“ለሰው ሁሉ የዋህነትን” አሳዩ
“ለሰው ሁሉ የዋህነትን” አሳዩ
“ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው።”—ቲቶ 3:1, 2
1. የዋህነትን ማሳየት ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ይህን ማሳሰቢያ ለመከተል ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የራስ ወዳድነት ምኞቶችንና የክርስቶስን ምሳሌ እንዳንከተል የሚያደርጉ ባሕርያትን ስለወረስን ይህን ማድረግ ቀላል እንደማይሆንልን አይካድም። (ሮሜ 3:23፤ 7:21-25) ይሁን እንጂ የዋህነት ማሳየትን በተመለከተ አስፈላጊውን ጥረት ካደረግን ሁላችንም ሊሳካልን ይችላል። ሆኖም የእኛ ጥረት ብቻውን በቂ አይደለም። ሌላ ምን ያስፈልጋል?
2. “ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ” ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
2 አምላካዊ የዋህነት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ክፍል ነው። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለሚሰጠን አመራር ታዛዥ በሆንን መጠን የመንፈሱን ፍሬዎች ይበልጥ እናፈራለን። ለሰው ሁሉ “የዋህነትን ሁሉ” ማሳየት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። (ቲቶ 3:2) እንግዲያው የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅና ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ‘የዕረፍት’ ምንጭ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።—ማቴዎስ 11:29፤ ገላትያ 5:22, 23
በቤተሰብ ክልል ውስጥ
3. የዓለም መንፈስ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ተጽዕኖ እንዳሳደረ የሚያሳየው ምንድን ነው?
3 የዋህነትን ማሳየት የሚኖርብን አንደኛው መስክ የቤተሰብ ክልል ነው። የመኪና አደጋና የወባ በሽታ አንድ ላይ ተዳምረው በሴቶች ላይ ከሚያስከትሉት ጉዳት ይልቅ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት በሴቶች ጤንነት ላይ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትል የዓለም ጤና ድርጅት ገምቷል። ለምሳሌ ያህል በእንግሊዝ፣ ለንደን ከሚፈጸመው ወንጀል ውስጥ አንድ አራተኛው የሚፈጸመው በቤት ውስጥ ነው። ብዙውን ጊዜ ፖሊሶች ስሜታቸውን ‘በጩኸትና በስድብ’ መግለጽ የሚቀናቸው ሰዎች ያጋጥሟቸዋል። ከዚህ የባሰው ደግሞ አንዳንድ ባልና ሚስት ‘መራርነት’ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት እንዲያበላሽባቸው ፈቅደዋል። እነዚህ ነገሮች “የዓለም መንፈስ” መጥፎ ነጸብራቅ ስለሆኑ በክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ ተቀባይነት የላቸውም።—ኤፌሶን 4:31፤ 1 ቆሮንቶስ 2:12
4. የዋህነት በቤተሰብ ውስጥ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል?
4 ዓለማዊ ዝንባሌዎችን ለመከላከል የአምላክ መንፈስ ያስፈልገናል። “የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ።” (2 ቆሮንቶስ 3:17) ፍቅር፣ ደግነት፣ ራስን መግዛትና ትዕግሥት ፍጽምና በሚጎድላቸው ባልና ሚስት መካከል ያለውን አንድነት ያጠናክራሉ። (ኤፌሶን 5:33) የዋህነትን ማሳየት በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ከሚታየው ጥልና ጭቅጭቅ በተቃራኒ በቤት ውስጥ ደስታ እንዲሰፍን ይረዳል። አንድ ሰው የሚናገረው ነገር ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ቢሆንም ውስጣዊ ስሜቱን የሚያሳየው ሐሳቡን የገለጸበት መንገድ ነው። የሚያሳስበንንና የሚያስጨንቀንን ነገር በየዋህነት መንፈስ መናገራችን ውጥረት ለማርገብ ያስችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች” ሲል ጽፏል።—ምሳሌ 15:1
5. የዋህነት በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ምን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል?
