በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ የምታደርገውን ነገር በቁም ነገር ይመለከተዋልን?

ይሖዋ የምታደርገውን ነገር በቁም ነገር ይመለከተዋልን?

ይሖዋ የምታደርገውን ነገር በቁም ነገር ይመለከተዋልን?

ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ? ብዙዎች ‘አምላክ እንደ ሙሴ፣ ጌዴዎንና ዳዊት ያሉ ሰዎች ያከናወኑትን ነገር እንደተመለከተ አምናለሁ፤ ሆኖም እኔ የማደርጋቸውን ነገሮች ከቁብ የሚቆጥራቸው መሆኑን እጠራጠራለሁ። ከሙሴ፣ ከጌዴዎን ወይም ከዳዊት ጋር ልወዳደር እንደማልችል የታወቀ ነው’ ይሉ ይሆናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ታማኝ ሰዎች እንደ ተአምር የሚታዩ የእምነት ሥራዎችን መፈጸማቸው እሙን ነው። ‘መንግሥታትን ድል ነስተዋል፣ የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል፣ የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል እንዲሁም ከሰይፍ ስለት አምልጠዋል።’ (ዕብራውያን 11:​33, 34) ሌሎች ግን እምነታቸውን ያሳዩት ከእነዚህ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ በማይባል መንገድ ሲሆን አምላክ የእነርሱንም የእምነት ሥራ በቁም ነገር እንደተመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል የአንድ እረኛ፣ የአንድ ነቢይና የአንዲት መበለትን ታሪክ ተመልከት።

አንድ እረኛ መሥዋዕት አቀረበ

የአዳምና የሔዋን ሁለተኛ ልጅ የነበረው የአቤል ስም ሲነሳ ምን ትዝ ይልሃል? በሰማዕትነት መሞቱን ታስታውስ ይሆናል፤ ይህም አብዛኞቻችን ይደርስብናል ብለን የማንጠብቀው ነገር ነው። ይሁን እንጂ አቤል በመጀመሪያ የአምላክን ትኩረት ለመሳብ የቻለው በሌላ ምክንያት ነበር።

አንድ ቀን ከመንጋው መካከል ምርጥ የሆኑትን እንስሳት ወስዶ ለአምላክ መሥዋዕት አቀረበ። ይህ ስጦታው በዛሬው ጊዜ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ቢችልም ይሖዋ ግን ስጦታውን በአድናቆት የተመለከተው ከመሆኑም በላይ በስጦታው መደሰቱን አሳይቷል። በዚህ ብቻ ግን አላበቃም፤ ወደ አራት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ይሖዋ በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ ስለዚህ ስጦታ እንዲጽፍ ሐዋርያው ጳውሎስን አነሳስቶታል። ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ አምላክ ይህን አነስተኛ ሊባል የሚችል መሥዋዕት አልረሳውም።​—⁠ዕብራውያን 6:​10፤ 11:​4

አቤል ምን ዓይነት መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለበት የወሰነው እንዴት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ባይነግረንም አቤል በምርጫው ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሳያስብበት አልቀረም። እረኛ ስለነበር ከበጎቹ መካከል ማቅረቡ የሚጠበቅ ነገር ነው። ሆኖም ምርጥ ከሆነው ማለትም “ከስቡ” እንዳቀረበ ልብ በል። (ዘፍጥረት 4:​4) እንዲሁም ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” ሲል ለእባቡ በተናገራቸው ቃላት ላይ በጥሞና አሰላስሎበት ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 3:​15፤ ራእይ 12:​ 9) ምንም እንኳን አቤል ‘የሴቲቱን’ እና ‘የዘርዋን’ ማንነት በግልጽ ባይረዳም የሴቲቱ ዘር ‘ሰኰና መቀጥቀጡ’ የደም መፍሰስን እንደሚጨምር ተገንዝቦ ሊሆን ይችላል። ሕይወትና እስትንፋስ ካለው ፍጡር የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር ሊኖር እንደማይችል ተገንዝቦ መሆን አለበት። ያም ሆነ ይህ ያቀረበው መሥዋዕት ፍጹም ትክክለኛ ነበር።

