በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንግሥቱን ማስቀደም የተረጋጋና አስደሳች ሕይወት ያስገኛል

መንግሥቱን ማስቀደም የተረጋጋና አስደሳች ሕይወት ያስገኛል

የሕይወት ታሪክ

መንግሥቱን ማስቀደም የተረጋጋና አስደሳች ሕይወት ያስገኛል

ጄታ ሱነል እንደተናገረችው

ቁርስ ከበላን በኋላ ራዲዮ ስናዳምጥ “የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ሕገ ወጥ ነው፤ ሥራቸውም ታግዷል” የሚል መግለጫ ሰማን።

ወቅቱ 1950 ሲሆን በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የምንገኘው አራት ሴቶች በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በሚስዮናዊነት እያገለገልን ነበር። እዚህ የመጣነው በ1949 ነበር።

ልጅ እያለሁ ሚስዮናዊ የመሆን ግብ አልነበረኝም። እርግጥ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን እሄድ ነበር። አባቴ ግን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆመ። በ1933 የኤፒስኮፓል ቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በሄድኩበት ቀን ጳጳሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጥቅስ ብቻ ካነበቡ በኋላ ስለ ፖለቲካ ማውራት ጀመሩ። እናቴ በሁኔታው በጣም ስለተናደደች ዳግመኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን አልሄደችም።

የሕይወት አቅጣጫችን ተለወጠ

የአባቴ የዊልያም ካርል እና የእናቴ የሜሪ አዳምስ ልጆች አምስት ነበርን። ወንዶቹ ዶን፣ ጆኤል እና ካርል ይባላሉ። ጆይ የተባለችው እህቴ የመጨረሻ ልጅ ስትሆን እኔ ደግሞ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። በ13 ዓመቴ ገደማ ይመስለኛል አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስመለስ እማማ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ አንድ ቡክሌት ስታነብ አገኘኋት። ቡክሌቱ የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ነበረው። እናቴ “እውነትን አገኘሁ” አለችኝ።

እማማ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትማራቸውን ነገሮች ለሁላችንም ትነግረን ነበር። ኢየሱስ ‘አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ፈልጉ’ ሲል የሰጠውን ምክር ጠቃሚነት በቃልም ሆነ በድርጊት አስገንዝባናለች።​—⁠ማቴዎስ 6:33

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የምትነግረንን መስማት አልፈልግም ነበር። በአንድ ወቅት “እማማ፣ በቃ መስማት አልፈልግም፤ እምቢ ካልሽ ሁለተኛ የታጠቡትን ዕቃዎች አላደርቅልሽም” አልኳት። ያም ሆኖ ቀስ እያለች በጥበብ ትነግረን ነበር። በኤልምኸረስት፣ ኢሊኖይ፣ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው ቤታችን አቅራቢያ በምትኖረው በክላራ ራያን ቤት ወደሚደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብሰባ አምስታችንንም አዘውትራ ትወስደን ነበር።

ክላራ ፒያኖም ታስተምር ነበር። ተማሪዎቿ በየዓመቱ ችሎታቸውን ለሕዝብ በሚያሳዩበት ጊዜ አጋጣሚውን በመጠቀም ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ትንሣኤ ተስፋ ትናገራለች። ሙዚቃ ስለምወድ (ከሰባት ዓመቴ ጀምሮ ቫዮሊን መጫወት ተምሬያለሁ) ክላራ የምትናገረውን አዳምጥ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ አምስታችንም ከእማማ ጋር ሆነን በምዕራብ ቺካጎ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መሰብሰብ ጀመርን። ወደቦታው ለመድረስ በአውቶቡስና በከተማ ባቡር ረጅም ርቀት መጓዝ የነበረብን ቢሆንም መንግሥቱን በማስቀደም ረገድ ከልጅነታችን ጀምሮ ሥልጠና አግኝተንበታል። በ1938፣ እናቴ ከተጠመቀች ከሦስት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው ከእሷ ጋር ሆኜ በቺካጎ በተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ስብሰባው በስልክ ከተላለፈባቸው 50 ከተሞች መካከል አንዱ ቺካጎ ነበር። በስብሰባው ላይ የተሰጠው ትምህርት ልቤን ነካው።