5 የዋህነት በተለይ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ባሕርይ ነው። የዋህነት በደግነት ምግባር ከታገዘ አማኝ ያልሆነው ወገን የይሖዋ አምላኪ እንዲሆን ሊረዳው ይችላል። ጴጥሮስ ለክርስቲያን ሚስቶች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።”—1 ጴጥሮስ 3:1-4
6. የዋህነት በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን ወዳጅነት ሊያጠናክር የሚችለው እንዴት ነው?
6 በተለይ የአንድ ቤተሰብ አባላት ለይሖዋ ፍቅር የሚጎድላቸው ከሆነ በወላጆችና በልጆች መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ ይሆናል። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ቤተሰቦች በሙሉ የዋህነትን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው” በማለት ለአባቶች ምክር ሰጥቷል። (ኤፌሶን 6:4) የዋህነት በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ወላጆችንና ልጆችን የሚያስተሳስራቸው ሰንሰለት ይጠናከራል። አራት ወንድሞች ያሉት ዲን ስለ አባቱ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “አባባ የዋህ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜዬ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜም እንኳ ከእርሱ ጋር የተጨቃጨቅንበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። የሚያናድድ ነገር ቢያጋጥመውም ይህ ባሕርይው አይለወጥም ነበር። ሳጠፋ ከመኝታ ክፍሌ እንዳልወጣ ወይም የምወዳቸውን ነገሮች እንዳላደርግ ይከለክለኛል እንጂ ተጨቃጭቀን አናውቅም። በመካከላችን የነበረው ዝምድና የአባትና የልጅ ብቻ ሳይሆን ጓደኛችንም ነበር። በመሆኑም እርሱን ላለማሳዘን እንጠነቀቃለን።” በእርግጥም የዋህነት በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ ያጠናክረዋል።
በአገልግሎት ላይ ስንሆን
7, 8. በመስክ አገልግሎት ላይ ስንሆን የዋህነት ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 ከዚህም በተጨማሪ በመስክ አገልግሎት ላይ በምንሆንበት ጊዜ የዋህነትን ማሳየታችን አስፈላጊ ነው። ለሌሎች የመንግሥቱን ምሥራች በምንሰብክበት ጊዜ የተለያየ ዓይነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ያጋጥሙናል። አንዳንዶች የተስፋውን መልእክት በደስታ ሲቀበሉ ሌሎች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ጥሩ ምላሽ ላይሰጡን ይችላሉ። እስከ ምድር ዳር ድረስ እንድንመሠክር የተሰጠንን ተልእኮ መፈጸም እንድንችል ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜ የዋህነትን ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ሥራ 1:8፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:5
8 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 3:15) ክርስቶስን ምሳሌያችን አድርገን በጥብቅ ስለምንከተል በምንመሠክርላቸው ጊዜ ለሚቃወሙን ሰዎች የዋህነትና አክብሮት ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። እንዲህ ማድረጋችን አብዛኛውን ጊዜ አስደናቂ ውጤት ያስገኛል።
9, 10. በመስክ አገልግሎት ላይ የዋህነትን ማሳየት ጠቃሚ መሆኑን የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
9 ኪት በራቸው ተንኳኩቶ ባለቤቱ በከፈተችበት ጊዜ እርሱ ውስጥ ነበር። የኪት ባለቤት በሩን ያንኳኳው ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ስታውቅ እናንተ ለልጆቻችሁ እንኳ የማታዝኑ ጨካኞች ናችሁ ብላ በንዴት ተናገረችው። ወንድም በትዕግሥት ካዳመጣት በኋላ ረጋ ባለ መንፈስ “እኛ እንኳ እንዲህ አናደርግም። ፈቃድሽ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው እንደሚያምኑ ብገልጽልሽ ደስ ይለኛል” ብሎ ነገራት። ኪት ሲያዳምጣቸው ከቆየ በኋላ ወደ እነርሱ መጥቶ ንግግሩን አስቆመው።
10 ቆየት ብሎ ባልና ሚስቱ ወንድምን ክፉ ቃል በመናገራቸው ጸጸት ተሰማቸው። ባሳየው የዋህነት በጥልቅ ተነኩ። ከአንድ ሳምንት በኋላ ተመልሶ በመምጣቱ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ ኪትና ባለቤቱ የሚያምንበትን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያሳያቸው ጠየቁት። “ከዚያ በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው በሚያነጋግሩን ጊዜ እናዳምጣቸው ነበር” በማለት ተናግረዋል። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ተስማምተው በመጨረሻ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት አሳዩ። ኪትንና ባለቤቱን መጀመሪያ ያነጋገራቸው ወንድም ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ይህ ወንድም ባልና ሚስቱን ከዓመታት በኋላ ባገኛቸው ጊዜ መንፈሳዊ ወንድሙና እህቱ መሆናቸውን አወቀ። የዋህነት ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
11. የዋህነት አንድ ሰው የክርስትና ትምህርቶችን እንዲቀበል ሁኔታዎችን ሊያመቻች የሚችለው እንዴት ነው?
