በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

እውነተኛ መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

እውነተኛ መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

“የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት . . . በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።”—⁠2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

1. በዛሬው ጊዜ ሰዎች መጽናኛ የሚያስፈልጋቸው እንዴት ያሉ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሟቸው ነው?

 አቅም የሚያሳጣ ሕመም አንድን ሰው የዋጋ ቢስነት ስሜት ሊያሳድርበት ይችላል። የመሬት መንቀጥቀጥ፣ አውሎ ነፋስና ረሃብ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ጦርነት የቤተሰብ አባላትን በሞት ሊነጥቅ፣ ቤቶችን ሊያወድም ወይም ሰዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ሊያደርግ ይችላል። የፍትሕ መጓደል ሰዎችን የት እንድረስ ሊያሰኛቸው ይችላል። እንደዚህ ዓይነት መከራ የደረሰባቸው ሰዎች በእጅጉ መጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

2. ከይሖዋ የሚገኘው መጽናኛ ወደር የማይገኝለት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

2 አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሰዎችን ለማጽናናት ጥረት ያደርጋሉ። መከራ የደረሰባቸው ሰዎች ሌሎች ቀርበው ሲያጽናኗቸው ደስ ይላቸዋል። እንደ ምግብ፣ መጠለያና ልብስ ያሉት አስፈላጊ ነገሮችም ለጊዜውም ቢሆን ችግራቸውን ለማቃለል ይረዳሉ። ሆኖም ችግሮችን በሙሉ አስወግዶ እንደዚህ ዓይነት መከራ ዳግም እንዳይከሰት በማድረግ ዘላቂ እፎይታ ሊያመጣ የሚችለው እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፣ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን።” (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ይሖዋ የሚያጽናናን እንዴት ነው?

ችግሩን ከሥሩ መንቀል

3. ከአምላክ የሚገኘው መጽናኛ የሰው ዘር ችግሮችን ከሥራቸው የሚነቅላቸው እንዴት ነው?

3 መላው የሰው ዘር በአዳም ኃጢአት ምክንያት አለፍጽምናን የወረሰ ሲሆን ይህም ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮች አስከትሎበታል። (ሮሜ 5:12) ሰይጣን ዲያብሎስ “የዚህ ዓለም ገዥ” መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ይሖዋ የሰው ዘር በተጋረጠበት አስከፊ ሁኔታ ከማዘንም አልፎ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የሰው ዘር የሚድንበትን መንገድ ያዘጋጀ ሲሆን በልጁ የምናምን ከሆነ የአዳም ኃጢአት ካስከተለብን መዘዝ መላቀቅ እንደምንችል ነግሮናል። (ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:10) በተጨማሪም በሰማይና በምድር ሥልጣን የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንንና በሥሩ ያለውን ክፉ ሥርዓት ጠራርጎ እንደሚያጠፋው አምላክ ተናግሯል።​—⁠ማቴዎስ 28:18፤ 1 ዮሐንስ 3:8፤ ራእይ 6:2፤ 20:10

4. (ሀ) ይሖዋ እርሱ በሰጠው ተስፋ ላይ ያለንን ትምክህት ለማጠናከር ምን አድርጓል? (ለ) እፎይታ የምናገኝበት ጊዜ መቃረቡን በምን እናውቃለን?

4 አምላክ እርሱ በሰጠን ተስፋዎች ላይ ያለንን ትምክህት ለማጠናከር የተናገረው ሁሉ እንደሚፈጸም የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። (ኢያሱ 23:14) አገልጋዮቹን በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ ሊወጧቸው ከማይችሏቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለማዳን ሲል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስመዝግቦልናል። (ዘጸአት 14:4-31፤ 2 ነገሥት 18:13 እስከ 19:37) እንዲሁም ይሖዋ ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ “በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ” የመፈወስ ዓላማ እንዳለው ኢየሱስ ክርስቶስ ባከናወናቸው ተአምራት አማካኝነት አሳይቷል። (ማቴዎስ 9:35፤ 11:3-6) ይህ ሁሉ የሚሆነው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር የሚተካው ይህ አሮጌ ሥርዓት መጨረሻው መቃረቡን የሚያሳዩ ምልክቶች ይዟል። ኢየሱስ የተናገራቸው የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች ፍጻሜያቸውን ባገኙበት ጊዜ ውስጥ እንኖራለን።​—⁠ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

