በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሃይማኖታቸው ምክንያት ስደት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

በሃይማኖታቸው ምክንያት ስደት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

በሃይማኖታቸው ምክንያት ስደት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

ሰዎች በሃይማኖታቸው ምክንያት ሊሰደዱ እንደሚገባ ይሰማሃል? ምናልባት የሌሎችን መብት እስካልተጋፉ ድረስ ሊሰደዱ አይገባም ትል ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖታቸው ምክንያት ይሰደዱ የነበረ ሲሆን ይህ ሁኔታ ዛሬም ቀጥሏል። ለምሳሌ ያህል፣ በአውሮፓና በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ሌሎች አገሮች የሚኖሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በ20ኛው መቶ ዘመን በተደጋጋሚ ጊዜያት መብታቸው ተረግጦ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተሠቃይተዋል።

በእነዚያ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በአውሮፓ በነበሩት በሁለት ዋና ዋና አምባገነናዊ አገዛዞች ሥር ጭካኔ የተሞላበት፣ የታሰበበትና ረዘም ላሉ ዓመታት የዘለቀ ስደት ደርሶባቸዋል። በሃይማኖት ምክንያት የሚሰነዘር ስደትን በተመለከተ ከእነርሱ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን? ለደረሰባቸው መከራ ከሰጡት ምላሽ ምን ልንማር እንችላለን?

“ከዓለም አይደሉም”

የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ አክባሪዎች፣ ሰላማውያንና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ለመሆን ይጥራሉ። መንግሥታትን አይቃወሙም ወይም ግጭት ለማስነሳት አይፈልጉም፤ ሰማዕት ለመሆን ብለውም በራሳቸው ላይ ስደት አይቆሰቁሱም። እነዚህ ክርስቲያኖች “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ [ተከታዮቼም] ከዓለም አይደሉም” ከሚሉት የኢየሱስ ቃላት ጋር በሚስማማ መልኩ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ ናቸው። (ዮሐንስ 17:16) አብዛኞቹ መንግሥታት የይሖዋ ምሥክሮችን የገለልተኝነት አቋም አይቃወሙም። አምባገነናዊ መሪዎች ግን ክርስቲያኖች የዓለም ክፍል መሆን እንደሌለባቸው የሚናገረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ መቀበል አይፈልጉም።

ለዚህ ምክንያቱ በኅዳር 2000 ጀርመን በሚገኘው ሂድልበርግ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ስብሰባ ላይ ተገልጿል። የስብሰባው ጭብጥ:- “የይሖዋ ምሥክሮች በብሔራዊ ሶሻሊዝምና በኮሚኒዝም አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር የደረሰባቸው ጭቆናና ለመብታቸው ያደረጉት ትግል” የሚል ነበር። በአምባገነናዊነት ላይ ጥናት የሚያደርገው ሃና አረንት ተብሎ የሚጠራው ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ክሌመንስ ፎልንሃልስ እንዲህ ብለዋል:- “አምባገነናዊ መንግሥታት ሥልጣናቸውን የሚጠቀሙበት ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ራሱን ሙሉ በሙሉ እንዲያስገዛላቸው ይፈልጋሉ።”

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለይሖዋ አምላክ ብቻ ሙሉ በሙሉ ለመገዛት ቃል ስለገቡ ለሰብዓዊ መንግሥታት በዚህ መንገድ መገዛት አይችሉም። አምባገነናዊ አገዛዝ በሰፈነባቸው አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ ጊዜ መንግሥት የሚጠብቅባቸው ነገር ከእምነታቸው ጋር ይጋጫል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜ ምን እርምጃ ወስደዋል? ታሪክ እንደሚመሠክረው የይሖዋ ምሥክሮች “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አቋም ተከትለዋል።​—⁠ሥራ 5:29

በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጭካኔ የተሞላበት ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም በእምነታቸው በመጽናት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ ሆነዋል። ሊጸኑ የቻሉት እንዴት ነው? እንደዚህ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ብርታት ያገኙትስ እንዴት ነው? እስኪ ራሳቸው ሲናገሩ እንስማ። የይሖዋ ምሥክሮች ሆንም አልሆን እያንዳንዳችን ከእነሱ ተሞክሮ ምን ልንማር እንደምንችልም እንመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ምሥክሮች በ20ኛው መቶ ዘመን ጀርመን ውስጥ በሁለት አምባገነናዊ አገዛዞች ሥር ረዘም ላሉ ዓመታት ጭካኔ የተሞላበት ስደት ደርሶባቸዋል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አምባገነናዊ መንግሥታት ሥልጣናቸውን የሚጠቀሙበት ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ሙሉ በሙሉ እንዲገዛላቸው ይፈልጋሉ።”-ዶክተር ክሌመንስ ፎልንሃልስ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኩሰሮ ቤተሰብ እምነታቸውን ለማላላት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ምክንያት ነፃነታቸውን ተነፍገዋል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሐንስ ሃርምዝ በእምነቱ ምክንያት በናዚ ወኅኒ ቤት ተገድሏል