በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስ የሚናገረውን አዳምጡ!

መንፈስ የሚናገረውን አዳምጡ!

መንፈስ የሚናገረውን አዳምጡ!

“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።”​ራእይ 3:22

1, 2. ኢየሱስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ለተጠቀሱት ሰባት ጉባኤዎች በላከው መልእክት ላይ ደጋግሞ የሰጠው ምክር የትኛው ነው?

 የይሖዋ አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ለተጠቀሱት ለሰባቱ ጉባኤዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረውን በትኩረት ማዳመጥ አለባቸው። በእርግጥም ለሰባቱም ጉባኤዎች የተላከው መልእክት “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” የሚል ምክር ይዟል።​—⁠ራእይ 2:​7, 11, 17, 29፤ 3:​6, 13, 22

2 ኢየሱስ በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ እና በጴርጋሞን ለሚገኙት መላእክት ወይም የበላይ ተመልካቾች የላከውን መልእክት ቀደም ሲል ተመልክተናል። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለሌሎቹ አራት ጉባኤዎች ከላከው መልእክት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

በትያጥሮን ወዳለው መልአክ

3. ትያጥሮን የምትገኘው የት ነበር? በተለይ ታዋቂ የሆነችው በምን ምርት ነበር?

3 “የእግዚአብሔር ልጅ” በትያጥሮን ለሚገኘው ጉባኤ ምስጋናም ሆነ እርማት ሰጥቷል። (ራእይ 2:​18-29ን አንብብ።) ትያጥሮን (የአሁኗ አክሂሳር) የምትገኘው በትንሿ እስያ በስተ ምዕራብ ለጌዲዝ (ጥንት ኸርመስ ይባል የነበረው) ገባር በሆነ ወንዝ ዳርቻ ነበር። ከተማዋ በተለያዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎች የታወቀች ነበረች። በዚያ የሚኖሩ ማቅለሚያ አምራቾች በጣም ተፈላጊ የሆነውን ቀይ ወይም ወይን ጠጅ ቀለም ለማዘጋጀት የእንሶስላ ዝርያ የሆነን ተክል ሥር ይጠቀሙ ነበር። ጳውሎስ በግሪክ ወደምትገኘው ፊልጵስዩስ በሄደበት ወቅት ክርስትናን የተቀበለችው ልድያ ‘ከትያጥሮን ከተማ የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ’ ነበረች።​—⁠ሥራ 16:12-15

4. በትያጥሮን የሚገኘው ጉባኤ የተመሰገነው በየትኞቹ ሥራዎቹ ነበር?

4 ኢየሱስ በትያጥሮን የሚገኘውን ጉባኤ ለመልካም ሥራው፣ ለፍቅሩ፣ ለእምነቱ፣ ለትዕግሥቱና በአገልግሎት ላከናወነው ሥራ አመስግኖታል። እንዲያውም ‘ከፊተኛው ሥራው ይልቅ የኋለኛው ይበዛል።’ ከዚህ ቀደም መልካም ስም ያተረፍን ቢሆንም እንኳ በሥነ ምግባር አቋማችን ረገድ ፈጽሞ ቸልተኞች መሆን የለብንም።

5-7. (ሀ) ‘ኤልዛቤል’ ተብለው የተጠሩት እነማን ነበሩ? የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በተመለከተስ ምን መደረግ ነበረበት? (ለ) ክርስቶስ ለትያጥሮን ጉባኤ የላከው መልእክት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች ምን እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል?

5 በትያጥሮን የሚገኘው ጉባኤ የጣዖት አምልኮን፣ የሐሰት ትምህርትንና የፆታ ብልግናን በቸልታ ተመልክቷል። በጉባኤው ውስጥ ‘ኤልዛቤል’ ተብለው የተጠሩ ሴቶች ነበሩ። ይህን መጠሪያ ያገኙት የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ንግሥት የነበረችው የክፉዋ ኤልዛቤል ዓይነት ባሕርይ ያንጸባርቁ ስለነበር ሊሆን ይችላል። በትያጥሮን “ነቢይ ነኝ” የሚሉ ሴቶች የነበሩ ሲሆን ክርስቲያኖች፣ ወንድና ሴት የንግድ ማኅበር አማልክትን እንዲያመልኩና ለጣዖት የተሠዋ ማዕድ በሚቀርብባቸው በዓላት ላይ እንዲሳተፉ ለማግባባት ጥረት አድርገው ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ተናግረዋል። ማንኛዋም ራሷን የሾመች ነቢይት ዛሬ ባለው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሌሎችን ለማሳሳት መሞከር የለባትም!

