በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፊትና አሁን—ሕይወቷ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ

በፊትና አሁን—ሕይወቷ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል”

በፊትና አሁን—ሕይወቷ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ

ማሴፓን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው አገር በሌሶቶ የምትኖር ወጣት ስትሆን ሕይወት በችግር የተሞላና ትርጉም የለሽ ሆኖባት ነበር! ማሴፓን ከልጅነቷ ጀምሮ ካቶሊክ ነበረች። ይሁን እንጂ ይህ እምነቷ ወደ አምላክ እንድትቀርብ አልረዳትም፤ እንዲያውም ሴት መነኮሳት በገንዘብ እያባበሉ ለብዙ ዓመታት በጾታ ያስነውሯት ነበር።

በዚህ የተነሳ ማሴፓን በሃይማኖት ላይ እምነት ያጣች ከመሆኑም በላይ ለሰብዓዊ ፍጡሮቹ ከልብ የሚያስብ አንድ አፍቃሪ ፈጣሪ አለ የሚለው ሐሳብ ሊዋጥላት አልቻለም። በሰዎች ችላ መባሏ ይፈጸምባት ከነበረው የጾታ በደል ጋር ተዳምሮ ከባድ የስሜት ጠባሳና የከንቱነት ስሜት አሳድሮባት ነበር። በዚህ የተነሳ ባሕርይዋ ተለውጦ ዓመፀኛና ተደባዳቢ ሆነች።

የኋላ ኋላ ማሴፓን ከወሮበሎች ጋር በመግጠም በባቡር ላይ የሰዎችን ንብረት መዝረፍ ጀመረች። በዚህም ምክንያት ተያዘችና በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ ወኅኒ ቤት ታሰረች። ከጊዜ በኋላ ወደ አገሯ ወደ ሌሶቶ የተባረረች ሲሆን እዚያም በወንጀል፣ በስካር፣ በዓመፅና በብልግና ድርጊቶች መካፈሏን ቀጠለች።

ማሴፓን በሕይወቷ ተስፋ ቆርጣ በነበረበት ወቅት አምላክ እንዲረዳት አምርራ በጸሎት ጠየቀችው። “ሕይወቴ ከተስተካከለልኝ አንተን ለማገልገል የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት ለአምላክ ቃል ገባች።

ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ሚስዮናውያን መጥተው አነጋገሯትና መጽሐፍ ቅዱስን አብራቸው እንድታጠና ግብዣ አቀረቡላት። ከጥናቷ አምላክ ለሰው ልጆች ችግሮች ደንታ የሌለውና የማያስብ አለመሆኑን ተገነዘበች። ደግሞም ‘የሐሰት አባት’ የሆነው ሰይጣን አንዳንዶች የከንቱነት ስሜት በውስጣቸው እንዲያድርባቸውና ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይወዳቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ መሰሪ ዘዴዎችን እንደሚጠቀም አስተዋለች።​—⁠ዮሐንስ 8:44፤ ኤፌሶን 6:11

በሌላ በኩል ደግሞ ለሠራነው ኃጢአት ንስሐ ከገባን፣ አምላክ ይቅር እንዲለን ከለመንነውና እርሱን ለማስደሰት ጥረት ካደረግን ለራሳችን ጥሩ ግምት ሊኖረን እንደሚችል ስታውቅ በጣም ተጽናናች። በተደረገላት እርዳታ “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ” መሆኑንና እኛ ራሳችንን ከምናይበት መንገድ ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ እንደሚመለከተን ለመገንዘብ ቻለች።​—⁠1 ዮሐንስ 3:19, 20

ማሴፓን “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት ስታነብ በጣም ተደሰተች። (መዝሙር 34:18) እሷም ‘መንፈሳቸው ከተሰበሩት’ መሃል አንዷ እንደመሆኗ ይሖዋ አገልጋዮቹ ስሜታቸው ቢደቆስ ወይም እንደማይረቡ ሆኖ ቢሰማቸው እንኳን ፈጽሞ እንደማይተዋቸው ተገነዘበች። አምላክ ለበጎቹ ሁሉ እንደሚያስብላቸውና በአስቸጋሪ ጊዜያት ከጎናቸው እንደሚቆም ስታውቅ ልቧ በደስታ ተሞላ። (መዝሙር 55:22፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) በተለይ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በሚሉት ቃላት ስሜቷ በጣም ተነካ።​—⁠ያዕቆብ 4:8

ብዙም ሳይቆይ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን ለመለወጥ ያለው ኃይል በማሴፓን ሕይወት ላይ በተግባር መታየት ጀመረ። ማሴፓን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትራ መገኘት የጀመረች ሲሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ድርጊቶችን እርግፍ አድርጋ ተወች። ይህስ ምን ውጤት አስገኘላት? ከዚያ በኋላ አምላክ እንደማይወዳትና በእርሷ እንደማይደሰት ተሰምቷት አያውቅም። ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥቱ ምሥራች አዋጅ ነጋሪ ሆና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዓታት በክርስቲያናዊው አገልግሎት አሳልፋለች። ያለፈው አኗኗሯ ያስከተለባት የስሜት ጠባሳ እንዳለ ቢሆንም ማሴፓን በአሁኑ ወቅት ሕይወቷ በደስታ የተሞላና ዓላማ ያለው ሆኗል። የማሴፓን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!​—⁠ዕብራውያን 4:​12

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሕይወቴ ከተስተካከለልኝ አንተን ለማገልገል የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ”

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸው ኃይል

የግፍ ሰለባዎች ለሆኑ ሰዎች መጽናኛ ከሚሰጡት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:-

“የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ልቤን ደስ አሰኛት።” (መዝሙር 94:19 አ.መ.ት ) በቃሉ ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ‘ማጽናኛዎች’ ትልቅ የመጽናናት ምንጭ ናቸው። በምናሰላስልበትና በምንጸልይበት ወቅት ስለ እነዚህ ማጽናኛዎች ማሰባችን እረፍት የሚነሱንን ሐሳቦች ከአእምሯችን ለማስወገድና ስሜታችንን እንደሚረዳልን ወዳጃችን አድርገን በአምላክ ላይ እምነት እንድንጥል ይረዳናል።

“[ይሖዋ] ልባቸውን የቈሰሉትን ይፈውሳል፣ ሕማማቸውንም ይጠግናል።” (መዝሙር 147:3) የይሖዋን ምሕረትና ኃጢአታችንን በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ለማስተሰረይ ያደረገውን ዝግጅት ከልብ የምናደንቅ ከሆነ ራሳችንን ሳንኮንን በሙሉ ልብ ወደ ይሖዋ መቅረብ እንችላለን። ይህም ወደር የሌለው መጽናናትና የአእምሮ ሰላም ያስገኝልናል።

“የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ሊመጣ የሚችል የለም፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” (ዮሐንስ 6:44) ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ አማካኝነት እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ ወደ ልጁ የሳበን ሲሆን የዘላለም ሕይወት ተስፋም ሰጥቶናል።