በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጌታን እራት ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

የጌታን እራት ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

የጌታን እራት ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

“ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና።”1 ቆሮንቶስ 11:23

1, 2. ኢየሱስ በ33 እዘአ በተከበረው የማለፍ በዓል ምሽት ላይ ምን አደረገ?

 የይሖዋ አንድያ ልጅ በቦታው ተገኝቷል። ‘በፈተናዎቹ ከእርሱ ጋር ጸንተው የኖሩት’ 11 ወዳጆቹም አብረውት ተገኝተዋል። (ሉቃስ 22:28) ዕለቱ ሐሙስ ምሽት መጋቢት 31, 33 እዘአ ሲሆን ሙሉዋ ጨረቃ በብርሃኗ የኢየሩሳሌምን ሰማይ አድምቃዋለች። ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ የማለፍን በዓል አክብረው መጨረሳቸው ነበር። ከዳተኛው የአስቆሮቱ ይሁዳ ከመካከላቸው እንዲወጣ ተደርጓል። ሌሎቹ ግን እዛው መቆየት ነበረባቸው። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የሚያከናውነው አንድ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ጉዳይ ነበረው። ይህ ምንድን ነው?

2 ሐዋርያው ማቴዎስ በቦታው ተገኝቶ ስለነበር የሆነውን ነገር ሲተርክልን እንስማው:- “ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና:- እንካችሁ፣ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ:- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” (ማቴዎስ 26:26-28) ይህ አንድ ጊዜ ብቻ ተከብሮ ያበቃለት በዓል ነውን? ምን ትርጉም ነበረው? በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛስ የያዘው ትርጉም ይኖር ይሆን?

“ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት”

3. ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 እዘአ ያቋቋመው በዓል ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 እዘአ ያደረገው ነገር በሕይወቱ ውስጥ በአጋጣሚ የተከሰተ ተራ ክንውን አይደለም። ኢየሱስ ያቋቋመው ይህ በዓል መከበር ከጀመረ ከ20 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ በዓሉ ማብራሪያ ሰጥቷል። ጳውሎስ በ33 እዘአ ከኢየሱስና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር በበዓሉ ላይ ባይገኝም እንኳ በዚያን ወቅት ስለተከናወኑት ነገሮች ከአንዳንድ ሐዋርያት ሰምቶ መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ከጳውሎስ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው በዓሉን የሚመለከቱ አንዳንድ ተጨማሪ መረጃዎች በራእይ ተገልጦለት ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፣ ቈርሶም:- እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ:- ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:23-25

4. ክርስቲያኖች የጌታን እራት ማክበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ትእዛዝ መስጠቱን ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ሉቃስ 22:19) ይህ በዓል ብዙውን ጊዜ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ተብሎ ይጠራል። በዓሉ የተቋቋመው ቀኑ ከመሸ በኋላ በመሆኑ ጳውሎስም ይህንን በዓል የጌታ እራት በማለት ጠርቶታል። በእርግጥም ተስማሚ ስያሜ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:20) ክርስቲያኖች የጌታን እራት እንዲያከብሩ ታዝዘዋል። ሆኖም ይህ በዓል የተቋቋመው ለምንድን ነው?

በዓሉ የተቋቋመው ለምንድን ነው?

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ያቋቋመበት አንደኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) የጌታ እራት የተቋቋመበትን ሁለተኛውን ምክንያት ተናገር።

5 የመታሰቢያው በዓል የተቋቋመበት አንደኛው ምክንያት የኢየሱስ ሞት ካከናወነው ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው። ኢየሱስ በሞቱ አማካኝነት በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የቆመ መሆኑን አሳይቷል። በመሆኑም ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ለጥቅማቸው ነው በማለት የውሸት ክስ ያስነሳው ሰይጣን ዲያብሎስ ሃሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል። (ኢዮብ 2:1-5) ኢየሱስ በታማኝነት መሞቱ ይህ የሰይጣን አባባል ውሸት መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝቷል።​—⁠ምሳሌ 27:11

6 የጌታ እራት የተቋቋመበት ሌላው ምክንያት ኢየሱስ ፍጹምና ምንም ኃጢአት የሌለበት ሆኖ በመሞት ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ መስጠቱን’ እንድናስታውስ ለማድረግ ነው። (ማቴዎስ 20:28) የመጀመሪያው ሰው በአምላክ ላይ ኃጢአት በመሥራቱ ፍጹም ሆኖ የመኖር መብቱንና የወደፊት ተስፋውን ሁሉ አጣ። ሆኖም ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:16) በእርግጥም “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6:23) የጌታን እራት ማክበራችን ከኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ጋር በተያያዘ ይሖዋ እና ልጁ ያሳዩንን ታላቅ ፍቅር እንድናስታውስ ያደርገናል። ሁለቱ ላሳዩን ፍቅር ምንኛ አመስጋኞች ነን!

