በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወላጆች የልጆቻችሁን ልብ ጥሩ አድርጋችሁ ቅረጹ!

እናንት ወላጆች የልጆቻችሁን ልብ ጥሩ አድርጋችሁ ቅረጹ!

እናንት ወላጆች የልጆቻችሁን ልብ ጥሩ አድርጋችሁ ቅረጹ!

አንድ በሙያው የተካነ ሸክላ ሠሪ ተራ የሸክላ አፈር ተጠቅሞ ውብ የሆነ የቤት ዕቃ ሊሠራ ይችላል። እንዲህ ያለውን ውብና ጠቃሚ ዕቃ የመሥራት ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎች ብዙ አይደሉም። የሰው ዘር በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሸክላ ሠሪ የእጅ ሥራ ውጤት በሆኑት ስኒዎች፣ ሰሐኖች፣ የሸክላ ድስቶች፣ ማሰሮዎችና የአበባ ማስቀመጫዎች ሲገለገል ቆይቷል።

በተመሳሳይም ወላጆች የልጆቻቸውን ጠባይና ባሕርይ ጥሩ አድርገው በመቅረጽ ለኅብረተሰቡ ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዳችንን ከአፈር ጋር የሚያመሳስለን ሲሆን አምላክም በሸክላ የተመሰሉትን ልጆቻቸውን እንዲቀርጹ ለወላጆች ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። (ኢዮብ 33:6፤ ዘፍጥረት 18:19) የተዋበ የሸክላ እቃ መሥራት ጥረት የሚጠይቅ እንደሆነ ሁሉ አንድን ልጅ ለወግ ለማዕረግ ማድረስም ቀላል ሥራ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ እንዲያው በአጋጣሚ የሚገኝ አይደለም።

የልጆቻችንን ልብ የሚቀርጹ በርካታ ኃይሎች አሉ። የሚያሳዝነው ግን ከእነዚህ ኃይሎች መካከል አንዳንዶቹ ጎጂ ውጤት የሚያስከትሉ መሆናቸው ነው። ስለዚህ አንድ አስተዋይ የሆነ ወላጅ ልጁ በራሱ እየተቀረጸ እንዲያድግ ከመተው ይልቅ ‘በሸመገለ ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ እንደማይል’ በመተማመን ‘ሊሄድበት በሚገባው መንገድ’ ይመራዋል።​—⁠ምሳሌ 22:6

አስተዋይ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች ረጅሙንና በውጣ ውረድ የተሞላውን ልጅን የማሳደግ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ በልጆቻቸው ልብ ላይ መጥፎ ውጤት የሚያስከትሉትን ተጽዕኖዎች ለመከላከል ጊዜ መመደብ አለባቸው። የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ሁሉ በትዕግሥት ተቋቁመው ልጃቸውን በክርስቲያናዊ “ምክርና በተግሣጽ” በሚያሳድጉበት ወቅት ለእርሱ ያላቸው ፍቅር ይፈተናል። (ኤፌሶን 6:4) እርግጥ ነው፣ ወላጆች ልጁ ገና ጨቅላ እያለ ሥልጠናውን ከጀመሩ ሥራቸው በእጅጉ ይቀልላቸዋል።

በሕፃንነታቸው መጀመር

ሸክላ ሠሪዎች ለሥራቸው የሚመርጡት ቅርጽ ለማስያዝ በሚመች ሁኔታ በሚገባ የለሰለሰና ቅርጹን እንደያዘ ለመቆየት የሚያስችል ጥንካሬ ያለውን የሸክላ ጭቃ ነው። የሸክላው አፈር ከተጣራ በኋላ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ቢሠራበት ጥሩ እንደሚሆን ያውቃሉ። በተመሳሳይም ወላጆች የልጆቻቸውን ልብ ቅርጽ ማስያዝ ያለባቸው ልጁ የወላጆቹን ሐሳብ ሳያንገራግር በሚቀበልበትና በቀላሉ ሊቀርጹት በሚችሉበት እድሜው ላይ ነው።

