በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍጹም ልባችሁ በይሖዋ ታመኑ

በፍጹም ልባችሁ በይሖዋ ታመኑ

በፍጹም ልባችሁ በይሖዋ ታመኑ

“ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ።”​መዝሙር 9:​10

1, 2. ሰዎች መተማመኛ እንዲሆኗቸው በከንቱ ተስፋ የሚጥሉባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

 ደህንነታችንን ሥጋት ላይ የሚጥሉ ብዙ ነገሮች ባሉበት በዛሬው ጊዜ መተማመኛ ሊሆን ወደሚችል አንድ ነገር ወይም አካል ዞር ማለት የተለመደ ነው። አንዳንዶች ገንዘብ ለመጪው ጊዜ መተማመኛ የሚሆናቸው ይመስላቸዋል፤ ሐቁ ግን ገንዘብ አስተማማኝ ያልሆነ መጠጊያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል” ይላል። (ምሳሌ 11:​28) ሌሎች ደግሞ ተስፋቸውን የሚጥሉት በሰብዓዊ መሪዎች ላይ ቢሆንም ከሁሉ የተሻሉ ናቸው የሚባሉት እንኳን ሳይቀሩ ይሳሳታሉ፣ በመጨረሻም ይሞታሉ። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” ብሎ መናገሩ ትክክል ነው። (መዝሙር 146:​3) እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት በራሳችን ጥረት ላይም እንኳ መመካት እንደማይገባን ያስጠነቅቁናል። እኛም ብንሆን ‘የሰው ልጆች’ ነን።

2 ነቢዩ ኢሳይያስ በዘመኑ የነበሩት የእስራኤል መሪዎች ‘ሐሰትን መሸሸጊያ’ በማድረጋቸው ነቅፏቸዋል። (ኢሳይያስ 28:​15-17) መተማመኛ በመሻት ከአጎራባች ብሔራት ጋር ፖለቲካዊ ስምምነት ፈጥረው ነበር። እንደዚህ ያሉት ስምምነቶች እምነት የማይጣልባቸውና ሐሰት ነበሩ። ዛሬም በተመሳሳይ ብዙ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከፖለቲካ መሪዎች ጋር ዝምድና ይመሠርታሉ። እነዚህ ስምምነቶችም ቢሆኑ ‘ሐሰት’ መሆናቸው አይቀርም። (ራእይ 17:​16, 17) ዘላቂ የሆነ ዋስትና የላቸውም።

ኢያሱና ካሌብ የተዉት ጥሩ ምሳሌ

3, 4. ኢያሱና ካሌብ የተናገሩት ነገር ከሌሎቹ አሥር ሰላዮች የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

3 ታዲያ መተማመኛ መሻት ያለብን ከየት ነው? በሙሴ ዘመን ኢያሱና ካሌብ መተማመኛ ካገኙበት ምንጭ ነው። እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተስፋ ወደተገባላቸው ወደ ከነዓን ምድር ለመግባት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ምድሪቱን እንዲሰልሉ አሥራ ሁለት ሰዎች ተላኩና ከአርባ ቀን በኋላ ተመልሰው መጡ። ከሰላዮቹ ውስጥ እስራኤላውያን ከነዓን ገብተው ስለሚያጋጥማቸው ነገር ጥሩ ዘገባ ያቀረቡት ሁለቱ ብቻ ማለትም ኢያሱና ካሌብ ነበሩ። የቀሩት አሥሩ ሰላዮች ምድሪቱ ለምና ያማረች መሆኗን ባይክዱም “በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው፣ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ፣ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ . . . በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም” ብለው ተናገሩ።​—⁠ዘኍልቍ 13:​27, 28, 31

4 እስራኤላውያን አሥሩ ሰላዮች የተናገሩትን ሲሰሙ ፍርሃት አደረባቸውና በሙሴ ላይ እስከ ማጉረምረም ደረሱ። በመጨረሻም ኢያሱና ካሌብ በልበ ሙሉነት “ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ” ብለው ተናገሩ። (ዘኍልቍ 14:​6-9) ከዚህ በኋላም ቢሆን እስራኤላውያን የተሰጣቸውን ማበረታቻ ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ተስፋ ወደተገባላቸው ምድር እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም።

5. ኢያሱና ካሌብ ጥሩ ዜና ያቀረቡት ለምን ነበር?

