ያዘኑትን አጽናኑ
ያዘኑትን አጽናኑ
‘የሚያለቅሱትን ሁሉ አጽናና ዘንድ ይሖዋ ቀብቶኛል።’—ኢሳይያስ 61:1, 2
1, 2. እነማንን ማጽናናት ይኖርብናል? ለምንስ?
የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው ይሖዋ መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች አሳቢነት እንድናሳይ አስተምሮናል። “የተጨነቁትን ነፍሳት” እና ያዘኑትን ሰዎች እንድናጽናና አስተምሮናል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW ) አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የእምነት ባልንጀሮቻችንን እናጽናናቸዋለን። የጉባኤው አባላት ላልሆኑ ሌላው ቀርቶ እኛን ለማይወዱን ሰዎችም እንኳ ፍቅር እናሳያለን።—ማቴዎስ 5:43-48፤ ገላትያ 6:10
2 ኢየሱስ ክርስቶስ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ . . . የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ” የሚለውን ትንቢት ካነበበ በኋላ ትንቢቱ በእርሱ ላይ እንደተፈጸመ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:16-19) በዚህ ዘመን ያሉ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ይህ ተልዕኮ ለእነርሱም እንደሚሠራ ከተገነዘቡ ቆይተዋል፤ ‘ሌሎች በጎችም’ ከእነርሱ ጋር በመተባበር በዚህ ሥራ በደስታ ይካፈላሉ።—ዮሐንስ 10:16
3. “አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ ሲደርስ በዝምታ የሚመለከተው ለምንድን ነው?” ብለው የሚጠይቁ ሰዎችን እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
3 ብዙውን ጊዜ ሰዎች አንድ ዓይነት አደጋ ደርሶባቸው ልባቸው በሐዘን ሲሰበር “አምላክ ይህ ሁሉ ሲሆን በዝምታ የሚመለከተው ለምንድን ነው?” ብለው ይጠይቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ይሰጣል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ላልሆነ ሰው መልሱን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ጊዜ ይወስድበት ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁአቸው ጽሑፎች በዚህ ረገድ ጠቃሚ እርዳታ ያበረክታሉ። a ኢሳይያስ 61:1, 2ን የመሳሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማንበቡ ብቻ እንኳን አንዳንዶችን አጽናንቷቸዋል፤ ጥቅሱ አምላክ ሰዎች መጽናኛ እንዲያገኙ እንደሚፈልግ ይገልጻል።
4. በፖላንድ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር በጭንቀት የተዋጠችን አንዲት ወጣት የረዳቻት እንዴት ነው? ሌሎችን ስለ መርዳት ከዚህ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
4 ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች መጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። በፖላንድ የምትኖር በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት ወጣት ያስጨነቃትን ነገር ለአንዲት የምታውቃት ሴት አወያየቻት። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ይህቺ ሴት ወጣቷን ቀስ ብላ አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ያስጨነቃትን ነገር ማወቅ ቻለች። ወጣቷን ያስጨነቋት ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ:- “ክፋት የበዛው ለምንድን ነው? ሰዎች የሚሰቃዩት ለምንድን ነው? እህቴ የአካል ጉዳተኛ የሆነችው ለምንድን ነው? እኔስ የልብ ሕመምተኛ የሆንኩት ለምንድን ነው? ይህ ሁሉ የአምላክ ሥራ እንደሆነ በቤተ ክርስቲያን ይነገረናል። እንደዚህ ከሆነ ከአሁን በኋላ በእርሱ አላምንም!” እህት በልቧ ወደ ይሖዋ ከጸለየች በኋላ “ስለዚህ ጉዳይ ስለጠየቅሽኝ ደስ ብሎኛል። ልረዳሽ እሞክራለሁ” አለቻት። ከዚያም እርሷ ራሷ ልጅ ሳለች ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደነበሯትና የይሖዋ ምሥክሮች መልስ እንደሰጧት ነገረቻት። አክላም እንዲህ አለቻት:- “አምላክ ሰዎችን እንደማያሰቃይ ከዚህ ይልቅ እንደሚወዳቸውና መልካም ነገሮችን እንዲያገኙ እንደሚፈልግ እንዲሁም በቅርቡ በዚህች ምድር ላይ ታላላቅ ለውጦችን እንደሚያመጣ ተማርኩ። ሕመም፣ እርጅናና ሞት የሚወገዱ ሲሆን ታዛዥ የሆኑ ሰዎች እዚችው ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” ራእይ 21:3, 4ን፤ ኢዮብ 33:25ን፤ ኢሳይያስ 35:5-7ን እና 65:21-25ን አነበበችላት። ረዘም ያለ ውይይት ካደረጉ በኋላ ወጣቷ ልጅ በእፎይታ ስሜት “አሁን የሕይወት ዓላማ ገብቶኛል። ሌላም ጊዜ መጥቼ ልንወያይ እንችላለን?” አለቻት። በሳምንት ሁለት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።
ከአምላክ በሚገኘው መጽናኛ ሌሎችን አጽናኑ
5. ሰዎችን ለማጽናናት በምን መጠቀም ይኖርብናል?