6 ክርስቶስ ‘ኤልዛቤል የተባለችውን ሴት [“በመከራ፣” አ.መ.ት ] አልጋ ላይ ይጥላታል፤ ከእርስዋ ጋር የሚያመነዝሩትንም ንስሐ ካልገቡ በታላቅ መከራ ይጥላቸዋል።’ የበላይ ተመልካቾች ለእንዲህ ዓይነቱ መጥፎ ትምህርትና ተጽዕኖ እጅ መስጠት አይኖርባቸውም። እንዲሁም ማንኛውም ክርስቲያን ‘የሰይጣን ጥልቅ ነገሮች’ ፈጽሞ መጥፎ መሆናቸውን ለማወቅ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ምንዝር መፈጸም ወይም ደግሞ በጣዖት አምልኮ መካፈል አይኖርበትም። ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በጥብቅ ከተከተልን ‘ያለንን እንጠብቃለን’ እንዲሁም ኃጢአት አይቆጣጠረንም። ትንሣኤ ያገኙት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች አምላክ የሚጠላቸውን ድርጊቶች፣ የሥጋ ፍላጎቶችና ግቦች በማስወገዳቸው ‘በአሕዛብ ላይ ሥልጣን’ የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ከክርስቶስ ጋር አሕዛብን ይቀጠቅጣሉ። በዛሬው ጊዜ ያሉ ጉባኤዎች ምሳሌያዊ ከዋክብት አሏቸው፤ በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ደግሞ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ‘የሚያበራ የንጋት ኮከብ’ ማለትም ሙሽራ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይሰጣቸዋል።​—⁠ራእይ 22:​16

7 የትያጥሮን ጉባኤ ክህደት የሚያስፋፉ ሴቶች የሚያሳድሩትን መጥፎ ተጽዕኖ በቸልታ እንዳያልፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል። ክርስቶስ በመንፈስ አነሳሽነት ለጉባኤው የላከው መልእክት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች በዛሬው ጊዜ አምላክ የሰጣቸውን ቦታ እንዲጠብቁ ይረዳቸዋል። በወንዶች ላይ ለመሠልጠን አይሞክሩም እንዲሁም ወንድሞች መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ምንዝር እንዲፈጽሙ አያነሳሱም። (1 ጢሞ​ቴዎስ 2:12) ከዚህ ይልቅ እንደዚህ ያሉት ሴቶች በመልካም ሥራዎችና ለአምላክ ውዳሴ የሚያመጣ አገልግሎት በማቅረብ ረገድ ምሳሌ ይሆናሉ። (መዝሙር 68:11፤ 1 ጴጥሮስ 3:1-6) ጉባኤው ያለውን ንጹሕ ትምህርትና ሥነ ምግባር እንዲሁም ውድ የሆነውን የመንግሥቱን አገልግሎት ጠብቆ ከቆየ ክርስቶስ የሚመጣው ለመቅጣት ሳይሆን ግሩም በረከቶችን ለመስጠት ይሆናል።

በሰርዴስ ወዳለው መልአክ

8. (ሀ) ሰርዴስ የምትገኘው የት ነበር? ስለ ከተማዋ የሚታወቅ ምን ተጨማሪ ነገር አለ? (ለ) በሰርዴስ የሚገኘው ጉባኤ እርዳታ ያስፈለገው ለምን ነበር?

8 በሰርዴስ የሚገኘው ጉባኤ በመንፈሳዊ ሁኔታ ስለሞተ አፋጣኝ እርዳታ ያስፈልገው ነበር። (ራእይ 3:​1-6ን አንብብ።) ከትያጥሮን በስተ ደቡብ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ላይ የምትገኘው ሰርዴስ ሞቅ ደመቅ ያለች ከተማ ነበረች። በአንድ ወቅት ወደ 50, 000 ገደማ ነዋሪዎች የነበሯት ሰርዴስ ንግድ የሚካሄድባት፣ ለም አፈር ያላት እንዲሁም ከሱፍ የተሠሩ ልብሶችና ምንጣፎች አምራች መሆኗ ባለ ጠጋ እንድትሆን አስችሏታል። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደዘገበው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ በሰርዴስ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩ ነበር። ከከተማዋ ፍርስራሽ መካከል የአይሁዶች ምኩራብና አርጤምስ የተባለችው የኤፌሶን ሴት አምላክ ቤተ መቅደስ ይገኛሉ።

9. ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት የይስሙላ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

