በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቦዔዝና የሩት ያልተጠበቀ ጋብቻ

የቦዔዝና የሩት ያልተጠበቀ ጋብቻ

የቦዔዝና የሩት ያልተጠበቀ ጋብቻ

ወቅቱ የበልግ ወራት በመሆኑ በቤተ ልሔም አቅራቢያ አዝመራ እየተሰበሰበ ነው። መዓዛው የሚያውደው የተጠበሰ እሸት በሥራ ተጠምደው ለዋሉት አጫጆች የምግብ ሰዓት መድረሱን ያበስራቸዋል። አሁን አንድ ላይ ተሰባስበው የድካማቸውን ፍሬ ይቋደሳሉ።

ቦዔዝ የተባለ አንድ ባለ ርስት በልቶ ጠጥቶ ከጠገበ በኋላ በተከመረው እህል አጠገብ ጋደም አለ። አመሻሹ ላይ አጫጆቹ ሌሊቱን የሚያሳልፉበት አመቺ ቦታ ፈልገው አንቀላፉ። በውሎው የተደሰተው ቦዔዝም መጎናጸፊያውን ደረብ አደረገና አሸለበ።

አንዲት ሴት በስውር ወደ አውድማው መጣች

እኩለ ሌሊት ላይ ቦዔዝ በጣም ስለበረደው ከእንቅልፉ ነቃ። እግሮቹን ሆን ብሎ የገለጠበት ሰው አለ፤ አንዲት ሴት ደግሞ ከግርጌው እንደተኛች አስተዋለ። በጨለማ ማንነቷን መለየት ስላልቻለ “ማን ነሽ?” ሲል ጠየቀ። ሴትዮዋም “እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ” አለችው።​—⁠ሩት 3:1-9

በጨለማው ውስጥ ማንም ሳይሰማቸው ማውራት ቀጠሉ። ሴቶች በውድቅት ሌሊት በአውድማ አካባቢ ብቻቸውን መገኘታቸው የተለመደ ነገር አልነበረም። (ሩት 3:14) ያም ሆኖ ቦዔዝ እስኪነጋ ድረስ ከግርጌው እንድትተኛ ፈቀደላት፤ ከዚያም መሠረተ ቢስ ለሆነ ነቀፋ እንዳይጋለጡ ጎህ ከመቅደዱ በፊት ተነሥታ ወደ ቤትዋ ሄደች።

ሩት ቦዔዝን ፍለጋ የሄደችው ተዋድደው ስለነበረ ነውን? ከአሕዛብ ወገን የመጣችው ድሃዋ ወጣት መበለት በዕድሜ በጣም የሚበልጣትን ባለጸጋ እያጠመደችው ይሆን? ወይስ ቦዔዝ ያለችበትን ሁኔታና ብቸኝነቷን ተመልክቶ በአጋጣሚው ለመጠቀም እየሞከረ ነበር? ፈጽሞ አይደለም። እንዲያውም ሁኔታው እነዚህ ሰዎች ለአምላክ የነበራቸውን ታማኝነትና ፍቅር የሚያሳይ ነው። ዝርዝር ዘገባዎቹም ጥልቅ ስሜት የሚያሳድሩ ናቸው።

ይሁን እንጂ ሩት ማን ናት? ወደ አውድማው የመጣችው ለምን ነበር? ቦዔዝ የተባለው ይህ ባለጸጋ ሰውስ ማን ነው?

