በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ብዙ ፍሬ አፍሩ’

‘ብዙ ፍሬ አፍሩ’

‘ብዙ ፍሬ አፍሩ’

‘ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ግለጡ።’​—⁠ዮሐንስ 15:8 አ.መ.ት

1. (ሀ) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የነገራቸው ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገው ብቃት ምንድን ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

 ዕለቱ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የነበረው ምሽት ሲሆን ረጅም ሰዓት ወስዶ የልቡን አውጥቶ በመናገር ለሐዋርያቱ ማበረታቻ ይሰጣል። በዚህ ጊዜ እኩለ ሌሊት ሳያልፍ አልቀረም፤ ሆኖም ኢየሱስ ለቅርብ ወዳጆቹ ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ የሚሰጣቸውን ማበረታቻ አልጨረሰም። በንግግሩ መሃል “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል” በማለት ደቀ መዛሙርት ለመሆን ማሟላት የሚያስፈልጋቸውን አንድ ሌላ ብቃት ነገራቸው። (ዮሐንስ 15:8) እኛስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገውን ይህንን ብቃት እናሟላለን? ‘ብዙ ፍሬ ማፍራት’ ሲባል ምን ማለት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ኢየሱስ በዚያ ምሽት ከሐዋርያቱ ጋር ያደረገውን ውይይት መለስ ብለን እንመልከት።

2. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ፍሬ ስለ ማፍራት ምን ምሳሌ ተናገረ?

2 ኢየሱስ ሐዋርያቱ ፍሬ እንዲያፈሩ የሰጣቸው ማበረታቻ የሚገኘው በነገራቸው አንድ ምሳሌ ውስጥ ነው። ምሳሌው እንዲህ ይላል:- “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግ[ደ]ዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፣ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። . . . ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። . . . ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።”​—⁠ዮሐንስ 15:1-10

3. የኢየሱስ ተከታዮች ፍሬ እንዲያፈሩ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

3 በዚህ ምሳሌ ውስጥ ይሖዋ በገበሬው፣ ኢየሱስ በወይኑ ግንድ እንዲሁም ያዳምጡት የነበሩ ሐዋርያት በቅርንጫፎቹ ተመስለዋል። ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ተጣብቀው ‘ለመኖር’ ጥረት ካደረጉ ፍሬ ማፍራታቸው አይቀርም። ከዚያም ኢየሱስ ሐዋርያቱ ይህን አንድነት እንዴት ጠብቀው መኖር እንደሚችሉ ሲገልጽ “ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” ብሏል። ከጊዜ በኋላም ሐዋርያው ዮሐንስ ለእምነት ባልንጀሮቹ “ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል” በማለት ተመሳሳይ ሐሳብ ተናግሯል። a (1 ዮሐንስ 2:​24፤ 3:​24) ስለሆነም ክርስቶስ የሰጣቸውን ትእዛዛት በመጠበቅ ተከታዮቹ በእርሱ መኖር ይችላሉ። ይህ አንድነት በአጸፋው ፍሬ እንዲያፈሩ ያስችላቸዋል። እንድናፈራ የሚጠበቅብን ፍሬ ምንድን ነው?

እድገት ማድረግ የሚቻልበት አጋጣሚ

4. ይሖዋ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ‘እንደሚያስወግደው’ ከሚገልጸው ሐሳብ ምን እንማራለን?

4 ስለ ወይኑ ግንድ በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ ይሖዋ አንድ ቅርንጫፍ ፍሬ የማያፈራ ከሆነ ‘እንደሚያስወግደው’ ወይም ቆርጦ እንደሚጥለው ተገልጿል። ይህ ምን ያስገነዝበናል? ሁሉም ደቀ መዛሙርት ፍሬ ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው ብቻ ሳይሆን ያሉበት ሁኔታ ወይም አቅማቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉም ፍሬ ማፍራት እንደሚችሉ ያስገነዝበናል። ይሖዋ አፍቃሪ አምላክ እንደመሆኑ መጠን አንድን ነገር ማከናወን ከአቅሙ በላይ የሆነበትን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ‘ያስወግደዋል’ ወይም ያግደዋል ማለቱ የማይመስል ጉዳይ ነው።​—⁠መዝሙር 103:​14፤ ቆላስይስ 3:​23፤ 1 ዮሐንስ 5:​3

5. (ሀ) ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ፍሬ በማፍራት ረገድ እድገት ማድረግ እንደምንችል የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በዝርዝር የምንመለከታቸው ሁለቱ የፍሬ ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?

