በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥንት ክርስቲያኖችና የሙሴ ሕግ

የጥንት ክርስቲያኖችና የሙሴ ሕግ

የጥንት ክርስቲያኖችና የሙሴ ሕግ

“ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል።”​—⁠ገላትያ 3:24

1, 2. እስራኤላውያን የሙሴን ሕግ በጥብቅ በመከተላቸው ያገኟቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

 በ1513 ከዘአበ ይሖዋ ለእስራኤላውያን በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ ሰጣቸው። ቃሉን ከሰሙ እንደሚባርካቸው እንዲሁም ደስታና እርካታ የሞላበት ሕይወት እንደሚያገኙ ነገራቸው።​—⁠ዘጸአት 19:5, 6

2 የሙሴ ሕግ ወይም በአጭሩ “ሕጉ” ተብሎ የሚጠራው በጽሑፍ የሰፈረው ሕግ ‘ቅዱስ፣ ጻድቅና በጎ’ ነበር። (ሮሜ 7:12) ሕጉ እንደ ደግነት፣ ሃቀኝነት፣ ንጹሕ ሥነ ምግባርና ለጎረቤት አሳቢ መሆንን የመሰሉ ግሩም ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። (ዘጸአት 23:4, 5፤ ዘሌዋውያን 19:14፤ ዘዳግም 15:13-15፤ 22:10, 22) በተጨማሪም አይሁዳውያን እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ያነሳሳቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:18) ከዚህም በላይ ሕጉ ከአሕዛብ ጋር እንዳይቀራረቡ ወይም ሚስቶችን ከእነርሱ እንዳይወስዱ ይከለክል ነበር። (ዘዳግም 7:3, 4) የሙሴ ሕግ በአይሁዳውያንና በአሕዛብ መካከል እንደ “ግድግዳ” ሆኖ የአምላክ ሕዝቦች በአረማውያን አስተሳሰብና አኗኗር እንዳይበከሉ ጠብቋቸዋል።​—⁠ኤፌሶን 2:14, 15፤ ዮሐንስ 18:28

3. ሕጉን ሙሉ በሙሉ መጠበቅ የሚችል ሰው አለመኖሩ ምን እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል?

3 ያም ሆኖ ግን ሕጉን በጥንቃቄ እንደሚጠብቁ የሚነገርላቸው አይሁዳውያን እንኳ የአምላክን ሕግ ሙሉ በሙሉ መጠበቅ አልቻሉም። ይህ የሆነበት ምክንያት ይሖዋ ከአቅማቸው በላይ ይጠብቅባቸው ስለነበር ይሆን? በፍጹም። ሕጉ ለእስራኤል የተሰጠበት አንደኛው ምክንያት ሰው ‘ሕግ ተላላፊ መሆኑን በግልጽ ለማሳወቅ’ ነው። (ገላትያ 3:19) ሕጉ ቀና አመለካከት የነበራቸው አይሁዳውያን የግድ አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። ይህ አዳኝ በተገለጠ ጊዜ ታማኝ አይሁዳውያን ተደስተው ነበር። ከኃጢአትና ከሞት ኩነኔ ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር!​—⁠ዮሐንስ 1:29

4. ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚት’ የሆነው በምን መንገድ ነው?

4 የሙሴ ሕግ የተሰጠው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንዲያገለግል ታስቦ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚት’ እንደሆነ ተናግሯል። (ገላትያ 3:24) በጥንት ዘመን አንድ ሞግዚት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ያመላልስ ነበር እንጂ እርሱ ራሱ ልጆቹን አያስተምርም። ኃላፊነቱ ልጆችን ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ማገናኘት ብቻ ነበር። በተመሳሳይም የሙሴ ሕግ የተሰጠበት ዓላማ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን አይሁዳውያን ወደ ክርስቶስ ለማድረስ ነው። ኢየሱስ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ” ከተከታዮቹ ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ስለዚህ የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ይህ ‘ሞግዚት’ ማለትም ሕጉ የሚሰጠው አገልግሎት አይኖርም። (ሮሜ 10:4፤ ገላትያ 3:25) ሆኖም አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ይህን መሠረታዊ እውነት ለመገንዘብ ጊዜ ወስዶባቸው ነበር። በዚህም የተነሳ ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላም አንዳንዶቹን የሕጉን ክፍሎች መጠበቃቸውን ቀጥለው ነበር። አንዳንዶች ግን አመለካከታቸውን አስተካክለዋል። በዚህ መንገድ ዛሬ ለምንኖረው ለእኛ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

የክርስትና መሠረተ ትምህርትን በተመለከተ የተገኘ አዲስ ግንዛቤ

5. ጴጥሮስ በራእይ ምን መመሪያ ተሰጠው? የደነገጠውስ ለምን ነበር?

