በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

“እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”​—⁠ዮሐንስ 13:​35

1. ኢየሱስ በሞቱ ዋዜማ ላይ ጎላ አድርጎ የገለጸው ባሕርይ የትኛው ነው?

 ኢየሱስ በሞቱ ዋዜማ፣ ምሽት ላይ ሐዋርያቱን “ልጆች ሆይ” በማለት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጠርቷቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:​33) ከዚህ ቀደም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ባለ አንጀት የሚበላ ቃል እንደጠራቸው የሚያሳይ የወንጌል ዘገባ አናገኝም። ይሁን እንጂ በዚያ ልዩ ምሽት ለተከታዮቹ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ ይህንን የፍቅር አጠራር ተጠቅሟል። እንዲያውም ኢየሱስ በዚያች ምሽት ስለ ፍቅር 30 የሚያህል ጊዜ ጠቅሶ ተናግሯል። ለዚህ ባሕርይ ይህን ያህል የጎላ ስፍራ የሰጠው ለምን ነበር?

2. ክርስቲያኖች ፍቅር ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ፍቅር በጣም አስፈላጊ ባሕርይ የሆነበትን ምክንያት ገልጿል። (ዮሐንስ 13:​35፤ 15:​12, 17) የክርስቶስ ተከታይ መሆንና የወንድማማች ፍቅር ማሳየት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት በተለየ አለባበስ ወይም እንግዳ የሆኑ ልማዶች በመከተላቸው ሳይሆን ለእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚያሳዩት ከልብ የመነጨ ፍቅር ነው። ጉልህ ስፍራ የሚሰጠውን ይህን ፍቅር ማሳየት በፊተኛው ርዕስ ውስጥ ከተገለጹት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ከሚያስፈልጉ ሦስት ብቃቶች መካከል ሁለተኛው ነው። ይህንን ብቃት እንድናሟላ ምን ሊረዳን ይችላል?

‘ከፊት ይልቅ ተዋደዱ’

3. ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅርን በሚመለከት ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ዛሬ ያሉት የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርትም እርስ በርስ ከልብ እንደሚዋደዱ በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤ እንዲሁ . . . [ለ]ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና” በማለት ጽፎላቸው ነበር። ያም ሆኖ ግን ጳውሎስ ‘ከፊት ይልቅ ልትበዙ [“እንድትወዱ፣” የ1980 ትርጉም ] . . . እለምናችኋለሁ’ ብሎ ከማሳሰብ ወደኋላ አላለም። (1 ተሰሎንቄ 3:​12፤ 4:​9, 10) እኛም የጳውሎስን ማሳሰቢያ ተከትለን እርስ በርሳችን “ከፊት ይልቅ” መዋደድ ይኖርብናል።

4. በጳውሎስ እና በኢየሱስ ማበረታቻ መሠረት የተለየ ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለእነማን ነው?

4 ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው በዚህ ደብዳቤ ላይ የእምነት ባልንጀሮቹ ‘የተጨነቁትን ነፍሳት እንዲያጽናኑና ደካሞችን እንዲደግፉ’ አበረታቷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:​14 NW ) በሌላ ጊዜ ደግሞ “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም” በማለት ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 15:​1) ኢየሱስም ደካሞችን ስለመርዳት አንዳንድ መመሪያዎችን ሰጥቷል። ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ጴጥሮስ እንደሚክደው ከነገረው በኋላ “አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና” ብሎት ነበር። ለምን? እንደ ጴጥሮስ እነርሱም ስለሚክዱትና በዚህም ምክንያት ማጽናኛ ስለሚያስፈልጋቸው ነው። (ሉቃስ 22:32፤ ዮሐንስ 21:​15-17) ስለሆነም የአምላክ ቃል በመንፈሳዊ ደክመው ከክርስቲያን ጉባኤ ለራቁትም ጭምር ፍቅር እንድናሳያቸው ያበረታታናል። (ዕብራውያን 12:​12) እንዲህ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ኢየሱስ የተናገራቸው ሁለት ምሳሌዎች መልሱን ይሰጡናል።

የጠፋው በግ እና የጠፋው ድሪም

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ምን ሁለት አጫጭር ምሳሌዎች ተናገረ? (ለ) እነዚህ ምሳሌዎች ስለ ይሖዋ ምን ያስተምሩናል?