መከራ ለደረሰባቸው የሚሆን መጽናኛ

5. ይሖዋ የጥንት እስራኤላውያንን ለማጽናናት ምን ነገሮች አስታውሷቸዋል?

5 ይሖዋ ከጥንት እስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት ስንመረምር በመከራቸው እንዴት እንዳጽናናቸው የሚገልጽ ትምህርት እናገኛለን። እርሱ ምን ዓይነት አምላክ መሆኑን አስታውሷቸዋል። ይህም ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ የነበራቸውን ትምክህት አጠናክሮላቸዋል። ነቢያቱ እውነተኛና ህያው አምላክ በሆነው በእርሱና ራሳቸውንም ሆነ አምላኪዎቻቸውን መጥቀም በማይችሉት ጣዖታት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወዳደር የሚያስችሉ ግልጽ ምሳሌዎችን እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። (ኢሳይያስ 41:10፤ 46:1፤ ኤርምያስ 10:2-15) ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል “አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ነቢዩ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን የይሖዋን ታላቅነት ጎላ አድርጎ ለመግለጽ የፍጥረት ሥራዎቹን እንደ ምሳሌ አድርጎ እንዲጠቀም አነሳስቶት ነበር።​—⁠ኢሳይያስ 40:1-31

6. ይሖዋ ሕዝቦቹ ነጻ የሚወጡበትን ወቅት ለይተው እንዲያውቁ የረዳቸው እንዴት ነው?

6 አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ የሚያወጣበትን ትክክለኛ ጊዜ በመግለጽ ያጽናናቸው ነበር። በግብፅ ባርነት ሥር የነበሩት እስራኤላውያን ነጻ የሚወጡበት ጊዜ ሲቃረብ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ ገና አንዲት መቅሠፍት አመጣለሁ፣ ከዚያ ወዲያም ይለቅቃችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዘጸአት 11:1) በንጉሥ ኢዮሣፍጥ የግዛት ዘመን ሦስት ብሔራት ግንባር ፈጥረው ይሁዳን በወረሩ ጊዜ ይሖዋ “ነገ” ለእነርሱ ሲል እንደሚዋጋ ነግሯቸው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 20:1-4, 14-17) በሌላ በኩል ኢሳይያስ ከባቢሎን ነፃ የሚወጡበትን ጊዜ የጻፈው ከ200 ዓመታት በፊት ሲሆን ኤርምያስ ደግሞ ነፃ ከመውጣታቸው ከ100 ዓመት ገደማ በፊት ተጨማሪ ሐሳቦችን ተናግሮ ነበር። እነዚህ ትንቢቶች ሕዝቡ ከምርኮ ነፃ የሚወጣበት ጊዜ ሲቃረብ የአምላክን አገልጋዮች ምንኛ አጽናንተዋቸው ይሆን!​—⁠ኢሳይያስ 44:26 እስከ 45:3፤ ኤርምያስ 25:11-14

7. ነፃ ስለመውጣት በሚናገሩ ተስፋዎች ውስጥ በአብዛኛው ምን ተካትቶ ነበር? ይህስ በእስራኤል የነበሩ ታማኝ ሰዎችን የነካው እንዴት ነበር?