5 ኢያሱና ካሌብ ዞረው ስላዩአት ምድር ጥሩ ዜና ሲያቀርቡ የቀሩት አሥሩ ግን መጥፎ ዜና ያቀረቡት ለምን ነበር? እነዚያን ጠንካራና የተመሸጉ ቅጥሮች ያሏቸውን ሕዝቦች የተመለከቱት አሥራ ሁለቱም ሰላዮች ናቸው። መጥፎ ዜና ያቀረቡት አሥሩ ሰዎች እስራኤላውያን እነዚያን ሕዝቦች አስለቅቀው ምድሪቱን መውረስ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሌላቸው የተናገሩት ትክክል ነበር። ኢያሱና ካሌብም ቢሆኑ ይህን ያውቃሉ። ይሁን እንጂ አሥሩ ሰላዮች ነገሮችን ያዩት በሰብዓዊ አመለካከት ነበር። በአንጻሩ ግን ኢያሱና ካሌብ በይሖዋ ታምነው ነበር። ይሖዋ በግብፅ ምድር፣ በቀይ ባሕርና በሲና ተራራ ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች ተመልክተዋል። ከአርባ ዓመት በኋላ የኢያሪኮዋ ረዓብ ስለ እነዚህ ድንቅ ሥራዎች የሰማቻቸው ወሬዎች ለይሖዋ ሕዝቦች ስትል ሕይወቷን አደጋ ላይ እንድትጥል አነሳስቷት ነበር። (ኢያሱ 2:​1–24፤ 6:​22-25) የይሖዋን ሥራዎች በዓይናቸው የተመለከቱት ኢያሱና ካሌብ ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል መዋጋቱን እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት ነበራቸው። ከአርባ ዓመት በኋላ አዲስ የእስራኤላውያን ትውልድ በኢያሱ መሪነት ወደ ከነዓን ዘምቶ ምድሪቱን ሲወርስ የኢያሱና የካሌብ እምነት ትክክል መሆኑ ተረጋግጧል።

በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

6. ዛሬ ክርስቲያኖች ከተለያየ አቅጣጫ ተጽዕኖ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? በማን መታመንስ ይኖርባቸዋል?

6 በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” እኛም እንደ እስራኤላውያን ከእኛ ከሚበልጡ ብርቱ ጠላቶች ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) በሥነ ምግባር፣ በመንፈሳዊና እንዲያውም አንዳንዴ በአካልም ጭምር ከፍተኛ ተጽዕኖ ይደርስብናል። የእነዚህ ግፊቶች ምንጭ ከሰው በላይ ኃይል ያለው ሰይጣን ዲያብሎስ ስለሆነ በራሳችን ብርታት ብቻ እነዚህን ግፊቶች መቋቋም አንችልም። (ኤፌሶን 6:​12፤ 1 ዮሐንስ 5:​19) ታዲያ እርዳታ ለማግኘት ፊታችንን ወዴት ማዞር እንችላለን? አንድ የጥንት የእምነት ሰው ለይሖዋ ሲጸልይ “ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ” ብሏል። (መዝሙር 9:​10) በእርግጥም ይሖዋን የምናውቅና ስሙ የቆመለትን ትርጉም የምንገነዘብ ከሆነ ልክ እንደ ኢያሱና ካሌብ እኛም ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንታመናለን።​—⁠ዮሐንስ 17:​3

7, 8. (ሀ) ፍጥረት በአምላክ እንድንታመን የሚያደርገን እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ለመታመን የሚያበቁ ምን ምክንያቶችን ያቀርብልናል?

7 በይሖዋ መታመን ያለብን ለምንድን ነው? ኢያሱና ካሌብ በይሖዋ የታመኑበት ከፊል ምክንያት የኃይሉን መግለጫዎች ስላዩ ነው። እኛም አይተናል። ለምሳሌ ያህል በቢልዮን የሚቆጠሩ የከዋክብት ረጨቶችን ያቀፈውን ጠፈር ጨምሮ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ተመልከት። ይሖዋ የሚቆጣጠራቸው ግዙፍ የተፈጥሮ ኃይሎች እሱ በእርግጥም ሁሉን የሚችል አምላክ መሆኑን ያሳያሉ። ድንቅ በሆኑት የፍጥረት ሥራዎች ላይ ስናሰላስል “[እሱን] የሚከለክለው ማን ነው? እርሱንስ:- ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?” ሲል ይሖዋን አስመልክቶ እንደተናገረው እንደ ኢዮብ ለማለት እንገደዳለን። (ኢዮብ 9:​12) በእርግጥም ይሖዋ ከእኛ ጋር ከሆነ በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ማንንም መፍራት አያስፈልገንም።​—⁠ሮሜ 8:​31

