በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የደረሰባቸውን ስደት በጽናት ተቋቁመዋል

የደረሰባቸውን ስደት በጽናት ተቋቁመዋል

የደረሰባቸውን ስደት በጽናት ተቋቁመዋል

ፍሬዳ የስ የተወለደችው በ1911 በዴንማርክ ሲሆን በኋላም ከወላጆቿ ጋር በሰሜናዊ ጀርመን ወደምትገኘው ወደ ሁዘም ተዛወሩ። ከዓመታት በኋላ በማግድበርግ ከተማ መሥራት ጀመረች፤ ከዚያም በ1930 ተጠምቃ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ የሚጠሩበት ስም ነው) ሆነች። በ1933 ሂትለር ሥልጣን ሲይዝ ፍሬዳ በአንድ ብቻ ሳይሆን በሁለት አምባገነን መንግሥታት ሥር ለ23 ዓመታት ያህል ያየችው ቁም ስቅል አንድ ብሎ ጀመረ።

በመጋቢት 1933 የጀርመን መንግሥት ሁሉንም ሰው የሚያሳትፍ አጠቃላይ ምርጫ እንዲከናወን ጥሪ አደረገ። በሃምበርግ አቅራቢያ የሚገኘው የኖየንጋሜ ማጎሪያ ካምፕ መታሰቢያ ቤተ መዘክር ዋና ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ዴትለፍ ጋርቢ እንዲህ ብለዋል:- “ብሔራዊ ሶሻሊስቶች አብዛኛው ሕዝብ ቻንስለርና መሪ የሆነውን አዶልፍ ሂትለርን እንዲመርጥ ለማስገደድ ይፈልጉ ነበር።” የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ እንዲሆኑና ‘የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ የሰጠውን ምክር በመከተል በምርጫው አልተካፈሉም። ውጤቱ ምን ሆነ? የምሥክሮቹ ሥራ ታገደ።​—⁠ዮሐንስ 17:16

ፍሬዳ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዋን በድብቅ ማካሄዷን ቀጠለች፤ ሌላው ቀርቶ መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት በማተሙ ሥራ ላይ ትካፈል ነበር። ፍሬዳ “ከምናትማቸው መጽሔቶች መካከል አንዳንዶቹ ለእምነት ባልደረቦቻችን በድብቅ ወደ ማጎሪያ ካምፖች ይገባላቸው ነበር” ትላለች። በ1940 ተይዛ በጌስታፖዎች ምርመራ ከተደረገባት በኋላ ለበርካታ ወራት ለብቻዋ ተገልላ ታሰረች። መከራውን መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? እንዲህ ትላለች:- “ጸሎት ጋሻ ሆኖልኝ ነበር። መጸለይ የምጀምረው ገና በማለዳው ሲሆን በቀኑ ውስጥም በተደጋጋሚ እጸልያለሁ። ጸሎት ኃይል እንዳገኝ እንዲሁም ከልክ በላይ እንዳልጨነቅ ረድቶኛል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ፍሬዳ ከእስር ብትፈታም በ1944 ጌስታፖዎች እንደገና ያዟት። በዚህ ጊዜ በቫልትሃይም ወኅኒ ቤት ለሰባት ዓመታት እንድትታሰር ተፈረደባት። ፍሬዳ ቀጥላ እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ከሌሎች ሴቶች ጋር ሆኜ መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ እንድሠራ መደቡኝ። አብዛኛውን ጊዜ የምሠራው ከቼኮዝሎቫኪያ ከመጣች አንዲት እስረኛ ጋር ስለነበር ስለ ይሖዋና ስለ እምነቴ ብዙ እነግራት ነበር። እንደዚያ ዓይነት ውይይት ማድረጋችን በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኜ እንድቀጥል ረድቶኛል።”