5 በ36 እዘአ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንግዳ የሆነ አንድ ራእይ ተመለከተ። ከሰማይ የመጣ አንድ ድምፅ በሕጉ ውስጥ ርኩስ እንደሆኑ ተደርገው የተገለጹ አእዋፋትንና እንስሳትን አርዶ እንዲበላ አዘዘው። እንዲህ ያለውን መመሪያ ሲሰማ በጣም ደነገጠ! ጴጥሮስ ከዚያ ቀደም ‘አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም በልቶ’ አያውቅም ነበር። ሆኖም “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።” (ሥራ 10:9-15) ጴጥሮስ ሕጉን የሙጥኝ ብሎ ከመከተል ይልቅ አመለካከቱን አስተካከለ። ይህም የአምላክን ዓላማ በተመለከተ አንድ አስገራሚ ግንዛቤ እንዲያገኝ ረዳው።

6, 7. ጴጥሮስ ለአሕዛብ መስበክ እንደሚችል ሆኖ የተሰማው ለምንድን ነው? ከዚህም በተጨማሪ ወደምን መደምደሚያ ደርሶ ሊሆን ይችላል?

6 ከዚያ በኋላ ሦስት ሰዎች ቆርኔሌዎስ ወደሚባል ፈሪሃ አምላክ ያለው ያልተገረዘ አሕዛብ ቤት አብሯቸው እንዲሄድ ለመጠየቅ ጴጥሮስ ወደሚኖርበት ቤት መጡ። እርሱም ባረፈበት ቤት በእንግድነት ተቀበላቸው። የራእዩን ትርጉም የተረዳው ጴጥሮስ በማግስቱ ከሦስቱ መልእክተኞች ጋር ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ለመሄድ ጉዞ ጀመረ። እዚያም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ግሩም ምሥክርነት ሰጠ። ጴጥሮስም እንዲህ በማለት ተናገረ:- “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።” ቆርኔሌዎስ ብቻ ሳይሆን መላው ዘመዶቹና የቅርብ ወዳጆቹ በኢየሱስ በማመናቸው “ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።” ጴጥሮስ በጉዳዩ ውስጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበት በመገንዘቡ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው።”​—⁠ሥራ 10:17-48

7 ጴጥሮስ በሙሴ ሕግ ሥር ያልነበሩት አሕዛብ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ መሆን ይችላሉ ወደሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ያደረገው ምንድን ነው? መንፈሳዊ ግንዛቤ አግኝቶ ስለነበረ ነው። አምላክ መንፈሱን ባልተገረዙት አሕዛብ ላይ በማፍሰስ የተቀበላቸው መሆኑን በማሳየቱ ጴጥሮስ ለጥምቀት የሚበቁ መሆናቸውን ተገንዝቧል። በተመሳሳይም ጴጥሮስ አሕዛብ ክርስቲያኖች ከመጠመቃቸው በፊት የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ አምላክ እንደማይፈልግባቸው የተገነዘበ ይመስላል። በዚያን ዘመን ኖረህ ቢሆን ኖሮ እንደ ጴጥሮስ አመለካከትህን ለማስተካከል ፈቃደኛ ትሆን ነበር?

አንዳንዶች ‘ሞግዚቱን’ መከተላቸውን ቀጥለው ነበር

8. በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ግዝረትን በሚመለከት ከጴጥሮስ የተለየ ምን አመለካከት ነበራቸው? ለምንስ?

8 ጴጥሮስ ከቆርኔሌዎስ ቤት ከወጣ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም አቀና። ያልተገረዙ አሕዛብ ‘የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ’ የሚገልጸው ዜና ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ጉባኤ ደረሰ። አንዳንድ አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት ይህን ሲሰሙ በጣም ተረበሹ። (ሥራ 11:1-3) “ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች” አሕዛብ የኢየሱስ ተከታዮች መሆን እንደሚችሉ ቢቀበሉም እነዚህ አይሁዳውያን ያልሆኑ አሕዛብ ለመዳን የሙሴን ሕግ መጠበቅ ይኖርባቸዋል ብለው ተከራከሩ። አሕዛብ በብዛት በሚገኙበት አካባቢ በሚኖሩት ጥቂት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ግን ግዝረት አከራካሪ ጉዳይ አልነበረም። እነዚህ ሁለት አመለካከቶች ለ13 ዓመታት ዘልቀው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ይህ ክርክር በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ በተለይ ደግሞ አይሁዳውያን አካባቢ ለሚኖሩ አሕዛብ ትልቅ ፈተና ሆኖ ነበር!