መከበር ያለበት መቼ ነው?

7. ቅቡዓን ከቂጣውና ከወይኑ በተካፈሉ ቁጥር የክርስቶስን ሞት የሚናገሩት እንዴት ነው?

7 ጳውሎስ የጌታን እራት በማስመልከት “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 11:26) ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ይካፈላሉ። ከቂጣውና ከወይኑ በተካፈሉ ቁጥር ይሖዋ አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ።

8. በቡድን ደረጃ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የጌታን እራት ማክበር ያለባቸው እስከ መቼ ነው?

8 በቡድን ደረጃ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስን የሞቱን መታሰቢያ የሚያከብሩት እስከ መቼ ነው? ጳውሎስ “ጌታ እስኪመጣ ድረስ” በማለት ተናግሯል። ጳውሎስ ይህን ሲናገር ኢየሱስ ‘በመገኘቱ’ ወቅት ቅቡዓን ተከታዮቹን በትንሣኤ ለመቀበል እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በዓሉ መከበሩን ይቀጥላል ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:14-17) ይህም ኢየሱስ ለአሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያት ከተናገራቸው ቃላት ጋር ይስማማል። “ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፣ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ብሏቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 14:3

9. ማርቆስ 14:​25 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

9 ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም የወይኑን ጽዋ አንስቶ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን “በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው።” (ማርቆስ 14:25) ኢየሱስ በሰማይ ቃል በቃል የወይን ጠጅ ሊጠጣ ስለማይችል ይህን የተናገረው የወይን ጠጅ የሚያመለክተውን ደስታ በአእምሮው ይዞ እንደሚሆን የታወቀ ነው። (መዝሙር 104:15፤ መክብብ 10:19) እርሱና የእርሱን ፍለጋ የተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ ይህን ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቁ ስለነበር በመንግሥቱ አንድ ላይ መሆናቸው ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል።​—⁠ሮሜ 8:23፤ 2 ቆሮንቶስ 5:2

10. የመታሰቢያው በዓል መከበር ያለበት በዓመት ስንት ጊዜ ነው?

10 የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል በየወሩ፣ በየሳምንቱ ወይም በየቀኑ መከበር አለበትን? የለበትም። ኢየሱስ የጌታን እራት ያቋቋመውም ሆነ የተገደለው እስራኤላውያን በ1513 ከዘአበ ከግብፅ ባርነት ነፃ በወጡበትና “መታሰቢያ” እንዲሆናቸው በሚያከብሩት የማለፍ በዓል ዕለት ነበር። (ዘጸአት 12:14) የማለፍ በዓል ይከበር የነበረው በዓመት አንድ ጊዜ ማለትም በአይሁዳውያን አቆጣጠር በኒሳን ወር በ14ኛው ቀን ነበር። (ዘጸአት 12:1-6፤ ዘሌዋውያን 23:5) ስለዚህ የኢየሱስ ሞት መከበር ያለበት በየወሩ፣ በየሳምንቱ ወይም በየቀኑ ሳይሆን የፋሲካ በዓል ይከበር እንደነበረው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

11, 12. በጥንት ጊዜ ይከበር ስለነበረው የመታሰቢያ በዓል ታሪክ ጸሐፊዎች ምን ብለዋል?

11 በመሆኑም የመታሰቢያውን በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ኒሳን 14 ላይ ማክበራችን የተገባ ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “በትንሿ እስያ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ኒሳን 14 ላይ ፋሲካን [የጌታን እራት] ያከብሩ ስለነበር ኩዋርቶዴሲማንስ [አሥራ አራተኛ ቀን አክባሪዎች] ተብለው ይጠሩ ነበር። . . . በዓሉ ዓርብ ዕለት ወይም በሳምንቱ ውስጥ በማንኛውም ቀን ላይ ይውል ነበር።”​—⁠ዘ ኒው ሻፍ-ሃርትሶክ ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሪሊጂየስ ኖውሌጅ፣ ጥራዝ 4 ገጽ 44

