል። ይህ ክፍል የያዛቸውን ምሳሌዎች መመርመራችን ‘በጎ ለማድረግ የሚያስችል ማስተዋል’ እንድናገኝ ይረዳናል። (መዝሙር 36:​3) ምሳሌዎቹ የያዙትን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን የአምላክን ሞገስ ያስገኝልናል።

ተግሣጽ በጣም አስፈላጊ ነው

ሰሎሞን “ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፤ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 12:1) ጥሩ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረግ ስለሚፈልግ ተግሣጽን ለማግኘት ይጓጓል። ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወይም ከሌሎች ጋር በግል ከሚያደርጋቸው ጭውውቶች የሚያገኘውን ምክር ነገ ዛሬ ሳይል ተግባራዊ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች የያዙትን ምክሮች የሚመለከታቸው ቀና በሆነው ጎዳና ላይ መጓዙን እንዲቀጥል እንደሚያደርግ መውጊያ ዘንግ ነው። እውቀት ለማግኘት የሚጣጣር ከመሆኑም በላይ ይህንንም መንገዱን ቀና ለማድረግ ይጠቀምበታል። አዎን፣ ተግሣጽን የሚወድድ ሰው እውቀትንም ይወድዳል።

እውነተኛ ክርስቲያኖች ተግሣጽ ማግኘታቸው በተለይ ደግሞ ራሳቸውን መገሠጻቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! ጥልቅ የሆነ የአምላክ ቃል እውቀት እንዲኖረን ልንመኝ እንችላለን። በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ላይ ይበልጥ ውጤታሞችና ጥሩ የአምላክ ቃል አስተማሪዎች መሆን እንፈልግ ይሆናል። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20) ይሁን እንጂ ይህን ምኞታችንን እውን ለማድረግ ራሳችንን መገሠጻችን አስፈላጊ ነው። በሌሎች መስኮችም ራስን መገሠጽ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ መጥፎ ፍላጎቶች በውስጣችን እንዲቀሰቀሱ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉ። ታዲያ ዓይናችን ተገቢ ያልሆነውን ነገር እንዳያይ ራሳችንን መገሠጽ አይኖርብንም? ከዚህም በላይ “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ” በመሆኑ አእምሯችን ሳይታወቀን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ሐሳብ ሊያበቅል ይችላል። (ዘፍጥረት 8:21) እነዚህን አሳቦች በአእምሯችን ላለማውጠንጠን ራሳችንን መገሠጻችን በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

በሌላ በኩል፣ ወቀሳን የሚጠላ ሰው ተግሣጽንም ሆነ እውቀትን አይወድም። ሰው ተግሣጽን ባይቀበል ራሱን ወደ እንስሳነት ደረጃ ዝቅ ስለሚያደርገው ሁላችንም እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌ መዋጋት ይኖርብናል።

‘የጻድቃን ሥር አይንቀሳቀስም’

ጥሩ ሰው ዓመፀኛ ወይም ፍርደ ገምድል እንደማይሆን የታወቀ ነው። ስለሆነም ጽድቅ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚያስፈልግ ሌላው ባሕርይ ነው። ንጉሥ ዳዊት “አንተ ጻድቁን ትባርከዋለህና፤ አቤቱ፣ እንደ ጋሻ በሞገስህ ከለልኸን” በማለት ተቀኝቷል። (መዝሙር 5:12) ሰሎሞን ጻድቅ ሰው ያለበትን ሁኔታ ከክፉ ሰው ጋር በማወዳደር “ሰውን ዓመፃ አያጸናውም፤ የጻድቃን ሥር ግን አይንቀሳቀስም” በማለት ተናግሯል።​​—⁠⁠ምሳሌ 12:3

አንዳንድ ጊዜ ክፉዎች ባለጸጋ መስለው ይታዩ ይሆናል። መዝሙራዊው አሳፍ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት። “እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፣ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ” ይላል። ለምን? አሳፍ “የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና” በማለት መልሱን ይሰጣል። (መዝሙር 73:2, 3) ወደ አምላክ ቤተ መቅደስ በተመለሰ ጊዜ ግን ይሖዋ እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን በሚያዳልጥ ስፍራ እንዳስቀመጣቸው ተገነዘበ። (መዝሙር 73:​17, 18) ክፉ ሰዎች ምንም ያህል የተሳካላቸው መስለው ቢታዩ ይህ ስኬት የሚቆየው ለጊዜው ብቻ ነው። ታዲያ እንደነዚህ ባሉ ሰዎች ላይ የምንቀናው ለምንድን ነው?

