በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በደረሰብኝ ከባድ መከራ ተፈተንኩ

በደረሰብኝ ከባድ መከራ ተፈተንኩ

የሕይወት ታሪክ

በደረሰብኝ ከባድ መከራ ተፈተንኩ

ፔርክሊዝ ያኖሪስ እንደተናገረው

የታፈገው የእስር ቤቱ ክፍል ቅዝቃዜ አጥንቴ ውስጥ ገባ። አንዲት ስስ ብርድ ልብስ ለብሼ ብቻዬን ተቀምጬ ሳለሁ ከሁለት ቀናት በፊት ሚሊሻዎች ከቤቴ እየገፈታተሩ ሲወስዱኝ ባለቤቴ እንዴት ትመለከተኝ እንደነበር እስከ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። ከእርሷና ታምመው ከነበሩት ሁለት ሕፃናት ልጆቻችን ነጥለው ወሰዱኝ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እምነቴን የማትጋራው ባለቤቴ አንድ የታሸገ ዕቃ ከማስታወሻ ወረቀት ጋር አያይዛ ላከችልኝ። ማስታወሻው “እነዚህን ዳቦዎች የላክሁልህ አንተም እንደ ልጆችህ እንድትታመም ብዬ ነው” የሚል ጽሕፈት ነበረው። በሕይወት ተርፌ ዳግም ቤተሰቤን አይ ይሆን?

በክርስቲያናዊ እምነቴ ለመጽናት ካደረግሁት ረጅምና መራራ ትግል ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ክስተት ነበር። በዚህ ፍልሚያ የቤተሰብ ተቃውሞ፣ እስር፣ የፍርድ ቤት ሙግትና ኃይለኛ ስደት አጋጥሞኛል። ሰላማዊና ፈሪሃ አምላክ ያለኝ ሰው ብሆንም እንኳ እንዲህ የመሰለ አስከፊ ችግር ሊደርስብኝ የቻለው እንዴት ነው? ለምንስ? እባካችሁ ታሪኬን ስተርክ በጥሞና ተከታተሉኝ።

ታላቅ ራእይ ያለው ምስኪን ልጅ

በ1909 ክሬት ውስጥ በስታቭሮሜኖ መንደር በተወለድኩበት ዓመት አገሪቱ በጦርነት፣ በድህነትና በረሃብ እየታመሰች ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እኔና አራቱ ታናናሾቼ ብዙዎችን ከፈጀው የኅዳር በሽታ ለጥቂት ተረፍን። ወላጆቻችን በበሽታው እንዳንያዝ ስለሰጉ አንዳንድ ጊዜ ለበርካታ ሳምንታት ቤት ውስጥ ይቆልፉብን ነበር።

ድኻ ገበሬ የነበረው አባቴ በጣም ሃይማኖተኛ ቢሆንም ነፃ አመለካከት ነበረው። ፈረንሳይና ማዳጋስካር ኖሮ ስለነበር በርካታ ሃይማኖታዊ እምነቶችን አይቷል። ይሁንና በቤተሰብ ደረጃ ታማኝ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ስለነበርን እሁድ እሁድ ከቅዳሴ አንቀርም እንዲሁም በየዓመቱ ለጉብኝት ይመጡ የነበሩት ጳጳስ እኛ ቤት ያርፉ ነበር። በወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ዘማሪ ነበርኩ፤ ሳድግ ደግሞ ቄስ የመሆን ምኞት ነበረኝ።