ስለ ልጆች የሚያጠኑ ባለሞያዎች አንድ ልጅ በስምንት ወር እድሜው የወላጆቹን ቋንቋ በድምፅ እንደሚለይ፣ ከወላጆቹ ጋር የቀረበ ትስስር እንደሚመሠርትና፣ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታውን እንደሚያዳብር፤ እንዲሁም የሚኖርበትን አካባቢ ማስተዋል እንደሚጀምር ይናገራሉ። የልጁ የጨቅላነት ዕድሜ ልቡን ለመቅረጽ የሚያስችል ተስማሚ ጊዜ ነው። ልጃችሁ ልክ እንደ ጢሞቴዎስ ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን ቢያውቅ’ ምንኛ ይጠቀማል!​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:15 a

ሕፃናት በተፈጥሯቸው ወላጆቻቸው የሚያደርጉትን ይኮርጃሉ። ድምፆችን፣ አባባሎችንና አካላዊ እንቅስቃሴዎችን አስመስለው ከመቅዳታቸው በተጨማሪ ወላጆቻቸው የሚያንጸባርቋቸውን እንደ ፍቅር፣ ደግነትና ርኅራኄ ያሉ ባሕርያትን ይኮርጃሉ። ልጆቻችንን በይሖዋ ሕግጋት ማሰልጠን ከፈለግን በመጀመሪያ የአምላክ ሕግጋት በራሳችን ልብ ውስጥ ጠልቀው መግባት ይኖርባቸዋል። ወላጆች ለአምላክ ሕግጋት ያላቸው ልባዊ አድናቆት ስለ ይሖዋና ስለ ቃሉ ዘወትር ከልጆቻቸው ጋር እንዲወያዩ ይገፋፋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ ስትተኛና ስትነሳም ስለ እነርሱ ተናገር” በማለት ያሳስባል። (ዘዳግም 6:6, 7 አ.መ.ት ) ፍራንሲስኮ እና ሮሳ ለሁለት ትንንሽ ልጆቻቸው ይህን እንዴት ተግባራዊ እንዳደረጉ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ። b

“የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን አንስተን ከምናደርገው ጭውውት በተጨማሪ በየቀኑ ከእያንዳንዳቸው ጋር ቢያንስ ለ15 ደቂቃ ያህል በግል ለመወያየት ጥረት እናደርጋለን። አንድ ችግር እንዳለ ከተሰማን ረዘም ያለ ጊዜ እናጠፋለን፤ ችግሮች ደግሞ ብዙውን ጊዜ አይጠፉም። ለምሳሌ አምስት ዓመት የሆነው ወንድ ልጃችን በቅርቡ ከትምህርት ቤት መጣና በይሖዋ እንደማያምን ነገረን። አንድ የክፍል ጓደኛው አምላክ የለም በማለት አሹፎበት ነበር።”

እነዚህ ወላጆች ልጆች በፈጣሪያቸው ላይ እምነት ማሳደር እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበዋል። ልጆች ለአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ያላቸውን ተፈጥሯዊ አድናቆት በመጠቀም እንዲህ ዓይነቱን እምነት መገንባት ይቻላል። ልጆች ከእንስሳት ጋር መጫወት፣ አበቦችን ከሜዳ ላይ መልቀም ወይም በሣር በተሸፈነ ሜዳ ላይ መቦረቅ በጣም ያስደስታቸዋል። በተፈጥሮና በፈጣሪ መካከል ያለውን ትስስር እንዲያስተውሉ ወላጆች ሊረዷቸው ይችላሉ። (መዝሙር 100:3፤ 104:​24, 25) ለይሖዋ የፍጥረት ሥራ የሚያዳብሩት የአድናቆትና የመደመም ስሜት በቀሪው የሕይወት ዘመናቸው ሁሉ አብሯቸው ሊዘልቅ ይችላል። (መዝሙር 111:2, 10) ከእንዲህ ዓይነቱ አድናቆት ጎን ለጎን ይሖዋን የማስደሰት ፍላጎትና እርሱን እንዳያሳዝኑ የሚያደርጋቸውን ፍርሃት ሊያዳብሩ ይችላሉ። ይህም ‘ከክፋት እንዲርቁ’ ይገፋፋቸዋል።​—⁠ምሳሌ 16:6 አ.መ.ት