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም እንደ አቤል ለአምላክ መሥዋዕት ያቀርባሉ። የሚያቀርቡት መሥዋዕት የእንስሳት በኩራት ሳይሆን ‘የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለአምላክ ስም የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ’ ነው። (ዕብራውያን 13:​15) እምነታችንን ለሌሎች ስናካፍል በከንፈሮቻችን ስለ ስሙ እንመሰክራለን።

የምታቀርበውን መሥዋዕት ጥራት ለማሻሻል ትፈልጋለህ? እንግዲያው በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉት ሰዎች ምን እንደሚያስፈልጋቸው በጥንቃቄ አስብበት። ምን ነገሮች ያሳስቧቸዋል? ትኩረታቸው ያረፈው ምን ላይ ነው? ትኩረታቸውን ሊስበው የሚችለው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ነው? ምሥራቹን ለሰዎች በተናገርህ ቁጥር ውጤታማነትህን ለማሻሻል በማሰብ አቀራረብህን መለስ ብለህ ገምግም። እንዲሁም ስለ ይሖዋ ስትመሰክር ከልብ በመነጨ ስሜትና በጽኑ እምነት ተናገር። የምታቀርበው መሥዋዕት እውነተኛ ‘የምስጋና መሥዋዕት’ እንዲሆን አድርግ።

ተቀባይ ላልሆኑ ሰዎች የሰበከ ነቢይ

አሁን ደግሞ የነቢዩ ሄኖክን ታሪክ ተመልከት። በወቅቱ ስለ ይሖዋ አምላክ ይመሰክር የነበረው እርሱ ብቻ ሊሆን ይችላል። እንደ ሄኖክ ከቤተሰቦችህ መካከል ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ያለኸው አንተ ብቻ ነህ? በክፍልህ ውስጥ ካሉት ተማሪዎች ወይም በሥራ ቦታህ ካሉት ሠራተኞች መካከል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የምትከተለው አንተ ብቻ ነህ? ከሆነ ተጽዕኖ ሊያጋጥምህ ይችላል። ጓደኞችህ፣ ዘመዶችህ፣ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ወይም የሥራ ባልደረቦችህ የአምላክን ሕግጋት እንድትጥስ ግፊት ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። “ያደረግኸውን ነገር ማንም ሊያውቅ አይችልም። ለማንም አንናገርብህም” ይሉህ ይሆናል። አምላክ የፈለግኸውን ነገር ብታደርግ ግድ ስለማይሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመጠበቅ መጨነቅህ ከንቱ ልፋት ነው እያሉ ይጎተጉቱህ ይሆናል። በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ከእነርሱ የተለየህ መሆንህ ስለሚያበሳጫቸው አቋምህን ለማዳከም የቻሉትን ሁሉ ያደርጉ ይሆናል።

ግልጹን ለመናገር፣ እንዲህ ዓይነቱን ተጽዕኖ መቋቋም ቀላል ባይሆንም ከአቅማችን በላይ ግን አይደለም። በአዳም የትውልድ መስመር ሰባተኛ የነበረውን የሄኖክን ሁኔታ ተመልከት። (ይሁዳ 14) ሄኖክ በተወለደበት ዘመን አብዛኞቹ ሰዎች የሥነ ምግባር አቋማቸው ተበላሽቶ ነበር። ንግግራቸው አስጸያፊ፣ ምግባራቸው ደግሞ እጅግ አስነዋሪ ነበር። (ይሁዳ 15) አኗኗራቸው በዛሬው ጊዜ ካሉት ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነበር።

ሄኖክ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት የቻለው እንዴት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ለእኛም ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። ምንም እንኳን ሄኖክ በወቅቱ በምድር ላይ ይሖዋን የሚያመልክ ብቸኛው ሰው ሊሆን ቢችልም ሙሉ በሙሉ ግን ብቻውን አልተተወም። በሚያደርገው ነገር ሁሉ አምላክ አልተለየውም።​—⁠ዘፍጥረት 5:22