11 ሃሮልድ በውትድርናው ዓለም ያሳለፈው ሕይወት ከባድ የበቀል ስሜት ያሳደረበት ከመሆኑም በላይ የአምላክን መኖር እንዲጠራጠር አድርጎታል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ጠጥቶ ሲያሽከረክር የነበረ ሰው ባደረሰበት አደጋ ምክንያት ሃሮልድ የአካል ጉዳተኛ ሆነ። የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቱ መጥተው ሲያነጋግሩት ሁለተኛ ቤቱ እንዳይመጡ አሳሰባቸው። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ቢል የተባለ የይሖዋ ምሥክር የሃሮልድ ጎረቤት ለሆነ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ሄደ። ቢል በስህተት የሃሮልድን በር አንኳኳ። ሃሮልድ በሁለት ምርኩዞች ታግዞ በሩን ከከፈተለት በኋላ ቢል እንደተሳሳተ ገብቶት ወዲያው ይቅርታ ጠየቀው። ሃሮልድ ምን ምላሽ ሰጠ? ሃሮልድ የይሖዋ ምሥክሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ እንደገነቡ የሚያሳይ ዜና በቴሌቪዥን ተመልክቶ ነበር። እርግጥ ቢል ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቀው ነገር የለም። በጣም ብዙ ሰዎች በአንድነት ሲሠሩ በማየቱ ከመደነቁ የተነሳ ለይሖዋ ምሥክሮች የነበረው አመለካከት ተለወጠ። ቢል በትህትና ይቅርታ በመጠየቁና ደስ የሚል የየዋህነት ባሕርይ በማሳየቱ ሃሮልድ ከዚህ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በመጡ ቁጥር የሚሉትን ለመስማት ፈቃደኛ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ አጥንቶ እድገት ካደረገ በኋላ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
በጉባኤ ውስጥ
12. የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የትኛውን ዓለማዊ ባሕርይ መከላከል ይኖርባቸዋል?
12 የዋህነት ማሳየት አስፈላጊ የሚሆንበት ሦስተኛው መስክ ክርስቲያን ጉባኤ ነው። በዛሬው ጊዜ በሰዎች መካከል ቅራኔ ሲፈጠር ማየት የተለመደ ነው። ሥጋዊ አመለካከት ባላቸው ሰዎች ዘንድ ሙግት፣ ጭቅጭቅና ንትርክ የዕለት ተዕለት ገጠመኝ ነው። እንዲህ ያለው ዓለማዊ ባሕርይ አልፎ አልፎ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሰርጎ በመግባት ጠብ ሲፈጠርና የቃላት ጦርነት ሲነሳ ይታያል። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ሲመለከቱ በጣም ያዝናሉ። ይሁንና ለይሖዋና ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር የተሳሳቱትን ለማስተካከል ጥረት እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል።—ገላትያ 5:25, 26
