“በጎ ሕሊና ይኑራችሁ”
“በጎ ሕሊና ይኑራችሁ”
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች “ሕሊናህን አዳምጥ” ሲሉ ይሰማሉ። ሆኖም ሕሊናችን አስተማማኝ መመሪያ እንዲሆነን ትክክልና ስህተት የሆነውን በመለየት ረገድ በሚገባ መሠልጠን ያለበት ከመሆኑም በላይ የሚሰጠንን መመሪያ በንቃት መከተታል አለብን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የዘኬዎስን ታሪክ ተመልከት። በኢያሪኮ የሚኖረው ዘኬዎስ የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃና ባለጸጋ ነበር። ሃብቱን ያከማቸው ሌሎችን በሚጎዳ መንገድ ማለትም በማጭበርበር እንደሆነ እርሱ ራሱ አምኖ ተናግሯል። ዘኬዎስ በዚህ መጥፎ ድርጊቱ የተነሳ ሕሊናው ይወቅሰው ነበር? ምናልባት ወቅሶት ሊሆን ይችላል፤ እርሱ ግን ችላ ይለው እንደነበር ድርጊቱ ይመሰክራል።—ሉቃስ 19:1-7
ይሁን እንጂ ዘኬዎስ አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲመለከት ያደረገው ሁኔታ ተከሰተ። ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ በመጣበት ወቅት ቁመቱ አጭር የሆነው ዘኬዎስ እሱን ለማየት ቢፈልግም ብዙ ሕዝብ አብሮት ስለነበር ሊሳካለት አልቻለም። ስለዚህ ኢየሱስን በደምብ ማየት እንዲችል ወደፊት ሮጦ ዛፍ ላይ ወጣ። ኢየሱስ፣ ዘኬዎስ እሱን ለመመልከት ባሳየው ጉጉት በመደነቅ ወደ ቤቱ እንደሚመጣ ነገረው። ዘኬዎስም ወደ ቤቱ የመጣውን ትልቅ እንግዳ ጥሩ አድርጎ አስተናገደው።
ዘኬዎስ ከኢየሱስ ጋር በነበረበት ወቅት ያየውና የሰማው ነገር ልቡን የነካው ሲሆን አካሄዱንም እንዲያስተካክል ገፋፍቶታል። “ጌታ ሆይ፣ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 19:8
ዘኬዎስ ሕሊናው በሚገባ መሥራት የጀመረ ሲሆን እሱም ሕሊናው የሚናገረውን ሰምቶ እርምጃ ወስዷል። እንዲህ ማድረጉ ትልቅ ጥቅም አስገኝቶለታል። ኢየሱስ “ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል” በማለት ሲናገር ዘኬዎስ ምን እንደተሰማው ገምት።—ሉቃስ 19:9
እንዴት ያለ የሚያበረታታ ምሳሌ ነው! ከዚህ በፊት የነበረን አኗኗር ምንም ዓይነት ይሁን ለውጥ ማድረግ እንደምንችል ያሳያል። እኛም እንደ ዘኬዎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት በመከተል ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታችንን ማዳበር እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ሐዋርያው ጴጥሮስ በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ‘በጎ ሕሊና ሊኖረን’ ይችላል። እንዲሁም የሠለጠነ ሕሊናችንን በማዳመጥ ትክክል የሆነውን ማድረግ እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 3:16