በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‘በአራራት’ እውነተኛውን አምልኮ አስከበረ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‘በአራራት’ እውነተኛውን አምልኮ አስከበረ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‘በአራራት’ እውነተኛውን አምልኮ አስከበረ

አንድ የሦስት ልጆች አባት የሆነ ጸጉረ ሸበቶ አርመናዊ በአገሩ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ተከስሶ ቀርቧል። የእርሱና የእምነት አጋሮቹ ነጻነት በአደጋ ላይ ነው። ይህ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ ስለ ሃይማኖታዊ እምነቶቹ ሲያብራራ ችሎቱ ያዳምጣል። ይህ የፍርድ ቤት ሙግት በዚያች አገር ለእውነተኛው አምልኮ እንዴት ታላቅ ድል እንዳስገኘ ለማወቅ እስቲ በመጀመሪያ ለጉዳዩ መነሻ የሆኑትን ክስተቶች እንመርምር።

አርሜኒያ ቱርክን በስተምሥራቅ የምታዋስንና ከታላቁ የካውካሰስ የተራራ ሰንሰለት በስተደቡብ የምትገኝ አገር ናት። ከሦስት ሚልዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች አሏት። ከዋና ከተማዋ ከየረቫን ሆኖ ዓይን የሚማርክ እይታ ያላቸውን ሁለቱን የአራራት ተራራ ጫፎች መመልከት የሚቻል ሲሆን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ወግ እንደሚለው ከዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ በኋላ የኖህ መርከብ ያረፈችው በእነዚህ ተራሮች ላይ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 8:4 a

የይሖዋ ምሥክሮች ከ1975 ጀምሮ በአርሜኒያ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። አርሜኒያ በ1991 ከቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን የሚመዘግብ የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ምክር ቤት ተቋቁሟል። ይሁን እንጂ ይህ ምክር ቤት የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት ያቀረቡትን ተደጋጋሚ ጥያቄ አልቀበልም ያለ ሲሆን ለዚህም በዋነኛነት ምክንያት ሆኖ የቀረበው ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ነው። በዚህም ምክ​ንያት ከ1991 ጀምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ ወጣት አርመናውያን ምሥክሮች ፍርድ ቤት ቀርበው የተወነጀሉ ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹ ወታደራዊ አገልግሎትን በተመለከተ ባላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋም የተነሳ ታስረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ የመንግሥት አቃቤ ሕግ ቢሮ በአካባቢው በሚገኘው የአቶሚክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በጥብቅና ሙያ ተቀጥሮ የሚሠራውንና ክርስቲያን ሽማግሌ የሆነውን የልዮቫ ማርካሪያንን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንዲመረምር ጥያቄ አቀረበ። በመጨረሻም ወንድም ማርካሪያን በክሩሽቼቭ አገዛዝ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና ለማጥፋት ተብሎ ከወጣው ሕግ የተወረሰውን አንቀጽ 244ን ተላልፏል በሚል ክስ ተመሠረተበት።

ይህ አንቀጽ ሃይማኖታዊ እምነቶችን ለማስተማር በሚል ሰበብ ‘ሕጋዊ እውቅና የሌለው ድርጅት በሚያደርገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ወጣቶችን የሚያባብል’ እና ‘አባላቱ የዜግነት ኃላፊነቶቻቸውን እንዳይወጡ ተጽዕኖ የሚያደርግ’ ሃይማኖታዊ ቡድንን ማደራጀትም ሆነ በበላይነት መምራት ወንጀል እንደሆነ ይደነግጋል። አቃቤ ሕጉ ክሱን በማስረጃ ለመደገፍ በሜትሳሞር ከተማ በሚደረገው በወንድም ማርካሪያን የሚመራው ስብሰባ ላይ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች የሚገኙ መሆኑን ጠቀሰ። እንዲሁም ወጣት የሆኑ የጉባኤው አባላት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ወንድም ማርካሪያን አስገድዷቸዋል በማለት ተከራከረ።