በ1929 የፖሊስ ሠራዊት አባል ሆንኩ። አባቴ በሞተበት ወቅት በሰሜን ግሪክ በምትገኘው በተሰሎንቄ ግዳጅ ላይ ነበርኩ። መጽናኛና መንፈሳዊ እውቀት ለማግኘት ስል በአቶስ ተራራ ወደሚገኘው የፖሊስ ሠራዊት ተዛወርኩ። a አቶስ በተሰሎንቄ አቅራቢያ የሚገኝ ገዳም ሲሆን በኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ እንደ “ቅዱስ ተራራ” የሚታይ ቦታ ነው። በዚያ ፖሊስ ሆኜ ባገለገልኩባቸው አራት ዓመታት የገዳም ሕይወት ምን እንደሚመስል በቅርብ ማየት ችያለሁ። ወደ አምላክ ይበልጥ ከመቅረብ ይልቅ መነኮሳቱ የሚፈጽሙት አስጸያፊ የሥነ ምግባር ብልግናና ቅጥፈት ጭራሹኑ ግራ እንድጋባ አደረገኝ። በአክብሮት እመለከተው የነበረ አንድ ቄስ ለብልግና ሲጠይቀኝ በጣም ተጸየፍኩት። እንዲህ ዓይነት ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ቢያጋጥመኝም እንኳ አምላክን የማገልገልና ቄስ የመሆን ፍላጎቴ አልጠፋም ነበር። እንዲያውም ማስታወሻ እንዲሆነኝ ብዬ የቄስ ልብስ ለብሼ የተነሳሁት ፎቶ እስከ አሁን ድረስ አብሮኝ አለ። በመጨረሻ ተመልሼ ወደ ክሬት ሄድኩ።

“እርሱ ሥጋ የለበሰ ዲያብሎስ ነው!”

በ1942 በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ያደገችውን ፍሮሲኒ የተባለች አንዲት ቆንጆ ልጅ አገባሁ። ቤተሰቦቿ አጥባቂ ሃይማኖተኛ ስለነበሩ ቄስ ለመሆን ያደረግሁት ውሳኔ ይበልጥ ተጠናከረ። b ወደ አቴንስ ሄጄ የሃይማኖት ትምህርት ቤት ለመግባት ቆረጥኩ። በ1943 መገባደጃ ላይ መርከብ ለመሳፈር ክሬት፣ ኢራክሊዮን ወደሚገኘው ወደብ ብሄድም ጉዞው ሳይሳካልኝ ቀረ። ይህ የሆነበት ምክንያት በመሃሉ መንፈስ የሚያድስ ሌላ መንፈሳዊ ትምህርት በማግኘቴ ሊሆን ይችላል። ያጋጠመኝ ነገር ምን ነበር?

የይሖዋ ምሥክሮች አባልና ቀናተኛ ሰባኪ የነበረው ወጣቱ ኢማኑኤል ሊዮኑዳኪስ ለተወሰኑ ዓመታት በመላው ክሬት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲያስተምር ቆይቷል። c አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ቃል በተመለከተ የሚሰጡት ግልጽ ትምህርት ስለማረካቸው ሐሰት ሃይማኖትን ጥለው ወጡ። በአቅራቢያችን በምትገኘው በሲትኢ ከተማ ቀናተኛ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ተቋቁሞ ነበር። ይህም በአካባቢው የሚኖሩትን ጳጳስ እረፍት ነሳቸው፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ በኖሩባቸው ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ሥራቸው በጣም ውጤታማ መሆናቸውን የተመለከቱ በመሆናቸው ነው። በእርሳቸው ክልል ውስጥ ያሉትን “መናፍቃን” ጠራርገው ለማጥፋት ቆርጠው ተነሱ። በእርሳቸው ቆስቋሽነት የይሖዋ ምሥክሮች በፖሊስ እየተያዙ ይታሰሩ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በተለያዩ የሐሰት ክሶች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ከቡድኑ አባላት አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን እውነት ነገረኝ። ሆኖም ፍላጎት የሌለኝ መስሎ ስለታየው ይበልጥ ልምድ ያለው ሰባኪ መጥቶ እንዲያነጋግረኝ አደረገ። ይህ ምሥክር መጥቶ ሲያነጋግረኝ ቆጣ ብዬ ስለመለስኩለት “ፔርክሊዝ የይሖዋ ምሥክር ይሆናል ማለት ዘበት ነው። እርሱ ሥጋ የለበሰ ዲያብሎስ ነው!” ሲል በቁጥር ትንሽ ለነበሩት የቡድኑ አባላት ነገራቸው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመኝ ተቃውሞ