አብዛኞቹ ልጆች አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ ጉጉትና በፍጥነት የመረዳት ችሎታ ያላቸው ቢሆንም የታዛዥነት ዝንባሌ ላይኖራቸው ይችላል። (መዝሙር 51:5) አንዳንድ ጊዜ በራሳችን መንገድ ካልሄድን ወይም የፈለግነውን ነገር ሁሉ ካላገኘን ይሉ ይሆናል። እነዚህ ዝንባሌዎች በልባቸው ውስጥ ሥር እንዳይሰዱ ለመከላከል ወላጆች ጥብቅ፣ ታጋሽና ተግሳጽ የሚሰጡ መሆን ያስፈልጋቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) አምስት ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ያሳደጉት ፊሊስና ፓውል እንዲህ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር።

ፊሊስ ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ባሕርያቸው የተለያየ ቢሆንም ሁሉም በራሳቸው መንገድ የመመራት ዝንባሌ ነበራቸው። ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም እያደር ግን ‘አይሆንም’ ማለት አይሆንም እንደሆነ ተገንዝበዋል።” ባለቤቷ ፓውልም እንዲህ ይላል:- “ነገሮችን መረዳት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ አብዛኛውን ጊዜ ውሳኔያችንን በምክንያት እናስረዳቸው ነበር። ሁልጊዜ በደግነት የምንይዛቸው ቢሆንም ከአምላክ ያገኘነውን የወላጅነት ሥልጣን ማክበር እንዳለባቸውም አስተምረናቸዋል።”

የልጅነት ዕድሜ የራሱ የሆኑ ችግሮች ያሉት ቢሆንም ትልቁ ችግር የሚመጣው ልጁ በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲገባና እምብዛም ያልበሰለው አእምሮው ለአዳዲስ ፈተናዎች መጋለጥ ሲጀምር እንደሆነ ብዙ ወላጆች ተገንዝበዋል።

የአንድን ወጣት ልጅ ልብ ማግኘት

ሸክላ ሠሪው የተቦካው ጭቃ ከመድረቁ በፊት ቅርጽ ማስያዝ መጀመር አለበት። ጭቃው ለስላሳና እርጥብ ሆኖ እንዲቆይ አልፎ አልፎ ውኃ ሊጨምርበት ይችላል። በተመሳሳይም ወላጆች የልጆቻቸው ልብ እንዳይደነድን ለማድረግ ጠንክረው መሥራት አለባቸው። ለዚህ የሚጠቀሙበት ዋነኛ መሣሪያ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ የታወቀ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው ልጃቸውን ‘መገሰጽ፣ ልቡን ማቅናትና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ እንዲሆን ማድረግ’ ይችላሉ።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:15-17

ይሁን እንጂ አንድ በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኝ ልጅ እንደ ልጅነቱ የወላጆቹን ምክር በቀላሉ ላይቀበል ይችላል። በዚህ እድሜ የሚገኙ ልጆች ጆሯቸውን ለእኩዮቻቸው መስጠት ስለሚጀምሩ እንደ በፊቱ ምንም ነገር ሳይደብቁ ሁሉን ነገር ለወላጆቻቸው መንገር ሊያቆሙ ይችላሉ። ይህ ወቅት የወላጅና የልጅ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የሚጀምርበት ስለሆነ ከበፊቱ ይበልጥ ትዕግሥተኛና ዘዴኛ መሆንን ይጠይቃል። ልጁ ከራሱ አካላዊና ስሜታዊ ለውጦች ጋር መላመድ አለበት። ለቀሪው የሕይወት ዘመኑ የሚጠቅሙትን ውሳኔዎች ማድረግና ግቦችን ማውጣት መጀመር አለበት። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በልቡ ላይ በጣም አደገኛ ውጤት ሊያስከትል የሚችልን አንድ ኃይል ማለትም እኩዮች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ማሸነፍ አለበት።