በአንጻሩ ግን የይሖዋን ሞገስ ያገኘ ሰው ያለ አንዳች ስጋት ተደላድሎ ይኖራል። ሰሎሞን የዛፍን ሥር እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም “የጻድቃን ሥር ግን አይንቀሳቀስም” ብሏል። በካሊፎርኒያ የሚበቅለውን የሴኮያ ዛፍ የመሳሰሉ ግዙፍ ዛፎች ሥሮቻቸው ከ1.5 ሄክታር የሚበልጥ ቦታ የሚሸፍኑ ሲሆን እነዚህ በሰፊው የተዘረጉት ሥሮች ጎርፍ ወይም ከባድ ነፋስ በሚመጣበት ጊዜ ዛፉ እንዳይገነደስ ቀጥ አድርገው ይይዙታል። ግዙፉን የሴኮያ ዛፍ የምድር መናወጥ እንኳን አይበግረውም።

የአንድ ዛፍ ሥሮች ገንቢ ንጥረ ነገር ለማግኘት በአፈር ውስጥ ሰርገው እንደሚገቡ ሁሉ የእኛም አእምሮና ልብ በአምላክ ቃል ውስጥ ሥር በመስደድ ሕይወት ሰጪ የሆነውን ውኃ መምጠጥ ይኖርበታል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጽኑ እምነትና አስተማማኝ ተስፋ ይኖረናል። (ዕብራውያን 6:​19) “በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም” ከመንሳፈፍ እንድናለን። (ኤፌሶን 4:14) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ከባድ ፈተናዎች ሊያጋጥሙንና ሊያናውጡን ይችላሉ። ሆኖም ‘ሥራችን ፈጽሞ አይናጋም።’

“ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት”

ብዙ ሰዎች “ሴት ታውቅ በወንድ ያልቅ” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ያውቃሉ። ሰሎሞን ለባልዋ ምርኩዝ ስለምትሆን ሴት ሲናገር “ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት” ይላል። (ምሳሌ 12:4) “ልባም” የሚለው ቃል ጥሩነት የሚገለጥባቸውን የተለያዩ ባሕርያት አጠቃልሎ የያዘ ነው። በምሳሌ ምዕራፍ 31 ውስጥ በዝርዝር እንደተገለጸው አንዲት ጥሩ ሚስት የምታሳየው በጎነት ታታሪነቷን፣ ታማኝነቷንና አስተዋይነቷንም ያጠቃልላል። እንዲህ ያሉ ባሕርያትን የምታንጸባርቅ አንዲት ሴት ባልዋ በሌሎች ዘንድ አክብሮት እንዲያተርፍና ላቅ ያለ ግምት እንዲያገኝ ስለምታደርግ ለባሏ ዘውድ ናት። ከእርሱ ልቃ የመታየት ፍላጎት አይታይባትም። ከዚህ ይልቅ ከጎኑ ሆና የምትደግፈው ረዳቱ ናት።

አንዲት ሴት ባለቤትዋ የሚያፍርባት ልትሆን የምትችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ያስከትላል? እዚህ ላይ የተጠቀሰው አሳፋሪ ድርጊት ከተጨቃጫቂነት ባሕርይ ምንዝር እስከ መፈጸም ሊደርስ ይችላል። (ምሳሌ 7:​10-23፤ 19:​13) አንዲት ሚስት የምትፈጽመው እንዲህ ያለው ድርጊት ባልዋን ከማቁሰል ሌላ የሚያስገኘው ውጤት የለም። እንዲህ ያለች ሴት “በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት።” ይህም ማለት አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደተናገረው “ውስጥ ውስጡን በልቶ አቅም እንደሚያሳጣ በሽታ ከፍተኛ ጉዳት ታደርሳለች።” አንድ ሌላ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ደግሞ “በዘመናችን የአንድን ሰው ኃይል ሙጥጥ አድርጎ እንደሚጨርስ ከሚታወቀው ‘የካንሰር’ በሽታ ጋር ሊወዳደር ይችላል” ብሏል። እንግዲያው ክርስቲያን ሚስቶች ልባም ሴት ያላትን በጎ ባሕርያት በማንጸባረቅ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት መጣጣር ይኖርባቸዋል።