አምላክ እንደዚያ አድርጎ ስላልተመለከተኝ ደስተኛ ነኝ። የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት እውነት መሆኑን አምኖ የተቀበለው ታናሽ ወንድሜ ዲማስትኒዝ የካቲት 1945 ያዘኑትን ሁሉ አጽናኑ (እንግሊዝኛ) የተባለ ቡክሌት ሰጠኝ። d ቡክሌቱ የያዘው ትምህርት አመለካከቴን ለወጠው። ወዲያውኑ ወደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቁመን በሲትኢ ከሚገኘው ቡድን ጋር መሰብሰብ ጀመርን። እንዲሁም ስለ አዲሱ እምነታችን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ነገርናቸው። ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበሉ። እንደፈራሁት ሁሉ ከሐሰት ሃይማኖት በመውጣቴ ባለቤቴና ቤተሰቦቿ አገለሉኝ እንዲሁም ጠሉኝ። ይባስ ብሎም አማቴ ከእኔ ጋር ንግግር አቆሙ። በቤታችን ውስጥ ግጭትና ጭቅጭቅ ነገሠ። እንዲህም ሆኖ ግንቦት 21, 1945 ወንድም ሚኖስ ኮኪናኪስ እኔንና ዲማስትኒዝን አጠመቀን። e

በመጨረሻ አምላክን የማገልገል ምኞቴ እውን ሆነ! ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ያገለገልኩበትን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም። ሠላሳ አምስት ቡክሌቶች በቦርሳ ይዤ በአውቶቡስ ወደ አንዲት መንደር ሄድኩ። ፍርሃቴን በውስጤ አምቄ የመጀመሪያውን ቤት አንኳኳሁ። ተጨማሪ በሮችን ባንኳኳሁ መጠን ይበልጥ ድፍረት እያገኘሁ ሄድኩ። በቁጣ የበገነ አንድ ቄስ አገኘኝና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ካልሄድክ ብሎ ሲያስቸግረኝ ሁሉንም ቤቶች አንኳኩቼ ሳልጨርስ ከአካባቢው እንደማልሄድ በድፍረት ነገርኩት። ልክ እንዳልኩትም አደረግሁ። በደስታ ከመፈንደቄ የተነሳ አውቶቡሱ እስኪመጣ ድረስ አልጠበቅሁም፤ የመጣሁትን 15 ኪሎ ሜትር በእግሬ ተጉዤ ተመለስኩ።

ጨካኝ የሆኑ አማጽያን ያደረሱብን ግፍ

መስከረም 1945 በሲትኢ በተቋቋመው አዲስ ጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጠኝ። ብዙም ሳይቆይ ግሪክ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳ። የደፈጣ ተዋጊ ቡድኖች ያለ ርኅራኄ እርስ በርሳቸው ይጨፋጨፉ ጀመር። ጳጳሱ አጋጣሚውን በመጠቀም በአካባቢው የሚገኘውን አንድ የአማጽያን ቡድን አመቺ ሆኖ ባገኘው በማንኛውም መንገድ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲያጠፋ ቅስቀሳ አደረጉ። (ዮሐንስ 16:​2) የአማጽያኑ ቡድን በአውቶቡስ እኛ ወደምንኖርበት መንደር ሲመጣ አብራቸው ተሳፍራ የነበረች ለእኛ ቀና አመለካከት ያላት አንዲት ሴት “ከአምላክ የተቀበሉትን” ተልዕኮ እንዴት እንደሚፈጽሙ ሲነጋገሩ የሰማችውን መጥታ ነገረችን። እኛም እንዳያገኙን ተደበቅን። ከዚያም አንድ ዘመዳችን እኛን ለማስጣል ጣልቃ በመግባቱ ሕይወታችን ሊተርፍ ቻለ።