5 ይሖዋ ጠፍተው ስለባዘኑት አገልጋዮቹ ያለውን አመለካከት ለማስተማር ኢየሱስ ለአድማጮቹ ሁለት አጫጭር ምሳሌዎችን ነገራቸው። አንደኛው ስለ እረኛ የሚናገር ሲሆን እንዲህ ይላል:- “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፣ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ:- የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።”​—⁠ሉቃስ 15:4-7

6 ኢየሱስ የተናገረው ሌላው ምሳሌ ስለ አንዲት ሴት ነው። እንዲህ ይላል:- “አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፣ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ:- የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች። እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።”​—⁠ሉቃስ 15:8-10

7. ስለጠፋው በግና ስለጠፋው ድሪም ከሚናገሩት ምሳሌዎች የምንቀስማቸው ሁለት ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

7 ከእነዚህ ሁለት አጫጭር ምሳሌዎች ምን እንማራለን? (1) በመንፈሳዊ ለደከሙ ክርስቲያኖች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምን መሆን እንደሚኖርበትና (2) እነርሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንደሚገባን እንማራለን። ከዚህ ቀጥሎ እነዚህን ነጥቦች እንመረምራለን።

ይጥፉ እንጂ ውድ ናቸው

8. (ሀ) እረኛውና ሴቲቱ የጠፋባቸው ንብረት እንዳለ ሲያውቁ ምን አደረጉ? (ለ) የጠፋባቸውን ፈልገው ለማግኘት የወሰዱት እርምጃ ለንብረቱ ያላቸውን አመለካከት የሚገልጽልን እንዴት ነው?

8 በሁለቱም ምሳሌዎች ውስጥ አንድ ነገር እንደጠፋ ተገልጿል፤ ሆኖም ባለቤቶቹ ምን እንዳደረጉ ልብ በል። እረኛው ‘99ኙ እስካሉልኝ ድረስ ለአንዱ ምን አስጨነቀኝ? አንዱ ቢጠፋ ምንም አያጎድለኝም’ አላለም። ሴትየዋም ‘ለአንዲት ድሪም ምን አስጨነቀኝ? ዘጠኝ ድሪም ካለኝ ይበቃኛል’ አላለችም። ከዚህ ይልቅ እረኛው አንድ በግ ብቻ ያለው ይመስል የጠፋውን ለማግኘት ፍለጋውን ተያያዘው። ሴትየዋም ከዚያ ሌላ ድሪም የሌላት ይመስል መጥፋቱ በጣም ቆጭቷታል። በሁለቱም ምሳሌዎች ውስጥ ባለቤቶቹ ውድ የሆነ ነገር እንደጠፋባቸው ተሰምቷቸዋል። ይህ ምን ያስተምረናል?

9. እረኛውና ሴትየዋ ለጠፋባቸው ንብረት የሰጡት ትኩረት የምን ምሳሌ ነው?

9 ኢየሱስ እያንዳንዱን ምሳሌ ተናግሮ ካበቃ በኋላ “እንዲሁ . . . ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል” እና ‘እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል’ እንዳለ ልብ በል። እረኛውና ሴትየዋ ለጠፋባቸው ንብረት የሰጡት ትኩረት ይሖዋና ሰማያዊ ፍጥረታቱ ምን እንደሚሰማቸው በመጠኑም ቢሆን ያሳያል። የጠፋው ነገር ለእረኛውም ሆነ ለሴትየዋ ውድ እንደሆነ ሁሉ ባዝነው ከሕዝቦቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋረጡ ሰዎችም በይሖዋ ፊት ውድ ናቸው። (ኤርምያስ 31:​3) እንደዚህ ያሉ ግለሰቦች በመንፈሳዊ ተዳክመው ይሆናል፤ ዓመፀኞች ናቸው ማለት ግን አይደለም። በመንፈሳዊ ይድከሙ እንጂ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይሖዋ ያወጣቸውን መስፈርቶች ይጠብቁ ይሆናል። (መዝሙር 119: 176፤ ሥራ 15:​28, 29) በመሆኑም ይሖዋ ከዚህ በፊትም እንዳደረገው ሁሉ ወዲያውኑ “ከፊቱ አልጣላቸውም።”​—⁠2 ነገሥት 13:​23

