በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህን?

ታስታውሳለህን?

ታስታውሳለህን?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ስለ ሳፋንና ቤተሰቡ በማንበብ ምን ጥቅም ማግኘት እንችላለን?

ሳፋን የይሁዳ ንጉሥ የነበረው የኢዮስያስ ጸሐፊና ገልባጭ ነበር። ትልቅ ሥልጣን የነበረው ሳፋን ንጉሡ እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ያደረገውን ዘመቻ ደግፏል። ሁለቱ የሳፋን ልጆች በታማኝነት ከኤርምያስ ጎን ቆመዋል። ሌላው ልጁና ሁለት የልጅ ልጆቹም በሰዎች ዘንድ የነበራቸውን ተሰሚነት እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ተጠቅመውበታል። እኛም በተመሳሳይ ሃብታችንንና ሥልጣናችንን እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ልንጠቀምበት ይገባናል።​—12/15 ገጽ 19-​22

አይሪን ሆከስተንባክ የነበረባትን ከባድ የጤና እክል ተቋቁማ ይሖዋን ለማገልገል የቻለችው እንዴት ነው?

የሰባት ዓመት ልጅ እያለች የመስማት ችሎታዋን አጣች። መስማት የተሳናት ብትሆንም ከሌሎች ጋር መግባባት ተምራ አሁን ከባለቤቷ ጋር (ተጓዥ የበላይ ተመልካች ነው) በኔዘርላንድ የሚገኙ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ያገለግላሉ።​—1/1 ገጽ 23-26

“ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የወጡት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሁለት ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው?

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ የተባለ መጽሐፍ መውጣቱን ሲሰሙ በጣም ተደስተው ነበር። ይህ መጽሐፍ አዳዲስ ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ በኋላ እንዲያጠኑት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በይሖዋ ባሕርያትና ባደረጋቸው ነገሮች ላይ የሚያተኩረው ይሖዋን የቅርብ ወዳጅህ አድርገው የተሰኘው መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ባሕርያቱን በማንጸባረቅ እንዴት ይሖዋን ልንኮርጀው እንደምንችልም ያብራራል።​—1/15 ገጽ 23-24

በምሳሌ 12:5 ላይ “የጻድቃን አሳብ ቅን ነው” ሲል ምን ማለቱ  ነው?

የጥሩ ሰዎች አሳብ ከሥነ ምግባር አንጻር ሲታይ ንጹሕ ሲሆን ከአድልዎ እንዲርቁና ትክክል የሆነውን እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል። ጻድቃን ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ስለሆነ ጥሩ ዝንባሌዎች ይኖሯቸዋል።​—1/15 ገጽ 30

አንድ ሰው ሰብዓዊ ሥራን በሚመለከት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው የሚረዳው ምንድን ነው?

ለሥራ ፍቅር እንዲያድርብን ከልጅነታችን ጀምሮ ሥልጠና ማግኘታችን ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የሥራ ልማድ እንዲኖረንና ስንፍናን እንድናስወግድ ያሳስበናል። (ምሳሌ 20:4) እንዲሁም ክርስቲያኖችን ከልክ በላይ በሥራ የተጠመዱ እንዳይሆኑ ያበረታታቸዋል። በሕይወታችን ውስጥ የላቀውን ቦታ ሊይዝ የሚገባው ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት መሆኑን መገንዘብ አለብን። (1 ቆሮንቶስ 7:29-31) በተጨማሪም እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ እንደማይተዋቸው ይተማመናሉ።​—2/1 ገጽ 4-6

መሠዊያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የት ላይ ነው?

በዘፍጥረት 8:20 ላይ ሲሆን ኖኅ ከውኃ ጥፋት በኋላ ከመርከቡ ሲወጣ የገነባው ነው። ይሁን እንጂ ቃየንና አቤል መሥዋዕት ያቀረቡት በመሠዊያ ላይ ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 4:3, 4)​—2/15 ገጽ 28

አንዳንድ ክርስቲያኖች የሁኔታዎች መለወጥ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በሚገባ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

አንዳንዶች በአገልግሎት የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችሏቸውን ለውጦች ራሳቸው አመቻችተዋል፤ ወይም አጋጣሚ የሚፈጥራቸውን ለውጦች ተጠቅመውባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸው አድገው ጎጆ ሲወጡ ወይም ይህን የመሳሰሉ የቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸውን የሚያቃልሉላቸው ለውጦች ሲያጋጥሟቸው በአምላክ አገልግሎት የሚያሳልፉትን ጊዜና የአገልግሎት መብቶቻቸውን ከፍ አድርገዋል።​—3/1 ገጽ 19-​22

የዮናስ እና የሐዋርያው ጴጥሮስ ታሪክ ሌሎችን በይሖዋ ዓይን መመልከት እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?

ዮናስም ሆነ ጴጥሮስ በአስተሳሰባቸው፣ ፈተናዎች ባጋጠሟቸው ጊዜ በወሰዷቸው እርምጃዎችና በታዛዥነት ረገድ ጉልህ ጉድለቶች ነበሩባቸው። ቢሆንም ይሖዋ የነበሯቸውን መልካም ባሕርያት ተመልክቶ በእነርሱ መጠቀሙን ቀጥሏል። እኛም ሌሎች ሲያሳዝኑን ወይም ሲያስቀይሙን መጀመሪያውኑ ወደ እነርሱ እንድንቀርብ ባደረጉን መልካም ባሕርያቶቻቸውና አምላክ ባገኘባቸው መልካም ነገር ላይ ማተኮር እንችላለን።​—3/15 ገጽ 16-​19

በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ለሚገኙት መዝሙራት የተሰጡት ቁጥሮች በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ልዩነት የሚታይባቸው ለምንድን ነው?

በዕብራይስጥ ቋንቋ በተጻፈው የመጀመሪያ ቅጂና በግሪክኛው የሴፕቱጀንት ትርጉም መካከል የቁጥር አሰጣጥ ልዩነት አለ። በቅርብ ጊዜ የወጡ ትርጉሞች የተዘጋጁት ከመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቅጂ ወይም ከሴፕቱጀንት ትርጉም ሊሆን ስለሚችል የቁጥር አሰጣጥ ልዩነት ይታያል።​—⁠4/1 ገጽ 31