5 ኢየሱስ ስለ ወይን ግንድ የተናገረው ምሳሌ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን አቅማችንና ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን እድገት ማድረግ እንደሚኖርብንም ይጠቁመናል። ኢየሱስ ምን እንዳለ ልብ በል:- ‘ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።’ (ዮሐንስ 15:2) ኢየሱስ በምሳሌው መጨረሻ ላይ ተከታዮቹ “ብዙ ፍሬ” እንዲያፈሩ አሳስቧቸዋል። (ቁጥር 8) ይህ ምን ያመለክታል? የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ቸልተኞች መሆን አይኖርብንም። (ራእይ 3:​14, 15, 19) ከዚህ ይልቅ ፍሬ በማፍራት ረገድ እድገት ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶችን መፈለግ ይኖርብናል። አብዝተን ማፍራት የሚገባን ፍሬ ምን ዓይነት መሆን ይኖርበታል? ልናፈራቸው የሚገቡ ሁለት ዓይነት ፍሬዎች አሉ። እነርሱም (1) “የመንፈስ ፍሬ” እና (2) የመንግሥቱ ፍሬ ናቸው።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23፤ ማቴዎስ 24:​14

ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማፍራት

6. ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው የመንፈስ ፍሬ ያለውን ጥቅም ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

6 ‘ከመንፈስ ፍሬ’ መካከል በመጀመሪያ የተጠቀሰው ፍቅር ነው። ክርስቲያኖች ኢየሱስ ፍሬ ስለ ማፍራት ከተናገረው የወይን ግንድ ምሳሌ ትንሽ ቀደም ብሎ የሰጣቸውን ትእዛዝ ስለሚጠብቁ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍቅርን በውስጣቸው ያፈራል። ሐዋርያቱን “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 13:34) እንዲያውም የምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ በሆነችው በዚያች ምሽት ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባደረገው ውይይት ፍቅር የማሳየትን አስፈላጊነት ደግሞ ደጋግሞ አሳስቧቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 14:​15, 21, 23, 24፤ 15:​12, 13, 17

7. ሐዋርያው ጴጥሮስ ፍሬ ማፍራት ክርስቶስ የነበሩትን ባሕርያት ከማንጸባረቅ ጋር ተዛማጅነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

7 በዚያ ምሽት በውይይቱ ላይ ተገኝቶ የነበረው ጴጥሮስ ክርስቶስ ያሳየውን ዓይነት ፍቅርና ከዚህ ባሕርይ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ሌሎች ባሕርያት እውነተኞቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማሳየት እንዳለባቸው ተገንዝቧል። ከብዙ ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ ክርስቲያኖች እንደ ራስ መግዛት፣ የወንድማማች መዋደድና ፍቅር የመሳሰሉ ባሕርያትን እንዲያፈሩ አበረታቷል። እንዲህ ማድረጉ “ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች” ከመሆን እንደሚጠብቀን ጨምሮ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 1:​5-8) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የመንፈስን ፍሬ ማፍራት ከአቅማችን በላይ አይደለም። እንግዲያው ፍቅርን፣ ደግነትን፣ የዋህነትንና ክርስቶስ የነበሩትን ሌሎች ባሕርያት ሙሉ በሙሉ ለማንጸባረቅ ጥረት እናድርግ። ምክንያቱም “እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል” ወይም የሚያግድ ሕግ የለም። (ገላትያ 5:​23) በእርግጥም ‘ብዙ ፍሬ’ ማፍራት ይጠበቅብናል።

የመንግሥቱን ፍሬ ማፍራት

8. (ሀ) በመንፈስ ፍሬና በመንግሥቱ ፍሬ መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? (ለ) ልንመረምረው የሚገባን ጥያቄ የትኛው ነው?