9 ክርስቶስ በሰርዴስ የነበረውን ጉባኤ መልአክ “ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” ብሎታል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ንቁ እንደሆንን ስም ያለን ቢሆንም እንኳ ለክርስቲያናዊ መብቶች ግድ የለሾች ከሆንንና አገልግሎታችን የይስሙላ ከሆነ እንዲሁም በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘ልንሞት’ የተቃረብን ብንሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሁኔታችን እንደዚህ ከሆነ የመንግሥቱን መልእክት ‘እንዴት እንደተቀበልንና እንደሰማን ማሰብ’ እንዲሁም በቅዱስ አገልግሎታችን የምናደርገውን ተሳትፎ እንደገና ማጠናከር ይኖርብናል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሙሉ ልብ መሳተፍ መጀመር እንደሚኖርብን የታወቀ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) ክርስቶስ በሰርዴስ የነበረውን ጉባኤ “ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም” በማለት አስጠንቅቆታል። ይህ ማስጠንቀቂያ በእኛ ዘመንስ ይሠራል? አዎን፣ በቅርቡ ሁላችንም መልስ የምንሰጥበት ጊዜ ይመጣል።

10. በሰርዴስ ጉባኤ የተከሰተው ዓይነት ሁኔታ እያለም እንኳ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ያደርጋሉ?

10 በሰርዴስ ጉባኤ የተከሰተው ዓይነት ሁኔታ እያለም እንኳ ‘ልብሳቸውን ያላረከሱና የተገባቸው ስለሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከክርስቶስ ጋር የሚሄዱ’ ጥቂት ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ። ከዚህ ዓለም ሥነ ምግባራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ እድፍ ራሳቸውን በመጠበቅ በማንኛውም ጊዜ ክርስቲያኖች መሆናቸው ተለይቶ እንዲታወቅ ያደርጋሉ። (ያዕቆብ 1:27) ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ ‘ስማቸውን ከሕይወት መጽሐፍ ላይ አይደመስሰውም። ከዚህ ይልቅ በአባቱና በመላእክቱ ፊት ይመሰክርላቸዋል።’ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈው የክርስቶስ ሙሽራ ክፍል ከእርሱ ጋር ለመሄድ የተገባቸው በመሆናቸው የአምላክ ቅዱሳንን የጽድቅ ሥራ የሚያመለክተውን ያጌጠ፣ ንጹሕና ያማረ ልብስ ይለብሳሉ። (ራእይ 19:8) በሰማይ የሚጠብቃቸው ግሩም የአገልግሎት መብት ይህንን ዓለም ለማሸነፍ ብርታት ይሰጣቸዋል። በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም የተዘጋጀላቸው በረከት አለ። የእነርሱም ስም በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፏል።

11. በመንፈሳዊ ሁኔታ ማንቀላፋት ብንጀምር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

11 ማንኛችንም ብንሆን በሰርዴስ የነበረው ጉባኤ ያጋጠመው ዓይነት አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ መውደቅ አንፈልግም። ሆኖም በመንፈሳዊ እያንቀላፋን እንዳለን ብንገነዘብስ? ለራሳችን ጥቅም ስንል ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ የሚጠላው አኗኗር እየማረከን ከሆነ ወይም በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን የማንገኝና በአገልግሎት የምናደርገው ተሳትፎ እየቀነሰ ከሆነ ይሖዋ እንዲረዳን ከልብ መጸለይ አለብን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበባችን እንዲሁም ቅዱሳን ጽሑፎችንና ‘ታማኙ መጋቢ’ የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች ማጥናታችን በመንፈሳዊ ንቁ እንድንሆን ይረዳናል። (ሉቃስ 12:42-44) እንዲህ ካደረግን በክርስቶስ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኙት በሰርዴስ እንደነበሩት ክርስቲያኖች ከመሆናችንም በላይ ለእምነት ባልደረቦቻችን በረከት እንሆናለን።

በፊልድልፍያ ወዳለው መልአክ

12. በጥንቷ ፊልድልፍያ የነበረው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

12 ኢየሱስ ለፊልድልፍያ ጉባኤ ምስጋና ልኳል። (ራእይ 3:​7-13ን አንብብ።) ፊልድልፍያ (የአሁኗ አላሴሂር) በትንሿ እስያ ምዕራባዊ ክፍል የምትገኝ በብልጽግናዋ የታወቀች ወይን አምራች ክልል ነበረች። እንዲያውም በዚያ በዋነኛነት የሚመለከው የወይን አምላክ የሆነው ዳይናይሰስ ነበር። በፊልድልፍያ የሚኖሩ አይሁዶች በከተማዋ ያሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ውስጥ የተካተቱትን አንዳንድ ልማዶች ይዘው እንዲቀጥሉ ወይም ወደዚያ እንዲመለሱ ለማሳመን ሙከራ ቢያደርጉም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ መረዳት ይቻላል።

13. ክርስቶስ ‘በዳዊት መክፈቻ’ የተጠቀመው እንዴት ነው?