13, 14. ‘ተቃዋሚዎችን በየዋህነት መቅጣት’ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ የጉባኤው አባላት በጳውሎስና በአገልግሎት ጓደኛው በጢሞቴዎስ ላይ ችግር ፈጥረውባቸው ነበር። ጳውሎስ “ለውርደት” በሆኑ ዕቃዎች ከተመሰሉ ወንድሞች ራሱን እንዲጠብቅ ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆታል። ጳውሎስ “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም . . . ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ” በማለት የዚህን ምክንያት ገልጾለታል። ቁጣ የሚያነሳሳ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜም የዋህነትን የምናሳይ ከሆነ መከፋፈልን የሚያመጡ ወንድሞች አብዛኛውን ጊዜ የሚሰነዝሩትን ትችት ቆም ብለው እንዲያስቡበት ያደርጋቸዋል። ጳውሎስ በመቀጠል እንደጻፈው ይሖዋ ደግሞ “እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋል።” (2 ጢሞቴዎስ 2:20, 21, 24, 25) ጳውሎስ ገርነትንና ትዕግሥትን ከየዋህነት ጋር አያይዞ እንደገለጸው ልብ በል።
14 ጳውሎስ ቃሉን በተግባር የሚያውል ሰው ነበር። በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩትን ‘ዋነኛ ሐዋርያት’ አስመልክቶ ሲናገር “እኔም ራሴ ጳውሎስ፣ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፣ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፣ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ” በማለት ወንድሞችን አሳስቧቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 10:1፤ 11:5) ጳውሎስ በእርግጥም ክርስቶስን በሚገባ መስሏል። እነዚህን ወንድሞች የመከረው በክርስቶስ “የዋህነት” መሆኑን ልብ በል። ራሱን እንደ አለቃ በመቁጠር አልተጫናቸውም። በጉባኤው ውስጥ የነበሩ ጥሩ ልብ ያላቸው ወንድሞች የተሰጣቸውን ምክር በደስታ እንደተቀበሉ ምንም ጥርጥር የለውም። በጉባኤው ውስጥ የነበረው የሻከረ ግንኙነት እንዲሻሻል እንዲሁም ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን በማድረግ ረድቷቸዋል። ይህ ሁላችንም ልንኮርጀው የሚገባ ባሕርይ አይደለምን? በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎች የክርስቶስንና የጳውሎስን አርዓያ መከተል ይኖርባቸዋል።
15. ምክር በምንሰጥበት ጊዜ የዋህነት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ሌሎችን የመርዳት ኃላፊነታችንን መወጣት የሚኖርብን የጉባኤው ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ችግሮች ከመከሰታቸውም በፊት ወንድሞች ፍቅራዊ መመሪያ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው . . . አቅኑት” ሲል አሳስቧል። ሆኖም ይህን ማድረግ ያለባቸው እንዴት ነው? “በየዋህነት መንፈስ” መሆን አለበት። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ “አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ” የሚለውን ምክር መከተል ይኖርባቸዋል። (ገላትያ 6:1) የተሾሙ ወንዶችን ጨምሮ ሁሉም ክርስቲያኖች የኃጢአት ዝንባሌ የሚያጠቃቸው በመሆኑ ‘የየዋህነትን መንፈስ’ ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። የሆነ ሆኖ የተሳሳተው ሰው በቀላሉ መስተካከል የሚችለው በየዋህነት መንፈስ ከተረዳ ነው።
16, 17. አንድ ሰው የሚሰጠውን ምክር ሳያንገራግር እንዲቀበል ምን ሊረዳው ይችላል?
