በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዩክሬን የተገኘ ግሩም የእምነት ምሳሌ

ከዩክሬን የተገኘ ግሩም የእምነት ምሳሌ

ከዩክሬን የተገኘ ግሩም የእምነት ምሳሌ

አንዳንድ ጊዜ ለወራት፣ ለዓመታት፣ ብሎም ለአሥርተ ዓመታት የሚዘልቁ የእምነት ፈተናዎች ያጋጥማሉ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ዩሪ ኮፖስ የተወለደውና ያደገው ኩስት በተባለችው የተዋበች የትራንስካርፓቲያ ከተማ አቅራቢያ ነው። በ1938 በ25 ዓመት ዕድሜው የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በ1940 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚን አገዛዝ ከሚደግፍ አንድ የሃንጋሪ ሠራዊት ጋር ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የስምንት ወር እስራት ተፈረደበት። በወቅቱ የነበረው የትራንስካርፓቲያ ሕግ ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ነገር አናደርግም በማለታቸው የታሰሩ እስረኞችን በሞት መቅጣት ስለማይፈቅድ ወንድሞች ይህ ዓይነቱን ቅጣት የሚፈቅደው የናዚ ሕግ ተግባራዊ ወደሚሆንበት ጦር ግንባር ይላኩ ነበር። በ1942 ወንድም ኮፖስንና 21 ምሥክሮችን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች በወታደሮች ታጅበው በሩሲያ፣ በስታሊንግራድ አቅራቢያ ወደሚገኘው የጦር ግንባር ተላኩ። ወደዚያ የተላኩት እንዲገደሉ ነበር። ይሁን እንጂ እዚያ ከደረሱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሶቪዬት ሠራዊት ማጥቃት ጀመረና የጀርመን ወታደሮችንና ወንድሞችን ማረኳቸው። ምሥክሮቹ ወደ ሶቪዬት ወኅኒ ቤት የተላኩ ሲሆን በ1946 ከእስር እስከተለቀቁበት ጊዜ ድረስ በዚያው ቆዩ።

ወንድም ኮፖስ ነጻ ሲለቀቅ ወደ ቀዬው ተመልሶ በአካባቢው ምሥራቹን በቅንዓት መስበክ ጀመረ። በዚህ ምክንያት በ1950 የሶቪዬት ባለ ሥልጣናት የ25 ዓመት እስራት ፈረዱበት። ይሁን እንጂ ከስድስት ዓመታት በኋላ ምሕረት ተደርጎለት ተፈታ።

በዚህ ወቅት እድሜው 44 ዓመት የሆነው ወንድም ኮፖስ ከሃና ሺሽኮ ጋር ለመጋባት አቀደ። እርስዋም የይሖዋ ምሥክር ስትሆን ለአሥር ዓመታት ታስራ ከቆየች በኋላ ገና መፈታቷ ነበር። ጋብቻቸውን ለማስመዝገብ ማመልከቻ አስገቡ። በሠርጋቸው ዕለት ዋዜማ ሁለቱም እንደገና ተያዙና የአሥር ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ መከራዎች በጽናት ተወጡ፤ እንዲሁም ሠርጋቸው ለአሥር ዓመት ቢዘገይም በመካከላቸው የነበረው ፍቅር ግን አልቀዘቀዘም። (1 ቆሮንቶስ 13:7) በመጨረሻ በ1967 ከእስር ከተፈቱ በኋላ ተጋቡ።