9. ግዝረትን በተመለከተ የተነሳው ውዝግብ መፍትሔ ማግኘት ያስፈልገው የነበረው ለምንድን ነው?

9 ኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች በ49 እዘአ ጳውሎስ ይሰብክ ወደነበረበት ወደ ሶርያ አንጾኪያ በመጡ ጊዜ አለመግባባቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። ከኢየሩሳሌም የመጡት እነዚህ ክርስቲያኖች ክርስትናን የተቀበሉ አሕዛብ በሕጉ መሠረት መገረዝ አለባቸው ብለው ማስተማር ጀመሩ። ይህም በእነርሱና በእነጳውሎስ መካከል ከፍተኛ ጠብና ጭቅጭቅ እንዲፈጠር አደረገ! ክርክሩ ቶሎ እልባት ካላገኘ ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ የመጡ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ማደናቀፉ የማይቀር ነበር። ስለሆነም ለተነሳው አከራካሪ ጉዳይ የማያዳግም እልባት ለማስገኘት ጳውሎስና ሌሎች ጥቂት ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱና የክርስቲያን የአስተዳደር አካሉን እንዲያነጋግሩ ዝግጅት ተደረገ።​—⁠ሥራ 15:1, 2, 24

ከብዙ አለመግባባት በኋላ የተገኘ የአቋም አንድነት!

10. የአስተዳደር አካሉ አሕዛብን በተመለከተ አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት የተነጋገረባቸው አንዳንድ ነጥቦች ምንድን ናቸው?

10 በዚህ ስብሰባ ላይ አንዳንዶች ግዝረትን ደግፈው ሌሎች ደግሞ የተለየ አቋም በመያዝ የተከራከሩ ይመስላል። ሆኖም በስሜት ለመመራት አልፈቀዱም። ከፍተኛ የሐሳብ ፍጭት ከተካሄደ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ ባልተገረዙ አሕዛብ መካከል ያደረገውን ታላቅ ሥራ ገለጹ። አምላክ ባልተገረዙ አሕዛብ ላይ ቅዱስ መንፈሱን እንዳፈሰሰ አብራሩ። ከዚያም ‘ታዲያ አምላክ የተቀበላቸውን ሰዎች ክርስቲያን ጉባኤ አልቀበልም ሊል ይችላልን?’ የሚል ጥያቄ አቀረቡ። ቀጥሎም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ከቅዱሳን ጽሑፎች አንድ ክፍል በማንበብ በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት እንዲገነዘቡ አደረገ።​—⁠ሥራ 15:4-17

11. ግዝረትን በተመለከተ ውሳኔውን ያስተላለፉት ሰዎች ምን ነገር እንዲያሸንፋቸው አልፈቀዱም? ያደረጉትን ውሳኔ ይሖዋ እንደባረከላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?

11 ሁሉም የአስተዳደር አካሉ የሚሰጠውን ውሳኔ ለመስማት በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። የአስተዳደር አካሉ አባላት አይሁዳዊ መሆናቸው ግዝረትን የሚደግፍ ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ይገፋፋቸው ይሆን? በጭራሽ። እነዚህ ታማኝ ወንዶች ቅዱሳን ጽሑፎች የሚናገሩትን ለመታዘዝና የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚሰጣቸውን አመራር ለመከተል የቆረጡ ነበሩ። የአስተዳደር አካሉ አግባብነት ያላቸውን አስተያየቶች በሙሉ ካዳመጠ በኋላ አሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝና የሙሴን ሕግ መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው በአንድ ድምፅ ወሰነ። ወንድሞች ይህን ውሳኔ ሲሰሙ እጅግ ደስ አላቸው፤ ጉባኤዎችም ‘በቁጥር ዕለት ዕለት ይበዙ’ ጀመር። ግልጽ ለሆነው ለዚህ ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ታዛዥነታቸውን ያሳዩ እነዚህ ክርስቲያኖች በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ መልስ በማግኘታቸው ተባርከዋል። (ሥራ 15:​19-​23, 28, 29፤ 16:​1-5) ሆኖም መልስ የሚያሻው አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይቀራል።

አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል?

