በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን ካልታወቀ ምንጭ ድምፅ የሚሰማ ከሆነ አጋንንት ተጽዕኖ እያደረጉበት ነው ብለን መደምደም ይኖርብናል?

አይኖርብንም። አጋንንት በዚህ መንገድ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ የሚታወቅ ቢሆንም ካልታወቀ ምንጭ ድምፅ የሚሰማቸው ወይም ሌላ ዓይነት ለመግለጽ የሚያስቸግር የመረበሽ ስሜት የሚያጋጥማቸው ብዙ ሰዎች የሕክምና ምርመራ ሲያደርጉ አንድ ዓይነት የጤና ችግር እንዳለባቸው ተገንዝበዋል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንኳ የአጋንንት ጥቃትና የጤና ችግሮች አንዳንድ ጊዜ ተመሳሳይ ምልክት ሊኖራቸው እንደሚችል በሚገባ ይታወቅ ነበር። በማቴዎስ 17:​14-18 ላይ ኢየሱስ ስለፈወሰው አንድ ወጣት የሚናገር ዘገባ እናገኛለን። ምንም እንኳ ልጁ ከባድ የሚጥል በሽታ እንዳለበት የሚያሳዩ ምልክቶች ቢታዩበትም የሥቃዩ መንስኤ ግን በውስጡ ያደረበት አጋንንት ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ብሎ ሰዎች ኢየሱስ እንዲፈውሳቸው ብዙ ሕሙማን ይዘው በመጡበት ወቅት ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ‘አጋንንት ያደረባቸው እና የሚጥል በሽታ ያለባቸው’ ነበሩ። (ማቴዎስ 4:​24 አ.መ.ት ) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሁሉ አጋንንት ያደረባቸው እንዳልሆኑ በወቅቱ ይታወቅ ነበር። የእነዚህ ሰዎች ችግር የጤና መቃወስ ነበር።

ስኪትሰፍሪኒያ በተባለ የአእምሮ በሽታ (አብዛኛውን ጊዜ በሕክምና ሊድን የሚችል ነው) የሚሰቃዩ አንዳንድ ሰዎች ካልታወቀ ምንጭ ድምፅ እንደሚሰሙ ወይም እንግዳ የሆኑ የጤና መቃወስ ምልክቶች እንደሚያጋጥሟቸው ተደርሶበታል። a የአእምሮ መዛባት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሌሎች የጤና ችግሮችም ያሉ ሲሆን አንዳንዶች የችግሩ መንስኤ የአጋንንት ተጽዕኖ ነው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። በመሆኑም አንድ ሰው ካልታወቀ ምንጭ ድምፅ ይሰማኛል ወይም የሚረብሽ ስሜት ያጋጥመኛል ካለ የችግሩ መንስኤ የአጋንንት ተጽዕኖ አይደለም ብሎ መደምደም ባይቻልም ከጤና እክል የመነጨ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሕክምና ምርመራ እንዲያደርግ ማበረታታት ይገባል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

aመጠበቂያ ግንብ ተጓዳኝ በሆነው በንቁ! መጽሔት የመስከረም 8, 1986 (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “ቴኪንግ ዘ ሚስትሪ አውት ኦቭ ሜንታል ኢልነስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።