በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት በስደተኞች መጠለያ ካምፕ

ሕይወት በስደተኞች መጠለያ ካምፕ

ሕይወት በስደተኞች መጠለያ ካምፕ

‘የስደተኞች መጠለያ ካምፕ’ ሲባል ምን ወደ አእምሮህ ይመጣል? እንዲህ ያለውን ቦታ የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝተህ ታውቃለህ? ለመሆኑ ምን ይመስላል?

ይህ ጽሑፍ በተጠናቀረበት ወቅት በምዕራብ ታንዛኒያ 13 የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ነበሩ። የታንዛኒያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በእርስ በርስ ጦርነት የተፈናቀሉትን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የመጡ ወደ 500,000 የሚጠጉ ስደተኞች በመርዳት ላይ ይገኛል። ታዲያ በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ያለው ሕይወት ምን ይመስላል?

በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ያለው ሁኔታ

በአሥራዎቹ እድሜ የምትገኝ ካንዲዳ የተባለች ወጣት ከጥቂት ዓመታት በፊት እሷና ቤተሰቦቿ ካምፑ ሲደርሱ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “እዚያ እንደደረስን የራሽን መቀበያ ካርድ ከተሰጠን በኋላ ወደ ኒሩጉሱ የስደተኞች ካምፕ ተወሰድን። እዚያም መጠለያ የምንሠራበት ቦታና የአካባቢው መለያ ቁጥር የተሰጠን ሲሆን ለመሥራት የሚያስችለንን ዛፍ ከየት እንደምንቆርጥና ሣር ከየት እንደምናጭድ አሳዩን። የጭቃ ጡብ ሠራን። ከዚያም የሠራነውን መጠለያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በሰጠን የፕላስቲክ ሸራ ጣሪያውን ሸፈንነው። ሥራው አድካሚ ቢሆንም በመጨረሻ ትንሿ ጎጆአችን ተጠናቅቃ በማየታችን በጣም ተደሰትን።”

ካንዲዳ “በየሁለት ሳምንቱ ዕሮብ ዕሮብ የራሽን ካርዳችንን በመያዝ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሚያከፋፍለንን ምግብ ተሰልፈን እንወስድ ነበር” በማለት ተናግራለች።

የአንድ ሰው የምግብ ራሽን ምን ያህል ነው?

“ለእያንዳንዳችን ሦስት ኩባያ የበቆሎ ዱቄት፣ አንድ ኩባያ አተር፣ ሃያ ግራም የአደንጓሬ ዱቄት፣ ሁለት የሾርባ ማንኪያ የምግብ ዘይት እንዲሁም አሥር ግራም ጨው ይታደለን ነበር። አልፎ አልፎ ደግሞ ለአንድ ወር የምንጠቀምበት አንድ ሳሙና ይሰጠን ነበር።”

ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? ሪዚኪ የተባለች አንዲት ወጣት እንደሚከተለው በማለት ትገልጻለች:- “ውሃ በካምፑ አቅራቢያ ከሚገኝ ወንዝ በቧንቧ አማካኝነት ወደ አንድ ትልቅ ማጠራቀሚያ ይገባል። በካምፑ ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ የቦኖ ውሃ ማከፋፈያዎች ከመሰራጨቱ በፊት ክሎሪን ይጨመርበታል። እንደዚያም ሆኖ በሽታ እንዳይዘን ስለምንፈራ አፍልተን ለመጠጣት እንሞክራለን። አንዳንድ ጊዜ ከእነዚህ ቦኖዎች ውሃ እየቀዳን ልብሳችንን ስናጥብ እንውላለን። በቀን የሚፈቀድልን ውሃ አንድ ባልዲ ተኩል ብቻ ነው።”

እነዚህን መጠለያ ካምፖች የመጎብኘት አጋጣሚ ብታገኝ አፀደ ሕፃናትን እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ ሌላው ቀርቶ የጎልማሶች ትምህርት ቤት ልታይ ትችላለህ። በካምፑ አቅራቢያ የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ለካምፑ ፀጥታና ደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በካምፑ ውስጥ ስደተኞቹ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ አሳ፣ ዶሮ እና ሌሎች ምግቦችን የሚሸምቱበት የገበያ ቦታ እንዳለም ልትመለከት ትችላለህ። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎችም ለመሸጥ ለመለወጥ በካምፑ ውስጥ ወደሚገኘው ወደዚህ ገበያ ይመጣሉ። ለመሆኑ ስደተኞቹ አንዳንድ ነገሮችን የሚገበዩበት ገንዘብ የሚያገኙት ከየት ነው? አንዳንዶቹ በጓሮዎቻቸው የተከሉትን አትክልት በመሸጥ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በራሽን የተሰጣቸውን ዱቄት በመሸጥ ስጋ ወይም ፍራፍሬ ይገዙበታል። የስደተኞቹ መኖሪያ ከካምፕ ይልቅ ትልቅ መንደር ይመስላል። አንዳንዶቹ በትውልድ ቀዬአቸው ይስቁ ይጫወቱ እንደነበረው አሁንም በገበያ ቦታ ይህን መመልከት የተለመደ ነው።

በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ወደሚገኘው ሆስፒታል ጎራ ብትል በካምፖቹ ውስጥ ቀላል የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ጥቂት የጤና ጣቢያዎች እንዳሉና ድንገተኛ አደጋና ከባድ የጤና እክሎች ግን ወደ ሆስፒታሉ እንደሚላኩ ከሐኪሞቹ አንዱ ሊነግርህ ይችላል። ከሆስፒታሉ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ ከፍተኛ አገልግሎት የሚያበረክተው የማዋለጃ ክፍሉ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም በመጠለያ ካምፑ ውስጥ 48, 000 ስደተኞች ያሉ ሲሆን በወር ወደ 250 የሚደርሱ እናቶች ይወልዳሉ።

መንፈሳዊ ምግብ አልተጓደለባቸውም

በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በታንዛኒያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙት መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ሁኔታ ያሳስባቸው ይሆናል። በእነዚህ ካምፖች ውስጥ 1, 200 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙ ሲሆን 14 ጉባኤዎችና 3 ቡድኖች አሉ። ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ምሥክሮቹ ወደ መጠለያ ካምፑ እንደደረሱ በመጀመሪያ ያቀረቡት ጥያቄ ለመንግሥት አዳራሽ መሥሪያ የሚሆን ቦታ ነበር። ይህም በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምሥክሮቹ ወደሚያደርጓቸው ሳምንታዊ ስብሰባዎች በቀላሉ እንዲመጡ ያስችላቸዋል። በሉጉፉ መጠለያ ካምፕ 659 አስፋፊዎች ያሉባቸው 7 ጉባኤዎች ይገኛሉ። በእነዚህ ጉባኤዎች እሁድ በሚደረገው ስብሰባ በጠቅላላ ወደ 1, 700 የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች ይገኛሉ።

በካምፖቹ ውስጥ የሚኖሩት ምሥክሮች ትላልቅ ስብሰባዎችንም ያደርጋሉ። በሉጉፉ መጠለያ ካምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውራጃ ስብሰባ ሲደረግ 2, 363 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። ምሥክሮቹ እዚያው ከስብሰባው ቦታ አጠገብ ጉድጓድ በመቆፈርና ውሃ መያዝ እንዲችል ውስጡ ፕላስቲክ በማንጠፍ መጠመቂያ ገንዳ አዘጋጅተው ነበር። ወንድሞች ገንዳውን ውሃ የሞሉት 2 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ከሚገኝ ወንዝ በብስክሌት ተመላልሰው በመቅዳት ነው። በአንድ ዙር የሚያመጡት ውሃ ከ20 ሊትር ስለማይበልጥ ገንዳውን ለመሙላት ብዙ ጊዜ መመላለስ አስፈልጓቸው ነበር። የጥምቀት እጩዎቹ ልከኛ ልብስ ለብሰው ለመጠመቅ ተሰልፈው ነበር። በአጠቃላይ 56 ተጠማቂዎች ነበሩ። በስብሰባው ላይ ቃለ መጠይቅ የተደረገለት አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለ40 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደመራና ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በስብሰባው ላይ መጠመቃቸውን ተናግሯል።

በእነዚህ ካምፖች ውስጥ ለሚገኙት ጉባኤዎች የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ቋሚ ጉብኝት እንዲያደርጉ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ዝግጅት አድርጓል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞቻችን ለአገልግሎት ከፍተኛ ቅንዓት አላቸው፣ ሰፊ የአገልግሎት ክልል አላቸው፤ በአንድ ጉባኤ ውስጥ እያንዳንዱ አስፋፊ በወር በአማካይ 34 ሰዓት በአገልግሎት ያሳልፋል። ብዙዎቹ 5 እና ከዚያ በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሏቸው። አንዲት አቅኚ ይህን የመሰለ የአገልግሎት ክልል የትም እንደማታገኝ ተናግራለች። በካምፑ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ጽሑፎቻችንን በጣም ያደንቃሉ።”