አሳብ ወደ ድርጊት፤ ድርጊት ወደ ውጤት ይመራል

አሳብ ወደ ድርጊት ይመራል፤ ድርጊት ደግሞ አንድ ዓይነት ውጤት ያስከትላል። ቀጥሎ እንደምንመለከተው ሰሎሞን ጻድቃንን ከክፉ ሰዎች ጋር በማወዳደር አሳብ ወደ ድርጊት የሚመራው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። ምሳሌው እንዲህ ይላል:- “የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፤ የኀጥኣን ምክር ግን ተንኰል ነው። የኀጥኣን ቃል ደምን ለማፍሰስ ትሸምቃለች፤ የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል።” ​​—⁠⁠ምሳሌ 12:5, 6

የጥሩ ሰዎች አሳብ ከሥነ ምግባር አንጻር ሲታይ ንጹሕ ሲሆን ሰዎቹን ከአድልዎ እንዲርቁና ትክክል የሆነውን እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል። ጻድቃን ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ስለሆነ ዝንባሌያቸው ጥሩ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ክፉ ሰዎች ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት በራስ ወዳድነት ስሜት ተገፋፍተው ነው። በዚህም ምክንያት ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙበት ዘዴ በሸፍጥ የተሞላ ነው። ሥራቸው ሁሉ ተንኮል ያለበት ነው። ሕግ ፊት ቀርበው በሐሰት በመወንጀል ንጹሑን ሰው ለማጥመድ ተንኮል ከመሸረብ አይመለሱም። ክፉ ሰዎች ንጹሐንን ማጥቃት ስለሚፈልጉ ቃላቸው ‘ደምን ለማፍሰስ እንደሚሸምቅ’ ተደርጎ ተገልጿል። ቅኖች የክፉ ሰዎችን ተንኮል ጠንቅቀው ስለሚያውቁና ጥንቃቄ ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ ስላላቸው ከተጠመደባቸው ወጥመድ ማምለጥ ይችላሉ። አልፎ ተርፎም የዋህ የሆኑ ሰዎችን አስቀድመው በማስጠንቀቅ ክፉዎች በዘረጉት ወጥመድ ሰለባ እንዳይሆኑ ሊረዷቸው ይችላሉ።

የጻድቃንና የክፉዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን? ሰሎሞን “ኀጥኣን ይገለበጣሉ፣ ደግሞም አይገኙም፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ምሳሌ 12:7) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳስቀመጠው ቤት የሚለው ቃል “መላውን ቤተሰብና ግለሰቡ በሕይወቱ ውስጥ የሚደሰትበትን አለኝ የሚለውን ውድ ነገር ሁሉ ያመለክታል።” ከዚህም በተጨማሪ ቃሉ የጻድቁን ዘር ሊያመለክት ይችላል። ያም ሆነ ይህ ከዚህ ምሳሌ የሚገኘው ትምህርት ግልጽ ነው፤ ጻድቅ መከራ ቢፈራረቅበትም ጸንቶ ይኖራል።

ትሑት ሰው መጨረሻው ያማረ ነው

የእስራኤል ንጉሥ የማስተዋል ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ሰው በጥበቡ [“በማስተዋል አፉ፣” NW ] ይመሰገናል፤ ልቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል።” (ምሳሌ 12:8) አስተዋይ ሰው አፉ እንዳመጣለት አይናገርም። ‘በማስተዋል የሚከፍተው አፉ’ ቃላትን እንዲመርጥ ስለሚያደርገው ከመናገሩ በፊት ያስባል፤ በዚህም ምክንያት ከሌሎች ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረዋል። አስተዋይ ሰው ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ሐሳብ ቢሰነዝሩበት እንኳን ‘በንግግሩ ቁጥብ ነው።’ (ምሳሌ 17:​27 አ.መ.ት ) እንዲህ ያለ ሰው ከሰዎች ምስጋና ይቸረዋል፤ ይሖዋም ደስ ይሰኝበታል። ‘ጠማማ ልብ’ ኖሮት ጠማማ ነገር ከሚናገር ሰው ምንኛ የተለየ ነው!