8 የሚያማምሩና ግሩም ጣዕም ያላቸው ፍሬዎች ለአንድ ዛፍ ውበት ይጨምሩለታል። ይሁን እንጂ የእነዚህ ፍሬዎች ጥቅም ዛፉን በማሳመር ብቻ የተወሰነ አይደለም። ፍሬ የተክሉን ዘር ለማራባትም በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም፣ የመንፈስ ፍሬ አንድ ክርስቲያን ግሩም ባሕርያት እንዲኖሩት ከማድረግ የበለጠ ጥቅም አለው። ፍቅርንና እምነትን የመሳሰሉ ባሕርያት በዘር የተመሰለውንና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የመንግሥቱን መልእክት እንድናሰራጭ ይገፋፉናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ፍሬና በመንግሥቱ ፍሬ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት አጉልቶ እንደገለጸው ልብ በል። “እኛ ደግሞ እናምናለን [እምነት ከመንፈስ ፍሬ አንዱ ነው] ስለዚህም እንናገራለን” በማለት ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 4:​13) ጳውሎስ “ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” እናቀርባለን በማለት ጨምሮ ተናግሯል። ልናፈራው የሚገባን ሁለተኛው ዓይነት ፍሬ ይህ ነው። (ዕብራውያን 13:15) የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን መጠን በዚህ ረገድ “ብዙ ፍሬ” እንድናፈራ የሚያስችሉ ምን አጋጣሚዎች አሉን?

9. ፍሬ ማፍራት ማለት ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው ሊባል ይቻላልን? አብራራ።

9 የዚህን ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ የመንግሥቱ ፍሬ የሚባለው ምን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። ፍሬ ማፍራት ማለት ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው ቢባል ትክክል ይሆናል? (ማቴዎስ 28:​19) የምናፈራው ፍሬ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያመለክተው የተጠመቁ የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ የረዳናቸውን ግለሰቦች ነውን? በፍጹም። ሁኔታው እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ለመንግሥቱ መልእክት በጎ ምላሽ በማይሰጡ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ለዓመታት በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ የይሖዋ ምሥክሮችን በእጅጉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ይሆን ነበር። አዎን፣ የምናፈራው የመንግሥቱ ፍሬ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ብቻ የሚያመለክት ቢሆን ኖሮ እነዚህ ትጉህ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ እንደተገለጹት የማያፈሩ ቅርንጫፎች በሆኑ ነበር! በእርግጥም ሁኔታው እንደዚያ አይደለም። እንግዲያው አገልግሎታችን የሚያስገኝልን ዋነኛው የመንግሥቱ ፍሬ ምንድን ነው?

የመንግሥቱን ዘር በማሰራጨት ፍሬያማ መሆን

10. ኢየሱስ ስለ ዘሪውና ስለተለያዩ የአፈር ዓይነቶች የተናገረው ምሳሌ የመንግሥቱ ፍሬ የሚባለው ምን እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ ስለ ዘሪውና ስለተለያዩ የአፈር ዓይነቶች የተናገረው ምሳሌ የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። የዚህ ጥያቄ መልስ እምብዛም ውጤታማ ባልሆኑ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ የሚያገለግሉትን በእጅጉ የሚያበረታታ እንደሚሆን እሙን ነው። ኢየሱስ ዘሩ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው የመንግሥቱ መልእክት እንደሆነና አፈሩ የአንድን ሰው ምሳሌያዊ ልብ እንደሚያመለክት ተናግሯል። አንዳንዱ ዘር “በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ . . . አፈራ።” (ሉቃስ 8:8) ምን ዓይነት ፍሬ? አንድ ስንዴ አፈራ የሚባለው አድጎ ከደረሰ በኋላ ዘር ሲሰጥ እንጂ ሌሎች አዳዲስ ቡቃያዎች ሲተካ አይደለም። በተመሳሳይም፣ አንድ ክርስቲያን የሚያፈራው ፍሬ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ሳይሆኑ አዳዲስ የመንግሥቱ ዘሮች ናቸው።

11. የመንግሥቱ ፍሬ ሲባል ምን ማለት ነው?