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ተጽዕኖ የሚመጣው በአጋጣሚ በሚፈጠር ክስተት ሳይሆን መንፈስን ለማዳከም ሆን ተብለው በተደጋጋሚ በሚሰነዘሩ ሐሳቦች ወይም ሁኔታዎች ነው። በሌሎች ወጣቶች እንዳይገለሉ የመፍራት ስሜት የብዙ ወጣቶች ሥር የሰደደ ችግር ስለሆነ የእኩዮች ተጽዕኖ በዚህ ደካማ ጎናቸው በኩል ያጠቃቸዋል። አንድ ወጣት ስለ ራሱ ከልክ በላይ የሚጨነቅና በሌሎች ወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የሚጣጣር ከሆነ እነሱ የሚወዷቸውን “በዓለም ያሉትን” ነገሮች መውደድ ሊጀምር ይችላል።​—⁠1 ዮሐንስ 2:15-17፤ ሮሜ 12:2

ይባስ ብሎ ደግሞ ፍጹም ባልሆነው ልቡ ውስጥ ያሉት ተፈጥሯዊ ፍላጎቶች እኩዮቹ የሚሉት ትክክል እንደሆነ አድርገው ያስተጋቡለታል። “ዓለምህን ቅጭ” እና “የፈለግኸውን አድርግ” የሚሉትን የመሰሉ ምክሮች ትክክል መስለው ሊታዩት ይችላሉ። ማሪያ ያጋጠማትን ሁኔታ እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “ወጣቶች ድርጊታቸው ስለሚያስከትለው ውጤት ሳይጨነቁ እንዳሻቸው የመሆን መብት አላቸው ብለው ከሚያምኑ ልጆች ጋር ገጠምኩ። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ የሚያደርጓቸውን ነገሮች በሙሉ መፈጸም ስለፈለግሁ ትልቅ ችግር ውስጥ ልገባ ምንም አልቀረኝም ነበር።” ወላጆች ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖዎችን እንዲቋቋም መርዳት እንደምትፈልጉ አያጠራጥርም። እንዲህ ማድረግ የምትችሉት ግን እንዴት ነው?

በቃልም ሆነ በድርጊት ለእነርሱ ደህንነት እንደምታስቡ በተደጋጋሚ አሳውቋቸው። ስለ አንዳንድ ነገሮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ችግሮቹን ለመረዳት ሞክሩ። እነዚህ ችግሮች እናንተ ተማሪ እያላችሁ ካጋጠሟችሁ ችግሮች በእጅጉ የሚከብዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ልጃችሁ በተለይ በዚህ እድሜ ላይ እያለ ሊተማመንባችሁ እንደሚችል ሆኖ ሊሰማው ይገባል። (ምሳሌ 20:5) ፊቱ ላይ ከሚታየው ስሜትና ከአጠቃላይ መንፈሱ በመነሳት የሚያስጨንቁት ወይም ግራ የሚያጋቡት ነገሮች መኖራቸውን ልታስተውሉ ትችላላችሁ። ችግሮቹን በግልጽ ባይነግራችሁም እነዚህን ምልክቶች በማየት ‘ልቡን አጽናኑ።’​—⁠ቆላስይስ 2:2

ትክክልና ስህተት የሆነውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ረገድ ጥብቅ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ አያጠራጥርም። ብዙ ወላጆች አልፎ አልፎ በእነርሱና በልጃቸው መካከል የሐሳብ አለመጣጣም እንደሚፈጠር አስተውለዋል። ውሳኔያቸው ትክክለኛ መሠረት ያለው እስከሆነ ድረስ ግን ፈጽሞ አቋማቸውን ማላላት አይኖርባቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ ፍቅራዊ ተግሣጽ ከመስጠታችሁ በፊት ስለተፈጸመው ነገር በቂ ግንዛቤ ያላችሁ መሆኑን አረጋግጡ፤ ተግሳጽ የሚያስፈልግም ከሆነ በምን መልክ መሰጠት እንዳለበት በጥሞና አስቡበት።​—⁠ምሳሌ 18:13