7 የአምላክን ሕዝቦች ለማጽናናት ተብለው የተነገሩት ተስፋዎች ብዙውን ጊዜ መሲሑን የሚመለከቱ ትንቢቶችን የያዙ መሆናቸው ትኩረት የሚስብ ነው። (ኢሳይያስ 53:1-12) ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ እነዚህ ትንቢቶች በርካታ ፈተናዎች ላጋጠሟቸው የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የተስፋ ብርሃን ፈንጥቀውላቸዋል። ሉቃስ 2:25 እንዲህ ይላል:- “እነሆም፣ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፣ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት [ወይም የመሲሑን መምጣት] ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፣ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ።” ስምዖን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ስለ መሲሑ የሚናገር ተስፋ ከማወቁም በላይ ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ በትኩረት ይከታተል ነበር። ስለ መሲሑ የተነገረው ተስፋ ፍጻሜውን እንዴት እንደሚያገኝ አያውቅም ነበር፤ አስቀድሞ የተነገረው የሰው ልጅ መዳን ሲፈጸምም አልተመለከተም። ሆኖም አምላክ ሰዎችን ‘ለማዳን’ የሚጠቀምበትን ሕፃን በተመለከተ ጊዜ ተደስቷል።​—⁠ሉቃስ 2:30

በክርስቶስ በኩል የሚገኝ መጽናኛ

8. ኢየሱስ ያከናወነው አገልግሎት ብዙዎች ከጠበቁት የሚለየው በምንድን ነው?

8 ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሰዎች ማግኘት የፈለጉትን ነገር ሁሉ አላደረገላቸውም። አንዳንዶች ከሮማውያን አስከፊ የአገዛዝ ቀንበር ነፃ የሚያወጣቸው መሲሕ እንደሚመጣ ይጠብቁ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ፖለቲካዊ ለውጥ የማምጣት ዓላማ አልነበረውም፤ ከዚህ ይልቅ “የቄሣርን ለቄሣር . . . አስረክቡ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 22:21) የአምላክ ዓላማ ሰዎችን ከአንድ ፖለቲካዊ አገዛዝ ነፃ በማውጣት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሕዝቡ ኢየሱስን ሊያነግሡት ፈልገው የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ’ እንደመጣ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 6:15) ኢየሱስ የንግሥና ሥልጣኑን የሚጨብጥበት ጊዜ ገና ያልደረሰ ከመሆኑም በላይ ንጉሥ አድርጎ የሚሾመው ይሖዋ እንጂ በሥርዓቱ ያልተደሰተው ሕዝብ አይደለም።

9. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎችን ለማጽናናት የሰበከው መልእክት ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ከሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር እንደሚዛመድ ያሳየው እንዴት ነበር? (ሐ) ኢየሱስ ያከናወነው አገልግሎት ለምን ነገር መሠረት ጥሏል?

9 ኢየሱስ ሰዎችን ያጽናናው “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል” በመስበክ ነበር። በደረሰባቸው ቦታዎች ሁሉ ስለዚህ መንግሥት ሰብኳል። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግላቸው በተግባር በማሳየት ይህ መልእክት ከሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ጎላ አድርጎ አሳይቷል። ማየት የተሳናቸውን፣ ዲዳዎችን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ የሥጋ ደዌ ሕሙማንንና ሌሎች ከበድ ያሉ በሽታዎች ያሉባቸውን ሰዎች በመፈወስ ደስታ የተሞላበት ሕይወት እንዲመሩ አስችሏቸዋል። (ማቴዎስ 12:22፤ ማርቆስ 2:3-12፤ 5:25-29፤ 10:51, 52፤ ሉቃስ 5:12, 13) ልጆችን ከሞት በማስነሳት በሐዘን የተደቆሱ ቤተሰቦቻቸውን አጽናንቷል። (ሉቃስ 7:11-15፤ 8:49-56) አስፈሪ የሆነ ማዕበልን የማስቆምና በርካታ ሰዎችን የመመገብ ችሎታ እንዳለው አሳይቷል። (ማርቆስ 4:37-41፤ 8:2-9) ከዚህም በላይ ኢየሱስ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችሉና ጽድቅ የሰፈነበት መሲሐዊ አገዛዝ እንደሚመጣ ተስፋ የሚፈነጥቁ ትምህርቶች ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን የሰጠው ትምህርት በወቅቱ ጆሮ ሰጥተው ያዳምጡ የነበሩትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ በነበሩት በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት የኖሩ ሰዎችንም ጭምር ለማጽናናት የሚያስችል መሠረት ጥሏል።

10. የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ምን ጥቅሞች አስገኝቶልናል?