10, 11. (ሀ) ከጉባኤ የጠፉ ሰዎችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? (ለ) ኢየሱስ በተናገራቸው ሁለት ምሳሌዎች መሠረት አሳቢነታችንን ልንገልጽላቸው የምንችለው እንዴት ነው?

10 እንደ ይሖዋና እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም በመንፈሳዊ ለደከሙትና ከክርስቲያን ጉባኤ ለጠፉት ሰዎች ከልብ እናስባለን። (ሕዝቅኤል 34:​16፤ ሉቃስ 19:​10) በመንፈሳዊ የደከመን ሰው እንደጠፋ በግ እንጂ የመመለስ ተስፋ እንደሌለው አድርገን ማየት አይኖርብንም። ‘ስለ ደከመ ሰው ምን አሳሰበኝ? የእርሱ መኖር አለመኖር በጉባኤው ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም’ ብለን ማሰብ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ የጠፉትን ሆኖም መመለስ የሚፈልጉትን ሰዎች ይሖዋ እነርሱን በሚያይበት መንገድ ይኸውም ውድ እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን።

11 ታዲያ አሳቢነታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? ከላይ የተመለከትናቸው ሁለቱ ምሳሌዎች (1) ቅድሚያውን በመውሰድ፣ (2) በደግነት በመያዝ እና (3) ከልብ ተነሳስተን በመርዳት አሳቢነት ማሳየት እንደምንችል ያስተምሩናል። እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከት።

ቅድሚያውን ውሰዱ

12. ‘የጠፋውን ለመፈለግ እንደሚሄድ’ የሚጠቁመው ሐሳብ ስለ እረኛው ምን ይገልጽልናል?

12 ኢየሱስ ከሁለቱ ምሳሌዎች ውስጥ በመጀመሪያው ላይ እረኛው ‘የጠፋውን ለመፈለግ እንደሚሄድ’ ተናግሯል። እረኛው ቀዳሚ በመሆን የጠፋውን በግ ፈልጎ ለማግኘት ጥረት አድርጓል። አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታ እንዲሁም ርቀት አላገደውም። እንዲያውም እረኛው “እስኪያገኘው ድረስ” ፍለጋውን ቀጥሏል።​—⁠ሉቃስ 15:​4

13. በጥንት ዘመን የኖሩ የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን የረዱት እንዴት ነበር? እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች መኮረጅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

13 በተመሳሳይም፣ ማበረታቻ የሚያስፈልገውን ሰው ለመርዳት በመንፈሳዊ ብርቱ የሆነው ሰው ቀዳሚ መሆን ይኖርበታል። በጥንት ዘመን የኖሩ የታመኑ ሰዎች ይህን ሁኔታ በደንብ ተረድተው ነበር። ለምሳሌ ያህል የንጉሥ ሳኦል ልጅ ዮናታን የልብ ጓደኛው ዳዊት ማበረታቻ እንደሚያስፈልገው በተገነዘበ ጊዜ ‘ተነሥቶ ዳዊት ወደሚገኝበት ወደ ጥሻው ሄዶ በእግዚአብሔር ስም አበርትቶታል።’ (1 ሳሙኤል 23:​15, 16) ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላም አገረ ገዥው ነህምያ ከአገሩ ልጆች መካከል አንዳንዶቹ ተስፋ እንደቆረጡ ባየ ጊዜ ‘ተነስቶ’ “የተፈራውን ጌታ አስቡ” በማለት አበረታታቸው። (ነህምያ 4:​14) በዛሬው ጊዜ እኛም በመንፈሳዊ የደከሙትን ለማበረታታት ቀዳሚ ሆነን ‘መነሳት’ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ከጉባኤ አባላት መካከል እንዲህ ማድረግ የሚኖርባቸው እነማን ናቸው?

14. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመንፈሳዊ የደከሙትን ወንድሞች መርዳት የሚኖርባቸው እነማን ናቸው?

14 በተለይ ደግሞ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ‘የደከሙትን እጆች የማበርታት፣ የላሉትን ጉልበቶች የማጽናት እንዲሁም ፈሪ ልብ ያላቸውን በርቱ አትፍሩ የማለት’ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ኢሳይያስ 35:​3, 4፤ 1 ጴጥሮስ 5:​1, 2) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ‘የተጨነቁ ነፍሳትን አጽናኗቸው’ እና ‘ደካሞችን ደግፏቸው’ በማለት የሰጠው ማበረታቻ ሽማግሌዎችን ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው “ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን” ነበር። (1 ተሰሎንቄ 1:​1፤ 5:​14 NW ) በመንፈሳዊ የደከሙ ወንድሞችን መርዳት ለሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጠ ኃላፊነት ነው። በምሳሌው ውስጥ እንደተጠቀሰው እረኛ እያንዳንዱ ክርስቲያን ‘የጠፋውን ፍለጋ ለመሄድ’ መነሳት ይኖርበታል። እርግጥ ነው እንዲህ ያለው ጥረት ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው ከሽማግሌዎች ጋር ተባብረን ስንሠራ ነው። አንተስ በጉባኤህ የሚገኝ በመንፈሳዊ የደከመን አንድ ሰው ለመርዳት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ?

ደግነት አሳዩ

15. እረኛው በጉን በጫንቃው ላይ የተሸከመው ለምን ሊሆን ይችላል?

15 እረኛው የጠፋበትን በግ ፈልጎ ሲያገኘው ምን ያደርጋል? “በጫንቃው ይሸከመዋል።” (ሉቃስ 15:5) እንዴት ያለ ልብ የሚነካ አገላለጽ ነው! በጉ ምናልባትም አዳኝ አንበሶች በሚገኙበት እንግዳ በሆነ አካባቢ ለብዙ ቀናት ሲቅበዘበዝ ቆይቶም ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 38:​39, 40) በረሃብ ተዳክሞ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። በጣም ከመዳከሙ የተነሳ ወደ መንጋው በሚመለስበት ጊዜ የሚያጋጥመውን ውጣ ውረድ ለማለፍ የሚያስችል ኃይል ይኖረዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ስለሆነም እረኛው ጎንበስ ብሎ በጉን በጥንቃቄ በማንሳት በጫንቃው ላይ ተሸክሞ እንቅፋቶችን ሁሉ አሳልፎ ወደ መንጋው ያደርሰዋል። እረኛው ለበጉ ያደረገውን እንክብካቤ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

16. እረኛው ለጠፋው በግ ያሳየውን አሳቢነት መኮረጅ የሚገባን ለምንድን ነው?

16 ከጉባኤው ጋር የነበረውን ግንኙነት ያቋረጠ ሰው በመንፈሳዊ ሁኔታ በእጅጉ መዳከሙ አይቀርም። እንዲህ ያለ ሰው ከእረኛው እንደጠፋው በግ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ እንዲሁ ሲንከራተት ቆይቶ ሊሆን ይችላል። በመንጋ ከተመሰለው የክርስቲያን ጉባኤ ጋር መሆን የሚያስገኘው ጥበቃ ስለሌለው “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ” ለሚዞረው ለዲያብሎስ ጥቃት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተጋልጧል። (1 ጴጥሮስ 5:​8) ከዚህም በተጨማሪ በመንፈሳዊ ምግብ እጦት በእጅጉ ተዳክሟል። በጣም ከመዳከሙ የተነሳ ወደ ጉባኤው ሲመለስ የሚያጋጥመውን መሰናክል ተቋቁሞ ማለፍ እንደማይችል የታወቀ ነው። ስለሆነም በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው እረኛ ጎንበስ ብለን በደግነት በመሸከም ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለስ ይኖርብናል። (ገላትያ 6:​2) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