ታሪካቸው ግን በዚህ አያበቃም። በ1973 ወንድም ኮፖስ በ60 ዓመት እድሜው በድጋሚ ታሰረና አምስት ዓመት በወኅኒ አምስት ዓመት ደግሞ በግዞት እንዲያሳልፍ ተፈረደበት። የግዞት ፍርዱን ከሚስቱ ከሃና ጋር ሆኖ ከትውልድ ሃገሩ ከኩስት 5, 000 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በሳይቤሪያ አሳለፈ። ወደዚያ አካባቢ በመኪናም ሆነ በባቡር መሄድ ስለማይቻል ብቸኛው አማራጭ አውሮፕላን ነበር። በ1983 ወንድም ኮፖስና ሚስቱ የግዞት ፍርዳቸውን ጨርሰው በኩስት ወደሚገኘው ቤታቸው ተመለሱ። ሃና በ1989 ሞተች። ወንድም ኮፖስም በ1997 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። ወንድም ኮፖስ በተለያዩ ወኅኒ ቤቶች ውስጥ 27 ዓመት፣ በግዞት ደግሞ 5 ዓመት ያሳለፈ ሲሆን በድምሩ 32 ዓመት ታስሮ ነበር።

ይህ ትሑትና የዋህ ወንድም የክፍለ ዘመኑን አንድ ሦስተኛ ያሳለፈው በሶቪየት ወኅኒ ቤቶችና የጉልበት ሥራ ማሰሪያ ካምፖች ውስጥ ነው። ይህ የሚደነቅ የእምነት ምሳሌ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ያላቸውን የአቋም ጽናት ጠላቶች ሊያጠፉት እንደማይችሉ በግልጽ ያሳያል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በ1958 የላከው ሪፖርት

“አሥር የኮሚኒስት ወጣቶች ድርጅት አባላት እያንዳንዱን ወንድም እንዲሰልሉ ይደረግ የነበረ መሆኑን ማወቃችን ሁኔታው ለወንድሞች ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር ለመገንዘብ ያስችለናል። በዚህ ላይ ደግሞ የሚጠቁሙ ክፉ ጎረቤቶችና አስመሳይ ወንድሞች እንዲሁም ማንኛውንም ነገር የሚቆጣጠሩ በርካታ ፖሊሶች አሉ፤ አንድ ወንድም ስለ አምላክ መንግሥት ትንፍሽ ሲል ቢሰማ እስከ 25 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድበት፣ ወደ ሳይቤሪያ በግዞት ሊወሰድ፣ ዕድሜ ልኩን በጉልበት ሥራ ካምፕ ውስጥ እንዲያሳልፍ ሊደረግና ምናልባትም ለረጅም ዓመት ብቻውን በጨለማ እስር ቤት ውስጥ ሊጣል ይችላል።

“ቢሆንም ወንድሞች ደፋሮች ናቸው። ለይሖዋ አምላክ ያላቸው ፍቅር ወሰን የለውም፤ ልክ መላእክት ያላቸው ዓይነት ዝንባሌ የነበራቸው ሲሆን ትግሉን የማቋረጡ ሐሳብ ጨርሶ ወደ አእምሯቸው አይመጣም። ሥራው የይሖዋ እንደሆነና በመጨረሻ ድል እስኪቀዳጁ ድረስ ወደፊት መግፋት እንዳለባቸው ያውቃሉ። ታማኝነታቸውን የሚጠብቁት ለማን እንደሆነም ያውቃሉ። ለይሖዋ ሲሉ መከራ መቀበል ለእነርሱ ደስታቸው ነው።”

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከማርያ ፖፖቪች ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

የትውልድ ዘመን:- 1932

የተጠመቀችበት ዓመት:- 1948

ያሳለፈችው ታሪክ:- ለስድስት ዓመታት በእስር ቤትና የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ቆይታለች። ከአሥር የሚበልጡ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ረድታለች።

ሚያዝያ 27, 1950 ተይዤ ስታሰር የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ነበርኩ። ሐምሌ 18 ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመስበኬ ምክንያት የአሥር ዓመት እስራት ፈረዱብኝ። ለፍርድ የቀረብነው አራት ወንድሞችና ሦስት እህቶች ስንሆን እያንዳንዳችን አሥር ዓመት እንድንታሰር ተፈረደብን። ነሐሴ 13 ቀን ወንድ ልጅ ተገላገልኩ።