“ምግባረ መልካም ሴት”

ይህ ክንውን ከመፈጸሙ ከዓመታት በፊት በይሁዳ ምድር ረሃብ ተከስቶ ነበር። በመሆኑም አቤሜሌክ፣ ሚስቱ ኑኃሚን እንዲሁም መሐሎንና ኬሌዎን የተባሉት ሁለት ወንዶች ልጆቹ ለም ወደ ሆነው የሞዓብ ምድር ተሰደዱ። በዚያም ልጆቹ ሩትና ዖርፋ የተባሉ ሁለት ሞዓባውያን ሴቶች አገቡ። አቤሜሌክና ሁለቱ ልጆቹ በሞዓብ እያሉ ከሞቱ በኋላ ባሎቻቸውን ያጡት ሦስቱ ሴቶች በእስራኤል ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መሆናቸውን ሰሙ። በዚህ ጊዜ ልጆችም ሆነ የልጅ ልጆች የሌሏትና ሐዘን ቅስሟን የሰበረው መበለቷ ኑኃሚን ወደ ትውልድ አገሯ ለመመለስ ወሰነች።​—⁠ሩት 1:1-14

ወደ እስራኤል እየተመለሱ እያለ ኑኃሚን ወደ ሕዝቧ እንድትመለስ ዖርፋን አሳመነቻት። ከዚያም ሩትን “እነሆ፣ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ” አለቻት። ሩት ግን “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፣ . . . እንድተውሽ . . . አታስቸግሪኝ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፣ በዚያም እቀበራለሁ” አለች። (ሩት 1:15-17) ስለዚህ ሁለቱ ምስኪን መበለቶች ተያይዘው ወደ ቤተ ልሔም ተመለሱ። በዚያም ሩት ለአማትዋ የነበራትን ፍቅርና የምታደርግላትን እንክብካቤ የተመለከቱት የኑኃሚን ጎረቤቶች በጣም ከመገረማቸው የተነሳ ‘ከሰባትም ወንዶች ልጆች ይልቅ ትሻልሻለች’ እስከማለት ደርሰው ነበር። ሌሎች ደግሞ ሩት “ምግባረ መልካም ሴት” እንደሆነች ተናግረዋል።​—⁠ሩት 3:11፤ 4:15

በቤተ ልሔም የገብስ አዝመራ የሚሰበሰብበት ወቅት ሲደርስ ሩት ለኑኃሚን “በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ” አለቻት።​—⁠ሩት 2:2

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሩት የአማችዋ የአቤሜሌክ ዘመድ ወደ ሆነው ወደ ቦዔዝ እርሻ መጣች። ከዚያም የአጫጆቹን አዛዥ ለመቃረም እንዲፈቅድላት ጠየቀችው። ሩት በትጋት ትቃርም ስለነበር የአጫጆቹ አዛዥ በቦዔዝ ፊት አሞገሳት።​—⁠ሩት 1:22 እስከ 2:7

ከለላና ድጋፍ አገኘች

ቦዔዝ ቀናተኛ የይሖዋ አምላኪ ነው። ሁልጊዜ ማለዳ ላይ አጫጆቹን “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን” በማለት ሰላምታ ሲያቀርብላቸው እነርሱ ደግሞ “እግዚአብሔር ይባርክህ” ብለው ይመልሱለት ነበር። (ሩት 2:4) ቦዔዝ የሩትን ታታሪነት ከተመለከተና ለኑኃሚን ያሳየችውን ታማኝነት ከሰማ በኋላ ያለችግር መቃረም እንድትችል ለየት ያለ ዝግጅት አደረገላት። ‘በእኔ እርሻ መቃረም ስለምትችዪ ወደ ሌላ እርሻ መሄድ አያስፈልግሽም። ከገረዶቼ አትራቂ፤ ከእነርሱ ጋር ከሆንሽ ምንም የሚያስፈራሽ ነገር አይኖርም። ጎበዛዝቱም እንዳያስቸግሩሽ አዝዣቸዋለሁ። ውሃ ሲጠማሽ እነርሱ ከቀዱት መጠጣት ትችያለሽ’ አላት።​—⁠ሩት 2:8, 9

