በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሠዊያ በአምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው?

መሠዊያ በአምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው?

መሠዊያ በአምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው?

መሠዊያ በአምልኮትህ ውስጥ ቁልፍ ቦታ እንዳለው ሆኖ ይሰማሃልን? የሕዝበ ክርስትና አባላት የሆኑ ብዙ ሰዎች መሠዊያ የአምልኳቸው መሠረታዊ ክፍል እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ መሠዊያን ለአምልኮ መጠቀምን በተመለከተ ምን እንደሚል ትኩረት ሰጥተህ አስበህበት ታውቃለህ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መሠዊያ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ኖኅ ከጥፋት ውኃ ተርፎ ከመርከብ ከወጣ በኋላ የእንስሳት መሥዋዕት ለማቅረብ መሠዊያ በሠራ ጊዜ ነበር። a​—⁠ዘፍጥረት 8:​20

በባቢሎን የሰዎች ቋንቋ ከተደባለቀ በኋላ የሰው ዘር በምድር ገጽ ላይ ተበተነ። (ዘፍጥረት 11:​1-9) እነዚህ ሰዎች ስለ አምላክ ያላቸው እውቀት እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም በተፈጥሮ ያገኙት የማምለክ ፍላጎት ወደ እርሱ የመቅረብ ምኞት ስላሳደረባቸው እርሱን ‘ለማግኘት’ በራሳቸው መንገድ ጥረት አድርገዋል። (ሥራ 17:​26, 27፤ ሮሜ 2:​14, 15) ከኖኅ ዘመን አንስቶ የተለያዩ ሕዝቦች ለአማልክቶቻቸው መሠዊያ ሠርተዋል። የተለያየ ሃይማኖትና ባሕል ያላቸው ሰዎች ለሐሰት አምልኮ መሠዊያዎችን ሠርተዋል። እውነተኛውን አምላክ የማያመልኩ አንዳንድ ሰዎች ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎችን ለአማልክቶቻቸው መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ መሠዊያን ዘግናኝ ለሆነ ተግባር ተጠቅመውበታል። አንዳንድ የእስራኤል ነገሥታት ይሖዋን በተዉበት ወቅት በዓልን ለመሳሰሉ የሐሰት አማልክት መሠዊያ ሠርተዋል። (1 ነገሥት 16:​29-32) ይሁን እንጂ መሠዊያ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ምን አገልግሎት ነበረው?

መሠዊያ እና በእስራኤል የነበረው እውነተኛ አምልኮ

ከኖኅ በኋላ ሌሎች የታመኑ ሰዎችም ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ ለሚያቀርቡት አምልኮ የሚያገለግል መሠዊያ ሠርተው ነበር። አብርሃም በሴኬም፣ በቤቴል አቅራቢያ፣ በኬብሮን እንዲሁም በይስሐቅ ፋንታ አምላክ ያዘጋጀለትን በግ መሥዋዕት ባደረገበት በሞሪያም ተራራ ላይ መሠዊያዎችን ሠርቷል። ከጊዜ በኋላም ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሙሴ በራሳቸው ፍላጎት ለአምላክ ለሚያቀርቡት አምልኮ የሚያገለግል መሠዊያ ሠርተዋል።​—⁠ዘፍጥረት 12:​6-8፤ 13:​3, 18፤ 22:​9-13፤ 26:​23-25፤ 33:​18-20፤ 35:​1, 3, 7፤ ዘጸአት 17:​15, 16፤ 24:​4-8