12 በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበረውን የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤል ፎን ሞሺም እንደተናገሩት ኩዋርቶዴሲማንስ ተብለው የሚጠሩት ክርስቲያኖች “ክርስቶስ የተወው ምሳሌ የሕግን ያህል የማስገደድ ኃይል እንዳለው ያምኑ ስለነበር” የመታሰቢያውን በዓል ኒሳን 14 ያከብሩ ነበር። ሌላ ታሪክ ጸሐፊም እንዲህ ብለዋል:- “በእስያ የሚገኙት የኩዋርቶዴሲማን አብያተ ክርስቲያናት ይከተሉት የነበረው ልማድ ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ጋር ተመሳሳይ ነበር። በሁለተኛው መቶ ዘመን እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የፋሲካን በዓል በሚያከብሩበት በኒሳን 14 ዕለት በክርስቶስ ሞት የተቋቋመውን የመዳን ዝግጅት ያከብሩ ነበር።”​—⁠ስቱዲያ ፓትሪስቲካ ጥራዝ 5፣ 1962 ገጽ 8

የቂጣው ትርጉም

13. ኢየሱስ የጌታን እራት ሲያቋቁም የተጠቀመው በምን ዓይነት ቂጣ ነው?

13 ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ባቋቋመበት ወቅት “እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም [ለሐዋርያቱ] ሰጣቸው።” (ማርቆስ 14:22) በዚህ በዓል ላይ የነበረው ቂጣ በማለፍ በዓሉ ላይ የቀረበው ያው ቂጣ ነበር። (ዘጸአት 13:6-10) ቂጣው በቀላሉ የሚቆረስና እርሾ ያልገባበት በመሆኑ ጠፍጣፋ ነበር። ለሁሉም እንዲዳረስ መቆራረስ ነበረበት። ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ በተአምር ያበዛው ቂጣም ለሁሉም እንዲዳረስ በቀላሉ ሊቆረስ የሚችል ነበር። (ማቴዎስ 14:​19፤ 15:​36) በመሆኑም የመታሰቢያው ቂጣ መቆራረሱ መንፈሳዊ ትርጉም የለውም።

14. (ሀ) የመታሰቢያው በዓል ቂጣ ያልቦካ መሆኑ ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ለጌታ እራት ምን ዓይነት ቂጣ መግዛት ወይም መጋገር ይቻላል?

14 ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም የተጠቀመበትን ቂጣ በማስመልከት “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 11:24፤ ማርቆስ 14:22) ቂጣው ያልቦካ መሆኑ ተገቢ ነበር። ለምን? ምክንያቱም እርሾ መጥፎነትን፣ ክፋትን ወይም ኃጢአትን ሊያመለክት ስለሚችል ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:6-8) ቂጣው ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን ኃጢአት የሌለበትን ፍጹሙን የኢየሱስ ሥጋ ያመለክታል። (ዕብራውያን 7:​26፤ 10:​5-​10) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በአእምሯቸው ይዘው በመታሰቢያው በዓል ላይ ያልቦካ ቂጣ በመጠቀም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ይከተላሉ። የሚገኝ ከሆነ እንደ ሽንኩርት ወይም እንቁላል ያሉ ነገሮች ያልተጨመሩበት አይሁዳውያን በማለፍ በዓላቸው ወቅት የሚበሉት ያልቦካ ቂጣ ይጠቀማሉ። የማይገኝ ከሆነም ጥቂት ዱቄት (የሚቻል ከሆነ የስንዴ ዱቄት) ከትንሽ ውኃ ጋር በመደባለቅ ያልቦካ ቂጣ ማዘጋጀት ይቻላል። ሊጡ በስሱ ከተዳመጠ በኋላ በቀላሉ ለመቁረስ እንዲቻል እስኪደርቅ ድረስ ትንሽ ዘይት ጠብ ባለበት መጥበሻ ላይ መጋገር ይቻላል።