ሩት በግምባርዋ ተደፍታ እጅ ከነሳች በኋላ ‘እኔ እንግዳ ሆኜ ሳለሁ በፊትህ እንዴት ሞገስ አገኘሁ?’ አለችው። ቦዔዝም እንዲህ በማለት መለሰላት:- ‘ባልሽ ከሞተ በኋላ ለአማትሽ ያደረግሽላትን ሁሉ፣ አባትና እናትሽን እንዲሁም ዘመዶችሽንና የተወለድሽበትን አገር ትተሽ ቀድሞ ከማታውቂው ሕዝብ ጋር ለመኖር እንደመጣሽ ሰምቻለሁ። ይሖዋ እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ደመወዝሽም ፍጹም ይሁን።’​—⁠ሩት 2:10-12

ቦዔዝ ልቧን ለመስረቅ እየሞከረ አልነበረም። ሩትን ያደነቃት ከልቡ ነበር። ሩትም በሚያበረታቱ ቃላት ስላጽናናት በትሕትና አመሰገነችው። ያደረገላት ደግነት የማይገባት እንደሆነ ስለተሰማት የበለጠ በርትታ ትሠራ ጀመር። በኋላም በምሳ ሰዓት ላይ ቦዔዝ ሩትን ጠርቶ ‘ወደዚህ ቀረብ በይና እንጀራሽን በሆምጣጤው እያጠቀስሽ ብዪ’ አላት። ሩት እስክትጠግብ ከበላች በኋላ የተረፋትን ለኑኃሚን ለመውሰድ አስቀመጠችው።​—⁠ሩት 2:14

በቀኑ መገባደጃ ላይ ሩት 22 ሊትር ያህል የሚይዝ ዕቃ የሚሞላ ገብስ ቃርማ ነበር። የቃረመችውን እህልና ከምሳዋ የተረፋትን ምግብ ተሸክማ ወደ ኑኃሚን ተመለሰች። (ሩት 2:15-18) ኑኃሚን የተትረፈረፈ ምግብ በማግኘታቸው ተደስታ “ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? . . . የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን” አለቻት። ሩት የቃረመችው በቦዔዝ እርሻ መሆኑን ስትነግራት “በጎነቱን ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ማድረጉን ያልተወ እግዚአብሔር ይባርከው። . . . ‘ሰውየው እኮ የሥጋ ዘመዳችን ነው፤ የመቤዠት ግዴታ ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው’ አለቻት።”​—⁠ሩት 2:19, 20 አ.መ.ት

የምታርፍበት ቦታ’ ማግኘት

ኑኃሚን በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም በሕጉ መሠረት የሚቤዣቸው ሰው የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ጀመረች፤ ይህም ምራትዋ ‘የምታርፍበት ቦታ’ ወይም ቤት እንድታገኝ ያስችላታል። (ዘሌዋውያን 25:25፤ ዘዳግም 25:5, 6) ኑኃሚን የቦዔዝን ትኩረት ለመሳብ ብልሃት የተሞላበት ዕቅድ ካወጣች በኋላ ሩት ምን ማድረግ እንዳለባት ነገረቻት። ከዚያም ሩት ከለባበሰች በኋላ ኑኃሚን የሰጠቻትን መመሪያ በመከተል ጨለማውን ተገን አድርጋ ወደ ቦዔዝ አውድማ ሄደች። በቦታው ስትደርስ ቦዔዝን ተኝቶ አገኘችው። እግሩን ገለጠችና እስኪነቃ መጠበቅ ጀመረች።​—⁠ሩት 3:1-7

ቦዔዝ ከእንቅልፉ ሲነቃ ሩት ያደረገችውን በመመልከት ‘ልብሱን በእርስዋ ላይ እንዲዘረጋ’ ያቀረበችለትን ጥያቄ ትርጉም ሳይገነዘብ አልቀረም። የሩት ድርጊት ይህ በዕድሜ የገፋ አይሁዳዊ የሟቹ ባልዋ የመሐሎን ዘመድ በመሆኑ የመቤዠት ግዴታ እንዳለበት እንዲያውቅ ረድቶታል።​—⁠ሩት 3:9

