የጌታ እራት ምንድን ነው?
የጌታ እራት ምንድን ነው?
“የጌታ እራት” ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ብዙዎች ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈውን ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር እራት ሲበላ የሚያሳየውን የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ (1452-1519) ሥዕል ያስታውሱ ይሆናል። ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ሠዓሊያን፣ ጸሐፊዎችና የሙዚቃ ሰዎች የጌታ እራትን አስመልክተው የተለያዩ ሥራዎች አዘጋጅተዋል።
ይሁን እንጂ የጌታ እራት ምንድን ነው? ዛሬ ለምንኖረው ለእኛስ ምን ትርጉም አለው? ኢንሳይክሎፔዲያዎችና መዝገበ ቃላት የጌታ እራት (የመጨረሻው እራት ተብሎም ይጠራል) ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ከሐዋርያቱ ጋር የተመገበው ማዕድ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ እራት ኢየሱስ ከታማኝ ተከታዮቹ ጋር የተመገበው የመጨረሻው ማዕድ በመሆኑ አንዳንዶች የመጨረሻው እራት ብለው ይጠሩታል። ይህንን በዓል ያቋቋመው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በመሆኑ የጌታ እራት ተብሎ መጠራቱም ተገቢ ነው።
ባለፉት ዘመናት ብዙ ሰዎች ላመኑበት ነገር ሕይወታቸውን ሠውተዋል። የአንዳንዶቹ ሞት ለጊዜውም ቢሆን ለተወሰኑ ሰዎች ጥቅም አስገኝቷል። ይሁን እንጂ የእነዚህ ሰዎች መሥዋዕታዊ ሞት የቱንም ያህል ከፍ ተደርጎ የሚታይ ቢሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ያህል የጎላ ትርጉም የለውም። በችግር በተሞላው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወደፊትም ቢሆን የኢየሱስን ሞት ያህል ሁሉንም ሰው የሚጠቅም ሞት ሊኖር አይችልም። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው?
የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘትና የክርስቶስ ሞት ለአንተ የሚኖረውን ትርጉም ለመረዳት እንድትችል የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።