8 የይሖዋ ቃል ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስም አስብ። ይህ የማያልቅበት የመለኮታዊ ጥበብ ምንጭ መጥፎ ልማዶችን እንድናሸንፍና ሕይወታችንን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር እንድናስማማ የመርዳት ኃይል አለው። (ዕብራውያን 4:​12) የይሖዋን ስምና የስሙን ትርጉም ልናውቅ የቻልነው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (ዘጸአት 3:​14) ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም የፈለገውን ማለትም አፍቃሪ አባት፣ ጻድቅ ፈራጅ፣ ድል አድራጊ ተዋጊ መሆን እንደሚችል እንገነዘባለን። ደግሞም ቃሉ ሁልጊዜ እንዴት በትክክል እንደሚፈጸም እንመለከታለን። የአምላክን ቃል ስናጠና እንደ መዝሙራዊው “በቃልህ ታምኛለሁ” ብለን ለመናገር እንገፋፋለን።​—⁠መዝሙር 119:​42፤ ኢሳይያስ 40:​8

9. ቤዛውና የኢየሱስ ትንሣኤ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩልን እንዴት ነው?

9 በይሖዋ እንድንታመን የሚያበቃን ሌላው ምክንያት ደግሞ ቤዛው ነው። (ማቴዎስ 20:​28) ለእኛ ቤዛ ሆኖ እንዲሞት አምላክ የገዛ ልጁን መላኩ እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው! በእርግጥም ቤዛው ጉልህ ጥቅም አለው። ንስሐ ገብተው በቅን ልብ ወደ ይሖዋ የሚመለሱ የሰው ልጆችን ኃጢአት ያስተሰርያል። (ዮሐንስ 3:​16፤ ዕብራውያን 6:​10፤ 1 ዮሐንስ 4:​16, 19) ቤዛው እንዲከፈል ካስፈለገ ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘት ነበረበት። በብዙ ምሥክሮች የተረጋገጠው ይህ የትንሣኤ ተአምር በይሖዋ ለመታመን የሚያስችል ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ነው። ተስፋችን ሳይፈጸም እንደማይቀር ዋስትና የሚሰጥ ነው።​—⁠ሥራ 17:​31፤ ሮሜ 5:​5፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​3-8

10. በይሖዋ ለመታመን የሚያበቁ ምን የግል ምክንያቶች አሉን?

10 ከላይ የተጠቀሱት በይሖዋ መታመን የምንችለው ለምን እንደሆነና ለምንስ በእርሱ መታመን እንዳለብን ከሚያሳዩት ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም ያሉ ሲሆን ከእነዚህም አንዳንዶቹ ከግል ሕይወታችን ጋር የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ሁላችንም በኑሯችን አልፎ አልፎ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሙናል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የይሖዋን አመራር በምንሻበት ጊዜ አመራሩ ምን ያህል ተግባራዊ እንደሆነ እናያለን። (ያዕቆብ 1:​5-8) በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በይሖዋ ላይ በታመንን መጠንና ይህም የሚያስገኘውን ጥሩ ውጤት በተመለከትን ቁጥር በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይበልጥ ይጠናከራል።

ዳዊት በይሖዋ ታምኗል

11. ዳዊት በይሖዋ የታመነው በምን ሁኔታ ውስጥ እያለ ነው?

11 በጥንቷ እስራኤል የነበረው ዳዊት በይሖዋ የሚታመን ሰው ነበር። ዳዊት ሊገድለው ይፈልግ ከነበረው ከንጉሥ ሳኦልና እስራኤልን ለማስገበር ይፈልጉ ከነበሩት ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ማስፈራሪያ ደርሶበት ነበር። ሆኖም ከዚህ ሁሉ የተረፈ ከመሆኑም በላይ ድል አድርጓል። ለምን? ዳዊት ራሱ ምክንያቱን ሲያስረዳ “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?” ብሏል። (መዝሙር 27:​1) እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ ከታመንን ድል ማድረግ እንችላለን።

12, 13. ጠላቶች በቃላት በሚወጉን ጊዜም ቢሆን በይሖዋ መታመን እንደሚኖርብን ዳዊት ያሳየው እንዴት ነው?