ከዚህ በኋላ ከባድ መከራ ይደርስብን ጀመር። ድብደባና ዛቻ የዕለት ተዕለት ቀለባችን ሆነ። ተቃዋሚዎቻችን ወደ ቀድሞው እምነታችን እንድንመለስ፣ ልጆቻችንን እንድናስጠምቅና እንድናማትብ ለማስገደድ ይሞክሩ ነበር። በአንድ ወቅት የሞተ መስሏቸው ትተውት እስኪሄዱ ድረስ ወንድሜን ደበደቡት። የሁለቱን እህቶቼን ልብስ ቀድደው ሲገርፏቸው መመለከት ለእኔ በጣም ከባድ ነበር። በዚያን ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ልጆች በግድ አጥምቃለች።

በ1949 እናቴ ሞተች። ቄሱ አሁንም ችግር ይፈጥርብን ጀመር። የቀብር ፈቃድ ለማግኘት የሚያስፈልገውን ሕጋዊ መሥፈርት አያሟሉም ሲል ከሰሰን። ችሎት ፊት ከቀረብሁ በኋላ በነፃ ተለቀቅሁ። ክሱ በተነበበበት ወቅት የይሖዋ ስም በመጠቀሱ ጉዳዩ ከፍተኛ ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል። ጠላቶቻችን “ወደ ልባችን እንድንመለስ” ሊያደርጉ የሚችሉበት የቀረው ብቸኛው መንገድ እኛን አስሮ በግዞት መላክ ነበር። ይህንንም ሚያዝያ 1949 አደረጉ።

ከባድ መከራ ገጠመን

ተይዘው ከታሰሩት ሦስት ወንድሞች መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስሬ እያለሁ ባለቤቴ ልትጠይቀኝ እንኳ አልመጣችም። በጉዟችን መሃል ኢራክሊዮን በሚገኝ እስር ቤት አቆዩን። መጀመሪያ ላይ እንደገለጽኩት ብቸኝነትና ከባድ ሐዘን ተሰማኝ። እምነቴን ከማትጋራው ወጣት ባለቤቴና ጨቅላ ሕፃናት ከሆኑት ሁለት ልጆቼ ለይተው ነበር የወሰዱኝ። ይሖዋ እንዲረዳኝ ከልብ ጸለይኩ። ዕብራውያን 13:​5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” የሚለው የአምላክ ቃል ትዝ አለኝ። ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን ጥበብ ያለበት ውሳኔ መሆኑን ተገነዘብኩ።​—⁠ምሳሌ 3:​5

ከግሪክ አቲካ የባሕር ዳርቻ ርቆ ወደሚገኘው ምድረ በዳ ወደሆነው የማክሮኒሶስ ደሴት ልንወሰድ መሆኑን ሰማን። ወኅኒ ቤቱ ድብደባና የጉልበት ሥራ የሚካሄድበት ቦታ በመሆኑ ማክሮኒሶስ የሚለውን ስም መስማቱ ብቻ ፍርሃት ያሳድራል። ወደዚያ ስንጓዝ ፒሬስ ላይ ጥቂት ቆይታ አደረግን። በካቴና ታስረን የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ወንድሞቻችን ጀልባው ላይ ወጥተው ሲያቅፉን በጣም ተጽናናን።​—⁠ሥራ 28:​14, 15

በማክሮኒሶስ ያሳለፍነው ሕይወት በሥቃይና በሰቆቃ የተሞላ ነው። ወታደሮቹ ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ እስረኞችን ይደበድቡ ነበር። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ እስረኞች አእምሯቸውን ስተዋል፣ ሌሎች ሕይወታቸው አልፏል እንዲሁም በጣም ብዙዎች ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል። ማታ ማታ እስረኞች ሲደበደቡ የሚያሰሙት ጩኸትና ለቅሶ ይሰማናል። የምለብሳት ስሷ ብርድ ልብስ ከሌሊቱ ቁር እምብዛም አታስጥለኝም ነበር።

ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ስም ሲጠራ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው ስም ይጠቀስ ስለነበር ቀስ በቀስ ካምፑ ውስጥ ሁሉም አወቁን። ከዚህም የተነሳ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል ብዙ አጋጣሚዎች አገኘን። መንፈሳዊ እድገት አድርጎ ሕይወቱን ለይሖዋ የወሰነን አንድ የፖለቲካ እስረኛ የማጥመቅ መብት አግኝቻለሁ።