12. መልስ ሳያገኝ የቀረው የትኛው ጥያቄ ነው?

12 የአስተዳደር አካሉ አሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝ እንደማያስፈልጋቸው በግልጽ አመልክቷል። ሆኖም አይሁዳውያን ክርስቲያኖችስ? የአስተዳደር አካሉ ባስተላለፈው ውሳኔ ውስጥ ይህን በተመለከተ የተጠቀሰ ነገር የለም።

13. ለመዳን የሙሴን ሕግ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ መከራከር ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?

13 ‘ለሕጉ ይቀኑ የነበሩ’ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ልጆቻቸውን መግረዝና ከሕጉ ውስጥ አንዳንድ ክፍሎችን መጠበቃቸውን ቀጥለውበት ነበር። (ሥራ 21:20) ሌሎች ደግሞ አልፈው በመሄድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ለመዳን ሕጉን መጠበቅ እንዳለባቸው እስከመከራከር ደርሰው ነበር። ይህም ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ አመለካከት እንደነበራቸው ያሳያል። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት የእንስሳት መሥዋዕት እንዴት ሊያቀርብ ይችላል? የእንስሳት መሥዋዕት በክርስቶስ መሥዋዕት ተተክቷል። አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር እንዳይቀራረቡ ስለሚያዝዘው ሕግስ ምን ለማለት ይቻላል? ቀናተኛ ክርስቲያን ወንጌላውያን ከዚህ ሕግ ነፃ ካልሆኑ ኢየሱስ አሕዛብን ሁሉ እንዲያስተምሩ የሰጣቸውን ተልእኮ እንዴት መፈጸም ይችላሉ? (ማቴዎስ 28:​19, 20፤ ሥራ 1:​8፤ 10:​28) a የአስተዳደር አካሉ ባደረጋቸው ስብሰባዎቸ ላይ ይህ ጉዳይ እንደተነሳ የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። ሆኖም ጉባኤው በራሱ ፍላጎት እንዲመራ አልተተወም።

14. ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸው ደብዳቤዎች ሕጉን በተመለከተ ምን መመሪያ ይዘዋል?

14 በዚህ ወቅት ከአስተዳደር አካሉ በተላከ ደብዳቤ ሳይሆን ሐዋርያት በመንፈስ አነሳሽነት በጻፏቸው ደብዳቤዎች አማካኝነት መመሪያ ደረሳቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት አይሁዳውያንና አሕዛብ ኃይለኛ መልእክት ያዘለ ደብዳቤ ላከ። በላከው በዚህ ደብዳቤ ላይ አንድ ሰው አይሁዳዊ የሚባለው ‘በስውር እንደሆነና መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ እንደሆነ’ አብራርቷል። (ሮሜ 2:28, 29) በዚሁ ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ ክርስቲያኖች በሕጉ ሥር እንዳልሆኑ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ተጠቀመ። አንዲት ሴት በአንድ ጊዜ ሁለት ባል ሊኖራት እንደማይችል ገለጸ። ሆኖም ባሏ ከሞተ ሌላ ለማግባት ነፃ ትሆናለች። ከዚያም ጳውሎስ ምሳሌውን በመጠቀም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ እየታዘዙ ለክርስቶስ ሊሆኑ እንደማይችሉ አስገነዘበ። ከክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን እንዲችሉ ‘ለሕጉ የሞቱ’ መሆን ነበረባቸው።​—⁠ሮሜ 7:1-5 አ.መ.ት

አንዳንድ አይሁዳውያን ነጥቡን ሳያስተውሉ የቀሩት ለምን ነበር?

15, 16. አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሕጉን በተመለከተ ነጥቡን መረዳት የተሳናቸው ለምን ነበር? ይህ ሁኔታ በመንፈሳዊ ነቅቶ የመኖርን አስፈላጊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

15 ጳውሎስ ሕጉን በማስመልከት የሰጠው ማብራሪያ የሚያሻማ አልነበረም። ታዲያ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነጥቡን ሳይገነዘቡ የቀሩት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት መንፈሳዊ ማስተዋል ይጎድላቸው ስለነበር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገብን ችላ ብለው ነበር። (ዕብራውያን 5:11-14) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ የመገኘት ልማድ አልነበራቸውም። (ዕብራውያን 10:23-25) ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ ቤተ መቅደስንና የክህነት አገልግሎትን የመሰሉ የሚታዩና የሚጨበጡ ነገሮችን ያቀፈ በመሆኑ አንዳንዶች ነጥቡን በቀላሉ እንዳይረዱ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። ስለዚህም መንፈሳዊ ማስተዋሉ የተዳከመበት አንድ አይሁዳዊ በማይታዩ እውነታዎች ላይ ያተኮረውንና ጥልቅ ትምህርቶች ያቀፈውን ክርስትናን ከመቀበል ይልቅ ሕጉን መከተል ይቀልለዋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:17, 18

