በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሁኔታዎች መለወጥ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በሚገባ ተጠቀምበት

የሁኔታዎች መለወጥ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በሚገባ ተጠቀምበት

የሁኔታዎች መለወጥ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በሚገባ ተጠቀምበት

ፐም፣ ያን፣ ድሬስና ኦቶ በኔዘርላንድ የሚኖሩ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሲሆኑ የሚመሳሰሉባቸው በርካታ ሁኔታዎች አሏቸው። አራቱም ትዳር መሥርተው ልጆች ወልደዋል። እንዲሁም ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ሁሉም የሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራ የነበራቸው ሲሆን ምቹ በሆነ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰብዓዊ ሥራቸውን አቁመው ሙሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የአምላክን መንግሥት ዓላማዎች ለማራመድ ማዋል ጀምረዋል። ይህን ለውጥ እንዲያደርጉ የረዳቸው ምንድን ነው? የሁኔታዎች መለዋወጥ የፈጠረውን አጋጣሚ በሚገባ መጠቀማቸው ነው።

ይዋል ይደር እንጂ በአብዛኞቻችን ሕይወት ውስጥ አንዳንድ ለውጦች መከሰታቸው አይቀርም። ትዳር መያዝን፣ ልጆች መውለድን ወይም በእድሜ የገፉ ወላጆችን መጦርን የመሳሰሉት ለውጦች ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ያስከትላሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ለውጦች ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ለማስፋት የምንችልበት ተጨማሪ አጋጣሚ የሚሰጡን ናቸው። (ማቴዎስ 9:37, 38) ለምሳሌ ያህል ልጆቻችን አድገው ራሳቸውን ሊችሉ ወይም ከሥራ ጡረታ ልንወጣ እንችላለን።

እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹ ለውጦች ያለ እኛ ፍላጎት የሚመጡ ቢሆኑም አንዳንድ ክርስቲያኖች በአገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች የሚከፍቱላቸውን ለውጦች ራሳቸው በመፍጠር ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ፐም፣ ያን፣ ድሬስ እና ኦቶም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። እንዴት?

ልጆች ራሳቸውን ችለው ከቤት ሲወጡ

ፐም በአንድ የመድኃኒት ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ውስጥ በሒሳብ ያዥነት ይሠራ ነበር። እሱና ባለቤቱ አኒ ከሁለት ሴቶች ልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ረዳት አቅኚ በመሆን ያገለግሉ ነበር። እንዲሁም ከሌሎች አቅኚዎች ጋር በአንድነት ለመዝናናት ዝግጅት ያደርጉ ነበር። ፐም እና አኒ “እንዲህ ማድረጋችን አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ከሚችል ሌላ ዓይነት ቅርርብ እንድንርቅ ረድቶናል” በማለት ይናገራሉ። ወላጆቻቸው ጥሩ አርአያ ስለሆኑላቸው ሁለቱም ልጆቻቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ የዘወትር አቅኚ ሆነዋል።

ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ከቤት ሲወጡ ፐምና አኒ ይህ አጋጣሚ አስደናቂ ቦታዎችን ለመጎብኘት ወይም ራሳቸውን ለማዝናናት የሚችሉበት ተጨማሪ ነጻነትና የገንዘብ አቅም እንደሚሰጣቸው ተገንዝበው ነበር። ቢሆንም ይህን አጋጣሚ ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሊጠቀሙበት ወሰኑ። ስለዚህ ፐም አሠሪውን ከሳምንቱ ውስጥ አንድ የሥራ ቀን እንዲቀንስለት ጠየቀው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጠዋት በ1:​00 ሥራ ገብቶ በ8:​00 መውጣት የሚችልበትን ሁኔታ አመቻቸ። እርግጥ ነው፣ አነስተኛ ሰዓት መሥራት በአነስተኛ ገቢ መተዳደርን የሚጠይቅ ነው። ቢሆንም የሚያገኙትን አነስተኛ ገቢ አብቃቅተው በመኖር በ1991 እሱም እንደ ባለቤቱ የዘወትር አቅኚ ሆነ።

ከዚያም ፐም በአንድ ትልቅ የይሖዋ ምሥክሮች የመ​ሰብሰቢያ አዳራሽ ወደሚገኝ አነስተኛ መኖሪያ ተዛውሮ አዳራሹን እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ግብዣ ቀረበለት። ይህ እሱም ሆነ ባለቤቱ ለ30 ዓመታት የኖሩበትን ቤት መልቀቅ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም የቀረበላቸውን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲህ ማድረጉ ከብዷቸው ነበር? አኒ የድሮ ቤቷ ሲናፍቃት ‘እንደ ሎጥ ሚስት እየሆንኩኝ ይሆን?’ በማለት ራሷን እንደምትጠይቅ ተናግራለች። ‘ወደ ኋላ ላለመመልከት’ ቆርጣ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 19:26፤ ሉቃስ 17:32

