የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ሴት አስገድዶ የመድፈር ጥቃት ሲሰነዘርባት መጮህ አለባት የሚለው ለምንድን ነው?
ተገዶ መደፈር የአንድን ሰው ሕይወት ምን ያህል ሊያመሰቃቅል እንደሚችል በደንብ የሚረዳው ይህ ሁኔታ የደረሰበት ሰው ብቻ ነው። ይህ መጥፎ ገጠመኝ በጣም አስፈሪ ከመሆኑ የተነሳ የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ሴት በቀሪው የሕይወት ዘመኗ ሁሉ ሁኔታው ትውስ እያላት ልትረበሽ ትችላለች። a ከዓመታት በፊት አስገድዶ የመድፈር ጥቃት የተሰነዘረባት አንዲት ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ትላለች:- “የዚያን ዕለት ምሽት የተሰማኝን ከባድ ፍርሃትም ሆነ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚሰማኝን የስሜት ቀውስ በቃላት መግለጽ አልችልም።” ብዙዎች ስለዚህ አስፈሪ ጉዳይ ጨርሶ ማሰብ እንኳን የማይፈልጉት ለምን እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም። የሆነ ሆኖ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ እስካለን ድረስ ተገዶ የመደፈርን ስጋት ማምለጥ አንችልም።
መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን ስለተፈጸሙ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችም ሆነ ሙከራዎች በግልጽ ይናገራል። (ዘፍጥረት 19:4-11፤ 34:1-7፤ 2 ሳሙኤል 13:1-14) ይሁን እንጂ አንዲት ሴት አስገድዶ የመድፈር ሙከራ ሲደረግባት ምን ማድረግ እንዳለባትም ይናገራል። ሕጉ ይህን ጉዳይ በተመለከተ የያዘው ሐሳብ በዘዳግም 22:23-27 ላይ ይገኛል። የጥቅሱ ሐሳብ ስለ ሁለት የተለያዩ ሁኔታዎች ይናገራል። በመጀመሪያው ሁኔታ አንድ ሰው አንዲትን ወጣት ሴት በከተማ ውስጥ አገኛትና ከእርስዋ ጋር ተኛ። ሆኖም ይህች ሴት ሰዎች እንዲደርሱላት አልጮኸችም። ስለዚህ ‘በከተማ ውስጥ ሳለች ባለመጮዃ’ ጥፋተኛ እንደሆነች ተደርጋ ትቆጠራለች። ጮኻ ቢሆን ኖሮ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ሰምተው ሊደርሱላትና ሊያድኗት ይችሉ ነበር። በሁለተኛው ሁኔታ ደግሞ አንድ ሰው አንዲትን ወጣት ሴት ከከተማ ውጭ አገኛትና “በግድ አሸንፎ” ደፈራት። ወጣቷ ሴት ራሷን ለመከላከል ‘ጮኻለች፣ ግን የሚደርስላት አልነበረም።’ ከመጀመሪያዋ ሴት በተቃራኒ ይህችኛዋ ሴት በድርጊቱ አለመስማማቷን በግልጽ ለማየት ይቻላል። ለእርዳታ በመጮህ አቅሟ በፈቀደው መጠን ድርጊቱን ተቃውማለች፤ ቢሆንም ለመቋቋም አልቻለችም። መጮዃ ድርጊቱ አለ ፈቃዷ እንደተፈጸመባት የሚያረጋግጥ ሲሆን በጥፋተኝነት አትጠየቅም።
በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም በሕጉ ውስጥ የተጠቀሱት መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደ መመሪያ ሊያገለግሉን ይችላሉ። ከላይ የተጠቀሰው ሐሳብ ድርጊቱን መቃወምና እርዳታ ለማግኘት መጮህ አስፈላጊ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል። አስገድዶ የመድፈር ሙከራ በሚሰነዘርበት ወቅት ለእርዳታ መጮሁ በዛሬው ጊዜም ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። አንድ የወንጀል መከላከል ባለሙያ “አንዲት ሴት ጥቃት ሲሰነዘርባት ከሁሉ የተሻለው የመከላከያ መሣሪያዋ ድምጿ ነው” ብለዋል። አንዲት ሴት መጮዃ ሊረዷት የሚችሉ ሰዎች እንዲደርሱላት ወይም ጥቃቱን የሚፈጽምባት ሰው እንዲደናገጥና እንዲሸሽ ሊያደርግ ይችላል። በአንድ አስገድዶ ደፋሪ ጥቃት የተሰነዘረባት አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “ባለ በሌለ ኃይሌ ስጮህ ሊደፍረኝ የሞከረው ሰው ወደ ኋላ አፈገፈገ። በድጋሚ ተመልሶ ሲመጣ ጮህኩና መሮጥ ጀመርኩ። ከዚህ ገጠመኝ በፊት ‘ስለ ጾታ ፍላጎቱ ብቻ የሚያስብ አንድ ጠብደል ሰው ቢይዘኝ መጮኼ ምን ሊጠቅመኝ ይችላል?’ ብዬ አስብ ነበር። አሁን ግን መጮህ ጥቅም እንዳለው ተምሬያለሁ።”
