በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስተማማኝና አስደሳች ሥራ ማግኘት አዳጋች ሆኗል

አስተማማኝና አስደሳች ሥራ ማግኘት አዳጋች ሆኗል

አስተማማኝና አስደሳች ሥራ ማግኘት አዳጋች ሆኗል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ዓለም አቀፋዊው የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ሁሉም ሰው “የመሥራት መብት” አለው ይላል። ይሁን እንጂ ይህ መብት የሚጣስባቸው ጊዜያት አሉ። አስተማማኝ ሥራ ማግኘት በበርካታ ሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። በዚህ ረገድ የየአገሮቹ የኢኮኖሚ ጥንካሬም ሆነ ዓለም አቀፉ የንግድ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በመሆኑም ሰዎች ከሥራ ገበታቸው ሲፈናቀሉ ወይም ሥራን የማጣት አደጋ ሲያጠላባቸው አብዛኛውን ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ሁከትና የሥራ ማቆም አድማ ይከሰታል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የማያጋጥማቸው አገሮች የሉም ለማለት ይቻላል። አንድ ጸሐፊ እንዳሉት “ሥራ” የሚለው ቃል ራሱ “ጥንትም ሆነ ዛሬ በሰዎች ላይ ልዩ ስሜት የሚያሳድር ቃል ነው።”

ሥራ ብዙ ጥቅሞች አሉት። መተዳደሪያ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ለአእምሯዊና ለስሜታዊ ጤንነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሥራ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተፈላጊ ሰው ሆኖ የመገኘትና ዓላማ ያለው ሕይወት የመምራት ፍላጎታችንን ያረካልናል። በተጨማሪም ለራሳችን ጥሩ ግምት እንዲኖረን ያስችለናል። ከዚህም የተነሳ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የሚያስችል ብዙ ገንዘብ ያላቸው ወይም ጡረታ መውጣት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ የደረሱ አንዳንድ ሰዎች መሥራትን ይመርጣሉ። አዎን፣ ሥራ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ሥራ አጥነት አብዛኛውን ጊዜ ከባድ ማኅበራዊ ቀውሶች ያስከትላል።

በአንጻሩ ደግሞ ሥራ ቢኖራቸውም ከሚያስከትልባቸው ጫና የተነሳ ሥራ የሚያስጠላቸው ሰዎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል በዛሬው ጊዜ ገበያ ለመቆጣጠር ከሚደረገው ከፍተኛ ፉክክር የተነሳ በርካታ ድርጅቶች ወጪ ለመቀነስ ሲሉ የሰው ኃይል ቅነሳ አድርገዋል። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ በሥራው ላይ ክፍተት ስለሚፈጥር በቀሪዎቹ ሠራተኞች ላይ የሥራ ጫና ይፈጥርባቸዋል።

ሥራን በማቀላጠፍ ቀላል ሕይወት ለመምራት ያስችላሉ የሚባልላቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችም እንኳ በሠራተኛው ላይ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ኮምፒውተሮች፣ የፋክስ ማሽኖችና ኢንተርኔት ሰዎች ከሥራ ሰዓት በኋላ ሥራቸውን በቤታቸው ማከናወን የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል። ይህም መኖሪያ ቤት የእረፍት ቦታ መሆኑ ቀርቶ ወደ ቢሮነት እንዲቀየር አድርጎታል። አንድ ሠራተኛ መሥሪያ ቤቱ የሰጠው ሞባይል ስልክ አለቃው እርሱን እንዳሻው የሚቆጣጠርበት ስውር ልጓም እንደሆነ ተሰምቶታል።

በጉልምስና ዕድሜያቸው ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች የመሥራት አቅሙ እያላቸው በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ ባለው የኢኮኖሚና የሥራ ሁኔታ ምክንያት ዋጋ እንደሌላቸው ተደርገው እንዳይቆጠሩ ይፈራሉ። ይህን በተመለከተ የቀድሞው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ክሪስ ሲዶቴ “ከ40 ዓመት በታች እስካልሆንክ ድረስ ከኮምፒውተሮችና ከአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር እኩል መራመድ አትችልም የሚል ጠባብ አመለካከት የሰፈነ ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ትጉ ሠራተኞች አሁን አሁን ጊዜ እንዳለፈባቸው ተደርገው ይታያሉ። እንዴት ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ነው!

በትጋት መሥራትና ለአንድ መሥሪያ ቤት ታማኝ መሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጠፋ እንደመጣ ግልጽ ነው። “ድርጅቶች አትራፊ አልሆንንም በሚል ሰበብ ሠራተኞቻቸውን ከሥራ በሚያባርሩበት በአሁኑ ጊዜ ለአንድ መሥሪያ ቤት ታማኝ መሆን ምንም ዋጋ አይኖረውም” ሲል በፈረንሳይኛ የሚታተመው ሊቤራሲዮ የተባለው መጽሔት አትቷል። “መሥራት እንዳለብህ የታወቀ ነው። ሆኖም የምትሠራው ለራስህ እንጂ ለመሥሪያ ቤቱ አይደለም።”

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ የሚሄዱ ችግሮች ቢኖሩም ሰዎች አሁንም ሥራ የመሥራት ተፈጥሯዊ ፍላጎት አላቸው። በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠ ባለው በዚህ ዘመን አንድ ሰው ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? እንዲሁም አስተማማኝና አስደሳች ሥራ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሥራ ቦታ ላይ ተጨማሪ ጫና አስከትሎ ሊሆን ይችላል