ፐም እና አኒ ይህ ውሳኔያቸው ብዙ በረከቶችን እንዳስገኘላቸው ይሰማቸዋል። ካገኟቸው በረከቶች መካከል አዳራሹን ለአውራጃ ስብሰባዎች ለማዘጋጀት የሚያደርጉት ተሳትፎና በአዳራሹ ንግግር ለማቅረብ ከሚመጡ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች (ተጓዥ አገልጋዮች) ጋር ለመገናኘት መቻላቸው ያስደስታቸዋል። አልፎ አልፎ ደግሞ ፐም ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲያገለግል የተለያዩ ጉባኤዎችን ይጎበኛሉ።

እነዚህ ባልና ሚስት አገልግሎታቸውን ለማስፋት እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው? ፐም እንዲህ በማለት ይመልሳል:- “በሕይወትህ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ሲያጋጥምህ ይህን ለውጥ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ቆራጥ መሆን አለብህ።”

ሕይወትን ቀላል ማድረግ

ያን እና ባለቤቱ ዎት ሦስት ልጆች አሏቸው። ፐምና ቤተሰቡ እንዳደረጉት ያንም የሁኔታዎች መለወጥ የፈጠረለትን አጋጣሚ በሚገባ ተጠቅሞበታል። ያን ለብዙ ዓመታት በአንድ ባንክ ውስጥ ዳጎስ ያለ ደመወዝ እየተከፈለው ይሠራ የነበረ በመሆኑ ቤተሰቡ ጥሩ ኑሮ ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ አገልግሎቱን ለማስፋት የነበረው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጣ። እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ባሳለፍኩት ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለእውነት ያለኝ አድናቆት እየጨመረና ለይሖዋ የነበረኝ ፍቅር እያደገ መጣ።” ስለዚህ በ1986 ያን በአኗኗሩ ላይ አንዳንድ ለውጦችን አደረገ። “በቢሮ ውስጥ አንዳንድ የሥራ መዋቅር ለውጦች ሲደረጉ አጋጣሚውን በመጠቀም ከበፊቱ ያነሰ ሰዓት መሥራት ጀመርኩ። በዚህ የተደነቁት የሥራ ባልደረባዎቼ ዲዎዶ የሚል ቅጽል ስም አወጡልኝ። ምክንያቱም የምሠራው ማክሰኞ [ንስዳግ]፣ ረቡዕ [ንስዳግ] እና ሐሙስ [ንደርዳግ] ብቻ ነበር። ደሞዜ 40 በመቶ ቀነሰ። ቤታችንን ሸጥኩና የመንግሥቱ አስፋፊዎች በይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል እንድንችል የጀልባ ቤት ገዛሁ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጡረታ የመውጫ ዕድሜዬ ከመድረሱ በፊት ጡረታ ወጣሁ። በዚህ ጊዜ ደግሞ ገቢዬ ሌላ 20 በመቶ ቀነሰ፤ ቢሆንም በ1993 የዘወትር አቅኚ ለመሆን ችያለሁ።”

በአሁኑ ወቅት ያን የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል ሲሆን በቋሚነት የአውራጃ ስብሰባ የበላይ ተመልካች በመሆን ያገለግላል። ዎትም የጤና ችግር ያለባት ቢሆንም አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ በመሆን ታገለግላለች። በአሁኑ ወቅት ሦስቱም ልጆቻቸው አግብተው ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር ቀናተኛ የመንግሥቱ አገልጋዮች ሆነዋል።

ያንና ዎት ቤተሰባቸውን በአነስተኛ ገቢ ማስተዳደር የቻሉት እንዴት ነው? ያን እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ደህና ገንዘብ በነበረን ወቅት ለቁሳዊ ነገሮች ከመጠን በላይ ፍቅር እንዳያድርብን እንጠነቀቅ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የፈለግነውን ነገር ወዲያውኑ መግዛት አለመቻላችን የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም ባገኘናቸው የተትረፈረፉ መንፈሳዊ በረከቶችና ልዩ የአገልግሎት መብቶች በእጅጉ ተክሰናል።”

እንደ ያንና ዎት ሁሉ ድሬስና ባለቤቱ ዬኒ ኑሯቸውን ቀላል ለማድረግና ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የበለጠ ጊዜ ለመስጠት ወስነዋል። ድሬስና ዬኒ ልጆች እስከወለዱበት ጊዜ ድረስ በአቅኚነት አገልግለዋል። ልጆች ሲወልዱ ግን ድሬስ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማሟላት በአንድ ትልቅ ድርጅት ውስጥ በአስተዳዳሪነት ተቀጠረ። ቀጣሪዎቹ በሥራው ስለተደሰቱ የደረጃ እድገት ሊሰጡት ፈለጉ። ድሬስ ግን የቀረበለት እድገት ለክርስቲያናዊ እንቅስ​ቃሴዎች የሚያውለውን ጊዜ ስለሚሻማበት ሳይቀበለው ቀረ።