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወደ መጠለያ ካምፖቹ የሚደርሱት እንዴት ነው? ቅርንጫፍ ቢሮው በባቡር አማካኝነት ከታንጋኒካ ሐይቅ በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ኪጐማ ከተማ እንዲደርስ ያደርጋል። ከዚያም ወንድሞች ጽሑፎቹን ከተረከቡ በኋላ ወደየጉባኤዎቹ እንዲደርስ ዝግጅት ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜ አነስተኛ የጭነት መኪናዎችን በመከራየት ወደ ሁሉም ካምፖች ያደርሳሉ። መንገዶቹ በጣም አስቸጋሪ በመሆናቸው ጉዞው ሦስትና አራት ቀናት ሊፈጅ ይችላል።

ቁሳዊ እርዳታ

በፈረንሳይ፣ በቤልጂየምና በስዊዘርላንድ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ካምፖች ለሚገኙ ስደተኞች እርዳታ በመለገስ ግምባር ቀደም ናቸው። አንዳንዶቹ ከተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽንና ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባገኙት ፈቃድ ካምፖቹን ጐብኝተዋል። በአውሮፓ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በርካታ ቶን የሚመዝን ዱቄት ወተት፣ አልባሳት፣ ጫማዎች፣ መማሪያ መጻሕፍትና ሳሙና አሰባስበዋል። እነዚህ የእርዳታ ቁሳቁሶች “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት በካምፖቹ ውስጥ ለሚገኙ ለሁሉም ስደተኞች ተከፋፍለዋል።​—⁠ገላትያ 6:​10

ለብዙዎቹ ስደተኞች የተደረገው ይህ ሰብአዊ እርዳታ ግሩም ውጤት አስገኝቷል። የስደተኞች ማኅበረሰብ ኮሚቴ በአንዱ መጠለያ ካምፕ ውስጥ እንዲህ ሲል አድናቆቱን ገልጿል:- “ድርጅታችሁ ሦስት ጊዜ ላደረገልን ሰብዓዊ እርዳታ በካምፑ ማህበረሰብ ስም በጣም ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። የተላኩት አልባሳት ችግር ላለባቸው 12,654 ወንዶች፣ ሴቶች፣ ልጆችና ሕፃናት ተከፋፍለዋል። በሙዮቮዚ የሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በአሁኑ ሰዓት 37,000 ነዋሪዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህ መካከል 12,654ቱ ማለትም 34.2% የሚሆኑት ከእርዳታ ዝግጅቱ ተጠቅመዋል።”

በሌላ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ 12,382 የሚሆኑ ስደተኞች እያንዳንዳቸው ሦስት ዓይነት ልብስ የታደላቸው ሲሆን በሌላ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች ደግሞ ለአፀደ ሕፃናት፣ ለአንደኛ ደረጃና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ መማሪያ መጻሕፍት ተከፋፍለዋል። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን የክልሉ የእርዳታ ማከፋፈያ ኃላፊ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “በካምፑ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች በማሟላት ረገድ ያደረጋችሁትን ልግስና ከልብ እናደንቃለን። በቅርቡ የላካችሁልንን 5 ኮንቴይነር ሙሉ የመማሪያ መጻሕፍት ለስደተኞች እንዲከፋፈል አድርገናል። . . . በጣም እናመሰግናችኋለን።”

የአገሪቱ ጋዜጦች እንኳን ሳይቀሩ የተደረገውን እርዳታ አስመልክተው ዘግበዋል። ግንቦት 20, 2001 የወጣው ሰንዴይ ኒውስ ጋዜጣ “በታንዛኒያ ለሚገኙ ስደተኞች የሚሆኑ አልባሳት በመጓጓዝ ላይ ናቸው” የሚል ዜና በዋና ርዕሱ ላይ አውጥቶ ነበር። በየካቲት 10, 2002 እትሙ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ይዞ ወጥቷል:- “ስደተኞቹ የተደረገላቸውን ልግስና ከልብ ያደንቃሉ፤ ልብስ አልቆባቸው ከትምህርት ቤት ቀርተው የነበሩ ልጆች አሁን ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።”

ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም ችለዋል

ብዙዎቹ ስደተኞች አዲሱን የካምፕ ሕይወት ለመልመድ ከዓመት ያላነሰ ጊዜ ይወስድባቸዋል። መሠረታዊ በሆኑት ነገሮች ረክተው ይኖራሉ። በካምፖቹ ውስጥ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች ለሌሎች ስደተኞች በመንገር ነው። “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም” የሚለው ትንቢት ስለሚፈጸምበት አዲሱ ዓለም ለጐረቤቶቻቸው ይናገራሉ። በእርግጥም አምላክ የሚያመጣው ይህ አዲስ ዓለም የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የሚባል ነገር አይኖርበትም።​—⁠ሚክያስ 4:​3,4፤ መዝሙር 46:​9

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእንዱታ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ቤቶች

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(በስተቀኝ) በሉኮሌ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ (ከታች) በሉጉፉ የተካሄደው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሉጉፉ መጠለያ ካምፕ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