17. በመንፈሳዊ የደከመን ሰው ሄደን ስንጠይቅ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ “ደካማ ማን ነው? እኔስ አብሬ አልደክምምን?” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 11:​29 አዲሱ መደበኛ ትርጉም፤ 1 ቆሮንቶስ 9:​22) ጳውሎስ በመንፈሳዊ የደከሙትን ጨምሮ ለሰዎች ያዝን ነበር። እኛም በመንፈሳዊ ለደከሙ ሰዎች ተመሳሳይ የርኅራኄ ስሜት ማሳየት እንፈልጋለን። በመንፈሳዊ የደከመን አንድ ክርስቲያን ሄደን በምናነጋግርበት ጊዜ በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆነና ክርስቲያን ባልንጀሮቹም በጣም እንደሚናፍቁት እንዲገነዘብ ልንገልጽለት ያስፈልጋል። (1 ተሰሎንቄ 2:​17) እርሱን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውንና ‘በመከራው እንደሚደርስለት ወንድም’ ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው አስረዱት። (ምሳሌ 17:​17፤ መዝሙር 34:​18) ከልብ በመነጨ ስሜት ሐሳባችንን መግለጻችን ሊያበረታታውና ውሎ አድሮ ወደ መንጋው እንዲመለስ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ከዚያስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ድሪም ስለጠፋባት ሴት የሚናገረው ምሳሌ ቀጥሎ ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ይጠቁመናል።

ጥረታችሁ ልባዊ ይሁን

18. (ሀ) በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰችው ሴት ተስፋ ያልቆረጠችው ለምን ነበር? (ለ) ሴትየዋ የጠፋባትን የብር ሳንቲም ወይም ድሪም ለማግኘት ምን ልባዊ ጥረት አደረገች? ውጤቱስ?

18 ድሪም ወይም ሣንቲም የጠፋባት ሴት ድሪሙን ፈልጎ ማግኘቱ ቀላል እንዳልሆነ ቢገባትም እንኳ ሊገኝ አይችልም ብላ ተስፋ አልቆረጠችም። ድሪሙ በቁጥቋጦ ውስጥ ወይም ጭቃ በሞላበት ጥልቅ ሐይቅ ውስጥ ወድቆባት ቢሆን ኖሮ ምንም ማድረግ እንደማትችል ተሰምቷት በተወችው ነበር። ይሁን እንጂ ድሪሙን ከቤትዋ ውጪ እንዳልጣለችውና ፈልጋ ልታገኘው እንደምትችል በመገንዘብ እያንዳንዱን ነገር እያነሳች ከልብ መፈለግዋን ተያያዘችው። (ሉቃስ 15:​8) በመጀመሪያ በደንብ እንዲታያት መብራት አበራች። ከዚያም ሣንቲሙ ሲያቃጭል ለመስማት ወለሉን በመጥረጊያ ጠረገች። በመጨረሻም የጠፋባትን የብር ሳንቲም እስክታገኝ ድረስ በየስርቻው ሳይቀር በጥንቃቄ መፈለግዋን ቀጠለች። የሴትየዋ ልባዊ ጥረት መና አልቀረም!

19. ድሪም የጠፋባት ሴት ከወሰደችው እርምጃ በመንፈሳዊ የደከሙትን ስለመርዳት ምን ትምህርት እናገኛለን?