አምላክ ለእስራኤላውያን ሕጉን በሰጣቸው ጊዜ ወደ እርሱ መቅረብ የሚቻልበት ዝግጅት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግልና በቀላሉ ከቦታ ቦታ ሊንቀሳቀስ የሚችል ማደሪያ ወይም ‘የመገናኛ ድንኳን’ እንዲሠሩ አዟቸዋል። (ዘጸአት 39:​32, 40) ይህ ማደሪያ ወይም ድንኳን ሁለት መሠዊያዎች ነበሩት። አንደኛው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት ነው። ይህ መሠዊያ ከግራር እንጨት ተሠርቶ በናስ የተለበጠና በድንኳኑ ፊት የተቀመጠ ሲሆን የሚያገለግለውም የእንስሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር። (ዘጸአት 27:​1-8፤ 39:​39፤ 40:​6, 29) የዕጣን መሠዊያውም ከግራር እንጨት የተሠራ ነበር፤ ሆኖም በወርቅ የተለበጠና በማደሪያው ውስጥ ከቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ ፊት ይቀመጥ ነበር። (ዘጸአት 30:​1-6፤ 39:​38፤ 40:​5, 26, 27) በዚህ መሠዊያ ላይ በቀን ሁለት ጊዜ ይኸውም ማለዳና ማታ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዕጣን ይጨስበታል። (ዘጸአት 30:​7-9) ንጉሥ ሰሎሞን የገነባው ቤተ መቅደስም እንደ መገናኛው ድንኳን ሁለት መሠዊያዎች ነበሩት።

‘እውነተኛይቱ ድንኳን’ እና ምሳሌያዊው መሠዊያ

ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ለአኗኗራቸው መመሪያ እንዲሁም ለአምላካቸው መሥዋዕትና ጸሎት እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው የሚገልጽ ደንብ የያዘ ብቻ አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው በሕጉ ውስጥ ከተካተቱት ሥርዓቶች መካከል አብዛኞቹ ‘ምሳሌ’ ወይም ‘ለሰማያዊ ነገር ጥላ’ ነበሩ። (ዕብራውያን 8:​3-5፤ 9:​9፤ 10:​1፤ ቆላስይስ 2:​17) በሌላ አነጋገር አብዛኛው የሕጉ ክፍል ክርስቶስ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ለእስራኤላውያን መመሪያ ሆኖ ከማገልገሉም በላይ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ፍጻሜውን ለሚያገኘው የአምላክ ዓላማም ጥላ ነበር። (ገላትያ 3:​24) አዎን፣ የሕጉ አንዳንድ ክፍሎች ትንቢታዊ ትርጉም ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ደሙ ለእስራኤላውያን የመዳን ምልክት ሆኖ ያገለግል የነበረው የማለፍ በግ ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል። ኢየሱስ በደሙ አማካኝነት ከኃጢአት ባርነት የምንላቀቅበት “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ነው።​—⁠ዮሐንስ 1:29፤ ኤፌሶን 1:7

በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደሱ ይከናወኑ የነበሩት አብዛኞቹ አገልግሎቶች በሰማይ ለሚፈጸሙት ነገሮች ምሳሌ ነበሩ። (ዕብራውያን 8:​5፤ 9:​23) እንዲያውም ጳውሎስ ‘እውነተኛይቱ ድንኳን’ “በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች” መሆኗን ጽፏል። ከዚህም በላይ ‘ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው በእጆችም ወዳልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ወዳልሆነች ድንኳን’ እንደገባ ተናግሯል። (ዕብራውያን 8:​2፤ 9:11) እዚህ ላይ ‘የምትበልጠውና የምትሻለው ድንኳን’ ተብሎ የተገለጸው ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ እንዳስቀመጡት ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሰዎች የኃጢአት ይቅርታ በሚያስገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚችሉበት ዝግጅት ነው።​—⁠ዕብራውያን 9:​2-10, 23-28

በሕጉ ውስጥ የተካተቱት አንዳንድ ሥርዓቶችና ደንቦች ይበልጥ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ መንፈሳዊ ተፈጻሚነት ያላቸው ምሳሌ መሆናቸውን ከአምላክ ቃል መገንዘባችን መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለመሆኑ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እንዲሁም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ለተገለጸው መለኮታዊ ጥበብ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል።​—⁠ሮሜ 11:​33፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16

የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያም ትንቢታዊ ትርጉም አለው። መሠዊያው አምላክ ኢየሱስ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ለመቀበል ያለውን “ፈቃድ” ወይም ፈቃደኝነቱን የሚያመለክት ይመስላል።​—⁠ዕብራውያን 10:​1-10

ጳውሎስ በዚሁ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ “መሠዊያ አለን፣ ከእርሱም ሊበሉ ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ መብት የላቸውም” በማለት ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ተናግሯል። (ዕብራውያን 13:10) ጳውሎስ የጠቀሰው መሠዊያ ምን ዓይነት ነው?