ያም ሆኖ ለሙዚቃ የነበረኝ ፍቅር ከልቤ አልጠፋም። በ1938 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅሁ። አባቴ ቺካጎ በሚገኝ አሜሪካን ኮንሰርቫቶሪ ኦቭ ሚውዚክ የተባለ ትምህርት ቤት እንድማር ሁኔታዎችን አመቻችቶልኝ ነበር። ስለዚህ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሙዚቃ ትምህርት እየተማርኩ በሁለት የሙዚቃ ባንዶች ውስጥ ተጫውቻለሁ፤ ግቤ በዚህ ሞያ ለመሰማራት ነበር።

የቫዮሊን አስተማሪዬ የነበረው ኸርበርት በትለር በዩናይትድ ስቴትስ ለመኖር ከአውሮፓ የመጣ ስደተኛ በመሆኑ ያነብበዋል በሚል ስደተኞች  a (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት ሰጠሁት። ቡክሌቱን ያነበበው ከመሆኑም በላይ በቀጣዩ ሳምንት የትምህርት ክፍለ ጊዜው እንዳበቃ እንዲህ አለኝ:- “ጄታ ጥሩ ችሎታ አለሽ፤ ትምህርትሽን ከቀጠልሽ በራዲዮ ኦርኬስትራ ውስጥ ልትቀጠሪ ወይም የሙዚቃ አስተማሪ ልትሆኚ ትችያለሽ።” ከዚያም የሰጠሁትን ቡክሌት በጣቱ እያመለከተ “እኔ ሳስበው ግን ልብሽ ያለው እዚህ ላይ ይመስለኛል። ለምን በዚህ ሥራ አትሰማሪም?” አለኝ።

ጉዳዩን በቁም ነገር አሰብኩበት። ከዚያም ትምህርቴን አቋረጥኩና ከእማማ ጋር ሆኜ ሐምሌ 1940 በዲትሮይት፣ ሚሽገን በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ለስብሰባው ተብሎ በተዘጋጀው ካምፕ በድንኳን ውስጥ አረፍን። ቫዮሊኔን ይዤው ስለነበር በአውራጃ ስብሰባው ላይ የነበረው የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ገባሁ። ሆኖም በጊዜያዊው ካምፕ ውስጥ ከበርካታ አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን) ጋር ተገናኘሁ። ሁሉም በጣም ደስተኞች ነበሩ። እኔም ተጠምቄ ለአቅኚነት ለማመልከት ወሰንኩ። ይሖዋ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቆየት እንድችል እንዲረዳኝ በጸሎት ጠየቅሁት።

አቅኚ ሆኜ ማገልገል የጀመርኩት በትውልድ መንደሬ ነበር። ቀጥሎም በቺካጎ አገለገልኩ። በ1943 ደግሞ ወደ ኬንተኪ ተዛወርኩ። በዚያ ዓመት ከአውራጃ ስብሰባው በፊት በነበረው የበጋ ወቅት በጊልያድ ትምህርት ቤት በሁለተኛው ክፍል ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ፤ ጊልያድ ለሚስዮናዊ አገልግሎት ሥልጠና የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ነው። ትምህርቱ የሚጀመረው በመስከረም 1943 ነበር።

በበጋው ወራት በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ወቅት ያረፍኩት አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤት ነበር፤ ይህቺ እህት ከሴት ልጅዋ ልብሶች መካከል የፈለግሁትን መርጬ እንድወስድ ጋበዘችኝ። ልጅዋ ወታደር ሆና ስለነበር እናቷ ዕቃዎቿን በሙሉ ለሰዎች እንድትሰጥ ነግራት ነበር። ይህ ዝግጅት ኢየሱስ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” በማለት የገባው ቃል ፍጻሜ ሆኖልኝ ነበር። (ማቴዎስ 6:33) በጊልያድ የቆየሁባቸው አምስት ወራት በፍጥነት አለፉ፤ ጥር 31, 1944 ስንመረቅ የሚስዮናዊነትን አገልግሎት ለመጀመር ጓጉቼ ነበር።

እነሱም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል መረጡ

እማማ በ1942 የአቅኚነት አገልግሎት ጀመረች። በዚያ ወቅት ሦስቱ ወንድሞቼና እህቴ ገና ትምህርታቸውን አልጨረሱም። አብዛኛውን ጊዜ እማማ ከትምህርት ቤት ሲወጡ ትጠብቃቸውና ወደ አገልግሎት ይዛቸው ትሄድ ነበር። የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወንም አስተምራቸዋለች። እሷ ራሷ ቀን በአገልግሎት መካፈል እንድትችል አብዛኛውን ጊዜ እያመሸች ልብሶችን ትተኩስና ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎችን ታከናውን ነበር።