ከጉባኤ ውስጥም ተጽዕኖዎች ሊመጡ ይችላሉ

አንድ የሸክላ እቃ ከተሠራ በኋላ ሲታይ ሁሉ ነገሩ ያለቀ ሊመስል ቢችልም በእሳት እስካልተተኮሰ ድረስ ውስጡ ፈሳሽ ሲጨመርበት በቀላሉ ሊፈረከስ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ፈተናዎችንና ችግሮችን እንዲህ ካለው በእሳት የመተኮስ ሂደት ጋር ያመሳስላቸዋል። ምክንያቱም ፈተናዎች ውስጣዊ ማንነታችን በግልጽ እንዲታይ ያደርጋሉ። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ እየተናገረ ያለው በእምነታችን ላይ ስለሚነሱት ፈተናዎች ቢሆንም ሐሳቡን ጠቅለል አድርገን ካየነው ግን ለሌሎች ፈተናዎችም ይሠራል። (ያዕቆብ 1:2-4) የሚያስገርመው ደግሞ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ከባድ ፈተናዎች የሚመጡት ከጉባኤ ውስጥ ነው።

በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኘው ልጃችሁ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያለው ቢመስልም በውስጡ ግን ልቡ ተከፍሎ ሊሆን ይችላል። (1 ነገሥት 18:21) ለምሳሌ ያህል ሜጋን ወደ መንግሥት አዳራሹ ከሚመጡ ሌሎች ወጣቶች የምትሰማቸው ዓለማዊ ሐሳቦች ፈተና ሆነውባት ነበር:-

“ክርስትናን አሰልቺና ደስታ ለማግኘት እንቅፋት እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ ወጣቶች ተጽዕኖ አሳድረውብኝ ነበር። ‘አሥራ ስምንት ዓመት ይሙላኝ እንጂ በእውነት ቤት መቀጠል አልፈልግም’ ወይም ‘በእውነት ቤት መኖር መሮኛል’ እንደሚሉት ያሉ ቃላትን ይናገራሉ። ሐሳባቸውን የማይደግፉ ሌሎች ወጣቶችን ‘የኛ ቅዱሳን’ እያሉ ያገልሏቸው ነበር።”

የሌሎችን አእምሮ ለመበከል መጥፎ አመለካከት ያላቸው አንድ ወይም ሁለት ወጣቶች ብቻ ይበቃሉ። በአንድ ቡድን ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ብዙውን ጊዜ አብዛኞቹ የቡድኑ አባላት የሚያደርጉትን ይከተላሉ። የቂልነት አካሄድና አጉል ጀብደኝነት ጥበብንና መልካም ምግባርን ቸል እንዲሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። በብዙ አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያን ወጣቶች ብዙኃኑን ተከትለው በመሄዳቸው ችግር ውስጥ የገቡባቸው አሳዛኝ አጋጣሚዎች አሉ።

እርግጥ ነው፣ ወጣቶች የሚዝናኑበት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ወላጆች እንደመሆናችሁ ለመዝናኛ የሚሆን ጊዜ ማመቻቸት የምትችሉት እንዴት ነው? ትኩረት ሰጥታችሁ አስቡበት፤ እንዲሁም ከቤተሰቡ ወይም ከሌሎች ወጣቶችና አዋቂዎች ጋር በመሆን የምትዝናኑበት አስደሳች ፕሮግራም አዘጋጁ። ከልጃችሁ ጓደኞች ጋር በሚገባ ተዋወቁ። ምሳ ወይም እራት ጋብዟቸው ወይም አንድ ምሽት መርጣችሁ አብራችሁ ተጫወቱ። (ሮሜ 12:13) ልጃችሁ አንድ ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ እንደ መጫወት፣ ሌላ ቋንቋ ወይም አንድ ዓይነት የእጅ ሙያ እንደ መማር ባሉ ጠቃሚ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈል አበረታቱት። በአብዛኛው እንዲህ ያሉ የጊዜ ማሳለፊያዎች ውጪ መውጣት ሳያስፈልገው እዚያው ቤት ውስጥ ሆኖ ሊያደርጋቸው የሚችላቸው ናቸው።