ብዙ የካቶሊክ ምሁራን በዕብራውያን 13:​10 ላይ የተጠቀሰው መሠዊያ ሥርዓተ ቅዳሴ በሚደረግበት ወቅት የክርስቶስን ሥጋና ደም ሆኖ የሚለወጠውን “ቅዱስ ቁርባን” ወይም ሥጋወ ደሙን ያመለክታል ይላሉ። ይሁን እንጂ ከጥቅሱ መንፈስ መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ስለ ምሳሌያዊ መሠዊያ ነው። በርካታ ምሁራን በዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀሰው “መሠዊያ” ምሳሌያዊ መሆኑን ይስማማሉ። ጁዜፔ ቦንሲርቨን የተባሉ አንድ የካቶሊክ እምነት ተከታይ “ይህም ጉዳይ ቢሆን [ለዕብራውያን ክርስቲያኖች] በተጻፈው መልእክት ውስጥ ከተጠቀሱት ሌሎች ምሳሌያዊ ነገሮች ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል” በማለት ተናግረዋል። በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል:- “ከክርስትና ዘመን አንስቶ ‘መሠዊያ’ የሚለው ቃል የሚያመለክተው መንፈሳዊ ነገርን ነው። ቃሉ ሥጋወ ደሙን በተለይ ደግሞ ሥጋወ ደሙ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛ ያመለክታል መባል የጀመረው ከኢራኒየስ በተለይም ከተርቱሊያንና ከቅዱስ ሲፕሪያን ዘመን በኋላ ነው።”

አንድ የካቶሊክ መጽሔት እንደገለጸው መሠዊያ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው “በቆስጠንጢኖስ ዘመን” “ግዙፍ ከሆኑ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ” ጋር ተያይዞ ነው። ሪቪስታ ዲ አርኪዮሎጂያ ክሪስቲያና የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “በመጀመሪያዎቹ ሁለት መቶ ዓመታት ክርስቲያኖች ቋሚ የአምልኮ ቦታ ነበራቸው ብሎ ለመናገር የሚያስችል ምንም ማስረጃ የለም። ከዚህ ይልቅ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ይካሄዱ ነበር . . . ስብሰባው ካበቃ በኋላ ቤቶቹ ወዲያውኑ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ።”

መሠዊያ በሕዝበ ክርስትና አምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ

ላ ቺቪልታ ካቶሊካ የተባለው የካቶሊክ መጽሔት “መሠዊያ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ብቻ ሳይሆን በዚያ ለሚሰበሰቡት ሰዎችም የአምልኮ እምብርት ነው” ይላል። ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠዊያ ላይ የሚከናወን ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት አላቋቋመም፤ ወይም ደቀ መዛሙርቱ መሠዊያ በመጠቀም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን እንዲያከናውኑ አላዘዘም። ኢየሱስ በማቴዎስ 5:​23, 24 እና በሌሎች ቦታዎችም ላይ ስለ መሠዊያ የተናገረው አይሁዳውያን ያከናውኗቸው የነበሩትን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በተመለከተ ነው። ይሁንና ተከታዮቹ መሠዊያ በመጠቀም አምላክን እንዲያመልኩ አልተናገረም።