ጊዜያዊ ነፃነት

በግንቦት 1945 የሶቪዬት ወታደሮች የቫልትሃይምን ወኅኒ ቤት ከናዚዎች ሲያስለቅቁት ፍሬዳ ወደ ማግድበርግ ለመመለስና በሕዝብ አገልግሎት ለመካፈል ነፃነት አገኘች፤ ሆኖም ነፃነቷ ብዙም አልዘለቀም። ምሥክሮቹ አሁንም በእምነታቸው ምክንያት የስደት ዒላማ ከመሆን አላመለጡም፤ በዚህ ወቅት ግን ስደቱን ያስነሱት በሶቪዬት ቁጥጥር ሥር የዋሉ ክልሎችን የሚያስተዳድሩት ባለ ሥልጣናት ነበሩ። በአምባገነናዊነት ላይ ጥናት የሚያደርገው ሃና አረንት ተብሎ የሚጠራው ተቋም ባልደረባ የሆኑት ጌራልት ሃክ “ጀርመን ውስጥ በሁለቱም አምባገነናዊ መንግሥታት አለማቋረጥ ስደት ከደረሰባቸው ጥቂት ማኅበራዊ ቡድኖች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል” በማለት ጽፈዋል።

ስደቱ በድጋሚ የተቀሰቀሰው ለምን ነበር? አሁንም ቢሆን አከራካሪው ጉዳይ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ነበር። በ1948 ምሥራቅ ጀርመን ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሚካፈልበት ምርጫ አዘጋጀች። ሃክ እንደተናገሩት “[በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት የተቀሰቀሰበት] ዋነኛው ምክንያት ምሥክሮቹ በምርጫው ስላልተሳተፉ ነበር።” ነሐሴ 1950 ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታገደ። ፍሬዳን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች ተያዙ።

ፍሬዳ እንደገና ፍርድ ቤት ቀረበችና የስድስት ዓመት እስር ተበየነባት። ስለ ሁኔታው ስትናገር “በዚህ ወቅት የታሰርኩት ከእምነት ባልደረቦቼ ጋር ነበር፤ አንድ ላይ መሆናችን በጣም ረድቶናል” ትላለች። ፍሬዳ በ1956 ከእስር ስትፈታ በምዕራብ ጀርመን መኖር ጀመረች። በ90ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ፍሬዳ አሁንም ሁዘም ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በማገልገል ላይ ትገኛለች።

ፍሬዳ ለ23 ዓመታት ያህል በሁለት አምባገነናዊ መንግሥታት ሥር ስደት ደርሶባታል። “ናዚዎች አካላዊ ሥቃይ ያደረሱብኝ ሲሆን ኮሚኒስቶች ደግሞ ቅስሜን ለመስበር ሞክረዋል። ይህንን ሁሉ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ያገኘሁት ከየት ነው? በነፃነቱ ጊዜ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማድ ነበረኝ፤ ለብቻዬ ተገልዬ በታሰርኩበት ወቅት ደግሞ አዘውትሬ እጸልይ ነበር፤ አጋጣሚው ሲገኝ ከእምነት ባልደረቦቼ ጋር እሰበሰብና ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ እምነቴን ለሌሎች አካፍል ነበር።”

ፋሺስታዊ አገዛዝ በሃንጋሪ

የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ስደት የቀመሱባት ሌላዋ አገር ሃንጋሪ ናት። አንዳንዶች በሁለት ብቻ ሳይሆን በሦስት አምባገነናዊ መንግሥታት ስደት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህ መካከል አዳም ዚንገር ይገኝበታል። አዳም በ1922 ሃንጋሪ ውስጥ በፓክስ ከተማ የተወለደ ሲሆን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ አደገ። በ1937 ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ አዳም ቤት ይመጣሉ፤ አዳምም ወዲያው ለመልእክታቸው ፍላጎት አሳየ። መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና እሱ ባለበት ቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አለመሆናቸውን ተገነዘበ። ስለዚህ ከፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ወጣና ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ጋር ማገልገል ጀመረ።