11 ስለሆነም በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰው ፍሬ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትንም ሆነ ግሩም የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አያመለክትም። የተዘራው ዘር የመንግሥቱ ቃል ስለሆነ ፍሬውም ስለ መንግሥቱ በየጊዜው የምንናገረውን መልእክት የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። እንግዲያው የመንግሥቱን ምሥራች መናገር ፍሬ እንደ ማፍራት ይቆጠራል። (ማቴዎስ 24:​14) እንዲህ ሲባል ታዲያ ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን የመንግሥቱን ፍሬ ማፍራት ማለትም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ ከአቅማችን በላይ አይደለም ማለት ነውን? አዎን፣ ከአቅማችን በላይ አይደለም! ኢየሱስ በዚያው ምሳሌ ውስጥ እንዲህ የምንልበትን ምክንያት ገልጾልናል።

የአቅማችንን በማድረግ አምላክን ማክበር

12. ሁሉም ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ፍሬ ማፍራት ይችላሉ? አብራራ።

12 ኢየሱስ “በመልካም መሬት የተዘራውም . . . አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል” ብሏል። (ማቴዎስ 13:23) በአንድ ማሳ ላይ የተዘራ ዘር የሚሰጠው ምርት እንደ ሁኔታው ሊለያይ ይችላል። በተመሳሳይም፣ ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ማከናወን የምንችለው ነገር ባለን ሁኔታ ላይ ይመካል። ኢየሱስም ይህን እንደሚረዳ ተናግሯል። አንዳንዶች ሰፋ ያለ ጊዜ ሲኖራቸው ሌሎች ደግሞ የተሻለ ጤንነትና የበለጠ ብርታት ይኖራቸው ይሆናል። ስለሆነም ማድረግ የምንችለው ነገር ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ያንስ ወይም ይበልጥ ይሆናል፤ ሆኖም አቅማችን የፈቀደውን እስካደረግን ድረስ ይሖዋ በደስታ ይቀበለዋል። (ገላትያ 6:​4) የዕድሜ መግፋት ወይም ህመም በስብከቱ ሥራ ላይ የምናደርገውን ተሳትፎ ቢገድብብንም እንኳን ርኅሩኅ የሆነው አባታችን ይሖዋ ‘ብዙ ፍሬ ከሚያፈሩት’ አገልጋዮቹ እኩል እንደሚመለከተን ምንም ጥርጥር የለውም። ለምን? ምክንያቱም ‘ያለንን ሁሉ’ ስለሰጠነው ማለትም በሙሉ ነፍሳችን ስላገለገልነው ነው። b​—⁠ማርቆስ 12:​43, 44፤ ሉቃስ 10:​27

13. (ሀ) የመንግሥቱን ፍሬ ማፍራታችንን ‘እንድንቀጥል’ የሚገፋፋን ከሁሉም የላቀው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) እምብዛም አዎንታዊ ምላሽ በማይገኝባቸው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ፍሬ ማፍራታችንን እንድንቀጥል ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው? (በገጽ 21 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

13 ያፈራነው የመንግሥቱ ፍሬ መጠን ምንም ያህል ቢሆን ሥራውን መሥራት የሚኖርብን ለምን እንደሆነ ምንጊዜም ማስታወሳችን ‘እንድንሄድና ፍሬ እንድናፈራ’ ይገፋፋናል። (ዮሐንስ 15:​16) ኢየሱስ “ብዙ ፍሬ ብታፈሩ . . . በዚህ አባቴ ይከበራል” በማለት የምንሰብክበትን ዋነኛ ምክንያት ገልጾልናል። (ዮሐንስ 15:8) አዎን፣ የስብከቱ ሥራችን የይሖዋ ስም በመላው የሰው ዘር ፊት እንዲቀደስ ያደርጋል። (መዝሙር 109:​30) ኦነር የሚባሉ በ70ዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኙ አንዲት ታማኝ የይሖዋ ምሥክር “ለመንግሥቱ መልእክት እምብዛም አዎንታዊ ምላሽ በማይገኝባቸው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ እንኳ ሳይቀር ልዑሉን አምላክ ወክሎ መናገር እጅግ ታላቅ መብት ነው” ብለዋል። ከ1974 አንስቶ በቅንዓት ሲያገለግሉ የቆዩ ክላውዲዮ የተባሉ አንድ የይሖዋ ምሥክር ምንም እንኳን ብዙዎች አዎንታዊ ምላሽ ባይሰጡም መስበካቸውን ለምን እንዳላቋረጡ ሲጠየቁ ኢየሱስ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ሲል የተናገረውን ዮሐንስ 4:​34ን ጠቀሱ። አክለውም “እኔም ልክ እንደ ኢየሱስ፣ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን የማከናውነውን ሥራ መጀመር ብቻ ሳይሆን መፈጸምም እፈልጋለሁ” ብለዋል። (ዮሐንስ 17:​4) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አባባል ይስማማሉ።​—⁠በገጽ 21 ላይ የሚገኘውን “‘በመጽናት ፍሬ ማፍራት’ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