በስደት በነበርኩበት ወቅት መልስ ባትሰጠኝም ለውዷ ባለቤቴ በተደጋጋሚ ደብዳቤ መጻፌን አላቆምኩም ነበር። ይህ ጊዜያዊ ችግር መሆኑንና እንደገና በደስታ እንደምንኖር በመግለጽ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሚያጽናኑ ቃላት መጻፌን ቀጠልኩ።

ሌሎች ተጨማሪ ወንድሞችም ታስረው ወደዚህ ቦታ በመምጣታቸው ቁጥራችን ጨመረ። የምሠራው ቢሮ ውስጥ ስለነበር የካምፑ አዛዥ ከሆኑት ኰሎኔል ጋር መቀራረብ ቻልኩ። ለይሖዋ ምሥክሮች አክብሮት ስለነበራቸው አቴንስ ከሚገኘው ቢሮአችን ጽሑፍ ማግኘት ይቻል እንደሆነ ደፍሬ ጠየቅኋቸው። “ይኼ እንኳ የማይመስል ነገር ነው። ግን እኮ፣ አቴንስ ያሉት ወንድሞቻችሁ ጽሑፉን በአንተ ሻንጣ ውስጥ አድርገው በእኔ ስም ሊልኩላችሁ ይችላሉ” አሉኝ። ማመን አቅቶኝ አፌን ከፍቼ ቀረሁ! ከጥቂት ቀናት በኋላ ከጀልባ ላይ ዕቃ እያራገፍን ሳለ አንድ ፖሊስ ለኰሎኔሉ ሰላምታ ከሰጠ በኋላ “ኰሎኔል፣ ሻንጣዎ መጥቷል” አላቸው። “የምን ሻንጣ?” ሲሉ መለሱለት። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በአቅራቢያቸው ስለነበርኩና የሚነጋገሩትን ስለሰማሁ “በነገሩኝ መሠረት በእርስዎ ስም የተላከልን ዕቃ ሊሆን ይችላል” ስል ቀስ ብዬ ነገርኳቸው። ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ እንድናገኝ ያደረገበት አንደኛው መንገድ ይህ ነበር።

ያልተጠበቀ በረከትና ተጨማሪ ስደት

በ1950 ማብቂያ ላይ ከእስር ተፈታሁ። ወደ ቤት ስመለስ ሰውነቴ ገር​ጥቶ፣ በጣም ከስቼና አቅም አጥቼ ነበር። ምን ዓይነት አቀባበል እንደሚደረግልኝም እርግጠኛ አልነበርኩም። ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር እንደገና በመገናኘቴ በጣም ተደሰትኩ! ከዚህም በላይ ፍሮሲኒ የነበራት ጥላቻ መርገቡ በጣም አስገረመኝ። ወኅኒ ቤት ሆኜ የጻፍኩላት ደብዳቤዎች ሥራቸውን ሠርተዋል። ያሳየሁት ትዕግሥትና ጽናት በጥልቅ ነክቷት ነበር። ወደ ቤት ከተመለስኩ ብዙም ሳይቆይ በመካከላችን ሰላም ለመፍጠር ረጅም ሰዓት የፈጀ ውይይት አደረግን። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች ከዚያም በይሖዋና በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት አሳደረች። በ1952 ራሷን የወሰነች የይሖዋ አገልጋይ ሆና አጠመቅኋት። በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከተደሰትኩባቸው ቀኖች አንዱ ይህ ነበር!