በዚህ ወቅት ፋሺዝም በሃንጋሪ እየተስፋፋ ነበር። ብዙውን ጊዜ ፖሊሶች አዳም ከቤት ወደ ቤት ሲሰብክ ካዩት ለምርመራ ወደ ጣቢያ ይወስዱት ነበር። በምሥክሮቹ ላይ የሚደረገው ተጽዕኖ እየተባባሰ ሄዶ በ1939 እስከጭራሹ ሥራቸው ታገደ። በ1942 አዳም ተይዞ ታሰረና በጣም ተደበደበ። በ19 ዓመቱ የደረሰበትን መከራና ለወራት ያሳለፈውን እስር ተቋቁሞ እንዲጸና የረዳው ምን ነበር? “ከመያዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቅ አጠና ስለነበር የይሖዋን ዓላማዎች በሚገባ ተገንዝቤ ነበር” በማለት ተናግሯል። የሚገርመው አዳም የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ከእስር ከተፈታ በኋላ ነበር፤ ይህ የሆነው በነሐሴ 1942 አንድ ምሽት ላይ በቤቱ አቅራቢያ በሚገኝ ወንዝ ውስጥ ነበር።

በሃንጋሪ እስር ቤትና በሰርቢያ ማጎሪያ ካምፕ

በዚህ መሃል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሃንጋሪ ከጀርመን ጋር በማበር ሶቪዬት ሕብረትን መውጋት ጀመረች፤ በ1942 የመከር ወራት ላይ አዳም ለውትድርና ታፈሰ። አዳም እንዲህ ይላል:- “ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀሰምኩት እውቀት ምክንያት በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል እንደማልችል እንዲሁም ገለልተኛ መሆኔን ነገርኳቸው።” አዳም የ11 ዓመታት እስር ተፈረደበት። ሆኖም በሃንጋሪ ብዙም አልቆየም።

በ1943 ወደ 160 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያየ ቦታ ከተሰበሰቡ በኋላ በዕቃ መጫኛ መርከቦች ተጭነው በዳኑቢ ወንዝ በኩል ወደ ሰርቢያ ተወሰዱ። አዳም ከእነዚህ ምሥክሮች መካከል ነበር። እስረኞቹ ከፊል ሰርቢያን ይቆጣጠር በነበረው በሂትለር ሦስተኛ ራይክ እጅ ወደቁ። በቦር ከተማ በሚገኘው የጉልበት ሥራ ካምፕ ውስጥ በመዳብ ማውጫ ቦታ እንዲሠሩ ተደረጉ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ እንደገና ወደ ሃንጋሪ ተወሰዱ፤ ከዚያም በ1945 የጸደይ ወራት የሶቪዬት ወታደሮች አዳምን ነፃ አወጡት።

ሃንጋሪ በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ወደቀች

ሆኖም ይህ ነፃነት ብዙም አልዘለቀም። በ1940ዎቹ መገባደጃ ላይ ሃንጋሪን የሚያስተዳድሩት የኮሚኒስት ባለሥልጣናት ከጦርነቱ በፊት ፋሺስቶች እንዳደረጉት የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ አገዱት። በ1952 አዳም አሁንም በውትድርና አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ተይዞ ለፍርድ ቀረበ፤ በወቅቱ 29 ዓመቱ ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር። አዳም ለፍርድ ቤቱ እንዲህ በማለት ለማስረዳት ሞክሮ ነበር:- “በወታደራዊ አገልግሎት አልካፈልም ስል ይህ የመጀመሪያዬ አይደለም። በጦርነቱ ወቅትም በዚሁ ምክንያት ታስሬና ወደ ሰርቢያ በግዞት ተልኬ ነበር። በወታደራዊ አገልግሎት የማልካፈለው ሕሊናዬ ስለማይፈቅድልኝ ነው። የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ነኝ።” አዳም የስምንት ዓመት እስር ተፈረደበት፤ በኋላ ግን የእስር ዘመኑ ወደ አራት ዓመት ተቀነሰ።