ቦዔዝ፣ ሩት በሌሊት እንደምትመጣ አልጠበቀም። ሆኖም ከሰጠው ምላሽ መረዳት እንደሚቻለው ሩት እንዲቤዣት ያቀረበችለት ጥያቄ ዱብ ዕዳ አልሆነበትም። በመሆኑም ጥያቄዋን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ነበር።

ሩት ስጋት እንዳደረባት ከድምፅዋ ቃና ስለተገነዘበ ሳይሆን አይቀርም ቦዔዝ እንደሚከተለው በማለት አበረታታት:- “አሁንም፣ ልጄ ሆይ፣ አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።”​—⁠ሩት 3:11

ቦዔዝ ሩት ያደረገችውን ነገር ከጨዋነት የመነጨ ድርጊት አድርጎ እንደተመለከተው ቀጥሎ ካለው አባባሉ መረዳት ይቻላል:- “ልጄ ሆይ፣ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ . . . ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW ] አድርገሻል።” (ሩት 3:10) ሩት በመጀመሪያ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር ያሳየችው ለኑኃሚን ነበር። በመጨረሻው ጊዜ ደግሞ ዋርሳዋ ስለሆነ በዕድሜ ብዙ የሚበልጣትን ቦዔዝን ለማግባት ፈቃደኛ በመሆኗ ፍቅራዊ ደግነት አሳይታለች። ለሟቹ ባልዋ ለመሐሎንና ለኑኃሚን ዘር ለመተካት ራስዋን በፈቃደኝነት አቅርባለች።

ለመቤዠት ፈቃደኛ ያልሆነው ዋርሳ

በማግስቱ ጠዋት ቦዔዝ ከእርሱ ይልቅ ለኑኃሚን የቅርብ ዘመድ የሆነውን ሰው በከተማይቱ በር አደባባይ አብሮት እንዲቀመጥ ጠራው። ከዚያም በከተማዋ ሕዝብና በሽማግሌዎቹ ፊት እንዲህ አለው:- ‘የጠራሁህ ኑኃሚን የባልዋን የአቤሜሌክን መሬት ልትሸጥ ስለሆነ መሬቱን የመግዛት መብት እንዳለህ ልነግርህ ነው። መሬቱን ለመግዛት ትፈልጋለህ? ካልሆነ እኔ እገዛዋለሁ።’ ሰውየው መሬቱን እንደሚገዛው ተናገረ።​—⁠ሩት 4:1-4

ሆኖም ይህ የኑኃሚን የቅርብ ዘመድ ያላወቀው ነገር ነበር። ቦዔዝ ቀጠለና በምሥክሮቹ ፊት “እርሻውን ከኑኃሚን እጅ በምትገዛበት ቀን፣ ለሞተው በርስቱ ስሙን እንድታስነሣለት ከምዋቹ ሚስት ከሞዓባዊቱ ከሩት ደግሞ ትገዛለህ” አለው። ሰውየውም የራሱን ርስት እንዳያበላሽ ስለፈራ “እኔ መቤዠቱን አልችልም” በማለት ርስቱን የመግዛት መብቱን አሳልፎ ሰጠው።​—⁠ሩት 4:5, 6

በባሕሉ መሠረት አንድ ሰው ለመቤዠት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ጫማውን አውልቆ ለባልንጀራው ይሰጠዋል። ስለዚህ የኑኃሚን የቅርብ ዘመድ የነበረው ሰው ጫማውን አወለቀና ቦዔዝን “አንተ ግዛው” አለው። ከዚያም ቦዔዝ ለሽማግሌዎቹና ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው:- “ለአቤሜሌክና ለኬሌዎን ለመሐሎንም የነበረውን ሁሉ ከኑኃሚን እጅ እንደ ገዛሁ እናንተ ዛሬ ምስክሮች ናችሁ። ደግሞም . . . የምዋቹን ስም በርስቱ ላይ እንዳስነሣ የመሐሎንን ሚስት ሞዓባዊቱን ሩትን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ወሰድሁአት፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ።”​—⁠ሩት 4:7-10