አንዲት ሴት ጥቃቱን መቋቋም አቅቷት በምትደፈርበት ጊዜም እንኳን መታገሏና ሰዎች እንዲደርሱላት መጮዃ እንዲያው ከንቱ ልፋት አይደለም። እንዲያውም በተቃራኒው ድርጊቱን ለመቃወም የምትችለውን ሁሉ ማድረጓን ያረጋግጣል። (ዘዳግም 22:26) ተገዳ ብትደፈርም እንኳን የሕሊናዋን ንጽሕና ለመጠበቅ፣ ለራስዋ ያላት ግምት እንዳይቀንስና በይሖዋ ፊት ንጹሕ መሆኗን ለማረጋገጥ ይረዳታል። የደረሰባት አሳዛኝ ገጠመኝ የስሜት ቁስል ቢያስከትልባትም ጥቃቱን ለመከላከል አቅሟ የሚፈቅድላትን ሁሉ እንዳደረገች ማወቅዋ ቁስሉ ቀስ በቀስ እንዲሽር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
በዘዳግም 22:23-27 ላይ ያለውን መመሪያ ለማስተዋል በምንሞክርበት ጊዜ ይህ አጭር ሐሳብ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ሁኔታዎች በሙሉ እንደማይሸፍን መገንዘብ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል ጥቃቱ የተፈጸመባት ሴት መናገር የማትችል በመሆኗ፣ ራስዋን በመሳትዋ፣ በድንጋጤ በድን በመሆኗ ወይም አፏ በእጅ ወይም በፕላስተር በመታፈኑ ላትጮህ ትችላለች። ሆኖም ይሖዋ ውስጣዊ ስሜታችንን ጨምሮ ሁሉንም ሁኔታዎች ማመዛዘን ስለሚችል እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን የሚያየው በማስተዋልና በፍትህ ነው፤ ምክንያቱም “መንገዱ ሁሉ የቀና ነው።” (ዘዳግም 32:4) ስለተፈጸመው ሁኔታና የጥቃቱ ሰለባ ድርጊቱን ለማስቀረት ስላደረገችው ጥረት ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ አንዲት ሴት መጮህ ባትችልም ሁኔታዎቹ በሚፈቅዱላት መጠን ጥቃቱን ከተቃወመች ከዚያ በኋላ ጉዳዩን ለይሖዋ ልትተወው ትችላለች።—መዝሙር 55:22፤ 1 ጴጥሮስ 5:7
እንዲያም ሆኖ አስገድዶ የመድፈር ጥቃት የተሰነዘረባቸውና ያለ ፍላጎታቸው የተደፈሩ አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማቸው ለረጅም ጊዜ ይሰቃያሉ። የተፈጸመውን ሁኔታ መለስ ብለው ሲያስቡ ድርጊቱን ለማስቀረት የበለጠ ነገር ማድረግ እንደነበረባቸው በማሰብ ይበሳጫሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ጥቃት የተፈጸመባቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን በመውቀስ ፋንታ ለይሖዋ በመጸለይ እርሱ እንዲረዳቸው መለመንና ፍቅራዊ ደግነቱን አትረፍርፎ እንደሚሰጣቸው ሙሉ ትምክህት ማሳደር ይችላሉ።—ዘጸአት 34:6፤ መዝሙር 86:5
በመሆኑም የተፈጸመባቸው ተገዶ የመደፈር ጥቃት ያስከተለባቸውን ስሜታዊ ስቃይ ችለው የሚኖሩ ክርስቲያን ሴቶች ይሖዋ ስሜታቸውን እንደሚረዳላቸው ሊተማመኑ ይችላሉ። የአምላክ ቃል “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል። (መዝሙር 34:18) በተጨማሪም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉት የእምነት አጋሮቻቸው ስሜታቸውን በቅንነት የሚረዱላቸውና በደግነት የሚደግፏቸው ከሆነ የደረሰባቸውን የስሜት ስቃይ መቋቋም ይችላሉ። (ኢዮብ 29:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) ከሁሉም በላይ የድርጊቱ ሰለባዎች መልካም በሆኑ ሐሳቦች ላይ ብቻ ለማተኮር ጥረት ማድረጋቸው “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም” እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።—ፊልጵስዩስ 4:6-9
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ ርዕስ የሚናገረው በሴቶች ላይ ስለሚፈጸመው አስገድዶ የመድፈር ጥቃት ቢሆንም የቀረቡት መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመሳሳይ ጥቃት ለሚሰነዘርባቸው ወንዶችም ሊሠሩ ይችላሉ።