አዳም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ መጀመሪያ ወደ ወላጆቹ ቤት ከመጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ ከ35 ለሚበልጡ ዓመታት ስደት ደርሶበታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አዳም ስድስት ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቦ የ23 ዓመታት እስር የተፈረደበት ሲሆን ቢያንስ በአሥር ወኅኒ ቤቶችና ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስሯል። በሦስት አምባገነናዊ አገዛዞች ሥር ማለትም ከጦርነቱ በፊት ሃንጋሪ ውስጥ በፋሺስቶች፣ ሰርቢያ ውስጥ በጀርመን ብሔራዊ ሶሻሊስቶች እና በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ደግሞ ሃንጋሪ ውስጥ በኮሚኒስቶች ያለማቋረጥ የደረሰበትን ስደት በጽናት ተቋቁሟል።

አዳም በአሁኑ ወቅት በትውልድ መንደሩ በፓክስ አምላክን በታማኝነት እያገለገለ ነው። የደረሰበትን መከራ በጽናት ለመወጣት የቻለው ከሰው በላይ የሆነ ችሎታ ስላለው ነው? አይደለም። እንዲህ ይላል:-

“የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ጸሎትና ከመሰል አማኞች ጋር መሰብሰብ በጣም አስፈላጊ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ ጠቃሚ የሆኑ ሁለት ነገሮችን ማጉላት እፈልጋለሁ። በመጀመሪያ ይሖዋ የብርታት ምንጭ ነው። ሕይወቴ የተመካው ከእርሱ ጋር በመሠረትኩት የቅርብ ዝምድና ላይ ነበር። ሁለተኛ ደግሞ በሮሜ ምዕራፍ 12 ላይ የሚገኘውን “ራሳችሁ አትበቀሉ” የሚለውን ምክር ማስታወሴ ጠቅሞኛል። በመሆኑም በማንም ላይ ቂም አልያዝኩም። ብዙ ጊዜ ስደት ያደረሱብኝን ሰዎች ለመበቀል የሚያስችል አጋጣሚ አግኝቼ የነበረ ቢሆንም ፈጽሞ እንደዚያ አላደረግሁም። ይሖዋ የሚሰጠንን ኃይል ክፉን በክፉ ለመመለስ ልንጠቀምበት አይገባም።”

ማንኛውም ስደት የሚያከትምበት ጊዜ

ፍሬዳና አዳም በአሁኑ ወቅት አለምንም እንቅፋት ይሖዋን ማምለክ ችለዋል። ይሁን እንጂ የእነርሱን የመሳሰሉት ተሞክሮዎች ሃይማኖታዊ ስደትን በተመለከተ ምን ያሳያሉ? ስደት እውነተኛ ክርስቲያኖች አቋማቸውን እንዲያላሉ እንደማያደርጋቸው ያሳያል። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰው ስደት ብዙ ወጪና በምሥክሮቹም ላይ ከፍተኛ ሥቃይ ቢያስከትልም ዓላማውን ማሳካት ግን አልቻለም። በአንድ ወቅት ሁለቱ ታላላቅ አምባገነናዊ አገዛዞች ይቆጣጠሯቸው በነበሩት የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ዛሬ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ሲደርስባቸው ምን አደረጉ? የፍሬዳ እና የአዳም ተሞክሮ እንደሚያሳየው ምሥክሮቹ “ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርገዋል። (ሮሜ 12:21) መልካም ነገር ክፋትን ማሸነፍ ይችላል? በአምላክ ላይ የጸና እምነት ካለን ይቻላል። የይሖዋ ምሥክሮች በአውሮፓ የደረሰባቸውን ስደት በጽናት መቋቋም የቻሉት በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ነው። ይህ መንፈስ እውነተኛ ክርስቲያኖች መልካም ነገር ለማድረግ የሚያስችል እምነት እንዲያፈሩ አድርጓቸዋል። (ገላትያ 5:22, 23) ይህ፣ በዚህ በዓመፅ በተሞላ ዓለም ውስጥ ሁሉም ሰው ክፉውን በመልካም ለማሸነፍ መጣር እንዳለበት ያስተምረናል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍሬዳ የስ (አሁን ቲሌ) በታሰረችበትና በአሁኑ ወቅት

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳም ዚንገር በእስር ላይ እያለና አሁን