10 ኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበና ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ካረገ ከ60 ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ ተነሳስቶ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ልጆቼ ሆይ፣ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱ ያስገኛቸው ጥቅሞች በእጅጉ ያጽናኑናል። ቤዛው የኃጢአት ሥርየት፣ ንጹሕ ሕሊና፣ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዳስገኘልን እናውቃለን።​—⁠ዮሐንስ 14:6፤ ሮሜ 6:23፤ ዕብራውያን 9:24-28፤ 1 ጴጥሮስ 3:21

መንፈስ ቅዱስ የሚያስገኘው መጽናኛ

11. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ሐዋርያቱን የሚያጽናና ምን ተጨማሪ ዝግጅት እንደተደረገ ገልጾ ነበር?

11 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት በሰማይ የሚኖረው አባቱ እነርሱን ለማጽናናት ስላደረገው ተጨማሪ ዝግጅት ነግሯቸዋል። እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም . . . የእውነት መንፈስ ነው፤ . . . መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐንስ 14:16, 17, 26) መንፈስ ቅዱስ ያጽናናቸው እንዴት ነበር?

12. መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት በማስታወስ ረገድ የተጫወተው ሚና ብዙዎችን ያጽናናው እንዴት ነው?

12 ሐዋርያት ከኢየሱስ ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶች ቀስመው ነበር። ከኢየሱስ ጋር ያሳለፉትን ጊዜ እንደማይዘነጉት ግልጽ ነው፤ ሆኖም የነገራቸውን ሁሉ ያስታውሱ ይሆን? ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት ኢየሱስ ያስተማራቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች ይዘነጓቸው ይሆን? ኢየሱስ ‘እርሱ የነገራቸውን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስታውሳቸው’ ማረጋገጫ ሰጥቷቸው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ከሞተ ከስምንት ዓመታት በኋላ ማቴዎስ ልብ የሚነኩ ትምህርቶችን የያዘውን የኢየሱስ የተራራ ስብከት፣ ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ የተናገራቸውን በርካታ ምሳሌዎችና መገኘቱን የሚጠቁሙ ዝርዝር ምልክቶች አካትቶ የያዘውን የመጀመሪያውን ወንጌል ጽፏል። ከ50 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ ቀናት ስላከናወናቸው ነገሮች በዝርዝር የሚገልጽ አስተማማኝ ዘገባ ጽፏል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ ዘገባዎች በዘመናችንም ቢሆን በእጅጉ ያጽናኑናል!

13. መንፈስ ቅዱስ ለጥንት ክርስቲያኖች እንደ አስተማሪ ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነበር?

13 መንፈስ ቅዱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች እንዲያስታውሱ ከመርዳቱም በላይ ስለ አምላክ ዓላማ የተሟላ እውቀት አስጨብጧቸዋል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እርሱ አብሯቸው እያለ ከነገራቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን በወቅቱ ሙሉ በሙሉ አልተረዷቸውም ነበር። በኋላ ግን ዮሐንስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ይሁዳና ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የአምላክ ዓላማ ፍጻሜውን ስለሚያገኝበት መንገድ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ ልክ እንደ አስተማሪ ሆኖ በማገልገል ደቀ መዛሙርቱ አምላክ እንደሚመራቸው እርግጠኞች እንዲሆኑ አድርጓል።

14. መንፈስ ቅዱስ የይሖዋን ሕዝቦች የረዳቸው በምን መንገዶች ነበር?