ክሱ መታየት ጀመረ

አርብ፣ ሐምሌ 20, 2001 በአማቪር የአውራጃ ፍርድ ቤት በዳኛ ማንዌል ሲሞንያን ሊቀመንበርነት ጉዳዩ መታየት ጀመረ። ሙግቱ እስከ ነሐሴ ወር ድረስ ቀጠለ። አቃቤ ሕጉ ያቀረባቸው ምሥክሮች ቃላቸውን ሲሰጡ በወንድም ማርካሪያን ላይ ከሰጡት የጽሑፍ ምሥክርነት ውስጥ ከፊሉን እንዲጽፉ ያዘዟቸው የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስቴር (በፊት ኬጂቢ ይባል የነበረው) አባላት እንደሆኑና በወረቀቶቹም ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት ተገድደው እንደሆነ አመኑ። እንዲያውም አንዲት ሴት “የይሖዋ ምሥክሮች መንግሥታችንን እና ሃይማኖታችንን ይቃወማሉ” ብላ እንድትመሰክር አንድ የደህንነት ኃላፊ እንዳዘዛት ተናገረች። ሴትየዋ በግል የምታውቀው አንድም የይሖዋ ምሥክር እንደሌለና በአገሪቱ ቴሌቪዥን በእነርሱ ላይ ሲሰነዘር ከምትሰማው ውንጀላ በስተቀር ስለ ምሥክሮቹ ብዙም የምታውቀው ነገር እንደሌለ ሳትሸሽግ ተናገረች።

ወንድም ማርካሪያን የሚናገርበት ተራ ሲደርስ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት በወላጆቻቸው ፈቃድ እንደሆነ ተናገረ። እንዲሁም በወታደራዊ አገልግሎት መካፈል አለመካፈል አንድ ሰው በግሉ የሚያደርገው ውሳኔ መሆኑን ገለጸ። አቃቤ ሕጉ ለወንድም ማርካሪያን ያቀረበለት መስቀለኛ ጥያቄ ለበርካታ ቀናት የዘለቀ ነበር። ወንድም ማርካሪያን እምነቱን በሚመለከት የሚቀርብለትን ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም በእርጋታ ሲመልስ አቃቤ ሕጉ በራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶቹን እያወጣ ይመለከት ነበር።

መስከረም 18, 2001 ዳኛው፣ ማርካሪያን “ወንጀል ፈጽሟል የሚያሰኝ ምንም ነገር” እንዳላደረገ በመግለጽ “ጥፋተኛ አይደለም” ብለው ፈረዱ። ጉዳዩን በዝርዝር የሚተነትን ዘገባ አሶሺዬትድ ፕሬስ በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “በአርሜኒያ የይሖዋ ምሥክሮች መሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ሃይማኖትን አስቀይሯል እንዲሁም ወጣቶች በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ግፊት አድርጎባቸዋል በሚል ከቀረበበት ክስ ነጻ ሆኗል። ፍርድ ቤቱ ለሁለት ወር ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ሌቮን ማርካሪያን [ልዮቫ ማርካሪያን] የተባለው ይህ መሪ እነዚህን ወንጀሎች ፈጽሟል ለማለት የሚያስችል በቂ ማስረጃ እንደሌለ ገልጿል። ማርካሪያን በወንጀሉ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ኖሮ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ይጠብቀው ነበር። . . . የአርሜኒያ ሕገ መንግሥት የሃይማኖት ነጻነትን የሚያስከብር ቢሆንም አዳዲስ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እውቅና ለማግኘት የሚቸገሩ ከመሆኑም በላይ ድንጋጌዎቹ የሚያደሉት በአገሪቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ለሚሰጣት የአርሜኒያ ሐዋርያዊ ቤተ ክርስቲያን ነው።” የአውሮፓ የደህንነትና የትብብር ድርጅት (ኦ ኤስ ሲ ኢ) ደግሞ መስከረም 18, 2001 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በደስታ የምንቀበል ቢሆንም መጀመሪያውኑ ክሱ በመቅረቡ ግን አዝነናል” በማለት ገልጿል።

ክሱ ቀጠለ

ሆኖም ጉዳዩን የያዙት ሁለቱ አቃቤያነ ሕግ ይግባኝ አሉና አራት ወራት የወሰደ የይግባኝ ችሎት ተካሄደ። በፍርድ ሂደቱ መጀመሪያ ላይ ወንድም ማርካሪያን የምሥክርነት ቃሉን የሚሰጥበት ተራ ሲደርስ ከዳኞቹ አንዱ የመጀመሪያውን ጥያቄ አቀረቡለት። ወንድም ማርካሪያን ለጥያቄው መልስ መስጠት ሲጀምር ችሎቱን የሚመሩት ዳኛ ጣልቃ በመግባት ተቃወሙት። ከዚያ በኋላ አንድ ጥያቄ እንኳን በአግባቡ ለመመለስ ዕድል አልሰጡትም። እንዲሁም ዳኛዋ ያለ ምንም ምክንያት ተከላካይ ጠበቃው ለወንድም ማርካሪያን ካቀረበለት ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከመዝገቡ ላይ እንዲሰረዙ አደረጉ። ክሱ በሚሰማበት ወቅት ፍርድ ቤቱን የሞሉት ሃይማኖታዊ አክራሪዎች በወንድም ማርካሪያን ላይ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። የመጀመሪያው የፍርድ ሂደት ካበቃ በኋላ ጉዳዩን በሚመለከት በርካታ የተሳሳቱና የተዛቡ ዘገባዎች በቴሌቪዥን የተሰራጩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወንድም ማርካሪያን ጥፋቱን እንዳመነ የሚናገር ዘገባም ነበረበት።

