በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአክብሮት ተጋብዘዋል

በአክብሮት ተጋብዘዋል

በአክብሮት ተጋብዘዋል

የዛሬ 2, 000 ዓመት ገደማ ኢየሱስ ክርስቶስ ያቋቋመው የጌታ እራት በዓል እንዲያው ተራ የሆነ ታሪካዊ ክንውን አይደለም። በዓሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከበረበት ዕለት አንስቶ በሰዎች ሕይወት ላይ የጎላ ተጽዕኖ አሳድሯል። ብዙዎች በዚያ ዕለት ስለ ተፈጸሙት ክንውኖች የሚተርኩትን የወንጌል ዘገባዎች ሲያነብቡ ልባቸው ስለሚነካ የጌታ እራትን በተለያዩ መንገዶች ለማክበር ጥረት አድርገዋል።

ተከታዮቹ ይህን ልዩ በዓል ዘወትር እንዲያከብሩት ትእዛዝ የሰጣቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ስለሆነ ሰዎች በዓሉን ለማክበር ማሰባቸው አያስገርምም። ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” የሚል ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር።​—⁠ሉቃስ 22:19፤ 1 ቆሮንቶስ 11:23-25

እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ከበዓሉ ሙሉ ጥቅም ማግኘት እንዲችል በዓሉ ያዘለውን ትርጉም በሚመለከት ከአምላክ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት አለበት። ከዚህም በላይ በዓሉ መቼና እንዴት መከበር እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሐሳብ ማወቁ ጠቃሚ ነው።

በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ትእዛዙን በመከተል የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16, 2003 ምሽት ይሰበሰባሉ። ይህ ሥነ ሥርዓት ቅዱሳን ጽሑፎችን የሚመረምሩበት ከመሆኑም በላይ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ሲል በተናገረው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ለማጎልበትና ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ለማጠንከር ያስችላቸዋል። (ዮሐንስ 3:16) አንተም በዚህ ዕለት ምሽት አብረሃቸው በመሰብሰብ ለኢየሱስ ክርስቶስና ለሰማያዊ አባታችን ለይሖዋ አምላክ ያለህን ፍቅር እንድታጠናክርና በእነርሱ ላይ ያለህን እምነት እንድታጎለብት ልባዊ ግብዣ ቀርቦልሃል።