በ1955 “የዓለም ብርሃን” ሕዝበ ክርስትና ነች ወይስ ክርስትና? (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት ቅጂ ለእያንዳንዱ ቄስ ለመስጠት ዘመቻ አካሄድን። በርካታ ቁጥር ያለን የይሖዋ ምሥክሮች ተይዘን ፍርድ ቤት ቀረብን። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተመሠረቱ በርካታ ክሶች ስለነበሩ ፍርድ ቤቱ ሁሉንም ክሶች ለማዳመጥ ከወትሮው በተለየ ችሎት ለመቀመጥ ተገድዶ ነበር። በዚያን ዕለት የከተማው የሕግ ባለሙያዎች በቦታው ከመገኘታቸውም በላይ ፍርድ ቤቱ በቄሶች ታጭቆ ነበር። ጳጳሱ ስለተጨነቁ መተላለፊያው ላይ ወዲያ ወዲህ ይንጎራደዱ ነበር። አንደኛው ቄስ እምነቴን ሊያስቀይረኝ ሞክሯል ሲል ከሰሰኝ። ዳኛው “አንዲት ብሮሹር በማንበብ እንዴት ሃይማኖትህን ትለውጣለህ? እምነትህ ያን ያህል ደካማ ነው ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ አቀረቡለት። በዚህ ጊዜ ቄሱ ክው ብሎ ቀረ። እኔ በነፃ ተለቀቅሁ፤ አንዳንድ ወንድሞች ግን የስድስት ወር እስራት ተበየነባቸው።

ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት በተደጋጋሚ ተይዘን የታሰርን ሲሆን የሚቀርቡብን ክሶችም እየተበራከቱ ሄዱ። ችሎት ፊት የሚሟገቱልን ጠበቆቻችን እረፍት አልነበራቸውም። በድምሩ 17 ጊዜ ያህል ፍርድ ቤት ቀርቤአለሁ። ተቃውሞ ቢደርስብንም ዘወትር በስብከቱ ሥራ እንሳተፍ ነበር። ይህን ፈታኝ ሁኔታ በደስታ የተቀበልነው ሲሆን የደረሱብን ከባድ ፈተናዎች የጠራ እምነት እንዲኖረን አስችለውናል።​—⁠ያዕቆብ 1:​2, 3

አዳዲስ የአገልግሎት መብቶችና ፈታኝ ሁኔታዎች

በ1957 ወደ አቴንስ ተዛወርን። እዛ እንደሄድኩ አዲስ በተቋቋመ ጉባኤ እንዳገለግል ተመደብኩ። ባለቤቴ የምትሰጠኝ የሙሉ ልብ ድጋፍ ኑሯችንን ቀላል በማድረግ ለመንፈሳዊ ሥራዎች ቅድሚያ እንድንሰጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል። ይህም አብዛኛውን ጊዜያችንን ለስብከቱ ሥራ እንድናውል አስችሎናል። በእነዚያ ዓመታት ሁሉ አገልጋይ በሚያስፈልግባቸው ጉባኤዎች ውስጥ እንድናገለግል ብዙ ጊዜ ጥያቄ ቀርቦልናል።

በ1963 ልጄ 21 ዓመት ስለሞላው ለውትድርና አገልግሎት መመዝገብ ነበረበት። ለዚህ ግዳጅ የሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ገለልተኛ አቋም ስለነበራቸው ድብደባ፣ ፌዝና ነቀፋ ይደርስባቸው ነበር። ልጄም ተመሳሳይ ሁኔታ ደርሶበታል። በመሆኑም በአቋማቸው የጸኑትን የቀድሞዎቹን የይሖዋ ምሥክሮች አርአያ እንዲከተል በምሳሌያዊ መንገድ ለማበረታታት ስል ከማክሮኒሶስ ያመጣሁትን ብርድ ልብስ ሰጠሁት። ለዚህ ግዳጅ የሚጠሩ ወንድሞች የሚዳኙት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከሁለት እስከ አራት ዓመት የሚደርስ እስራት ይፈረድባቸው ነበር። ከተፈቱ በኋላ እንደገና ይጠሩና ይታሰሩ ነበር። የሃይማኖታዊ ድርጅት አገልጋይ እንደመሆኔ መጠን እስረኞችን የመጠየቅ መብት ነበረኝ። ስለሆነም በተወሰነ መጠን ከልጄም ሆነ ከሌሎች ታማኝ ወንድሞች ጋር መገናኘት ችያለሁ። ልጄ ከስድስት ዓመት በላይ በእስር ቆይቷል።