16 ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ አይሁዳውያን ሕጉን መጠበቅ አለብን ብለው እንዲከራከሩ ያደረጋቸው ሌላ ምክንያት ምን እንደሆነ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በግልጽ አስፍሯል። እነዚህ ሰዎች አብዛኛው ሕዝብ የሚያምንበትን ሃይማኖት በመከተል በሕዝቡ ዘንድ ከበሬታን ማግኘት ፈልገው እንደነበር ገልጿል። በማኅበረሰቡ ዘንድ ክርስቲያን ሆነው ከመታወቅ ይልቅ የሕዝቡን ተቀባይነት ለማግኘት ማንኛውንም የአቋም ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች ነበሩ። ይበልጥ የሚያስደስታቸው የአምላክን ሞገስ ማግኘት ሳይሆን የሰዎችን ተቀባይነት ማግኘት ነበር።​—⁠ገላትያ 6:12

17. ሕግ መጠበቅን በተመለከተ ሁሉም ነገር በማያሻማ መንገድ ግልጽ የሆነው መቼ ነው?

17 ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያኖች በመንፈስ ተነሳስተው የጻፏቸውን ደብዳቤዎች በጥንቃቄ ያጠኑ አስተዋይ ክርስቲያኖች ሕጉን በሚመለከት ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ሆኖም ሁሉም አይሁዳዊ ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ መጠበቅን በተመለከተ ሁኔታው ይበልጥ ግልጽ የሆነላቸው በ70 እዘአ ነበር። በዚህ ዓመት አምላክ ኢየሩሳሌምን፣ ቤተ መቅደሱንና ከክህነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ዝርዝር መረጃዎችን በሙሉ እንዲጠፉ ባደረገ ጊዜ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው በማያሻማ መንገድ ግልጽ ሆነላቸው። ጥፋቱ የትኛውንም የሙሴን ሕግ ክፍል ለመጠበቅ ወደማይችሉበት ደረጃ ላይ አደረሳቸው።

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት

18, 19. (ሀ) በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነን ለመኖር ምን ዓይነት አመለካከት ማዳበር አለብን? ምንስ ዓይነት አመለካከት ማስወገድ ይኖርብናል? (ለ) ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚሰጡንን መመሪያ በመከተል ረገድ ከጳውሎስ ምን እንማራለን? (ገጽ 24 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

18 ይህን የጥንት ታሪክ ከመረመርን በኋላ ምናልባት የሚከተሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል:- ‘በዚያ ዘመን ኖሬ ቢሆን ኖሮ ደረጃ በደረጃ ለተገለጠው ለአምላክ ፈቃድ ምን ዓይነት አመለካከት ይኖረኝ ነበር? ሕጉን በግትርነት እከተል ነበር? ወይስ ትክክለኛው ግንዛቤ እስኪገለጥ ድረስ በትዕግሥት እጠባበቅ ነበር? ትክክለኛው ግንዛቤ በሚገለጥበት ጊዜስ በደስታ እቀበለው ነበርን?’

19 በዚያን ጊዜ ኖረን ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት አመለካከት እንይዝ እንደነበር አሁን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ሆኖም እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ‘በዛሬው ጊዜ በምናምንባቸው በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ማስተካከያ ቢደረግ የተደረገውን ለውጥ እንቀበላለን? (ማቴዎስ 24:45) ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ በሚሰጥበት ጊዜ በሕጉ ቃል ላይ ድርቅ ከማለት ይልቅ ሕጉ የተሰጠበትን ዓላማ ተረድተን በሥራ ላይ ለማዋል እንጥራለን? (1 ቆሮንቶስ 14:20) ለጥያቄዎቻችን መልስ እንዳላገኘን ሲሰማን ይሖዋ ነገሮችን ግልጽ የሚያደርግበትን ጊዜ በትዕግሥት እንጠባበቃለን?’ በዛሬ ጊዜ የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ ጥሩ አድርገን መመገባችን እጅግ አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን “እንዳንወሰድ” ይጠብቀናል። (ዕብራውያን 2:1) ይሖዋ በቃሉ፣ በመንፈሱና በምድራዊ ድርጅቱ በኩል መመሪያ በሚሰጠን ጊዜ በጥንቃቄ እናዳምጥ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ደስታና እርካታ የሞላበት የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ጴጥሮስ ወደ ሶርያ አንጾኪያ በሄደ ጊዜ እዚያ የነበሩ አሕዛብ አማኞች ተቀብለው አስተናግደውት ነበር። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም በመጡ ጊዜ ጴጥሮስ ‘ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ አፈገፈገ።’ ክርስትናን የተቀበሉት አሕዛብ በጣም የሚያከብሩት እንዲህ ያለው ሐዋርያ ከእነርሱ ጋር ላለመብላት ወደኋላ ማፈግፈጉን ሲመለከቱ ስሜታቸው ተነክቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።​—⁠ገላትያ 2:11-13