16 “አቅኑት” ተብሎ የተተረጎመው የጥንቱ ግሪክኛ ቃል ውልቃትን ወደ ቦታው መመለስን ሊያመለክት ይችላል። ይህም ከባድ ሥቃይ የሚያስከትል ሕክምና ነው። ወጌሻው እሽቱ ጥሩ ውጤት እንደሚኖረው በእርግጠኝነትና በልበ ሙሉነት መናገሩ በራሱ የሚያረጋጋ ነው። ታማሚው ይህን ሲሰማ ጭንቀቱ ይቀንስለታል። በተመሳሳይም መንፈሳዊ የማቅናት ሥራ ህመም ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም የዋህነት ምክርን በቀላሉ ለመቀበል ይረዳል። በመሆኑም እንደቀድሞው ሰላማዊ ዝምድና እንዲሰፍን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የተሳሳተው ሰው አካሄዱን እንዲለውጥ ይረዳዋል። መጀመሪያ ላይ ምክሩን ለመቀበል ቢያንገራግርም እንኳን ምክር ሰጪው ወንድም የዋህነት ማሳየቱ ቅዱስ ጽሑፋዊውን ምክር ላለመቀበል የሚቀርብን ሰበብ ለማሸነፍ ያስችላል።—ምሳሌ 25:15
17 ሌሎችን ለማቅናት እርዳታ ሲሰጥ ምክሩ ብዙውን ጊዜ እንደ ወቀሳ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “ለሌሎች እርማት በምንሰጥበት ጊዜ ቁጣ ሊቀናን ስለሚችል ትሕትና ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው።” ከትሕትና የመነጨ የዋህነት ማዳበር ምክር ሰጪው እንዲህ ያለውን አደጋ እንዲያስወግድ ይረዳዋል።
“ለሰው ሁሉ”
18, 19. (ሀ) ክርስቲያኖች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባላቸው ግንኙነት የዋህነትን ማሳየት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ለባለሥልጣናት የዋህነትን እንዲያሳዩ ምን ይረዳቸዋል? ይህስ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
18 ብዙዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት የዋህነትን ማሳየት ይከብዳቸዋል። በሥልጣን ላይ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ኃይለኛና አዘኔታ የሌላቸው እንደሆኑ አይካድም። (መክብብ 4:1፤ 8:9) ይሁን እንጂ ለይሖዋ ያለን ፍቅር አቻ የሌለውን ሥልጣኑን እንድንቀበልና ለመንግሥት ባለሥልጣኖች የሚገባቸውን አንጻራዊ ተገዥነት እንድናሳይ ይረዳናል። (ሮሜ 13:1, 4፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2) በከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ለሕዝብ የምንሰጠውን ምሥክርነት ለማስቆም ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜም እንኳ ለይሖዋ የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ ክፍት በሆኑልን አጋጣሚዎች ሁሉ ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን።—ዕብራውያን 13:15
19 ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ወደ ጠብ ማምራት አንፈልግም። የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሳንጥስ ምክንያታዊነት ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። በዓለም ዙሪያ በ234 አገሮች ውስጥ ወንድሞቻችን አገልግሎታቸውን ማከናወን የቻሉት በዚህ መንገድ ነው። ጳውሎስ “ለገዦችና ለባለሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው” በማለት የሰጠውን ምክር እንከተላለን።—ቲቶ 3:1, 2
20. የዋህነትን የሚያሳዩ ክርስቲያኖች ምን በረከት ይጠብቃቸዋል?
20 የዋህነትን የሚያሳዩ ሁሉ ወደፊት የተትረፈረፈ በረከት ያገኛሉ። ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:5) በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ወንድሞች የዋህነትን ማሳየት መቀጠላቸው ደስታቸውንና በምድር ላይ የመግዛት መብታቸውን እንዳያጡ ያስችላቸዋል። “የሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የዋህነትን ማሳየታቸውን በቀጠሉ መጠን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ሊጠባበቁ ይችላሉ። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16፤ መዝሙር 37:11) እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይጠብቀናል! እንግዲያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት” ኑሩ በማለት የሰጣቸውን ማሳሰቢያ ፈጽሞ ቸል አንበል።—ኤፌሶን 4:1, 2
ለክለሳ ያህል
• የዋህነትን ማሳየት
• በቤተሰብ ውስጥ፣
• በመስክ አገልግሎት ላይና
• በጉባኤ ውስጥ ምን ጥቅም አለው?
• የዋህ የሆኑ ሰዎች ምን በረከቶችን ያገኛሉ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተለይ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የዋህነትን ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዋህነት የቤተሰብን አንድነት ያጠናክራል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ እምነትህ ስታስረዳ የዋህነትና ጥልቅ አክብሮት አሳይ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በየዋህነት የተሰጠ ምክር አንድን የተሳሳተ ክርስቲያን እንዲመለስ ይረዳል