ልጆችን ማሳደግና የዬኒን እናት ማስታመም የእሱንና የባለቤቱን ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ ነበር። ያም ሆኖ የነበራቸውን የአቅኚነት መንፈስ አላጠፉም። እንዲህ እንዲያደርጉ የረዳቸው ምንድን ነው? ዬኒ እንዲህ ትላለች:- “አብረውን የሚኖሩ አቅኚዎች የነበሩ ሲሆን ሌሎች አቅኚዎችን ምሳ ወይም እራት ከእኛ ጋር እንዲመገቡ እንጋብዝ እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በቤታችን እንዲያርፉ እናደርግ ነበር።” ድሬስ አክሎ ሲናገር “አኗኗራችን ቀላል የነበረ ሲሆን ምንም ዓይነት ዕዳ ውስጥ እንዳንገባ እንጠነቀቅ ነበር። ወደፊት እንቅፋት እንዳይፈጥሩብን በትላልቅ የንግድ ውሎች ውስጥ ላለመግባትም ሆነ በዱቤ ቤት ላለመግዛት ወስነን ነበር።”

ድሬስና ዬኒ የአምላክን መንግሥት ዓላማ ለማራመድ የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ጊዜ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያደረጉት ውሳኔ አርኪ ውጤት አስገኝቶላቸዋል። አሁን ሁለቱም ወንዶች ልጆቻቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች ሲሆኑ አንደኛው ከባለቤቱ ጋር የዘወትር አቅኚ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ድሬስና ዬኒ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ ከጊዜ በኋላ ዬኒ ከድሬስ ጋር በወረዳ ሥራ አብራው አገልግላለች። በአሁኑ ወቅት ድሬስ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል ሆኖ በሚያገለግልበት ቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው።

ቀደም ብሎ ጡረታ መውጣት

እንደ ድሬስና ዬኒ ኦቶና ባለቤቱ ጁዲም ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን ከመውለዳቸው በፊት አቅኚዎች ነበሩ። ጁዲ የመጀመሪያ ልጅዋን እርጉዝ እያለች ኦቶ በመምህርነት ሥራ ተቀጠረ።

ልጆቻቸው በማደግ ላይ እያሉ ኦቶና ጁዲ አቅኚዎችን ብዙ ጊዜ ቤታቸው እየጋበዙ ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ያላቸውን ደስታ እንዲመለከቱ ያደርጉ ነበር። በኋላ ትልቋ ልጃቸው አቅኚ ሆነች። ከዚያም በጊልያድ ትምህርት ቤት ከተካፈለች በኋላ ከባለቤቷ ጋር በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ በሚስዮናዊነት በማገልገል ላይ ትገኛለች። ትንሿ ልጃቸውም በ1987 አቅኚ የሆነች ሲሆን እናታቸው ጁዲም እንዲሁ አቅኚ ሆናለች።

ኦቶ በትምህርት ቤት አንዳንድ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት የሚያገኘውን ትርፍ ጊዜ በአቅኚነት ለማገልገል ይጠቀምበት ነበር። በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ ሥራውን ተወ። በአሁኑ ወቅት ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ በማገልገል በመምህርነት ያካበተውን ችሎታ ጉባኤዎችን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ይጠቀምበታል።

ኦቶ የጡረታ እድሜያቸው ከመድረሱ በፊት ጡረታ ለሚወጡ ምን ምክር ይሰጣል? “ጡረታ ስትወጡ እስቲ አንድ ሁለት ዓመት ልረፍ ብላችሁ አታስቡ። በቀላሉ ከእረፍት ጋር ትላመዱና ሳይታወቃችሁ አቅኚ የመሆኑ ሐሳብ ጨርሶ ከአእምሯችሁ ይጠፋል። ከዚህ ይልቅ ወዲያውኑ በክርስቲያናዊ አገልግሎት የምታደርጉትን ተሳትፎ አሳድጉት።”

የሕይወት ተሞክሯችሁን በሚገባ ተጠቀሙበት

እርግጥ ነው፣ እንደ ፐም፣ ያን፣ ድሬስና ኦቶ ያሉ ወንድሞች በወጣትነታቸው የነበራቸውን ዓይነት ኃይልና ብርታት እንደማይኖራቸው የታወቀ ነው። ሆኖም የተሻለ ብስለት፣ ተሞክሮና ጥበብ አላቸው። (ምሳሌ 20:29) አባት መሆን ምን ምን ኃላፊነቶች እንዳሉት የሚያውቁ ከመሆኑም በላይ ከሚስቶቻቸው ጋር ሲኖሩ እናትነት ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ተምረዋል። ከሚስቶቻቸው ጋር በመሆን አንዳንድ የቤተሰብ ችግሮችን መፍታት ችለዋል፤ እንዲሁም ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦችን አውጥተዋል። ኦቶ እንዲህ ይላል:- “የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል ከቤተሰብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክር በምሰጥበት ወቅት የራሴን ቤተሰብ በማስተዳደር ያገኘሁት ተሞክሮ በጣም ይጠቅመኛል።” በተመሳሳይም ድሬስ በአባትነት ያካበተው ተሞክሮ ብዙ ወጣት ሠራተኞች በሚገኙበት በቤቴል ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አስችሎታል።