የወይኑ ትርጉም

15. ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ሲያቋቁም በጽዋው ውስጥ የነበረው ምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ያልቦካው ቂጣ እንዲዞር ካደረገ በኋላ ጽዋውን “አንስቶ አመስግኖም [ለሐዋርያቱ] ሰጣቸው፣ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።” ከዚያም ኢየሱስ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” በማለት ተናገረ። (ማርቆስ 14:23, 24) በጽዋው ውስጥ የነበረው ምንድን ነው? የወይን ጭማቂ ሳይሆን የፈላ የወይን ጠጅ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ወይን ጠጅ በሚናገሩበት ጊዜ ስላልፈላ የወይን ጭማቂ መናገራቸው አይደለም። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እንደተናገረው ‘ያረጀውን አቁማዳ’ ሊያፈነዳ የሚችለው የወይን ጭማቂ ሳይሆን የፈላ የወይን ጠጅ ነው። እንዲሁም የክርስቶስ ጠላቶች ኢየሱስ “የወይን ጠጅ ጠጭ” እንደሆነ ተናግረው ነበር። ወይኑ የወይን ጭማቂ ቢሆን ኖሮ ክሳቸው ምንም ትርጉም አይኖረውም ነበር። (ማቴዎስ 9:​17፤ 11:​19) የማለፍ በዓል በሚከበርበት ጊዜ የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር፤ ኢየሱስም የሞቱን መታሰቢያ በዓል ሲያቋቁም ይህን መጠጥ ተጠቅሟል።

16, 17. ለመታሰቢያው በዓል ተስማሚ የሆኑት የወይን ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ?

16 በጽዋው ውስጥ የነበረው መጠጥ የሚያመለክተው የፈሰሰውን የኢየሱስ ደም ሲሆን ለዚህ ደግሞ ተስማሚ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው ቀይ የወይን ጠጅ ብቻ ነው። ኢየሱስ ራሱ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” በማለት ተናግሯል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፣ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።”​—⁠1 ጴጥሮስ 1:18, 19

17 ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ቀይ የወይን ጠጅ እንደተጠቀመ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ቀይ ወይኖች አልኮል፣ ብራንዲ ወይም ሌሎች ነገሮች ስለሚጨመርባቸው ለበዓሉ ተስማሚ አይሆኑም። የኢየሱስ ደም ፍጹም በመሆኑ በወይን ጠጁ ውስጥ ምንም ነገር መጨመር አያስፈልግም። ስለዚህም ማጠናከሪያ የተቀላቀለባቸው ወይኖች ለበዓሉ ተስማሚ አይደሉም። የመታሰቢያው ወይን ምንም ዓይነት ማጣፈጫ ያልተጨመረበትና አልኮል ያልገባበት መሆን አለበት። ማጣፈጫ ያልተጨመረበት ቤት ውስጥ የተዘጋጀ ቀይ የወይን ጠጅ ወይም እንደ ቀይ ቡርጋንዲና ክላሬት ያሉ ወይን ጠጆችን ወይም የኢትዮጵያ ዱከም ወይን ጠጅን መጠቀም ይቻላል።

18. ኢየሱስ የመታሰቢያውን ቂጣና ወይን በተአምር ያልለወጣቸው ለምንድን ነው?

18 ኢየሱስ የጌታን እራት ሲያቋቁም ምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ቃል በቃል ተለውጦ የራሱን ሥጋና ደም እንዲሆን በማድረግ ተአምር አልፈጸመም። የሰው ሥጋ መብላትና ደም መጠጣት ዘግናኝ ድርጊት ከመሆኑም በላይ የአምላክን ሕግ የሚፃረር ነው። (ዘፍጥረት 9:​3, 4፤ ዘሌዋውያን 17:​10) በዚያን ምሽት ኢየሱስ ከነ ሥጋዊ አካሉ የነበረ ሲሆን ሥጋውም ሆነ ደሙ ፍጹም መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው በአይሁዳውያን አቆጣጠር ኒሳን 14 ቀን ከሰዓት በኋላ ነበር። ስለዚህ የመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን ምሳሌያዊ ሲሆኑ የክርስቶስን ሥጋና ደም ያመለክታሉ። a