በከተማይቱ በር አደባባይ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ቦዔዝን እንዲህ አሉት:- “እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት የእስራኤልን ቤት እንደ ሠሩ እንደ ሁለቱ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ ባለጠጋ ሁን፣ ስምህም በቤተ ልሔም ይጠራ።”​—⁠ሩት 4:11, 12

ቦዔዝ የሕዝቡን ምርቃት ተቀብሎ ሩትን ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት። እርስዋም ኢዮቤድ የተባለ ልጅ ወለደችለት፤ በዚህ መንገድ ሩትና ቦዔዝ የንጉሥ ዳዊት በኋላም የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት ለመሆን በቁ።​—⁠ሩት 4:13-17፤ ማቴዎስ 1:5, 6, 16

‘ፍጹም ደመወዝ’

ቦዔዝ ለአጫጆቹ በደግነት ሰላምታ እንደሰጣቸው ከሚናገረው ዘገባ ጀምሮ የአቤሜሌክ ቤተሰብ ስም እንዳይጠፋ ለማድረግ ኃላፊነቱን እንደተቀበለ እስከሚገልጸው ዘገባ ድረስ ባለው ታሪክ ማየት እንደሚቻለው ኃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ የተግባር ሰው ነበር። ራሱን የሚገዛ፣ እምነትና ጽኑ አቋም ያለው ሰው መሆኑንም አሳይቷል። ከዚህም በላይ ለጋስ፣ ደግ፣ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለውና ለይሖዋ ትእዛዛት ሙሉ በሙሉ የሚገዛ ሰው ነበር።

ሩት ለይሖዋ ባላት ፍቅር፣ ለኑኃሚን ባሳየችው ፍቅራዊ ደግነት፣ በታታሪነቷና በትሕትናዋ የላቀ ምሳሌ ትታለች። በሰዎች ዘንድ “ምግባረ መልካም ሴት” የሚል ስም ማትረፏ የተገባ ነው። ሩት ‘የሀኬትን እንጀራ የማትበላ’ ከመሆንዋም በላይ ትጉህ ሠራተኛ ስለነበረች ችግረኛ አማትዋን መደገፍ ችላለች። (ምሳሌ 31:27, 31) ኑኃሚንን የመንከባከቡን ኃላፊነት በመቀበልዋ ከመስጠት የሚገኘውን ደስታ እንዳገኘች ጥርጥር የለውም።​—⁠ሥራ 20:35፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8

የሩት መጽሐፍ እንዴት ያሉ ግሩም ምሳሌዎች ይዞልናል! ይሖዋ መበለቷን ኑኃሚንን አልረሳትም። ሩት የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት በመሆንዋ ‘ፍጹም ደመወዝ’ አግኝታለች። ቦዔዝ ደግሞ ‘ምግባረ መልካም የሆነች ሚስት’ በማግኘት ተባርኳል። እኛም እነዚህ ሰዎች ካሳዩት እምነት ብዙ መማር ችለናል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የተስፋ ጭላንጭል

በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እንደምትኖር ሆኖ ከተሰማህ የሩት ታሪክ የተስፋ ብርሃን ሊፈነጥቅልህ ይችላል። ታሪኩ ለመሳፍንት መጽሐፍ ጥሩ መደምደሚያ ነው። የሩት መጽሐፍ ይሖዋ ከባዕድ አገር በመጣች አንዲት ትሑት ሞዓባዊት መበለት አማካኝነት ለሕዝቡ ንጉሥ እንዳስገኘላቸው ይተርካል። ሩት ያሳየችው ታማኝነት በመሳፍንት ዘመን ከተፈጸሙት ክንውኖች ጎልቶ የሚታይ ነው። የሩት ታሪክ ጊዜው ምንም ያህል ቢከፋ አምላክ ሕዝቡን ከመንከባከብና ዓላማውን ከማስፈጸም የሚያግደው ነገር እንደማይኖር ማረጋገጫ ይሰጠናል።