5 ሰዎችን ስናጽናና በአዘኔታ ስሜት ማነጋገሩ በጣም አስፈላጊ ነው። በንግግራችንም ሆነ በድምፃችን ቃና ሐዘን ለደረሰበት ሰው በጥልቅ እንደምናስብ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። መናገር የሌለብንን ነገር እንዳንናገር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንደሚሆንልን’ ይነግረናል። (ሮሜ 15:4) ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ተስማሚ የሆነ ጊዜ መርጠን የአምላክ መንግሥት ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ይህ መንግሥት ዛሬ ያሉትን ችግሮች እንዴት እንደሚያስወግድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ልናሳያቸው እንችላለን። ከዚያም ተስፋው እምነት የሚጣልበት የሆነው ለምን እንደሆነ ልንነግራቸው እንችላለን። በዚህ መንገድ ሰዎችን እናጽናናለን።
6. ሰዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኘው መጽናኛ የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
6 አንድን ሰው ለማጽናናት የምናደርገው ጥረት ግቡን እንዲመታ ግለሰቡ እውነተኛውን አምላክና ባሕርያቱን ማወቅ እንዲሁም የሰጣቸው ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ መገንዘብ ይኖርበታል። የይሖዋ አምላኪ ያልሆነን ሰው ለመርዳት ጥረት በምናደርግበት ጊዜ የሚከተሉትን ነጥቦች ማብራራት ይኖርብናል:- (1) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መጽናኛ ምንጭ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው። (2) ይሖዋ አፍቃሪና ሁሉን ቻይ ከመሆኑም በላይ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንዲሁም ፍቅራዊ ደግነቱና እውነቱ የበዛ አምላክ ነው። (3) የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደ አምላክ ከቀረብን ችግሮቻችንን ለመወጣት የሚያስችል ብርታት እናገኛለን። (4) መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ግለሰቦች ስላጋጠሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች የሚናገሩ ጥቅሶች ይዟል።
7. (ሀ) ከአምላክ የሚገኘው መጽናኛ ‘በክርስቶስ በኩል እንደሚበዛ’ ጎላ አድርገን መጥቀሳችን ምን ጥቅም አለው? (ለ) መጥፎ ነገር እንደሠራ የሚሰማውን ሰው ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?
7 አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያነቡ ሐዘን ያጋጠማቸው ሰዎች 2 ቆሮንቶስ 1:3-7ን በማንበብ አጽናንተዋቸዋል። ጥቅሱን ሲያነቡ ‘መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና’ የሚለውን ሐሳብ ጎላ አድርገው አብራርተውላቸዋል። ይህ ጥቅስ ግለሰቡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጽናኑ ሐሳቦች የያዘ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል። ከዚህም በላይ በሌላ ጊዜ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ መንገድ ይከፍታል። ግለሰቡ መከራ የደረሰበት መጥፎ ነገር በመሥራቱ እንደሆነ ከተሰማው ፈራጅ ሳንሆን በ1 ዮሐንስ 2:1, 2ና መዝሙር 103:11-14 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች ማወቁ እንደሚያጽናና ልንነግረው እንችላለን። በእነዚህ መንገዶች ከአምላክ በሚገኘው መጽናኛ ሌሎችን ማጽናናት እንችላለን።
በዓመፅና በኢኮኖሚያዊ ችግሮች መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት
8, 9. የዓመፀኞች ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማጽናናት የሚቻለው እንዴት ነው?