12 በአንድ ወቅት ዳዊት “አምላክ ሆይ፤ የብሶት ቃሌን ስማ፤ ሕይወቴንም ከሚያስፈራ የጠላት ዛቻ ከልላት። ከክፉዎች አድማ ሰውረኝ፤ ከዓመፀኞችም ሸንጎ ጋርደኝ። እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤ መርዘኛ ቃላቸውንም እንደ ፍላጻ ያነጣጥራሉ። አሸምቀው ንጹሑን ሰው ይነድፉታል” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 64:​1-4 አ.መ.ት ) ዳዊት እነዚህን ቃላት እንዲጽፍ የገፋፋው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት አናውቅም። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜም እንደ ጥንቶቹ ተቃዋሚዎች ቃላትን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም ‘ምላሳቸውን የሚስሉ’ እንዳሉ እናውቃለን። እንከን የሌላቸው ክርስቲያኖችን ስም ለማጥፋት ቃላትንና ጽሑፍን እንደ “ፍላጻ ያነጣጥራሉ።” በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ የምንታመን ከሆነ ውጤቱ ምን ይሆናል?

13 ዳዊት በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤ እነርሱም ድንገት ይቆስላሉ። በገዛ ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል፤ . . . ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይበለው፤ እርሱንም መጠጊያ ያድርገው።” (መዝሙር 64:​7-10 አ.መ.ት ) አዎን፣ ጠላቶች በእኛ ላይ ምላሳቸውን ቢስሉም በፍጻሜው ግን የገዛ ‘ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል።’ የታመኑበት ሰዎች በእሱ መደሰት ይችሉ ዘንድ ይሖዋ ውሎ አድሮ ነገሮች ለበጎ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ሕዝቅያስ በይሖዋ በመታመኑ ተክሷል

14. (ሀ) ሕዝቅያስ በይሖዋ የታመነው በምን አደገኛ ሁኔታ ላይ እያለ ነው? (ለ) ሕዝቅያስ የአሦራውያንን ውሸት እንዳላመነ ያሳየው እንዴት ነበር?

14 በይሖዋ በመታመኑ የተካሰው ሌላው ሰው ንጉሥ ሕዝቅያስ ነው። በሕዝቅያስ የግዛት ዘመን ኃያሉ የአሦር ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ስጋት ላይ ጥሏት ነበር። ያ ሠራዊት ብዙ መንግሥታትን ድል አድርጓል። ኢየሩሳሌም ብቻ ስትቀረው ሌሎች የይሁዳ ከተሞችን ሁሉ ተቆጣጥሮ ስለነበር ሰናክሬም ኢየሩሳሌምንም ቢሆን ከእጁ ሊያስጥላት የሚችል ኃይል እንደማይኖር ፎክሮ ነበር። እርዳታ ለማግኘት በግብፅ መታመን ከንቱ መሆኑን (ደግሞም ትክክል ነው) በራፋስቂስ በኩል ተናገረ። ይሁን እንጂ ቀጥሎ “ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ” በማለት ተናገረ። (ኢሳይያስ 37:​10) የሆነ ሆኖ ሕዝቅያስ ይሖዋ እንደማያታልለው ያውቅ ነበር። በመሆኑም “አምላካችን አቤቱ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን” በማለት ጸለየ። (ኢሳይያስ 37:​20) ይሖዋም የሕዝቅያስን ጸሎት ሰማ። አንድ መልአክ በአንድ ሌሊት 185, 000 የአሦር ወታደሮችን ገደለ። ኢየሩሳሌም ከጥፋት ዳነች፤ ሰናክሬምም የይሁዳን ምድር ለቅቆ ሄደ። ይህን ታሪክ የሰሙ ሁሉ ይሖዋ ታላቅ አምላክ መሆኑን አውቀዋል።

15. በዚህ አስተማማኝ ባልሆነ ዓለም ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሙን ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ የሚረዳን ምን ብቻ ነው?

15 ዛሬም እኛ እንደ ሕዝቅያስ በጦርነት ላይ እንገኛለን። እኛ የምናደርገው ውጊያ ግን መንፈሳዊ ነው። ይሁንና መንፈሳዊ ዘማቾች እንደመሆናችን በመንፈሳዊ ሕያው ሆነን መቀጠል የምንችልበትን ሕይወት አድን ስልቶች ማጎልበት ይኖርብናል። ሊሰነዘሩብን የሚችሉትን ጥቃቶች ከወዲሁ በማየት ለመመከት መዘጋጀት ይገባናል። (ኤፌሶን 6:​11, 12, 17) በዚህ አስተማማኝ ባልሆነ ዓለም ሁኔታዎች በድንገት ሊለወጡ ይችላሉ። ድንገት ሳይታሰብ ሕዝባዊ ረብሻ ሊነሳ ይችላል። ሃይማኖታዊ መቻቻል ሰፍኖባቸው የነበሩ አገሮች ይህን አቋማቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ። ሊገጥሙን የሚችሉትን ነገሮች በተሳካ ሁኔታ መወጣት የምንችለው እንደ ሕዝቅያስ በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት በማጎልበት ራሳችንን ካዘጋጀን ብቻ ነው።

በይሖዋ መታመን ሲባል ምን ማለት ነው?