የሄኖክ ሕይወት ያተኮረው አምላክን በማስደሰት ላይ ነበር። አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ ማለት በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆነ አኗኗር መከተል ማለት ብቻ አለመሆኑን ተገንዝቧል። ይሖዋ እንዲሰብክ ይጠብቅበት ነበር። (ይሁዳ 14, 15) በወቅቱ ለነበሩት ሰዎች ኃጢአታቸው በአምላክ ዘንድ የተሰወረ እንዳልሆነ ማስጠንቀቂያ ሊነገራቸው ይገባ ነበር። ሄኖክ ከ300 ለሚበልጡ ዓመታት አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጎ ኖሯል፤ ይህም ማናችንም ብንሆን በጽናት ካሳለፍናቸው ዓመታት እጅግ የላቀ ነው። እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል።​—⁠ዘፍጥረት 5:23, 24

እኛም እንደ ሄኖክ የስብከት ተልዕኮ ተሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:14) ከቤት ወደ ቤት ከምናደርገው የስብከት ሥራችን በተጨማሪ ለዘመዶቻችን፣ በሥራ ጉዳይ ለምናገኛቸው ሰዎችና አብረውን ለሚማሩት ልጆች ምሥራቹን ለማካፈል ጥረት እናደርጋለን። አንዳንድ ጊዜ ግን በድፍረት ለመመሥከር እናመነታ ይሆናል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ተስፋ አትቁረጥ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የተዉትን አርዓያ ኮርጅ፤ እንዲሁም ድፍረት እንዲሰጥህ ወደ አምላክ ጸልይ። (ሥራ 4:29) አካሄድህን ከአምላክ ጋር እስካደረግህ ድረስ ብቻህን የተተውክ አለመሆንህን ፈጽሞ አትዘንጋ።

አንዲት መበለት ምግብ አዘጋጀች

በስም ያልተጠቀሰች አንዲት መበለት ምግብ በማዘጋጀቷ ብቻ ከአንድም ሁለት በረከት አግኝታለች! በአሥረኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በሰራፕታ ከተማ ትኖር የነበረችው ይህቺ መበለት ከእስራኤል ወገን አልነበረችም። ለረጅም ጊዜ የዘለቀው የድርቅና የረሃብ ዘመን ማብቂያ እየተቃረበ ሲመጣ መበለቲቱ የነበራት ምግብ ተሟጥጦ የቀራት አንድ እፍኝ ዱቄትና ለእርሷና ለልጅዋ የመጨረሻ ማዕድ ለማዘጋጀት የሚበቃ ዘይት ብቻ ነበር።

በዚህ ወቅት አንድ እንግዳ መጣባት። እሱም የአምላክ ነቢይ የሆነው ኤልያስ ሲሆን ካላት ምግብ እንድታካፍለው ጠየቃት። ምግቡ ለእንግዳው ልታካፍለው ይቅርና ለእርሷና ለልጅዋ እንኳን በሚገባ የሚያጠግባቸው አልነበረም። ይሁንና ኤልያስ ከምግቡ ካካፈለችው እርሷና ልጅዋ እንደማይራቡ ይሖዋ በገባው ቃል መሠረት ዋስትና ሰጣት። የእስራኤል አምላክ ለአንዲት የባዕድ አገር መበለት ትኩረት ይሰጣል ብሎ መቀበል እምነት ይጠይቃል። ቢሆንም ኤልያስን አምና የተቀበለችው ሲሆን ይሖዋም ክሷታል። “በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፣ ዘይቱም ከማሰሮው አልጐደለም።” መበለቲቷ እና ልጅዋ የረሃቡ ዘመን እስኪያበቃ ድረስ የሚበሉት ምግብ አላጡም።​—⁠1 ነገሥት 17:8-16

ይሁን እንጂ መበለቲቱ ያገኘችው በረከት በዚህ ብቻ አያበቃም። ይህ ተአምር ከተፈጸመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የምትወደው ልጅዋ ታሞ ሞተ። ኤልያስ በጣም ስላዘነላት ልጁን ከሞት እንዲያስነሳው ይሖዋን ተማጸነው። (1 ነገሥት 17:17-24) ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ ተአምር መፈጸምን ይጠይቃል። ከዚህ በፊት ከሞት የተነሳ ሰው ተሰምቶ አይታወቅም! ይሖዋ ለዚህች መበለት ዳግመኛ ርኅራኄ ያሳያት ይሆን? አዎን፣ ርኅራኄ አሳይቷታል። ይሖዋ ልጁን ከሞት እንዲያስነሳው ለኤልያስ ኃይል ሰጥቶታል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ልዩ ቸርነት ስለተደረገላት ስለዚህች መበለት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- ‘በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ ኤልያስ ግን የተላከው በሲዶና አገር ወዳለች ወደ ሰራፕታ ወደ አንዲት መበለት ነበር።’​—⁠ሉቃስ 4:25, 26