በጥር 1943 በኬንተኪ አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ እያለ ወንድሜ ዶንም አቅኚ ሆነ። አባታችን ልክ እንደ እሱና እንደ እማማ ሁሉም ልጆቹ ኮሌጅ ገብተው እንዲማሩ ይፈልግ ስለነበረ በዚህ አልተደሰተም። ዶን ለሁለት ዓመት ገደማ አቅኚ ሆኖ ካገለገለ በኋላ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እንዲያገለግል ተጋበዘ።

ሰኔ 1943 ጆኤል እቤት ሆኖ በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ። በዚያን ወቅት አባባን በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ቢጋብዘውም ፈቃደኛ አልሆነለትም። ሆኖም ጆኤል በዚያ አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ሲመለከት አባባ “ነጻ የሚያወጣው እውነት” (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ እንዲያስጠናው ተስማማ። አባባ ጥያቄዎቹን በቀላሉ ይመልስ የነበረ ቢሆንም በመጽሐፉ ውስጥ ለቀረበው ሐሳብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ እንዲያሳየው ጆኤልን ያፋጥጠው ነበር። ይህም ጆኤል የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በደንብ እንዲገባው ረድቶታል።

ጆኤል፣ ዶን ሃይማኖታዊ አገልጋይ በመሆኑ ከወታደራዊ ግዳጅ ነጻ እንዲሆን የወሰነው የምልመላ ቦርድ ለእሱም ተመሳሳይ ውሳኔ እንደሚሰጠው አስቦ ነበር። ሆኖም ቦርዱ ጆኤል ሃይማኖታዊ አገልጋይ ተደርጎ ለመቆጠር ዕድሜው ገና ነው ብሎ ስለደመደመ ለወታደራዊ አገልግሎት እንዲመዘገብ ማዘዣ ላከለት። እሱም ለውትድርና አገልግሎት ለመቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ እንዲታሰር ትእዛዝ ተላለፈ። የፌደራሉ የምርመራ ቢሮ ያዘውና ለሦስት ቀናት ያህል በኩክ ግዛት ባለው ወኅኒ ቤት ታሰረ።

አባባ ቤታችንን አስይዞ አስፈታው። ከዚያም በኋላ ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ወጣት ምሥክሮች በዚሁ መንገድ አስፈትቷቸዋል። አባባ በዚህ የፍትሕ መጓደል በጣም ስለተናደደ ይግባኝ ለመጠየቅ ከጆኤል ጋር ወደ ዋሽንግተን ዲ ሲ ሄዱ። በመጨረሻም ጆኤል ሃይማኖታዊ አገልጋይ መሆኑ ተቀባይነት በማግኘቱ ፋይሉ ተዘጋ። አባቴ “ላገኘነው ድል ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ ይሰማኛል!” በማለት ጻፈልኝ። በነሐሴ 1946 መገባደጃ ላይ ጆኤልም በብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት እንዲያገለግል ተጋበዘ።

ካርል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከማጠናቀቁ በፊት በእረፍት ጊዜው በተደጋጋሚ አቅኚ ሆኖ ያገለግል ነበር። በ1947 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነ። በወቅቱ አባባ ጥሩ ጤንነት ስላልነበረው ካርል አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ወደሌላ ቦታ እስከሄደበት ጊዜ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ያህል በሥራው ያግዘው ነበር። በ1947 መገባደጃ ላይ ካርል በብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆኖ ከዶንና ከጆኤል ጋር ማገልገል ጀመረ።

ጆይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ አቅኚ ሆነች። ከዚያም በ1951 ከወንድሞቿ ጋር በቤቴል ማገልገል ጀመረች። በጽዳትና የመጽሔት ኮንትራት ክፍል ውስጥ ሠርታለች። በ1955 ሮጀር ሞርጋን የተባለ ቤቴላዊ አገባች። ሰባት ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ የራሳቸውን ቤተሰብ መመሥረት ስለፈለጉ ከቤቴል ወጡ። ከጊዜ በኋላ ሁለት ልጆች የወለዱ ሲሆን እነሱም ይሖዋን ያገለግላሉ።

ሁላችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ በነበርንበት ጊዜ እማማ መንፈሳዊ ማበረታቻ ትሰጠው ስለነበር በ1952 አባባ ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠመቀ። ከዚያ በኋላ በሕይወት በቆየባቸው 15 ዓመታት የጤና እክል ተሳትፎውን ቢገድብበትም እንኳን የመንግሥቱን እውነት ለሌሎች በጥበብ ያካፍል ነበር።

እማማ፣ አባባ በመታመሙ ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ያህል አቅኚነቷን ብታቋርጥም እንኳ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ በአቅኚነት አገልግላለች። እማማ መኪናም ሆነ ብስክሌት ኖሯት አያውቅም፤ ቁመናዋ አጠር ያለ ሲሆን የትም ቦታ ስትሄድ የምትጓዘው በእግሯ ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜ ራቅ ወዳሉት ገጠራማ አካባቢዎች በእግሯ እየሄደች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ትመራ ነበር።

በሚስዮናዊነት አገልግሎት መካፈል

ከጊልያድ ትምህርት ቤት ከተመረቅን በኋላ የተወሰንነው ለጉዞ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ሰነዶች እስኪዘጋጁልን ድረስ በሰሜናዊ ኒው ዮርክ ለአንድ ዓመት ያህል በአቅኚነት አገለገልን። በመጨረሻም በ1945 ወደ ምድብ ቦታችን ወደ ኩባ ሄድንና አዲስ ዓይነት ሕይወት ጀመርን። ሰዎች ለስብከቱ ሥራችን ጥሩ ምላሽ ይሰጡ የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ሁላችንም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አገኘን። ለተወሰኑ ዓመታት በዚያ ስናገለግል ከቆየን በኋላ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ እንድናገለግል ተመደብን። አንድ ቀን አገልግሎት ላይ ያገኘኋት አንዲት ሴት፣ ሱዛን ኦንፍሯ የተባለች ፈረንሳዊት ደንበኛዋ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናት ሰው ስለምትፈልግ እንዳነጋግራት ጠየቀችኝ።

ሱዛን አይሁዳዊት በመሆንዋ ሂትለር ፈረንሳይን በወረረበት ወቅት ባለቤትዋ እሷንና ሁለት ልጆቿን ወደሌላ አገር ወስዷቸው ነበር። ሱዛን የተማረችውን ነገር ወዲያው ለሌሎች ትናገር ነበር። መጀመሪያ እሷን እንዳነጋግራት ለጠየቀችኝ ሴት ከዚያም ብሎንሽ ለተባለች ከፈረንሳይ ለመጣች ጓደኛዋ መሰከረችላቸው። ሁለቱም እድገት አድርገው ተጠመቁ።

ሱዛን “ልጆቼን ልረዳቸው የምችለው እንዴት ነው?” ስትል ጠየቀችኝ። ወንድ ልጅዋ ሕክምና እያጠና ሲሆን ሴት ልጅዋ ደግሞ ኒው ዮርክ በሚገኘው ሬዲዮ ሲቲ ሚውዚክ ሆል ተወዛዋዥ ለመሆን የባሌ ዳንስ እየተማረች ነበር። ሱዛን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ኮንትራት እንዲደርሳቸው አደረገች። ከዚህም የተነሳ የሱዛን ወንድ ልጅ፣ ሚስቱና የሚስቱ መንትያ እህት የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። የሱዛን ባለቤት ሉዊ በወቅቱ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ሥራችን ታግዶ ስለነበር ሚስቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያላት ግንኙነት አሳስቦት ነበር። ሆኖም መላው ቤተሰብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተዛወረ በኋላ እሱም የይሖዋ ምሥክር ሆነ።

በእገዳ ሥር ብንሆንም ማገልገላችንን አላቆምንም

በ1949 በዶሚኒካን ሪፑብሊክ እንድናገለግል ከተመደብን ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ቢታገድም ከሰው ይልቅ አምላክን ለመታዘዝ ቆርጠን ነበር። (ሥራ 5:29) ኢየሱስ ተከታዮቹን ባዘዛቸው መሠረት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጅ መንግሥቱን ማስቀደማችንን ቀጠልን። (ማቴዎስ 24:14) ሆኖም በስብከቱ ሥራ በምንካፈልበት ጊዜ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” መሆን እንዳለብን ተገንዝበን ነበር። (ማቴዎስ 10:16) ለምሳሌ ያህል ቫዮሊኔ በጣም ጠቅሞኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ስሄድ ይዤው እሄዳለሁ። ተማሪዎቼ ቫዮሊን ተጫዋቾች አልሆኑም፤ ሆኖም በርካታ ቤተሰቦች የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት ችያለሁ!