የመታሰቢያው በዓል የሕብረት ማዕድ ነው

19. በጌታ እራት በዓል ላይ ከአንድ በላይ ሳህንና ጽዋ መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ታማኝ ሐዋርያቱ ከአንዱ ጽዋ እንዲጠጡ ጋብዟቸዋል። የማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- “[ኢየሱስ] ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ:- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ።” (ማቴዎስ 26:27) በበዓሉ ላይ ከቂጣውና ከወይኑ የተካፈሉት አሥራ አንዱም ሐዋርያት የተቀመጡት በአንድ ማዕድ ዙሪያ ስለሚሆንና ጽዋውን መቀባበል ስለሚችሉ በዛ ያሉ ጽዋዎችን ከመጠቀም ይልቅ ‘አንድ ጽዋ’ ብቻ መጠቀሙ ችግር የሚፈጥር አልነበረም። በዚህ ዓመት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጌታን እራት ለማክበር በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ94, 000 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይሰበሰባሉ። በዚህ ምሽት የሚደረጉት ስብሰባዎች በጣም ብዙ በመሆናቸው ሁሉም በአንድ ጽዋ ብቻ መጠቀም አይችሉም። ሆኖም በርካታ ጽዋዎችን በመጠቀም መሥዋዕት ሆኖ የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም የሚወክለውን ጽዋ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ማዞር ይቻላል። ይህም ምሳሌያዊውን ወይን በማዞር ብዙ ሰዓት እንዳይባክን ይረዳል። በተመሳሳይም ቂጣውን ለማዞር በርከት ያሉ ሳህኖችን መጠቀም ይቻላል። ወይኑ የተቀዳበት ጽዋ ወይም ብርጭቆ አንድ ዓይነት ቅርጽ ሊኖረው እንደሚገባ የሚጠቁም አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አናገኝም። ሆኖም ጽዋውም ሆነ ቂጣው የሚዞርበት ሳህን ክብር ለተላበሰው ለዚህ በዓል የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። ወይኑ በሚዞርበት ጊዜ እንዳይፈስ ጽዋውን እስከ አፉ ድረስ መሙላት አያስፈልግም።

20, 21. የመታሰቢያው በዓል የሕብረት ማዕድ ነው ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

20 በበዓሉ ላይ በርካታ ሳህኖችንና ጽዋዎችን ማዞር ቢቻልም የመታሰቢያው በዓል የሕብረት ማዕድ ነው። በጥንቷ እስራኤል አንድ እስራኤላዊ ወደ አምላክ ቤተ መቅደስ አንድ እንስሳ ወስዶ በማረድ የደህንነት መሥዋዕት ማቅረብ ይችል ነበር። የእንስሳው የተወሰነ ክፍል በመሠዊያው ላይ ይቃጠላል፤ የተወሰነው ክፍል ደግሞ የመሥዋዕቱን ሥርዓት ለሚያካሂደው ካህን ይሰጣል። የተቀረው የእንስሳው ክፍል ደግሞ መሥዋዕቱን ካቀረበው ሰውና ከቤተሰቡ ጋር አብረው እንዲመገቡ ካህናት ሆነው ለሚያገለግሉት ለአሮን ልጆች ይሰጣል። (ዘሌዋውያን 3:​1-​16፤ 7:​28-​36) የመታሰቢያው በዓልም በማዕድ አብሮ መካፈልን የሚጠይቅ በመሆኑ የሕብረት ማዕድ ነው።

21 ይህን ሥርዓት ያወጣው ይሖዋ እንደመሆኑ እርሱም በዚህ የሕብረት ማዕድ ይካፈላል። መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው ኢየሱስ ሲሆን ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ተባባሪ በመሆን ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ይካፈላሉ። ከይሖዋ ማዕድ መመገባቸው ተካፋዮቹ ከይሖዋ ጋር ሰላም እንዳላቸው ያሳያል። ከዚህ ጋር በመስማማት ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፣ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:16, 17

22. የመታሰቢያውን በዓል በተመለከተ የምንመረምራቸው ምን ጥያቄዎች አሉ?

22 የጌታ እራት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከብሩት ብቸኛው ዓመታዊ በዓላቸው ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ስላዘዛቸው ይህን በዓል ማክበራቸው የተገባ ነው። በመታሰቢያው በዓል ላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት ያስከበረውን የኢየሱስን ሞት እናከብራለን። እስከ አሁን እንደተመለከትነው በዚህ የሕብረት ማዕድ ላይ የሚቀርበው ቂጣ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን የክርስቶስ ሰብዓዊ አካል የሚያመለክት ሲሆን ወይኑ ደግሞ የፈሰሰውን ደሙን ያመለክታል። ሆኖም ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የመታሰቢያው በዓል ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ለማይካፈሉ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ምን ትርጉም አለው? ከሁሉም በላይ ደግሞ የጌታ እራት ለአንተ በግልህ ምን ትርጉም አለው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 271ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ የጌታን እራት ያቋቋመው ለምንድን ነው?

• የመታሰቢያው በዓል በዓመት ስንት ጊዜ መከበር አለበት?

• የመታሰቢያው በዓል ያልቦካ ቂጣ ምን ያመለክታል?

• የመታሰቢያው በዓል ወይን ምን ያመለክታል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የጌታን እራት አቋቋመ