19 ከምሳሌው እንደምንረዳው በመንፈሳዊ የደከመን አንድ ክርስቲያን የመርዳቱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት ከአቅማችን በላይ ሊሆንብን አይችልም። ይሁንና ይህን ኃላፊነት መወጣት ከልብ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅብን መዘንጋት አይኖርብንም። በእርግጥም፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ‘እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን እርዱ’ ብሏቸው ነበር። (ሥራ 20:35ሀ) ሴትየዋ የጠፋባትን ድሪም ወይም ሳንቲም እንደነገሩ ፈለግ ፈለግ አድርጋ እንዲያው በአጋጣሚ እንዳላገኘችው ልብ ማለት ይገባል። ሊሳካላት የቻለው የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅማ “እስክታገኘው ድረስ” ስለፈለገችው ነው። በተመሳሳይም በመንፈሳዊ የደከመን ሰው ለመርዳት የምናደርገው ጥረት ከልብ የመነጨና የታሰበበት መሆን ይኖርበታል። ምን ማድረግ እንችላለን?

20. በመንፈሳዊ የደከሙትን ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል?

20 በመንፈሳዊ የደከመ ሰው እምነቱንና አድናቆቱን እንዲገነባ እንዴት መርዳት እንችላለን? ተስማሚ በሆነ ክርስቲያናዊ ጽሑፍ አማካኝነት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጉ ብቻ እንኳን ሊረዳው ይችላል። በመንፈሳዊ ለደከመ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ቀጣይነት ባለው መንገድ የተሟላ እርዳታ ለመስጠት እንደሚያስችል የታወቀ ነው። እንዲህ ያለውን እርዳታ ማን ቢሰጥ የተሻለ እንደሚሆን የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ቢወስን ይመረጣል። ጥናቱ በየትኞቹ ርዕሶች ላይ ማተኮር እንዳለበትና የትኛው ጽሑፍ ቢጠና ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን ሐሳብ መስጠት ይችላል። በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰችው ሴት ጠቃሚ መሣሪያዎችን ተጠቅማ ግብዋን እንደመታች ሁሉ እኛም በመንፈሳዊ የደከሙትን እንድንረዳ አምላክ የሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉን የተለያዩ መሣሪያዎች አሉን። በዚህ ረገድ እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ እና ይሖዋን የቅርብ ወዳጅህ አድርገው የተባሉት ሁለቱ አዳዲስ መሣሪያዎቻችን ወይም መጽሐፎቻችን ይበልጥ ሊረዱን ይችላሉ። a

21. በመንፈሳዊ የደከሙትን መርዳት ለሁሉም በረከት የሚያስገኘው እንዴት ነው?

21 በመንፈሳዊ የደከሙ ሰዎችን መርዳት ለሁሉም በረከት ያስገኛል። እርዳታ የሚደረግለት ግለሰብ ከእውነተኛ ወዳጆቹ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደገና ስለሚያድስ ደስ ይለዋል። እኛም መስጠት የሚያስገኘውን እውነተኛ ደስታ እናገኛለን። (ሉቃስ 15:​6, 9፤ ሥራ 20:​35ለ) የጉባኤው አባላት እንዲህ እርስ በርሳቸው ሲረዳዱና ሲተሳሰቡ የጉባኤው ፍቅር ይጨምራል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንዲህ ያለው አድራጎት በመንፈሳዊ የደከሙትን የመርዳት ፍላጎታቸው በምድራዊ አገልጋዮቻቸው የተንጸባረቀው እረኞቻችንን ማለትም ይሖዋን እና ኢየሱስን ያስከብራል። (መዝሙር 72:​12-​14፤ ማቴዎስ 11:​28-​30፤ 1 ቆሮንቶስ 11:​1፤ ኤፌሶን 5:​1) እንግዲያው ‘እርስ በርሳችን እንድንፋቀር’ የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለን!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

ልታብራራ ትችላለህን?

• እያንዳንዳችን ፍቅር ማሳየታችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

• በመንፈሳዊ የደከሙትንም ጭምር ማፍቀር የሚገባን ለምንድን ነው?

• ስለ ጠፋው በግና ስለጠፋው ድሪም ከሚናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

• በመንፈሳዊ የደከሙትን ለመርዳት ልንወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመንፈሳዊ የደከሙትን ለመርዳት ቅድሚያውን መውሰድ፣ ደግነት ማሳየትና ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመንፈሳዊ የደከሙትን መርዳት ለሁሉም በረከት ያስገኛል