በፍርድ ሂደቱ አጋማሽ ላይ ሦስት ዳኞችን ያቀፈውን ችሎት የሚመሩት ዳኛ የአቃቤ ሕጉ ቢሮ በወንድም ማርካሪያን ላይ እርምጃ እንዲወስድበት የሚጠይቅ ከአገሪቱ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ምክር ቤት የተላከ ደብዳቤ ሲያቀርቡ የችሎቱ ታዛቢዎች ተገረሙ። ይህ ድርጊት በተለይ የፍርድ ሂደቱን ሲከታተሉ የነበሩትን ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በእጅጉ ያስገረመ ነበር። ምክንያቱም አርሜኒያ የአውሮፓ ምክር ቤት አባል ለመሆን ስታመለክት “ሁሉም ቤተ ክርስቲያኖችና ሃይማኖታዊ ቡድኖች፣ በተለይ ‘መጤዎች’ የሚባሉት ምንም አድልዎ ሳይደረግባቸው አምልኳቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ” ግዴታዋን እንደምትወጣ ገልጻ ነበር።

የፍርድ ሂደቱ በቀጣዮቹ ሳምንታት እየቀጠለ ሲሄድ ውጥረቱ እየተባባሰ መጣ። ተቃዋሚዎች በፍርድ ቤቱ ውስጥም ሆነ ከፍርድ ቤቱ ውጭ ምሥክሮቹን ማንገላታትና መምታታቸውን ቀጠሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ሴቶችን እግራቸውን ይመቷቸው ነበር። አንድ ምሥክር ለሰነዘሩበት ጥቃት አጸፋውን ባለመመለሱ ከኋላ አከርካሪው ላይ ክፉኛ መቱትና ለሆስፒታል ተዳረገ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍርድ ሂደቱን በሊቀመንበርነት የሚመሩ አዲስ ዳኛ ተሾሙ። ከአድማጮቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ተከላካዩን ጠበቃ ለማስፈራራት ቢሞክሩም አዲሱ ዳኛ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ሥርዓት እንዲሰፍን አደረጉ። እንዲያውም በተከላካዩ ጠበቃ ላይ እየጮኸች ስትዝትበት የነበረችን አንዲት ሴት ፖሊስ ከፍርድ ቤቱ እንዲያስወጣት አድርገዋል።

ጉዳዩ ወደ አርሜኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራ

በመጨረሻ መጋቢት 7, 2002 በዋለው ችሎት የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአውራጃው ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ብይን በድጋሚ አጸደቀ። የሚያስገርመው ውሳኔው ከመተላለፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የአገሪቱ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ምክር ቤት ተበተነ። አሁንም ግን የአቃቤ ሕጉ ቢሮ የካሴሽን ችሎት ተብሎ ወደሚጠራው የአርሜኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለ። በዚህ ወቅት ሁለቱ አቃቤያነ ሕግ “ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን ይተላለፍ ዘንድ” የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በድጋሚ እንዲመለከቱት የሚያዝ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጥያቄ አቀረቡ።