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የሙሴ ሕግ ‘ወደ ክርስቶስ ከሚያመጣ ሞግዚት’ ጋር የተመሳሰለው በምን መንገድ ነው?

• እውነትን በተመለከተ የተገኘውን አዲስ ግንዛቤ በመቀበል ረገድ በጴጥሮስና ‘ከተገረዙት ወገን በሆኑት ሰዎች’ መካከል የታየውን ልዩነት እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?

• በዛሬው ጊዜ ይሖዋ እውነትን ስለሚገልጥበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23, 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጳውሎስ ያጋጠመውን ፈተና በትሕትና ተወጣ

ጳውሎስ የተሳካ ሚስዮናዊ ጉዞ ካደረገ በኋላ በ56 እዘአ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እዚያም ያልጠበቀው አንድ ፈተና ገጠመው። ጳውሎስ ሕጉ በክርስቲያኖች ላይ አይሠራም ብሎ እንዳስተማረ የሚገልጸው ዜና ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ጉባኤ ደርሶ ነበር። ሽማግሌዎች በቅርቡ ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዳውያን ጳውሎስ ሕጉን በማስመልከት የሰጠውን ግልጽ ትምህርት ሲሰሙ ክርስቲያኖች ለይሖዋ ዝግጅቶች አክብሮት እንደሌላቸው አድርገው በማሰብ ይሰናከሉ ይሆናል የሚል ፍርሃት አድሮባቸው ነበር። በጉባኤው ውስጥ ስለት ምናልባትም የናዝራዊነትን ስለት የተሳሉ አራት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነበሩ። በሕጉ መሠረት የተሳሉትን ለመፈጸም ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ነበረባቸው።

ሽማግሌዎቹ ጳውሎስ ከእነዚህ አራት ሰዎች ጋር ወደ ቤተ መቅደስ አብሯቸው እንዲሄድና ወጪያቸውን እንዲሸፍን ጠየቁት። ጳውሎስ ለመዳን ሕጉን መጠበቅ እንደማያስፈልግ የሚያብራሩ ቢያንስ ሁለት ደብዳቤዎች በመንፈስ አነሳሽነት ጽፎ ነበር። እንደዚያም ሆኖ ለሌሎች ሰዎች ሕሊና ያስብ ነበር። ከዚያ ቀደም ሲል “ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፣ . . . ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ” በማለት ጽፎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:20-23) ጳውሎስ ወሳኝ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንደሚጥስ ሆኖ ስላልተሰማው ሽማግሌዎቹ በሰጡት ሐሳብ መሠረት ከሰዎቹ ጋር አብሮ ለመሄድ ተስማማ። (ሥራ 21:15-26) ሽማግሌዎቹ ያሉትን ቢያደርግ ምንም ስህተት የለውም። የስለት ሥርዓት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ አልነበረም። ቤተ መቅደሱም የጣዖት አምልኮ ሳይሆን ንጹሕ አምልኮ የሚካሄድበት ሥፍራ ነው። ስለዚህም ጳውሎስ ለሌሎች እንቅፋት እንዳይሆን ሲል እንደተባለው አደረገ። (1 ቆሮንቶስ 8:13) ጳውሎስ እንዲህ ለማድረግ ትሕትና እንደጠየቀበት ምንም ጥርጥር የለውም። ይህም ለእርሱ ያለንን አድናቆት ከፍ ያደርገዋል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለተወሰኑ ዓመታት የሙሴን ሕግ የሚመለከቱ የተለያዩ አመለካከቶች በክርስቲያኖች መካከል ሰፍነው ነበር