8 በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ በተስፋፋው ዓመፅ ወይም በጦርነት ምክንያት ሕይወታቸው ተመሰቃቅሏል። ልናጽናናቸው የምንችለው እንዴት ነው?
9 እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም ላይ በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ በአንደበታቸውም ሆነ በድርጊታቸው የትኛውንም ተፋላሚ አንጃ ላለመደገፍ ይጠነቀቃሉ። (ዮሐንስ 17:16) ሆኖም ዛሬ ያሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚወገዱበት ጊዜ እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ያስረዳሉ። ይሖዋ ዓመፅን ስለሚወዱ ሰዎች ያለውን አመለካከት ለማሳየት መዝሙር 11:5ን ያነብባሉ፤ ወይም በደል ሲፈጸምብን አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ በአምላክ ልንታመን እንደሚገባ ለማሳየት መዝሙር 37:1-4ን ሊያነቡ ይችላሉ። መዝሙር 72:12-14 በአሁኑ ወቅት በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ የሚገኘው ታላቁ ሰሎሞን ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓመፅ ድርጊት ለሚፈጸምባቸው ንጹሐን ሰዎች ያለውን ስሜት ይገልጻል።
10. ለዓመታት በጦርነት በሚታመስ አካባቢ ከኖርህ በአንቀጹ ውስጥ ያሉት ጥቅሶች ሊያጽናኑህ የሚችሉት እንዴት ነው?
10 አንዳንድ ሰዎች ተፋላሚ አንጃዎች አንድን አካባቢ ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ሳቢያ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጦርነት በሚካሄድባቸው ቦታዎች ይኖራሉ። ጦርነትና ጦርነትን ተከትለው የሚመጡት ችግሮች የሕይወታቸው ክፍል እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ብቸኛው አማራጭ ወደ ሌላ አገር መሸሽ እንደሆነ ያስባሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ እንደዚህ ለማድረግ አይሳካላቸውም፤ ወደ ሌላ አገር ለመሸሽ የሞከሩ አንዳንዶች ደግሞ በዚሁ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ተሳክቶላቸው ወደ ሌላ አገር የሄዱትም ቢሆኑ ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በአብዛኛው ከችግር አላመለጡም። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ወደ ሌላ አገር ከመሰደድ የተሻለ ተስፋ እንዲኖራቸው ለመርዳት መዝሙር 146:3-6ን ልናነብላቸው እንችላለን። በማቴዎስ 24:3, 7, 14 እና በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ ያሉት ትንቢቶች ሰዎች የሚደርስባቸው መከራ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለውና ችግሮቹ እየተባባሱ የመጡት በዚህ አሮጌ ሥርዓት መጨረሻ ዘመን ላይ ስለምንኖር እንደሆነ እንዲያስተውሉ ይረዷቸዋል። እንደ መዝሙር 46:1-3, 8, 9 እና ኢሳይያስ 2:2-4 የመሳሰሉት ጥቅሶች ወደፊት ሰላም የሰፈነበት ጊዜ እንደሚመጣ እንዲገነዘቡ ሊረዷቸው ይችላሉ።
11. በምዕራብ አፍሪካ የምትኖርን አንዲት ሴት ያጽናኗት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው? ለምንስ?
11 ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጦርነት በሚካሄድባት አንዲት የምዕራብ አፍሪካ አገር የምትኖር አንዲት ሴት በጥይት እሩምታ መሃል ቤተሰቧን ይዛ ተሰደደች። ልብዋ በፍርሃት፣ በሐዘንና በተስፋ መቁረጥ ተሞልቶ ነበር። ቤተሰቡ በሌላ አገር መኖር ከጀመረ በኋላ ባለቤቷ የጋብቻ የምሥክር ወረቀታቸውን ለማቃጠልና በወቅቱ ነፍሰ ጡር የነበረችውን እሷንና የአሥር ዓመት ልጃቸውን አባርሮ ቄስ ለመሆን ፈለገ። ይህቺ ሴት ፊልጵስዩስ 4:6, 7ና መዝሙር 55:22 እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ የወጡ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ሲነበቡላት ከመጽናናቷም በላይ ሕይወት ዓላማ እንዳለው ተገነዘበች።
12. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ሰዎች ምን መጽናኛ ይዞላቸዋል? (ለ) በእስያ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ደንበኛዋን ያጽናናቻት እንዴት ነው?