16, 17. በይሖዋ እንደምንታመን እንዴት እናሳያለን?

16 በይሖዋ መታመን ማለት በአፍ ከመናገር የሚበልጥ ነገር ማድረግን የሚጠይቅ ነው። ልባችንንም የሚጨምር ሲሆን በተግባራችን የሚገለጽ ባሕርይ ነው። በይሖዋ የምንታመን ከሆነ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስም ሙሉ በሙሉ እንታመናለን። በየዕለቱ እናነበዋለን፣ በእርሱ ላይ እናሰላስላለን እንዲሁም ሕይወታችንን እንዲመራልን እንፈቅድለታለን። (መዝሙር 119:​105) በይሖዋ መታመን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ መታመንንም ይጨምራል። በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ይሖዋን የሚያስደስት ፍሬ ልናፈራና ሥር የሰደዱ መጥፎ ልማዶችንም ልናሸንፍ እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 6:​11፤ ገላትያ 5:​22-24) በመሆኑም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ብዙ ሰዎች ሲጋራ ማጨስ ወይም አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ሊያቆሙ ችለዋል። ሌሎች ደግሞ ሥነ ምግባር ከጎደለው አኗኗር ተላቅቀዋል። አዎን፣ በይሖዋ ከታመንን በራሳችን ሳይሆን ይሖዋ በሚሰጠን ብርታት ለተግባር እንንቀሳቀሳለን።​—⁠ኤፌሶን 3:​14-18

17 በተጨማሪም በይሖዋ መታመን ማለት እሱ በሚታመንባቸው ሰዎችም መታመን ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ በምድር ያለውን የመንግሥቱን ፍላጎት እንዲያሟላ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ አዘጋጅቷል። (ማቴዎስ 24:​45-47) በይሖዋ ዝግጅቶች የምንታመን በመሆናችን ከዚህ ታማኝ ባሪያ ተነጥለንና ሹመቱን ችላ ብለን በራሳችን ሐሳብ ለመመራት አንሞክርም። ከዚህም ሌላ ሽማግሌዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን እነሱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው። (ሥራ 20:​28) በጉባኤ ውስጥ ካለው የሽማግሌዎች ዝግጅት ጋር በመተባበር በይሖዋ እንደምንታመን ልናሳይ እንችላለን።​—⁠ዕብራውያን 13:​17

የጳውሎስን ምሳሌ ተከተሉ

18. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የጳውሎስን አርአያ የሚከተሉት እንዴት ነው? ይሁን እንጂ በምን አይታመኑም?

18 ሐዋርያው ጳውሎስ እኛን እንደሚያጋጥመን ሁሉ በአገልግሎቱ ብዙ ተጽዕኖ ደርሶበታል። በእርሱ ዘመን ክርስትና በባለ ሥልጣናት ዘንድ መጥፎ ስም ይሰጠው ስለነበር አንዳንድ ጊዜ እነዚያን የተሳሳቱ አስተያየቶች ለማረም ወይም የስብከቱን ሥራ በሕግ ለማስከበር ይጥር ነበር። (ሥራ 28:​19–22፤ ፊልጵስዩስ 1:​7) በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች የእርሱን ምሳሌ ይከተላሉ። የተገኘውን ዘዴና አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም በተቻለን መጠን ሌሎች ስለ ሥራችን ትክክለኛ እውቀት እንዲኖራቸው እንረዳቸዋለን። እኛም ለምሥራቹ ጥብቅና በመቆም በሕግ ለማስከበር ተግተን እንሠራለን። ይሁን እንጂ ስኬታችን የሚለካው በፍርድ ቤት ሙግቶች በመርታት ወይም በሕዝብ ዘንድ ጥሩ ስም በማግኘታችን እንዳልሆነ ስለምናምን በእነዚህ ጥረቶች ሙሉ በሙሉ አንታመንም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ እንታመናለን። ይሖዋ ለጥንቱ እስራኤል “በፀጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል” በማለት የሰጠውን ማበረታቻ እናስታውሳለን።​—⁠ኢሳይያስ 30:​15

19. ወንድሞቻችን ሲሰደዱ በይሖዋ ላይ እንደሚታመኑ ያስመሰከሩት እንዴት ነው?