ትምህርትን በትጋት መከታተል ጥበቃ ሊሆን ይችላል

አንድ በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኝ ልጅ ትምህርቱን በትጋት መከታተሉ ከልክ በላይ በመዝናኛ ጊዜ እንዳያጠፋ ሊያደርገው ይችላል። በአንድ ትልቅ ትምህርት ቤት ውስጥ በርዕሰ መምህርነት ለ20 ዓመት ያገለገለችው ሎሊ እንዲህ ትላለች:- “ትምህርት ቤት ገብተው የተማሩ በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አውቃለሁ። አብዛኞቹ በምግባራቸው የሚመሰገኑ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ግን ከሌሎቹ ተማሪዎች ምንም የተለዩ አልነበሩም። በምግባራቸው ጥሩ ምሳሌ የነበሩት ትምህርታቸውን ትኩረት ሰጥተው የሚከታተሉት ናቸው። ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ትምህርት ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ፣ አስተማሪዎቻቸውን በግል እንዲያውቋቸውና ጥሩ ውጤት ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ለልጆቻቸው እንዲያሳምኗቸው ለማሳሰብ እወዳለሁ። አንዳንዶቹ የላቀ ውጤት ማምጣት ይችሉ ይሆናል፤ ሁሉም ግን አጥጋቢ ውጤት ማምጣትና በመምህሮቻቸው ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፍ ይችላሉ።”

ልጆች ትምህርታቸውን በትጋት መከታተላቸው መንፈሳዊ እድገትም እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲኖራቸው፣ ራስን መግዛት እንዲማሩና ኃላፊነት እንዲሰማቸው ሊረዳቸው ይችላል። አጥርቶ የማንበብና ሐሳቦችን በሚገባ የመረዳት ችሎታቸው ጥሩ የአምላክ ቃል ተማሪዎችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው አያጠራጥርም። (ነህምያ 8:8) የትምህርት ቤት ሥራቸውና መንፈሳዊ ጥናታቸው የሚወስድባቸው ጊዜ በመዝናኛ ረገድ ሚዛናዊ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል።

ለእናንተና ለይሖዋ ክብር ያመጣሉ

በጥንት ግሪክ ከሸክላ የተሠሩ በርካታ የአበባ ማስቀመጫዎች የሸክላ ሠሪውና ሸክላውን ያስጌጠው ሰው ፊርማ ይሠፍርባቸዋል። በቤተሰብ ውስጥም አብዛኛውን ጊዜ ልጆችን በመቅረጹ ሥራ የሚካፈሉት ሁለት ሰዎች ናቸው። የልጁን ልብ በመቅረጹ ሥራ አባትም እናትም የሚካፈሉ ሲሆን በምሳሌያዊ ሁኔታ ልጁ የሁለታችሁንም “ፊርማ” ይይዛል። እንደ ሸክላ ሠሪው ወይም ሸክላውን እንዳስጌጠው ሰው እናንተም ልጃችሁን ጥሩ አድርጋችሁ በመቅረጻችሁ ልትኮሩ ትችላላችሁ።​—⁠ምሳሌ 23:24, 25

የድካማችሁን ማግኘታችሁ የተመካው የልጃችሁን ልብ ጥሩ አድርጋችሁ በመቅረጻችሁ ላይ ነው። “የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፣ በእርምጃውም አይሰናከልም” ብላችሁ በድፍረት መናገር እንደምትችሉ ተስፋ እናደርጋለን። (መዝሙር 37:31) የልጃችሁ ልብ ይሄን ያህል ሊደከምለት የሚገባው እንጂ እንዲያው በራሱ እንዲቀረጽ የሚተው አይደለም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው ገና አራስ እያለ መጽሐፍ ቅዱስ ያነቡለታል። የሚሰማው ረጋ ያለ ድምፅና ይህ ወቅት የሚሰጠው ደስታ በቀሪው የሕይወት ዘመኑ ጥሩ የንባብ ፍላጎት እንዲያዳብር ሊረዳው ይችላል።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።