እገዳ ከተጣለ በኋላ አራታችን ማለትም እኔ፣ ሜሪ አንዮል፣ ሶፍያ ሶቪየክ እና ኢደዝ ሞርጋን በሳን ፍራንሲስኮ ደ ማኮሪስ ከሚገኘው የሚስዮናውያን ቤት በዋና ከተማው ሳንቶ ዶሚንጎ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ወደሚገኝ የሚስዮናውያን ቤት ተዛወርን። ሆኖም በየወሩ መጀመሪያ ወደተመደብንበት ቦታ እየሄድኩ ሙዚቃ አስተምር ነበር። በዚያውም በቫዮሊን መያዣው ውስጥ ለክርስቲያን ወንድሞቻችን የሚሆን መንፈሳዊ ምግብ ይዤ እሄድና ስመለስ የመስክ አገልግሎት ሪፖርታቸውን አመጣለሁ።

በሳን ፍራንሲስኮ ደ ማኮሪስ የሚገኙት ወንድሞች በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት በሳንትያጎ ሲታሰሩ ገንዘብና ከተቻለም መጽሐፍ ቅዱሶች እንድወስድላቸው እንዲሁም ያሉበትን ሁኔታ አጣርቼ ለቤተሰባቸው እንድነግር ተላክሁ። በሳንቲያጎ ወኅኒ ቤት ጠባቂዎቹ የቫዮሊን መያዣውን ሲያዩ “ይህ ደግሞ ምን ያደርጋል?” ሲሉ ጠየቁኝ። እኔም “ላዝናናቸው አስቤ ነው” በማለት መለስኩላቸው።

ለወንድሞች ከተጫወትኩላቸው መዝሙሮች መካከል በናዚ ማጎሪያ ካምፕ በእስር ላይ የነበረ አንድ ወንድም የጻፈው መዝሙር ይገኝበታል። ይህም በይሖዋ ምሥክሮች የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው 29ኛው መዝሙር ነው። ይህንን መዝሙር የተጫወትኩት በእስር ላይ የነበሩት ወንድሞቻችን መዝሙሩን እንዲማሩት ብዬ ነበር።

አብዛኞቹ ምሥክሮች የአገሪቱ መሪ ወደሆነው ወደ ትሩሂሎ የእርሻ ቦታ እንደተዛወሩ ሰማሁ። ቦታው አውቶቡስ ከሚያልፍበት መንገድ ብዙም እንደማይርቅ ተነገረኝ። ስለዚህ በምሳ ሰዓት አካባቢ ከአውቶቡስ ወረድኩና ምልክት መጠየቅ ጀመርኩ። የአንድ ትንሽ ሱቅ ባለቤት ቦታው የሚገኘው ከተራሮቹ ባሻገር መሆኑን ከነገረኝ በኋላ ለመያዣነት ቫዮሊኔን ትቼ ከሄድኩ ፈረሱን ሊሰጠኝና መንገዱን የሚያሳየኝ አንድ ትንሽ ልጅ አብሮኝ ሊልክ ተስማማ።

ከኮረብታው ባሻገር ወንዝ ስለነበር ሁለታችንም ፈረሱ ላይ ተቀምጠን ወንዙን ተሻገርን። እዚህ ቦታ በአረንጓዴና በሰማያዊ ቀለማት ያሸበረቀ ላባ ያላቸው በቀቀኖች ተመለከትን፤ ላባቸው ላይ የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍ እይታው በጣም ያምር ነበር! “ይሖዋ እንደዚህ ውብ አድርገህ ስለፈጠርካቸው አመሰግንሃለሁ” ስል ጸለይኩ። በመጨረሻም ከቀኑ አሥር ሰዓት ላይ እርሻ ቦታው ደረስን። ጠባቂ የነበረው ወታደር ወንድሞችን እንዳነጋግር እንዲሁም አንዲት ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ያመጣሁላቸውን ነገሮች በሙሉ እንድሰጣቸው በደግነት ፈቀደልኝ።