ይሖዋ ብርታት ሰጥቶናል

በግሪክ የሃይማኖት ነፃነት ከተገኘ በኋላ በሮዴስ ደሴት በጊዜያዊ ልዩ አቅኚነት የማገልገል መብት አገኘሁ። ከዚያም በ1986 ክርስቲያናዊ አገልግሎቴን በጀመርኩበት በክሬት ሲትኢ አገልጋዮች አስፈለጉ። ድሮ ከማውቃቸው ውድ ወንድሞች ጋር እንደገና የማገልገል መብት በማግኘቴ የአገልግሎት ምድቡን በደስታ ተቀበልኩ።

በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰባችን አባሎች የሁሉም ታላቅ ስሆን 70 የሚሆኑ ዘመድ አዝማዶቼ ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ በማየቴ ደስተኛ ነኝ። ሌሎች ዘመዶቼም ወደ እውነት እየመጡ ነው። አንዳንዶች ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮች፣ አቅኚዎች፣ ቤቴላውያንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆነው እያገለገሉ ናቸው። በደረሰብኝ ከባድ መከራ ከ58 ለሚበልጡ ዓመታት እምነቴ ተፈትኗል። አሁን የ93 ዓመት አዛውንት ነኝ፤ መለስ ብዬ ያለፈውን ስመለከት አምላክን በማገልገል ባሳለፍኩት ሕይወት ፈጽሞ አልቆጭም። ይሖዋ “ልጄ ሆይ፣ ልብህን ስጠኝ፣ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ” በማለት ያቀረበልኝን ፍቅራዊ ግብዣ እንድቀበል የሚያስችል ብርታት ሰጥቶኛል።​—⁠ምሳሌ 23:26

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የታኅሣሥ 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30-1ን ተመልከት።

b የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄሶች ሚስት ማግባት አይከለከሉም።

c የኢማኑኤል ሊዮኑዳኪስን የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 25-9 ላይ ማንበብ ይቻላል።

d በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

e ከሚኖስ ኮኪናኪስ ጋር በተያያዘው የፍርድ ቤት ጉዳይ የተገኘውን ድል መስከረም 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27-31 ላይ ማንበብ ይቻላል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ማክሮኒሶስ አስፈሪዋ ደሴት

ከ1947 እስከ 1957 በነበሩት አሥር ዓመታት ደረቅና ባድማ የሆነችው የማክሮኒሶስ ደሴት ከ100, 000 የሚበልጡ እስረኞችን አስተናግዳለች። ከእነዚህ መካከል በክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸው የተነሳ ወደዚያ የተጋዙ በርካታ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። የስደቱ ቆስቋሾች በአመዛኙ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት ሲሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ኮምኒስቶች ናቸው በማለት በሐሰት ይወነጅሏቸው ነበር።

በማክሮኒሶስ ይሰጥ የነበረውን “የተሃድሶ” ሂደት በተመለከተ ፓፒሮስ ላሩስ ብሪታኒካ የተባለው የግሪክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “በተለያዩ መንገዶች የሚፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ፣ . . . በሰለጠኑ አገሮች ተቀባይነት የሌለው የመኖሪያ ሁኔታ እንዲሁም ጠባቂዎቹ በእስረኞቹ ላይ የሚፈጽሙት ወራዳ ተግባር . . . የግሪክን ታሪክ ያጎደፉ ድርጊቶች ናቸው።”

አንዳንድ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ካልካዱ በስተቀር ፈጽሞ እንደማይፈቱ ተነግሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ ከአቋማቸው ፍንክች አላሉም። እንዲያውም የሚያገኟቸውን አንዳንድ የፖለቲካ እስረኞች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ አድርገዋል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚኖስ ኮኪናኪስ (ከቀኝ በኩል ሦስተኛው) እና እኔ (ከግራ በኩል አራተኛው) በማክሮኒሶስ ደሴት ታስረን ሳለ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወጣትነቴ ምሥራቹን እሰብክበት በነበረው በክሬት ሲትኢ ከአንድ ወንድም ጋር ሳገለግል