19 በዘመናዊው ታሪካችን በምሥራቅና በምዕራብ አውሮፓ፣ በአንዳንድ የእስያና የአፍሪካ ክፍሎች እንዲሁም በደቡብና በሰሜን አሜሪካ አገሮች ሥራችን የታገደባቸው ወቅቶች ነበሩ። ታዲያ ይህ በይሖዋ መታመናችን ከንቱ መሆኑን የሚያሳይ ነው? በፍጹም። ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ተገቢ ነው ብሎ ባመነበት ምክንያት መራራ ስደት እንዲደርስ ቢፈቅድም የስደቱ ገፈት ቀማሽ የሆኑትን ክርስቲያኖች በፍቅር አበረታቷቸዋል። በስደቱ ወቅት ብዙ ክርስቲያኖች በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸውና በእርሱ እንደሚታመኑ የሚያሳይ አስደናቂ ታሪክ አስመዝግበዋል።

20. በሕግ ካገኘነው ነፃነት ተጠቃሚዎች ብንሆንም በምን ረገድ አቋማችንን ፈጽሞ አናላላም?

20 በሌላ በኩል ደግሞ በብዙ አገሮች ሕጋዊ እውቅና ያለን ሲሆን አንዳንድ ጊዜም በመገናኛ ብዙኃን ስለ እኛ ጥሩ አስተያየት ይሰነዘራል። ለዚህም አመስጋኞች ስንሆን ይህም ቢሆን የይሖዋን ዓላማዎች ለማሳወቅ ይረዳል። እሱ በሚሰጠን በረከትም የተገኘውን ታላቅ ነጻነት የግል ኑሯችንን ለማሻሻል ሳይሆን ይሖዋን በይፋና በተሟላ መልኩ ለማገልገል እንጠቀምበታለን። ይሁን እንጂ በባለ ሥልጣናት ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ ብለን የገለልተኝነት አቋማችንን አናላላም፣ የስብከት እንቅስቃሴአችንን አንቀንስም ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት አናቀዘቅዝም። የመሲሐዊው መንግሥት ዜጎች ስለሆንን ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጎን ጸንተን እንቆማለን። ተስፋችን በዚህ ሥርዓት ላይ ሳይሆን ሰማያዊው መሲሐዊ መንግሥት ብቸኛው የምድር ገዢ በሚሆንበት አዲስ ዓለም ላይ ነው። ፈንጂዎች፣ ሚሳይሎች፣ ወይም የኑክሌር ጥቃቶች ተስፋ የምናደርገውን መንግሥት ሊያናውጡት ወይም ከሰማይ ሊያወርዱት አይችሉም። መሲሐዊው መንግሥት ሊሸነፍ የማይችልና የይሖዋን ዓላማዎች ዳር የሚያደርስ ነው።​—⁠ዳንኤል 2:​44፤ ዕብራውያን 12:​28፤ ራእይ 6:​2

21. ምን ዓይነት አካሄድ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል?

21 ጳውሎስ “እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ብሏል። (ዕብራውያን 10:​39) እንግዲያስ ሁላችንም ይሖዋን እስከ ፍጻሜው በታማኝነት እናገልግል። አሁንም ሆነ ለዘላለሙ በይሖዋ እንድንታመን የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉን።​—⁠መዝሙር 37:​3፤ 125:​1

ምን ተምረናል?

• ኢያሱና ካሌብ ጥሩ ዜና ይዘው የመጡት ለምን ነበር?

• በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

• በይሖዋ መታመን ማለት ምን ማለት ነው?

• በይሖዋ መታመንን በተመለከተ ምን ዓይነት አቋም ለመያዝ ቆርጠናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢያሱና ካሌብ ጥሩ ዜና ያቀረቡት ለምንድን ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍጥረት በይሖዋ ለመታመን የሚያበቃ ጠንካራ ምክንያት ይሰጠናል

[ምንጭ]

የሦስቱም ፎቶዎች ምንጭ:- Courtesy of Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ መታመን ማለት እሱ በሚታመንባቸው ሰዎች መታመንንም ይጨምራል