ስንመለስ መሽቶ ስለነበር እስክንደርስ ድረስ እየጸለይኩ ነበር። ሱቁ ጋር ስንደርስ በዝናብ በስብሰናል። የመጨረሻው አውቶቡስ አምልጦኝ ስለነበር የሱቁ ባለቤት በዚያ የሚያልፍ የጭነት መኪና እንዲያስቆምልኝ ጠየቅሁት። መኪናው ውስጥ ካሉት ሁለት ወንዶች ጋር አብሮ መሄዱ ያዋጣል? አንደኛው “ሶፊን ታውቂያታለሽ? እሷ እኮ የእህቴ አስጠኚ ነበረች” አለኝ። ይህ ይሖዋ ለጸሎቴ የሰጠው መልስ እንደሆነ ተሰማኝ። ሰዎቹ በሰላም ወደ ሳንቶ ዶሚንጎ አደረሱኝ።

በ1953 የይሖዋ ምሥክሮች በኒው ዮርክ ከተማ ያንኪ ስታዲየም ባደረጉት ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ ከሄዱት ልዑካን መካከል ነበርኩ። አባቴን ጨምሮ መላው ቤተሰባችን በስብሰባው ላይ ተገኝቶ ነበር። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በስብከቱ ሥራ ስለተገኘው እድገት ሪፖርት ከቀረበ በኋላ እኔና አብራኝ በሚስዮናዊነት የምታገለግለው ሜሪ አንዮል በእገዳ ሥር የስብከቱን ሥራ እንዴት እንደምናከናውን የሚያሳይ አጠር ያለ ሠርቶ ማሳያ አቀረብን።

ጉባኤዎችን መጎብኘት የሚያስገኘው ልዩ ደስታ

በዚያ ዓመት የበጋ ወራት ከሩዶልፍ ሱነል ጋር ተዋወቅን፤ ከዚያም በቀጣዩ ዓመት ተጋባን። የሩዶልፍ ቤተሰቦች የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአልጌኒ፣ ፔንስልቬኒያ ነበር። ሩዶልፍ በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተፈረደበትን እስራት ከጨረሰ በኋላ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ቤቴል ማገልገል ጀመረ። ከተጋባን ብዙም ሳንቆይ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ጉባኤዎችን እንዲጎበኝ ተመደበ። ከዚያ በኋላ ለ18 ዓመታት ያህል የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲያገለግል አብሬው ተጉዣለሁ።

በዚህ አገልግሎት በርካታ ቦታዎችን የጎበኘን ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፔንስልቬኒያ፣ ዌስት ቨርጂኒያ፣ ኒው ሃምፕሻየር እና ማሳቹሴትስ ይገኙበታል። አብዛኛውን ጊዜ የምናርፈው በክርስቲያን ወንድሞቻችን ቤት ነበር። ከወንድሞቻችን ጋር በቅርብ መተዋወቅና ከእነሱ ጋር ይሖዋን ማገልገል በጣም አስደሳች ነው። ፍቅራቸውና እንግዳ ተቀባይነታቸው ሁልጊዜም ሞቅ ያለና ከልብ የመነጨ ነበር። ጆኤል ቀድሞ በሚስዮናዊነት አብራኝ ታገለግል የነበረችውን ሜሪ አንዮልን ካገባ በኋላ በፔንስልቬኒያና በሚሽገን የሚገኙ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ለሦስት ዓመታት ያህል አገለገሉ። ከዚያም በ1958 ጆኤል ከሜሪ ጋር ሆኖ በቤቴል እንዲያገለግል እንደገና ተጋበዘ።

ካርል በቤቴል ለሰባት ዓመታት ያህል ካገለገለ በኋላ ተጨማሪ ልምድ እንዲያገኝ ሲባል ለጥቂት ወራት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ። ከዚያም የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆነ። በ1963 ቦቢን ያገባ ሲሆን ቦቢ በጥቅምት 2002 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በቤቴል በታማኝነት ስታገለግል ቆይታለች።

ዶን በቤቴል ባገለገለባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ የዞን የበላይ ተመልካች ሆኖ ወደተለያዩ አገሮች በመጓዝ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥና በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉ ወንድሞችን ጎብኝቷል። በዚህም ምክንያት ወደ ሩቅ ምሥራቅ፣ ወደ አፍሪካ፣ ወደ አውሮፓና ወደ ተለያዩ የአሜሪካ አገሮች ተጉዟል። ታማኝ የሆነችው ሚስቱ ዶሎሪስም አብዛኛውን ጊዜ አብራው ተጉዛለች።