14 ተአምራዊ የሆኑት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችም አምላክ የአይሁድን ብሔር መተዉንና ሞገሱን ለክርስቲያን ጉባኤ መስጠቱን ለማሳየት አገልግለዋል። (ዕብራውያን 2:4) ከዚህም በላይ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የሚያፈራው ፍሬ እውነተኛዎቹን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለይቶ ለማወቅ አስችሏል። (ዮሐንስ 13:35፤ ገላትያ 5:22-24) እንዲሁም ይህ መንፈስ በወቅቱ የነበረው ጉባኤ አባላት ደፋር ምሥክሮች እንዲሆኑ ብርታት ሰጥቷቸዋል።​—⁠ሥራ 4:31

ከባድ ችግር ሲያጋጥም እርዳታ ማግኘት

15. (ሀ) ጥንትም ሆነ ዛሬ ክርስቲያኖች ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? (ለ) ሌሎችን ሲያበረታቱ የነበሩ ክርስቲያኖች ራሳቸው አንዳንድ ጊዜ መጽናኛ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

15 ለአምላክ ያደሩና ለእርሱ ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች በሙሉ ስደት ሊያጋጥማቸው ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ይሁን እንጂ በርካታ ክርስቲያኖች በጣም ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። በዚህ ዘመን አንዳንዶች ሕዝባዊ ዓመፅ ተፈጽሞባቸዋል፣ በማጎሪያ ካምፖችና በወኅኒ ቤቶች ተጥለዋል እንዲሁም የጉልበት ሥራ በሚሠራባቸው ቦታዎች ሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ እንዲሠሩ ተደርገዋል። መንግሥታት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት በመቀስቀስ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ሆነዋል፤ አሊያም አንዳንድ ግለሰቦች በምሥክሮቹ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ በቸልታ ተመልክተዋል። ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች ከባድ የጤና እክሎችና የቤተሰብ ችግሮችም አጋጥመዋቸዋል። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር የሚገኙ የእምነት ባልደረቦቹን ለመርዳት የሚጥር አንድ የጎለመሰ ክርስቲያንም እንኳ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ሌሎችን ሲያበረታታ የነበረው ክርስቲያን ራሱ መጽናኛ ማግኘት ያስፈልገው ይሆናል።

16. ዳዊት ከባድ ችግር ባጋጠመው ጊዜ እርዳታ ያገኘው እንዴት ነው?

16 ዳዊት ንጉሥ ሳኦል በነፍስ ይፈልገው በነበረበት ወቅት “አቤቱ፣ ጸሎቴን ስማኝ፣ . . . በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ” በማለት አምላክ እንዲረዳው ለምኗል። (መዝሙር 54:2, 4፤ 57:1) ዳዊት የፈለገውን እርዳታ አግኝቶ ይሆን? አዎን አግኝቷል። በዚያ ወቅት ይሖዋ በነቢዩ ጋድና በካህኑ አብያታር በመጠቀም ለዳዊት መመሪያ የሰጠው ሲሆን በሳኦል ልጅ በዮናታን በኩል ደግሞ አበረታቶታል። (1 ሳሙኤል 22:1, 5፤ 23:9-13, 16-18) ይሖዋ ፍልስጥኤማውያን ምድሪቱን እንዲወርሩ በመፍቀድ ሳኦል ዳዊትን ከማሳደድ እንዲመለስ አድርጓል።​—⁠1 ሳሙኤል 23:27, 28

17. ኢየሱስ አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥመው እርዳታ የጠየቀው ከማን ነው?