መስበክና ማስተማር

14. (ሀ) መጥምቁ ዮሐንስም ሆነ ኢየሱስ ያከናወኑት ሥራ ምን ጥምር ዓላማ ነበረው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን ሥራ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?

14 በወንጌሎች ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኘው የመጀመሪያው የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። (ማቴዎስ 3:​1, 2፤ ሉቃስ 3:​18) ተቀዳሚ ዓላማው ‘መመስከር’ የነበረ ሲሆን ይህን ዓላማውን ከልብ በመነጨ እምነትና ‘ሁሉ እንዲያምኑ’ ተስፋ በማድረግ አከናውኗል። (ዮሐንስ 1:​6, 7) ዮሐንስ የሰበከላቸው አንዳንድ ሰዎች የኋላ ኋላ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ ይታወቃል። (ዮሐንስ 1:​35-37) ስለሆነም ዮሐንስ ሰባኪና ደቀ መዝሙር አድራጊ ነበር ማለት ይቻላል። ኢየሱስም ሰባኪና አስተማሪ ነበር። (ማቴዎስ 4:​23፤ 11:​1) እንግዲያው ኢየሱስ ተከታዮቹ የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰብኩ ብቻ ሳይሆን መልእክቱን የተቀበሉ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ትእዛዝ መስጠቱ አያስደንቅም። (ማቴዎስ 28:​19, 20) እኛም በዚህ ዘመን የምናከናውነው ሥራ ስብከትንና ደቀ መዝሙር ማድረግን አጣምሮ የያዘ ነው።

15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በተከናወነው የስብከት ሥራና በዘመናችን እየተከናወነ ባለው ሥራ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ ሲሰብክና ሲያስተምር ያዳምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል “እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፣ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም።” (ሥራ 28:24) ዛሬም ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ተመሳሳይ ነው። አብዛኛው የመንግሥቱ ዘር በማያፈራ የአፈር ዓይነት ላይ መውደቁ ያሳዝናል። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው አንዳንዱ ዘር በመልካሙ አፈር ላይ ወድቆ ሥር በመስደድ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም። እንዲያውም በዓለም ዙሪያ በየሳምንቱ በአማካይ ከ5, 000 የሚበልጡ ሰዎች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ! እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ከአብዛኞቹ ሰዎች በተለየ መልኩ ‘የተነገራቸውን አምነዋል።’ በልባቸው ላይ የተዘራው የመንግሥቱ መልእክት ሥር እንዲሰድ የረዳቸው ምንድን ነው? አንድ ሰው የተከለውን ችግኝ ውኃ እንደሚያጠጣውና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግለት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ለሰዎቹ ያሳዩት አሳቢነት ለውጥ አምጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 3:​6) በዚህ ረገድ ከብዙ ምሳሌዎች መካከል እስቲ ሁለቱን ብቻ እንመልከት።

አሳቢነት ማሳየት ለውጥ ያመጣል

16, 17. በአገልግሎታችን ለምናገኛቸው ሰዎች አሳቢነትን ማሳየት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