በአነጋገሩ ቁጥብ የሆነ ሰው እንደሚመሰገን ተመልክተናል፤ የሚከተለው ምሳሌ ደግሞ ትሕትና ያለውን ጥቅም ያስተምረናል። ምሳሌው እንዲህ ይላል:- “የሚበላው ሳይኖረው ከሚኩራራ ይልቅ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል።” (ምሳሌ 12:9 አ.መ.ት ) ሰሎሞን እዚህ ላይ ምንም ሳይኖረው እንዳለው ሆኖ ለመታየት ከሚሞክር ሰው ይልቅ አንድ አገልጋይ ብቻ ያለው ዝቅተኛ ኑሮ የሚመራ ሰው ይሻላል ማለቱ ሊሆን ይችላል። ይህ ምሳሌ እንደ አቅም መኖርን የሚያበረታታ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ይዞልናል!

ከግብርና ሕይወት ስለ ጥሩነት መማር ይቻላል

ሰሎሞን ግብርናን ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም ስለ ጥሩነት ሁለት ትምህርቶችን ሰጥቷል። እንዲህ አለ:- “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው።” (ምሳሌ 12:10) ጻድቅ ሰው ለከብቶቹ ይራራል። ምን እንደሚያስፈልጋቸው የሚያውቅ ሲሆን ስለ ደህንነታቸውም ያስባል። ክፉ ሰው ስለ ከብቶቹ እንደሚያስብ ይናገር ይሆናል፤ ሆኖም ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ምንም ግድ አይሰጠውም። እርሱ የሚያስበው ጥቅሙን ብቻ ነው፤ ለከብቶቹ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ከእነርሱ የሚያገኘውን ጥቅም ግምት ውስጥ አስገብቶ ነው። እንዲህ ያለው ሰው ከብቶቼን ምንም አላጓደልኩባቸውም የሚለው በጭካኔ እያንገላታቸው ሊሆን ይችላል።

እንስሳትን በሚመለከት የተነገረው ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ውሻና ድመትን ለመሳሰሉ የቤት እንስሳትም ይሠራል። እነዚህን የቤት እንስሳት አሳድጋለሁ ብሎ ወስዶ ችላ በማለትና በማንገላታት ለሥቃይ መዳረግ እንዴት ያለ የጭካኔ ድርጊት ነው! አንድ የቤት እንስሳ በበሽታ ወይም በአደጋ ምክንያት በእጅጉ ሲሰቃይ ዝም ብሎ ከማየት ይልቅ መግደሉ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

ሰሎሞን ሌላውን የግብርና ዘርፍ ይኸውም እርሻን ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም “ምድሩን የሚሠራ ሰው እንጀራ ይጠግባል” በማለት ይናገራል። ጠንክሮ መሥራት ውጤት እንደሚያስገኝ የታወቀ ነው። “ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን አእምሮ የጐደለው ነው።” (ምሳሌ 12:11) “አእምሮ የጎደለው” ሰው ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ወይም ማስተዋል ስለሚጎድለው ገና ለገና ትርፍ ያስገኝልኛል በሚል ስሜት በአደገኛ ንግድ ሥራ ይጠመዳል። ከእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ርኅሩኅና ትጉሕ ሠራተኞች ስለመሆን ትምህርት እናገኛለን።

ጻድቃን ፍሬ ያፈራሉ

ጠቢቡ ንጉሥ “ኀጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:12ሀ አ.መ.ት ) ኀጥእ ሰው ይህን ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? ክፉዎች ያለ አግባብ እጃቸው ያስገቡትን እቃ በመመኘት ነው።

ስለ ጥሩ ሰውስ ምን ለማለት ይቻላል? እንዲህ ያለው ሰው ተግሣጽን የሚወድድ ከመሆኑም በላይ በእምነት ሥር ሰድዷል። ጻድቅ፣ ልባም፣ ትሑት፣ ርኅሩኅና ትጉህ ነው። ሰሎሞን “የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 12:​12ለ) አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል” ይላል። እንዲህ ያለው ሰው ተረጋግቶና ተማምኖ ያለ ስጋት ይኖራል። በእርግጥም፣ ‘ጥሩ ሰው የአምላክን ሞገስ ያገኛል።’ እንግዲያው ‘በይሖዋ እንታመን፣ መልካምንም እናድርግ።’​—⁠መዝሙር 37:3

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጻድቃን እምነት እንደተመቸው ዛፍ ሥር ይሰድዳል