12 የኢኮኖሚ ውድቀት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አመሰቃቅሏል። አንዳንድ ጊዜ ለዚህ ምክንያት የሚሆኑት ጦርነትና ጦርነትን ተከትለው የሚመጡ ችግሮች ናቸው። መንግሥታት የሚከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲ እንዲሁም በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ስግብግቦችና እምነት አጉዳዮች መሆናቸውም ሕዝቡ ለነገ ብሎ የቋጠረውንና አለኝ የሚለውን ንብረቱን እንዲያጣ አድርጎታል። ሌሎች ደግሞ ምንም የሌላቸው ድሆች ናቸው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በሙሉ አምላክ በእርሱ ለሚታመኑት እፎይታ እንደሚያስገኝላቸውና ሰዎች በእጃቸው ሥራ ደስ የሚሰኙበት ጽድቅ የሰፈነበት ዓለም እንደሚያመጣ ማወቃቸው ሊያጽናናቸው ይችላል። (መዝሙር 146:6, 7፤ ኢሳይያስ 65:17, 21-23፤ 2 ጴጥሮስ፤ 3:13) በአንዲት የእስያ አገር በሱቅ ውስጥ የምትሠራ የይሖዋ ምሥክር አንድ ደንበኛቸው አገሪቱ ያለችበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባት ስትናገር ሰማች፤ ምሥክሯም በእነርሱ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ገለጸችላት። በማቴዎስ 24:3-14 እና በመዝሙር 37:9-11 ላይ ከተወያዩ በኋላ ሴትዮዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች።
13. (ሀ) ቃል የተገባላቸው ነገር የሕልም እንጀራ የሆነባቸውን ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ልናጽናናቸው የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የሚደርስባቸው ክፉ ነገር አምላክ አለመኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንደሆነ የሚሰማቸውን ሰዎች እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?
13 ሰዎች ለበርካታ ዓመታት መከራ ሲደርስባቸው ወይም ቃል የተገባላቸው ነገር የሕልም እንጀራ ሆኖ ሲቀር ‘ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ’ ቃሉን እንዳልሰሙት በግብጽ እንደነበሩት እስራኤላውያን ሊሆኑ ይችላሉ። (ዘጸአት 6:9 አ.መ.ት) እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ እንዲወጡና ሕይወታቸውን ሊያበላሹባቸው ከሚችሉ ስሕተቶች እንዲርቁ እንዴት እንደሚረዳቸው ጎላ አድርጎ መጥቀስ ጠቃሚ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:8ለ) አንዳንዶች እነርሱ ያሉበት መጥፎ ሁኔታ አምላክ እንደሌለ፣ ቢኖርም ስለ እነርሱ እንደማያስብ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ይናገራሉ። አምላክ ሰዎችን ለመርዳት ቢፈልግም ሰዎች ፈቃደኛ እንዳልሆኑ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ተስማሚ ጥቅሶችን በመጠቀም ልታስረዳቸው ትችላለህ።—ኢሳይያስ 48:17, 18
በአውሎ ነፋስና በመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት
14, 15. የይሖዋ ምሥክሮች በሽብርተኞች ጥቃት ምክንያት በሐዘን የተዋጡ ሰዎችን ለማጽናናት ምን አድርገዋል?
14 በአውሎ ነፋስ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በእሳት አደጋ ወይም በፍንዳታ ምክንያት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስባቸውና በሐዘን ሊዋጡ ይችላሉ። በሕይወት የተረፉትን ሰዎች ለማጽናናት ምን ማድረግ ይቻላል?
15 ሰዎች የሚያስብላቸው አካል እንዳለ ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። በአንድ አገር ሽብርተኞች በሰነዘሩት ጥቃት ሳቢያ በደረሰው አደጋ ሕዝቡ በጣም አዝኖ ነበር። ብዙዎች የቤተሰባቸውን አባላት፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪያቸውን፣ ወዳጆቻቸውንና ሥራቸውን ከማጣታቸውም በላይ በምንም ነገር መተማመን እንደማይችሉ ተሰምቷቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው የሚኖሩ ሰዎችን በሁኔታው ማዘናቸውን በመግለጽ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሱ አጽናንተዋቸዋል። ብዙዎች በአሳቢነት ስለተደረገላቸው ነገር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
16. በኤል ሳልቫዶር አደጋ በደረሰ ጊዜ በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በመስክ አገልግሎታቸው ውጤታማ የሆኑት ምን በማድረጋቸው ነው?