17 ኢየሱስ ክርስቶስም ምድራዊ ሕይወቱን ሊያጠናቅቅ በተቃረበበት ወቅት በጣም ተጨንቆ ነበር። እርሱ የሚወስደው እርምጃ የሰማያዊ አባቱን ስምና የሰው ልጆችን የወደፊት ሕይወት እንዴት እንደሚነካ በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። ‘በፍርሃት እያጣጣረ’ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። አምላክም በዚያ አስጨናቂ ሰዓት ኢየሱስ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሰጥቶታል።​—⁠ሉቃስ 22:41-44

18. አምላክ ከባድ ስደት የደረሰባቸውን የጥንት ክርስቲያኖች ያጽናናቸው እንዴት ነበር?

18 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ከባድ ስደት በመቀስቀሱ ከሐዋርያት በስተቀር ሁሉም ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም ሸሹ። አሳዳጆቻቸው ወንዶችና ሴቶችን ከገዛ ቤታቸው ጎትተው በማውጣት ያስሯቸው ነበር። አምላክ ያጽናናቸው እንዴት ነው? ከክርስቶስ ጋር ሰማያዊ ውርሻቸውን በማግኘት “የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ” እንደሚቀበሉ በቃሉ ውስጥ የተሰጣቸው ተስፋ አጽናንቷቸዋል። (ዕብራውያን 10:34፤ ኤፌሶን 1:18-20) መስበካቸውን በቀጠሉ መጠን የአምላክ መንፈስ ከእነርሱ ጋር መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አገኙ፤ በአገልግሎታቸው ያገኙት ስኬትም ተጨማሪ ደስታ አስገኝቶላቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 5:11, 12፤ ሥራ 8:1-40

19. ጳውሎስ ከባድ ስደት ቢያጋጥመውም ከአምላክ ስለሚገኘው መጽናኛ ምን ተሰምቶት ነበር?

19 በአንድ ወቅት ኃይለኛ አሳዳጅ የነበረው ሳውል (ጳውሎስ) ክርስቲያን በመሆኑ ምክንያት ውሎ አድሮ እርሱ ራሱ የጥቃት ዒላማ ሆኗል። በቆጵሮስ ደሴት ላይ አንድ ጠንቋይ ጳውሎስን በመቃወም አገልግሎቱን ለማስተጓጎል ጥረት አድርጓል። ጳውሎስ በገላትያ ራሱን እስኪስት ድረስ በድንጋይ ተወግሯል። (ሥራ 13:8-10፤ 14:19) በመቄዶንያ ደግሞ በበትር ተደብድቧል። (ሥራ 16:22, 23) በኤፌሶን የሕዝብ ረብሻ ከተቀሰቀሰበት በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቈርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፣ . . . እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።” (2 ቆሮንቶስ 1:8, 9) ሆኖም ጳውሎስ በዚያው ደብዳቤ ላይ በዚህ ርዕስ ሥር አንቀጽ 2 ላይ የተጠቀሱትን የሚያጽናኑ ቃላት ጽፏል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

20. በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመለከታለን?

20 አንተስ ሌሎችን ማጽናናት የምትችለው እንዴት ነው? በዘመናችን በአንድ አካባቢ በብዙ ሺዎች ላይ በሚደርስ አደጋ ወይም በግለሰብ ደረጃ በደረሰባቸው መከራ ምክንያት ያዘኑና መጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በሚቀጥለው ርዕስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸውን ሰዎች እንዴት ማጽናናት እንደምንችል እንመለከታለን።

ታስታውሳለህን?

• ከአምላክ የሚገኘው መጽናኛ ተወዳዳሪ የለውም የምንለው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ በክርስቶስ ተጠቅሞ ሰዎችን ያጽናናው እንዴት ነው?

• መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ የሆነው እንዴት ነው?

• አምላክ አገልጋዮቹ ከባድ ችግር ሲያጋጥማቸው እንዴት እንዳጽናናቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሕዝቦቹን ነፃ በማውጣት እንዳጽናናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በማስተማር፣ የታመሙትን በመፈወስና ሙታንን በማስነሳት ሰዎችን አጽናንቷል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ከይሖዋ እርዳታ አግኝቷል