ጆርጅ ፉት ሙር (1851-1931) የተባሉ አንድ አሜሪካዊ የታሪክ ምሁር እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የክርስትና እምነት ዋና ዋና ገጽታዎች መቼም ቢሆን ተለውጠው አያውቁም። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ጀስቲን በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የጠቀሳቸው ቀላል የአምልኮ ሥርዓቶች መልካቸውን ቀይረው በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩ የተንዛዙ ሥርዓቶች ሆኑ።” የካቶሊክ የአምልኮ ሥርዓቶችና ሃይማኖታዊ በዓላት ብዛት ያላቸውና የተወሳሰቡ ከመሆናቸው የተነሳ በካቶሊክ መንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ በትምህርት ደረጃ ይቀርቡ ጀመር። ሙር በመቀጠል እንዲህ ብለዋል:- “ብሉይ ኪዳን ማንኛውም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይበልጥ እየተንዛዛ እንዲሄድ ተጽእኖ ሊያሳድር የቻለው የክርስትና ቀሳውስት የጥንቱን የክህነት ሥርዓት ይተካሉ የሚለው እምነት ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱ ነው። ሊቀ ካህኑ የሚለብሰው የተለየ ልብስ፣ የሌሎች ካህናት ልብሰ ተክህኖ፣ የቅዳሴ ሥርዓቱ፣ መዘምራኑ የሚያሰሙት ዝማሬ፣ በጥናዎች ላይ እጣን ማሳረጉ ሁሉ በአምላክ ትእዛዝ የሚከናወን የአምልኮ ሥርዓት ስለሚያስመስለው ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከጥንቶቹ ሃይማኖቶች ባላነሰ እንዲያውም በላቀ ሁኔታ እንድታከናውን አድርጓታል።”

አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችና ክብረ በዓሎች፣ የቀሳውስቱ አልባሳትና በተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ለአምልኮ የሚውሉ ሌሎች ዕቃዎች ከወንጌል የመነጩ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ሳይሆኑ ከአይሁድ እምነትና ከአረማውያን የተወረሱ ልማዶችና ሥርዓቶች መሆናቸውን ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ኢንሲክሎፔዲያ ካቶሊካ የካቶሊክ እምነት “ለአምልኮ በመሠዊያ የመጠቀምን ልማድ የወረሰችው ከአይሁድ እምነት፣ በከፊል ደግሞ ከአረማዊ አምልኮ ነው” በማለት ተናግሯል። በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረውና የክርስቲያኖች ተሟጋች የነበረው ሚኑኪየስ ፌሊክስ ክርስቲያኖች ‘ቤተ መቅደስም ሆነ መሠዊያ’ እንዳልነበራቸው ጽፏል። ሬሊጆኒ ኤ ሚቲ (ሃይማኖትና አፈ ታሪክ) የተባለው መዝገበ ቃላት “የጥንት ክርስቲያኖች ከአይሁድ እምነትም ሆነ ከአረማዊ አምልኮ የተለዩ ሆነው ለመታየት መሠዊያን ለአምልኮ ተጠቅመው አያውቁም” በማለት ተመሳሳይ ሐሳብ አስፍሯል።

የክርስትና እምነት የተመሠረተው በማንኛውም አገር፣ በእያንዳንዱ ሰው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ በሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በመሆኑ በምድር ላይ ቅድስት ከተማ ወይም መሠዊያ ያለበት ቤተ መቅደስ ብሎም በማዕረግ ስም የሚጠሩና የተለየ የአለባበስ ሥርዓት የሚከተሉ ቀሳውስት አያስፈልጉትም። ኢየሱስ “በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። . . . በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት” ይሰግዳሉ በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:21, 23) የተንዛዙ የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶችን የሚከተሉ እና በመሠዊያ የሚጠቀሙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ኢየሱስ፣ እውነተኛው አምላክ እንዴት መመለክ እንዳለበት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ፍጹም አይስማሙም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከዚያ ቀደም ሲል ቃየንና አቤል ለይሖዋ መሥዋዕት ባቀረቡበት ወቅት መሠዊያ ተጠቅመው ሊሆን ይችላል።​—⁠ዘፍጥረት 4:​3, 4