16 በኤል ሳልቫዶር በ2001 የደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና ናዳ የብዙዎችን ሕይወት አጥፍቷል። የአንዲት እህት የ25 ዓመት ወንድ ልጅና የእጮኛው ሁለት እህቶች በአደጋው ሕይወታቸውን አጥተዋል። የልጁ እናትና እጮኛው ጊዜ ሳያጠፉ ራሳቸውን በመስክ አገልግሎት አስጠመዱ። ካነጋገሯቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በአደጋው የሞቱትን ሰዎች አምላክ ወደ ራሱ እንደወሰዳቸው ወይም አደጋው የአምላክ ቁጣ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ምሥክሮቹ አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲደርስብን እንደማይፈልግ ለማስረዳት ምሳሌ 10:22ን ጠቀሱላቸው። ሰዎች የሚሞቱት አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት እንደሆነና ሞትን ያመጣው አምላክ እንዳልሆነ ሮሜ 5:12ን በመጥቀስ አስረዷቸው። ከዚህም በተጨማሪ በመዝሙር 34:18፤ 37:29፤ በኢሳይያስ 25:8 እና በራእይ 21:3, 4 ላይ የሚገኘውን የሚያጽናና መልእክት ጠቀሱላቸው። ሁለቱ እህቶች ራሳቸው በአደጋው የቤተሰባቸውን አባላት ያጡ በመሆናቸው ሰዎች ትኩረት ሰጥተው ያዳምጧቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምረዋል።
17. አደጋ ሲከሰት ምን ዓይነት እርዳታ ማበርከት ትችላለህ?
17 አንድ ዓይነት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ትመለከት ይሆናል። ጉዳት የደረሰበትን ሰው ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ወይም ምግብና ልብስ ለማቅረብ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ። በ1998 ኢጣሊያ ውስጥ አደጋ በደረሰበት ወቅት አንድ ጋዜጠኛ የይሖዋ ምሥክሮች “ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ጉዳት የደረሰባቸውን ሁሉ ለመርዳት የታሰበበት ጥረት አድርገዋል” ሲል የታዘበውን ዘግቧል። የመጨረሻውን ዘመን እንደሚያመለክቱ በትንቢት የተነገሩት ክስተቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህ ክስተቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ መሆናቸውን በማስረዳትና የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘር እውነተኛ ደህንነት እንደሚያመጣ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በመጥቀስ ሰዎችን ለማጽናናት ሞክረዋል።—ምሳሌ 1:33፤ ሚክያስ 4:4
የቅርብ ዘመዳቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን ማጽናናት
18-20. የቅርብ ዘመዳቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን ለማጽናናት ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ ትችላለህ?
18 በየዕለቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው መሪር ሐዘን ይደርስባቸዋል። በአገልግሎት ላይ እያለህ ወይም ዕለታዊ እንቅስቃሴዎችህን በምታከናውንበት ጊዜ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ታገኝ ይሆናል። እነዚህን ሰዎች ለማጽናናት ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ ትችላለህ?