አዎን፣ እነዚህ ወንድሞች ከግል ሕይወታቸው ያገኙት ተሞክሮ የተለያዩ የጉባኤ ጉዳዮችን በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን ይረዳቸዋል። ያካበቱት ተሞክሮ ጉልበትን እንደሚቆጥብ የተሳለ መሣሪያ የተለያዩ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን አስችሏቸዋል። (መክብብ 10:10) እንዲያውም ብዙውን ጊዜ አካላዊ ጥንካሬ እያላቸው ልምድ ከሚጎድላቸው ሰዎች የበለጠ ማከናወን ይችላሉ።

እነዚህ ወንድሞችና ሚስቶቻቸው በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ለሚገኙት ወጣቶች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ወጣቶች እንደነዚህ ያሉት ባልና ሚስቶች በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን አብዛኞቹን ፈታኝ ሁኔታዎችም ሆኑ በረከቶች በሕይወታቸው እንደተመለከቱ ይገነዘባሉ። እድሜው እየገፋ ቢሄድም ከባድ ኃላፊነት ለመቀበል ራሱን በፈቃደኝነት እንዳቀረበው እንደ ካሌብ ያሉ ወንዶችና ሴቶችን በመካከላችን ማየት በጣም የሚያበረታታ ነው።​—⁠ኢያሱ 14:10-12

የእምነት ምሳሌነታቸውን ኮርጁ

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀረቡት ባልና ሚስቶች የነበራቸውን እምነትና ይህን እምነታቸውን በሥራ ያሳዩበትን መንገድ መኮረጅ ትችላለህ? እውነትን የሕይወታቸው ዋነኛ ክፍል እንዳደረጉት አስታውስ። አቅኚ የመሆንን ፍላጎት በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ተክለዋል። ያን እንደተናገረው እንዲህ ሊያደርጉ የቻሉት “ይሖዋንና ድርጅቱን ከልብ በመውደድ ረገድ ምሳሌ በመሆን፣ ጥሩ አርአያ ከሚሆኑ ወዳጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚቻልባቸውን ዝግጅቶች በማድረግና ልጆቹ ራሳቸውን እንዲችሉ በማሰልጠን” ነው። እንዲሁም በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው ይሠሩና ይዝናኑ ነበር። ፐም “በእረፍት ጊዜያችን ወቅት የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ መላው ቤተሰብ በስብከቱ ሥራ ያሳልፍና ከሰዓት በኋላ አንድ ላይ ሆነን እንዝናና ነበር” በማለት ያስታውሳል።

በተጨማሪም እነዚህ ክርስቲያኖች ወደፊት የሁኔታዎች መለወጥ የሚፈጥረውን አጋጣሚ እንዴት በሚገባ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አስቀድመው እቅድ ያወጡ ነበር። ግብ ያወጡ እንዲሁም ግባቸውን ዳር ለማድረስ የሚያስችላቸውን ቁርጥ ያለ እርምጃ ይወስዱ ነበር። በሰብዓዊ ሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ መቀነስ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ያመቻቹ የነበረ ሲሆን በአነስተኛ ገቢ ኑሯቸውን ለመግፋትም ፈቃደኛ ሆነዋል። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) ሚስቶቻቸውም ለባሎቻቸው ሙሉ ድጋፍ ይሰጧቸው ነበር። ባሎቹም ሆኑ ሚስቶቹ ‘ሥራ በሞላበት ትልቅ በር’ ለመግባት ጠንካራ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን በውጤቱም ይሖዋ የተትረፈረፉ በረከቶችን ሰጥቷቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:9፤ ምሳሌ 10:22

አንተ በተመሳሳይ በአገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ ፍላጎቱ አለህ? ከሆነ ለዚህ የሚረዳህ የሁኔታዎች መለወጥ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፐም እና አኒ የመሰብሰቢያ አዳራሹን ሲንከባከቡ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያን እና ዎት በስብከቱ ሥራ ላይ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድሬስና ዬኒ በቤቴል ሲያገለግሉ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኦቶና ጁዲ የሚቀጥለውን ጉባኤ ለመጎብኘት ሲንቀሳቀሱ