ሚያዝያ 19, 2002 ከረፋዱ 5:​00 ላይ በዳኛ መሄር ኻቻትራያን የሚመራ ስድስት ዳኞችን ያቀፈ ችሎት ተሰየመ። ከአቃቤያነ ሕጉ አንደኛው የክስ ማቅረቢያ ንግግሩን ሲከፍት ከዚህ ቀደም ጉዳዩን ያዩት ሁለት ፍርድ ቤቶች ወንድም ማርካሪያንን ከክስ ነጻ በማድረጋቸው የተሰማውን ከፍተኛ ቁጣ ገለጸ። በዚህ ጊዜ ግን ንግግሩን ሳይጨርስ ተቃውሞ የገጠመው አቃቤ ሕጉ ነበር። ከዚያም አራት ዳኞች በጥያቄ ያፋጥጡት ጀመር። አንደኛው ዳኛ አቃቤ ሕጉ በአንቀጽ 244 ላይ እንደ ወንጀል ተደርገው ያልተጠቀሱትን መስበክንና ሕጋዊ እውቅና ሳያገኙ መንቀሳቀስን በወንድም ማርካሪያን ላይ በቀረበው ክስ ውስጥ በማካተት የችሎቱን አመለካከት ለማዛባት በመሞከሩ በግልጽ ነቀፉት። ከዚያም ዳኛው የአቃቤ ሕጉን ድርጊት “ወንጀልን ሰበብ በማድረግ በወንድም ማርካሪያን ላይ የተፈጸመ ስደት” እንደሆነ ተናገሩ። ሌላኛው ዳኛ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች እምነት በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ሕጋዊ ከለላ ያገኘ “የታወቀ ሃይማኖት” መሆኑን የሚገልጹ ብያኔዎች የተላለፉባቸውን በአውሮፓ ፍርድ ቤቶች የተደረጉ የተለያዩ የፍርድ ሂደቶችን ጠቀሱ። በዚህ ጊዜ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበረ አንድ ቄስ የይሖዋ ምሥክሮች አገሪቱን እየከፋፈሉ ነው ሲል ጮኸ። ችሎቱ ዝም እንዲል አዘዘው።

ከዚያም ዳኞቹ ልዮቫ ማርካሪያንን ከተመልካቾቹ መካከል ጠሩት፤ ይህ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ታሪክ ፈጽሞ ያልተለመደ ድርጊት ነበር። ወንድም ማርካሪያን የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ክርስቲያናዊ አቋም በተመለከተ ግሩም ምሥክርነት ሰጠ። (ማርቆስ 13:9) ዳኞቹ ለብቻቸው በጉዳዩ ላይ ለጥቂት ጊዜ ከተወያዩበት በኋላ ችሎቱ በድጋሚ ተሰየመና በሙሉ ድምፅ “ጥፋተኛ አይደለም” የሚለውን ብይን አጸደቁ። በዚህ ጊዜ ወንድም ማርካሪያን የተሰማው እፎይታ በግልጽ ይታይ ነበር። ችሎቱ በጽሑፍ ባሰፈረው ውሳኔ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ይህ [የልዮቫ ማርካሪያን] ድርጊት በአሁኑ ወቅት ባለው ሕግ መሠረት እንደ ወንጀል ተደርጎ የማይቆጠር ከመሆኑም በላይ እንዲህ ዓይነቱ ውንጀላ ከአርሜኒያ ሕገ መንግሥት 23ኛ አንቀጽና ከአውሮፓ ሰብዓዊና መሠረታዊ መብቶች ድንጋጌ 9ኛ አንቀጽ ጋር ይቃረናል።”

ብይኑ ያስገኛቸው ውጤቶች

አቃቤ ሕጉ ያሰበው ቢሳካ ኖሮ በመላው አርሜኒያ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ በሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ መንገድ ይከፍት ነበር። ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ግልጽ ውሳኔ እንዲህ ዓይነቱን ችግር እንደሚያስቀር ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህም በላይ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከዚህ የተለየ ቢሆን ኖሮ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሚያቀርቡትን ጥያቄ ላለመቀበል ሰበብ ሊሆን ይችል ነበር። ፍርድ ቤቱ ይህን የሐሰት ክስ ውድቅ ማድረጉ ያስመሰግነዋል።

በዚህች አገር የሚገኙት ከ7, 000 በላይ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ያግኙ አያግኙ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። እስከዚያው ግን እውነተኛው አምልኮ ‘በአራራት’ መስፋፋቱንና መበልጸጉን ይቀጥላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አርመናውያን አገራቸውን ከአራራት ተራሮች ጋር የሚያዛምዱበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። በጥንት ጊዜ አርሜኒያ እነዚህ ተራሮች ያሉበትን ቦታ የምታጠቃልል ሰፊ ግዛት ነበረች። በዚህም ምክንያት የግሪክኛው ሴፕቱጀንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በኢሳይያስ 37:38 ላይ ያለውን ‘የአራራት አገር’ የሚለውን አባባል “አርሜኒያ” በማለት ተርጉሞታል። በአሁኑ ወቅት የአራራት ተራሮች በቱርክ ውስጥ በምሥራቃዊው ድንበር ላይ ይገኛሉ።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልዮቫ ማርካሪያን በችሎት ፊት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድም ማርካሪያንና ቤተሰቡ