አንዳንድ ለውጦች ለማድረግ ተገደድን

አባቴ ለረዥም ጊዜ ታምሞ ከቆየ በኋላ በሞት አንቀላፋ። ከመሞቱ በፊት ግን ይሖዋ አምላክን ለማገልገል በመምረጣችን በጣም ደስተኛ መሆኑን ነገሮኛል። እሱ እንዳሰበው ኮሌጅ ገብተን ቢሆን ኖሮ ብዙ በረከት ያመልጠን እንደነበር ተናግሯል። እማማ እህቴ ጆይ ወደምትኖርበት አካባቢ እንድትዛወር ከረዳኋት በኋላ የባለቤቴ እናት በወቅቱ የእኛ እርዳታ ያስፈልጋቸው ስለነበር አጠገባቸው መሆን እንድንችል እኔና ባለቤቴ በኒው ኢንግላንድ በአቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። የባለቤቴ እናት ከሞቱ በኋላ እማማ ለ13 ዓመታት ያህል ከእኛ ጋር ኖራለች። ከዚያም ጥር 18, 1987 በ93 ዓመቷ ምድራዊ ሕይወቷን አጠናቀቀች።

እማማ ሁሉም ልጆችዋ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረግ በመቻልዋ ጓደኞቿ ሲያደንቋት “እንዲህ ያለ ጥሩ ውጤት ሊገኝ የቻለው ‘መልካም መሬት’ ሆነው ስለተገኙ ነው” በማለት በትሕትና ትመልስ ነበር። (ማቴዎስ 13:23) ቅንዓትና ትሕትና በማሳየት ረገድ መልካም ምሳሌ የሚሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች በማግኘታችን በጣም ተባርከናል!

አሁንም ቢሆን መንግሥቱን ማስቀደም

አሁንም ቢሆን የአምላክን መንግሥት በሕይወታችን ውስጥ ማስቀደማችንን የቀጠልን ሲሆን ኢየሱስ ለጋሶች እንድንሆን የሰጠውን ምክርም ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን። (ሉቃስ 6:38፤ 14:12-14) በምላሹም ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሁሉ አብዝቶ ሰጥቶናል። የተረጋጋና አስደሳች ሕይወት አሳልፈናል።

ሩዶልፍና እኔ ለሙዚቃ ያለን ፍቅር አሁንም አልጠፋም። እንደኛው ሙዚቃ የሚወዱ ጓደኞቻችን ወደ ቤታችን ሲመጡ አብረን በሙዚቃ መሣሪያችን እየተጫወትን ማምሸት ያስደስተናል። ሆኖም ሙዚቃ በሕይወት ውስጥ ደስታ የሚጨምር ትርፍ ነገር እንጂ ዋናው ሥራዬ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ እኔና ባለቤቴ የአቅኚነት አገልግሎታችን ያስገኛቸውን ፍሬዎች ማለትም ባለፉት ዓመታት የረዳናቸውን ሰዎች መመልከት ችለናል።

በአሁኑ ወቅት የጤና እክሎች ቢኖሩብንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍናቸው ከ60 የሚበልጡ ዓመታት አስደሳችና የተረጋጋ ሕይወት አሳልፈናል ማለት እችላለሁ። ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ከበርካታ ዓመታት በፊት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስጀምር ላቀረብኩት ልመና መልስ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ፤ እንዲሁም ‘በዛሬው ዕለት መንግሥቱን ለማስቀደም ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብዬ አስባለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤተሰባችን በ1948 (ከግራ ወደ ቀኝ):- ጆይ፣ ዶን፣ እማማ፣ ጆኤል፣ ካርል፣ እኔ፣ አባባ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እማማ በአገልግሎቱ ቀናተኛ በመሆን ምሳሌ ትታልናለች

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ 50 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ካርል፣ ዶን፣ ጆኤል፣ ጆይ እና እኔ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከግራ ወደ ቀኝ:- እኔ፣ ሜሪ አንዮል፣ ሶፍያ ሶቪየክ እና ኢደዝ ሞርጋን በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ሚስዮናውያን ሆነን ስናገለግል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 በያንኪ ስታዲየም ከሜሪ (በግራ በኩል) ጋር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ጋር በወረዳ ሥራ ላይ በነበረበት ወቅት