እስር ቤት መግባቴ ተስፋ አላስቆረጠኝም። ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ በመሆኔ ሳይሆን ክርስቲያን በመሆኔ ምክንያት ስደት ቢደርስብኝ ልደሰት እንደሚገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬ ነበር። በመሆኑም ደስተኛ ነበርኩ። ለብቻዬ ተገልዬ እንድታሰር ሲያደርጉኝ በእስር ቤት ክፍሌ ውስጥ ወዲያና ወዲህ እየተመላለስኩ እዘምር ነበር።

አንድ ወታደር ትንሿን መስኮት ከፍቶ “በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለሽም ትዘምሪያለሽ?” አለኝ።

እኔም “በማንም ላይ ምንም መጥፎ ነገር ስላልሠራሁ ደስተኛ ነኝ” አልኩት። ምንም ሳይናገር መስኮቱን ዘጋው። አልደበደቡኝም።

“እስኪ ያለሽበትን ሁኔታ ተመልከቺ። እምነትሽን ብትክጂ ይሻልሻል” ይሉኝ ነበር። በእስር ቤት እንደምወልድ መናገራቸው ነበር። እኔ ግን የታሰርኩት በአምላክ ቃል ላይ ባለኝ እምነት ምክንያት በመሆኑ ደስተኛ ነበርኩ። ወንጀለኛ እንዳልሆንኩና ስደት የሚደርስብኝ በይሖዋ በማመኔ ምክንያት እንደሆነ አውቃለሁ። ይህም ደስተኛ ሆኜ እንድቀጥል ረድቶኛል። በእስር ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህንን ይመስል ነበር።

በኋላ ላይ በካምፑ ውስጥ እየሠራሁ ሳለ እጄ ከቅዝቃዜው የተነሳ በድን ስለሆነ ወደ ሆስፒታል ተላክሁ። በዚያ ያለችው ዶክተር ወደደችኝ። “ጤንነትሽ ጥሩ አይደለም። ለምን እዚህ መጥተሽ ከእኔ ጋር አትሠሪም?” አለችኝ።

የካምፑ ዲሬክተር በዚህ ሐሳብ አልተስማማም። “ይቺ ሴት ከአንቺ ጋር እንድትሠራ የፈለግሽው ለምንድን ነው? ከሌላ ክፍል አንድ ሰው ውሰጂ” አላት።

እሷ ግን “እኔ ሌላ ሰው አልፈልግም፤ በሆስፒታሌ ውስጥ እንዲሠሩ የምፈልገው ጥሩና ታማኝ ሰዎችን ነው። ስለዚህ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ የምትሠራው እሷ ናት። ምንም ነገር እንደማትሰርቅ እንዲሁም አደገኛ መድሃኒቶችን እንደማትወስድ አውቃለሁ” አለችው።

እኛን ያምኑን ነበር። ሃይማኖተኛ ለሆኑ ሰዎች የተለየ አክብሮት ነበራቸው። ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችንን ተመልክተው ነበር። ይህም ጠቅሞናል።

በመጨረሻም ዶክተሯ ዲሬክተሩን አሳመነችው። እሱም ሊለቀኝ ያልፈለገው ዛፍ በመቁረጥ ጎበዝ ስለነበርኩ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች የትም ብንመደብ በሥራችን ሁልጊዜ ታማኝና ትጉህ ነበርን።

ማስታወሻ:- ማርያ ልጅዋን የወለደችው በቪኒትስያ፣ ዩክሬን በሚገኝ ወኅኒ ቤት ነበር። ሕፃኑ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ወኅኒ ቤት በሚገኘው እጓለማውታ ማሳደጊያ ውስጥ እንዲቆይ ተደረገ። ከዚያም ዘመዶቻቸው ሕፃኑን ወደ ሳይቤሪያ በግዞት ተወስዶ ወደነበረው አባቱ ዘንድ ላኩት። እህት ማርያ ከእስር ስትፈታ ልጅዋ ስድስት ዓመት ሆኖት ነበር።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከፍዮደር ካሊን ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