16 በቤልጅየም የምትኖር ካሮሊን የተባለች አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር ለአንዲት አረጋዊት ሴት የመንግሥቱን መልእክት ስትነግራቸው ምንም ፍላጎት ሳያሳዩ ይቀራሉ። ካሮሊን እና የአገልግሎት ጓደኛዋ ሴትየዋ እጃቸው በፋሻ መጠቅለሉን ሲያስተውሉ ሥራ ሊያግዟቸው እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል። ሴትየዋ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም። ከሁለት ቀናት በኋላ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሴትየዋ ቤት ተመልሰው በመሄድ ተሽሏቸው እንደሆነ ጠየቋቸው። ካሮሊን ስለ ሁኔታው ስትናገር “በዚህ ጊዜ ሁኔታው ተለወጠ። በእርግጥ ከልብ እንዳሰብንላቸው ሲሰማቸው በጣም ተገረሙ። ወደ ቤት እንድንገባ ጋበዙንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርን” ብላለች።

17 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሳንዲ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክርም ለምትሰብክላቸው ሰዎች አሳቢነት ታሳያለች። በአካባቢው በሚታተም ጋዜጣ ላይ በየጊዜው የሚወጣውን የአራስ እናቶች ስም ዝርዝር እየተከታተለች ቤታቸው ድረስ በመሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ትሰጣቸዋለች። c እነዚህ አራስ እናቶች ብዙውን ጊዜ ከቤት ስለማይጠፉና ሊጠይቃቸው ለመጣ እንግዳ ልጃቸውን ማሳየት ስለሚያስደስታቸው ከእነርሱ ጋር ውይይት መክፈት ቀላል ነው። ሳንዲ ስለሁኔታው ስትናገር “ለአራስ ሕጻናት ማንበብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ እንዲሁም አሁን ባለንበት ሥርዓት ውስጥ ልጆችን ማሳደግ ምን ያህል ተፈታታኝ እንደሆነ ለወላጆቹ እነግራቸዋለሁ” ብላለች። እንዲህ ያለ ጥረት በማድረግዋ በቅርቡ አንዲት እናት እና ስድስት ልጆች ይሖዋን ማገልገል ጀምረዋል። ቀዳሚ ሆኖ ሄዶ ማነጋገርና አሳቢነት ማሳየት አስደሳች የሆኑ ተመሳሳይ ውጤቶችን ያስገኛል።

18. (ሀ) ‘ብዙ ፍሬ ማፍራት’ ከአቅማችን በላይ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ማሟላት ያለብን ሦስቱ ብቃቶች የትኞቹ ናቸው?

18 ‘ብዙ ፍሬ እንድናፈራ’ የሚጠበቅብን ብቃት፣ ከአቅማችን በላይ እንዳልሆነ ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ወጣትም ሆንን አረጋውያን፣ ጥሩ ጤና ኖረንም አልኖረን፣ የአገልግሎት ክልላችን ጥሩም ይሁን መጥፎ ሁላችንም ብዙ ፍሬ ማፍራት እንችላለን። እንዴት? የመንፈስን ፍሬ ሙሉ በሙሉ በማፍራትና የአምላክን መንግሥት መልእክት አቅማችን በፈቀደ መጠን በማሰራጨት ነው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ‘በኢየሱስ ቃል እንኖራለን’ እንዲሁም ‘እርስ በርሳችን ፍቅር ይኖረናል።’ አዎን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተገለጹትንና የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን የሚያስፈልጉትን እነዚህን ሦስት አስፈላጊ ብቃቶች በማሟላት ‘በእውነት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት’ መሆናችንን እናስመሰክራለን።​—⁠ዮሐንስ 8:​31፤ 13:​35

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በምሳሌው ውስጥ የተገለጸው የወይን ቅርንጫፍ የኢየሱስን ሐዋርያትና በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ ቦታ ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያመለክት ቢሆንም ምሳሌው በዛሬው ጊዜ ያሉትን የክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ የሚጠቅም ትምህርት ይዟል።​—⁠ዮሐንስ 3:​16፤ 10:​16

b በዕድሜ መግፋት ወይም በህመም ምክንያት ከቤት የማይወጡ ክርስቲያኖች ደብዳቤ በመጻፍ ወይም የሚቻል ከሆነ ስልክ በመደወል መመስከር ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ሊጠይቋቸው ለሚመጡ ሰዎች ምሥራቹን ማካፈል ይችላሉ።

c በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ።

የክለሳ ጥያቄዎች

• በብዛት ማፍራት ያለብን የትኛውን ፍሬ ነው?