የበለጸጉ በሚባሉት አገሮች እንኳን ሳይቀር በዛሬው ጊዜ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ይታያል። አንዳንድ ትላልቅ ድርጅቶች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሏቸውን ሠራተኞች ከሥራ ቀንሰዋል። አንድ ክርስቲያን ከሥራ የመቀነስ አጋጣሚ ሲከሰት ድርጅቱ ታታሪነቴን ተመልክቶ በሥራው እንድቆይ ይፈቅድልኛል በሚል ተስፋ ረጅም ሰዓት ለመሥራት ይፈተን ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ወይም የቤተሰቡን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስፈልገውን ጊዜ ሊያሳጣው ይችላል። በሥራው ላይ ለመቆየት ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ማድረግ እንዳለበት ይሰማው ይሆናል።

በእንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ሁኔታው ቢያሳስበው አያስገርምም። በአሁኑ ጊዜ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። አብዛኞቻችን የምንጣጣረው ሃብታም ለመሆን ሳይሆን በሰራፕታ ትኖር እንደነበረችው መበለት የዕለት ጉርሳችንን ለማግኘት ነው። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” በማለት የገባልንን ቃል አስታውሶናል። “ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” ብለን በሙሉ ልብ መናገር እንችላለን። (ዕብራውያን 13:5, 6) ጳውሎስ በዚህ ተስፋ ላይ ሙሉ እምነት ነበረው፤ ይሖዋም እስከ መጨረሻው ተንከባክቦታል። እስካልተውነው ድረስ አምላክ ለእኛም እንዲሁ ያደርግልናል።

እንደ ሙሴ፣ ጌዴዎንና ዳዊት ያሉት መንፈሳዊ ሰዎች ያከናወኗቸውን ዓይነት ድንቅ ሥራዎች መስራት እንደማንችል ይሰማን ይሆናል፤ እምነታቸውን ግን መኮረጅ እንችላለን። እንዲሁም አቤል፣ ሄኖክና የሰራፕታዋ መበለት የፈጸሙትን አነስተኛ ሊባል የሚችል የእምነት ሥራ ማስታወስ እንችላለን። ይሖዋ በሁሉም ዓይነት የእምነት ሥራዎች፣ አነስተኛ በሚባሉትም ጭምር ይደሰታል። አምላክን ላለማሳዘን የሚፈልግ አንድ ተማሪ ከእኩዮቹ አደገኛ ዕፅ አልቀበልም ሲል፣ አንድ ክርስቲያን በሥራ ቦታው ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽም የሚቀርብለትን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ወይም አንድ በዕድሜ የገፉ ምሥክር ያለባቸውን ድካምና የጤና እክል ተቋቁመው በታማኝነት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ይሖዋ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ይደሰትባቸዋል።​—⁠ምሳሌ 27:11

የሌሎችን ጥረት በአድናቆት ትመለከታለህ?

አዎን፣ ይሖዋ የምናደርጋቸውን ነገሮች ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታል። እንግዲያው አምላክን ለመምሰል የምንጥር እንደመሆናችን መጠን ሌሎች የሚያደርጉትን ጥረት ለመመልከት ንቁ መሆን አለብን። (ኤፌሶን 5:1) ክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተወጥተው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት ለመካፈልና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ለማከናወን የሚያደርጉትን ጥረት ለምን ትኩረት ሰጥተህ አትመለከትም?

ከዚያም እነዚህ የእምነት አጋሮችህ የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታደንቅ ንገራቸው። ይህ የሚያስደስታቸው ከመሆኑም በላይ አሳቢነትህ ይሖዋ የሚያደርጉትን ነገር በቁም ነገር እንደሚመለከተው ሊያረጋግጥላቸው ይችላል።