የትውልድ ዘመን:- 1931

የተጠመቀበት ዓመት:- 1950

ያሳለፈው ታሪክ:- ከ1951-65 በግዞት። ከ1962-5 በእስር።

በአንድ ወቅት በወኅኒ ቤት በምርመራ ላይ ሳለሁ ይሖዋ አንድ ያልተጠበቀ ነገር አድርጎልኛል። ይህ ለእኔ እንደ ተአምር ነበር። አንድ የኬ ጂ ቢ (የመንግሥት የደህንነት ኮሚቴ) ዲሬክተር በእጁ አንድ ወረቀት ይዞ መጣ። መርማሪውና አቃቤ ሕጉ ጎን ለጎን ተቀምጠው ነበር። የኬ ጂ ቢ ዲሬክተሩ ለመርማሪው “ይህንን ወረቀት ስጠውና ያንብበው! በአሜሪካ ያሉት ወንድሞቹ የማይረቡ መሆናቸውን ይመለከታል!” አለው።

ከዚያም ወረቀቱን ሰጡኝ። በአውራጃ ስብሰባ ላይ የተላለፈውን የአቋም መግለጫ የያዘ ወረቀት ነበር። አንድ ጊዜ ከወጣሁት በኋላ እንደገና በጥንቃቄ ማንበብ ጀመርኩ። አቃቤ ሕጉ ትዕግስቱ እያለቀ መጣ። “ሚስተር ካሊን! እያጠናኸው ነው እንዴ?” አለኝ።

እኔም “መጀመሪያ ላይ እንዲሁ ገረፍ ገረፍ አድርጌ ነበር ያነበብኩት። አሁን ግን በደንብ ልረዳው ስለፈለግሁ ነው” አልኩት። በውስጤ የደስታ እንባ እያነባሁ ነበር። የአቋም መግለጫውን አንብቤ ስጨርስ መልሼ ሰጠዃቸውና እንዲህ አልኳቸው:- “በጣም አመሰግናችኋለሁ፤ በተለይ ግን እንደዚህ እንድታደርጉ ስላነሳሳችሁ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ዛሬ ይህንን የአቋም መግለጫ በማንበቤ እምነቴ በጣም ተጠናክሯል! ከእነዚህ ምሥክሮች ጋር በመሆን የአምላክን ስም ያለምንም ገደብ ማወደሴን እቀጥላለሁ። በካምፑ ውስጥም ሆነ በእስር ቤት ላሉት ሰዎች እንዲሁም በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ስለ አምላክ እናገራለሁ። ተልዕኮዬ ይህ ነው!

“ምንም ያህል ብታሰቃዩኝ ስለ አምላክ እንዳልናገር ልታደርጉኝ አትችሉም! በዚህ የአቋም መግለጫ ላይ ምሥክሮቹ ዓመፅ እናነሳሳለን አላሉም፤ ከዚህ ይልቅ ከባድ ስደትን ጨምሮ ምንም ይምጣ ምን ይሖዋ ታማኝ ሆነው እንዲጸኑ እንደሚረዳቸው በመተማመን እሱን ማገልገላቸውን ለመቀጠል ቆርጠዋል! ይሖዋ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በእምነቴ እንድጸና እንዲያበረታኝ እጸልያለሁ።

“ፈጽሞ አልፈራም! ይህ የአቋም መግለጫ በጣም አጠናክሮኛል። በጥይት ልትገድሉኝ ብትነሱ እንኳን ከአቋሜ ፍንክች አልልም። ይሖዋ በትንሣኤ እንደሚያስነሣኝ አምናለሁ!”

መርማሪዎቹ ያሰቡት ስላልተሳካ ወሽመጣቸው እንደተቆረጠ ያስታውቅ ነበር። ትልቅ ስህተት እንደፈጸሙ ተገንዝበው ነበር። እምነቴን ለማዳከም ብለው የሰጡኝ የአቋም መግለጫ እነርሱ ባላሰቡት መንገድ እምነቴን አጠናክሮልኛል።