• ‘ብዙ ፍሬ ማፍራት’ ከአቅማችን በላይ ሊሆንብን የማይችለው ለምንድን ነው?

• በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን የሚያስፈልጉት ሦስቱ ብቃቶች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘በመጽናት ፍሬ ማፍራት’ የሚቻለው እንዴት ነው?

ለመንግሥቱ መልእክት እምብዛም አዎንታዊ ምላሽ በማይገኝባቸው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ በታማኝነት መስበክህን እንድትቀጥል ምን ሊረዳህ ይችላል? ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆኑ ጠቃሚ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

“በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈን ማወቃችን አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረንና እንድንጸና ያበረታታናል።”​—⁠ሃሪ፣ ዕድሜ 72፤ በ1946 የተጠመቁ ወንድም።

ሁለተኛ ቆሮንቶስ 2:​17 ምንጊዜም ያበረታታኛል። ጥቅሱ አገልግሎታችንን የምናከናውነው “በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን” እንደሆነ ይናገራል። ከሁሉም የላቁ ወዳጆቼ ከሆኑት ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር አብሬ ማገልገሌ ያስደስተኛል።”​—⁠ክላውዲዮ፣ ዕድሜ 43፤ በ1974 የተጠመቀ ወንድም።

“ግልጹን ለመናገር፣ ስብከት ለእኔ ተፈታታኝ ሥራ ነው። ሆኖም ‘በአምላኬ ቅጥሩን እዘላለሁ’ የሚለውን የመዝሙር 18:​29 አባባል በራሴ ሕይወት ውስጥ እውነት ሆኖ አይቼዋለሁ።”​—⁠ጌሪት፣ ዕድሜ 79፤ በ1955 የተጠመቁ ወንድም።

“አገልግሎት ላይ ቢያንስ አንድ ጥቅስ ሳነብብ አንድ ሰው ልቡን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት እንዲመረምር እንደረዳሁ ስለሚሰማኝ እረካለሁ።”​—⁠ኢለነር፣ ዕድሜ 26፤ በ1989 የተጠመቀች እህት።

“የተለያዩ መግቢያዎችን ለመጠቀም እሞክራለሁ። እጅግ የተለያዩ በርካታ መግቢያዎች ስላሉ ዕድሜ ልኬን ብጠቀምባቸው እንኳ ልዘልቃቸው አልችልም።”​—⁠ፖል፣ ዕድሜ 79፤ በ1940 የተጠመቁ ወንድም።

“የሰዎች ምላሽ ምንም ያህል መጥፎ ቢሆን ቅር አልሰኝም። በአገልግሎት ላይ የማገኛቸውን ሰዎች ዘና ብዬ ለመቅረብ ይኸውም ውይይት ለማድረግና የሚሰጡትን አስተያየት ለማዳመጥ ጥረት አደርጋለሁ።”​—⁠ዳንኤል፣ ዕድሜ 75 ፤ በ1946 የተጠመቁ ወንድም።

“በስብከቱ ሥራ የማደርገው እንቅስቃሴ የይሖዋ ምሥክር እንዲሆኑ አስተዋጽኦ እንዳደረገ የሚነግሩኝ አዳዲስ ተጠማቂዎች ያጋጥሙኛል። ከሰበክሁላቸው በኋላ እኔ ሳላውቅ ሌላ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን አስጠንቶ እድገት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። አገልግሎታችን የቡድን ሥራ መሆኑን ማወቄ ያስደስተኛል።”​—⁠ጆአን፣ ዕድሜ 66፤ በ1954 የተጠመቁ እህት።

አንተስ ‘በመጽናት ፍሬ እንድታፈራ’ የረዳህ ምንድን ነው?​—⁠ሉቃስ 8:​15

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንፈስን ፍሬ በማፍራትና የመንግሥቱን መልእክት በማወጅ ብዙ ፍሬ ማፍራት እንችላለን

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሐዋርያቱን ‘ብዙ ፍሬ አፍሩ’ ሲላቸው ምን ማለቱ ነበር?