19 ግለሰቡ ሐዘኑ ጎድቶታል? በቤቱ ውስጥ የሐዘንተኛው ዘመዶች የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ? ሐዘንተኛውን ለማጽናናት ብዙ ልትናገር የምትችለው ነገር ቢኖርም ሚዛናዊ መሆን አስፈላጊ ነው። (መክብብ 3:1, 7) እንዲህ ባለው ወቅት በሁኔታው ማዘንህን ገልጸህ ተስማሚ የሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ (ብሮሹር፣ መጽሔት ወይም ትራክት) ትተህ መሄዱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልግ እንደሆነ ለመመልከት በሌላ ጊዜ ተመልሰህ መምጣት ትችላለህ። ሁኔታው አመቺ በሚሆንበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመህ የሚያጽናኑ ሐሳቦች አካፍለው። እንደዚህ ማድረግህ ሐዘን የደረሰበት ሰው እንዲረጋጋና እንዲጽናና ሊረዳው ይችላል። (ምሳሌ 16:24፤ 25:11) ኢየሱስ እንዳደረገው የሞቱትን ሰዎች ማስነሳት እንደማትችል የታወቀ ነው። በዚህ ወቅት የተሳሳቱ ትምህርቶችን ለማረም መሞከሩ ተገቢ ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ምን እንደሚል ልትነግራቸው ትችላለህ። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ስለ ትንሣኤ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አብራችሁ ልታነቡ ትችላላችሁ። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) ትንሣኤ ስላገኙ ሰዎች የሚዘግቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን አንስተህ በማወያየት ትንሣኤ ምን እንደሆነ ልታስረዳቸው ትችላለህ። (ሉቃስ 8:49-56፤ ዮሐንስ 11:39-44) እንዲሁም የትንሣኤን ተስፋ የሰጠን አፍቃሪ አምላክ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ጎላ አድርገህ ግለጽለት። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐንስ 3:16) ስለ ትንሣኤ ማወቅህ አንተን በግልህ እንዴት እንደጠቀመህና ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንድትሆን ያደረገህን ምክንያት ግለጽለት።
20 ሐዘን የደረሰበትን ሰው አፍቃሪና አጽናኝ የሆኑ ሰዎች ወደሚሰበሰቡበት ወደ መንግሥት አዳራሹ መጋበዝ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በስዊድን የምትኖር አንዲት ሴት ወደ መንግሥት አዳራሹ ከመጣች በኋላ ለረጅም ጊዜ ስትመኘው የነበረውን ነገር እንዳገኘች ተናግራለች።—ዮሐንስ 13:35፤ 1 ተሰሎንቄ 5:11
21, 22. (ሀ) ሌሎችን ለማጽናናት ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? (ለ) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎችን ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?
21 ሐዘን የደረሰበት ሰው የይሖዋ ምሥክር ይሁንም አይሁን ግለሰቡን ለማጽናናት ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ እንዳለብህ ግራ ገብቶህ ያውቃል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መጽናኛ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ከጎኔ ሁን” ማለት ነው። እውነተኛ አጽናኝ መሆን ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ራስን ማቅረብን ይጠይቃል።—ምሳሌ 17:17
22 ሐዘን የደረሰበት ሰው ስለ ሞት፣ ስለ ቤዛው ዝግጅትና ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያውቅ ቢሆንስ? የእርሱ ዓይነት እምነት ያለው ወዳጁ አብሮት መሆኑ ብቻ እንኳን ሊያጽናናው ይችላል። ሐዘንተኛው ሲናገር ጆሮህን ሰጥተህ አዳምጠው። የግድ መናገር እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ አውጥታችሁ የምታነብቡ ከሆነ የምታነቡት ነገር አምላክ ሁለታችሁንም ለማበርታት የተናገረው እንደሆነ አድርገህ ተናገር። ሁለታችሁም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱት ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ያላችሁን ጠንካራ እምነት ግለጽ። እንደ አምላክ ያለ ርኅራኄ በማሳየትና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ውድ እውነት በማካፈል ያዘኑ ሰዎች “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ መጽናኛና ብርታት እንዲያገኙ ልትረዳቸው ትችላለህ።—2 ቆሮንቶስ 1:3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ምዕራፍ 8፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር ገጽ 392-398 እና 427-431፣ ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) ምዕራፍ 10፣ እንዲሁም አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባሉትን ጽሑፎች ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ብዙ ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው ተጠያቂ የሚያደርጉት ማንን ነው? እንዴትስ ልንረዳቸው እንችላለን?
• ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው መጽናኛ የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?
• አንተ በምትኖርበት አካባቢ ሰዎች ምን አሳዛኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል? እንዴትስ ልታጽናናቸው ትችላለህ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስደተኞች መጠለያ ካምፕ:- UN PHOTO 186811/J. Isaac
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ እውነተኛ መጽናኛ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ለሌሎች ማካፈል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዘንተኛው ወዳጁ አብሮት መሆኑ ብቻ እንኳን ያጽናናዋል