13 ክርስቶስ “የዳዊት መክፈቻ ያለው” በመሆኑ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሙሉ እንዲሁም የእ​ምነት ቤተሰቡን የማስተዳደሩ ኃላፊነት በአደራ ተሰጥቶታል። (ኢሳይያስ 22:22፤ ሉቃስ 1:32) ኢየሱስ በዚህ መክፈቻ በመጠቀም በጥንቷ ፊልድልፍያና በሌሎች ጉባኤዎች ለሚገኙ ክርስቲያኖች ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ መብቶችንና የኃላፊነት ቦታዎችን የማግኘት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ከ1919 አንስቶ ማንኛውም ተቃዋሚ ሊዘጋው የማይችል የመንግሥቱ ስብከት ሥራ የሚከናወንበት “ትልቅ በር” ‘ለታማኙ መጋቢ’ ከፍቷል። (1 ቆሮንቶስ 16:9፤ ቆላስይስ 4:2-4) እርግጥ ነው፣ ‘የሰይጣን ማህበር’ ተብለው የተጠሩት መንፈሳዊ እስራኤላውያን ባለመሆናቸው ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ መብቶችን የሚያስገኘው በር ተዘግቶባቸዋል።

14. (ሀ) ኢየሱስ በፊልድልፍያ ለሚገኘው ጉባኤ ምን ተስፋ ሰጥቷል? (ለ) ‘በፈተናው ሰዓት’ ከመውደቅ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ በጥንቷ ፊልድልፍያ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ይህን ተስፋ ሰጥቷቸዋል:- “የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።” የስብከቱ ሥራ ኢየሱስ ያሳየው ዓይነት ጽናት ይጠይቃል። ለጠላቱ ፈጽሞ እጅ አልሰጠም፤ ከዚህ ይልቅ የአባቱን ፈቃድ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት አግኝቷል። እኛም ይሖዋን ለማምለክ ያደረግነውን ውሳኔ አጥብቀን ከያዝንና ምሥራቹን በመስበክ መንግሥቱን የምንደግፍ ከሆነ ‘የፈተናው ሰዓት’ በተባለው በአሁኑ ወቅት ባለው ፈተና ከመውደቅ እንጠበቃለን። ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙት ጉዳዮች እንዲስፋፉ ጥረት በማድረግ ከክርስቶስ የተቀበልነውን ‘አጽንተን እንይዛለን።’ እንደዚህ በማድረጋቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዋጋ ሊተመን የማይችል አክሊል በሰማይ የሚያገኙ ሲሆን ታማኝ የሆኑ ባልደረቦቻቸው ደግሞ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።

15. ‘በአምላክ መቅደስ ዓምድ’ የሚሆኑት የትኛውን ብቃት እንዲያሟሉ ይጠበቅባቸዋል?

15 ክርስቶስ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፣ . . . የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፣ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፣ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።” በመንፈስ የተቀቡ የበላይ ተመልካቾች እውነተኛውን አምልኮ መደገፍ አለባቸው። ስለ አምላክ መንግሥት በመስበክና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን በመጠበቅ ‘የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም’ አባላት ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ሳያጓድሉ መቀጠል አለባቸው። በሰማይ በሚገኘው ክብር በተጎናጸፈው ቤተ መቅደስ ውስጥ ዓምድ ለመሆን፣ በሰማይ የመኖር ውርሻ አግኝተው የአምላክን ከተማ ስም ለመሸከም እንዲሁም ሙሽራው በመሆን በክርስቶስ ስም ለመጠራት ከፈለጉ ይህን ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ ‘መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን የሚሰማ’ ጆሮ ሊኖራቸው ይገባል።

በሎዶቅያ ወዳለው መልአክ

16. ሎዶቅያን በተመለከተ ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

16 ክርስቶስ በሎዶቅያ የሚገኘውን ጉባኤ በቸልተኝነቱ ምክንያት ገሥጾታል። (ራእይ 3:​14-22ን አንብብ።) ከኤፌሶን በስተ ምሥራቅ 150 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘውና የሉከስ ወንዝ በሚያልፍበት ለም ሸለቆ ውስጥ ታላላቅ የንግድ መስመሮች በሚገናኙበት ቦታ ያለችው ሎዶቅያ የተለያዩ ዕቃዎች የሚመረቱባትና የገንዘብ ልውውጥ የሚካሄድባት በጣም የበለጸገች ከተማ ነበረች። በዚያ አካባቢ ከሚገኝ ጥቁር ሱፍ የሚዘጋጁ ልብሶች በጣም ተወዳጅ ነበሩ። በሎዶቅያ ታዋቂ የሆነ የሕክምና ትምህርት ቤት ይገኝ ስለነበር በዱቄት መልክ የሚዘጋጀው የፈርጂያ የዓይን መድኃኒት የሚመረተው በዚያ ሳይሆን አይቀርም። የሕክምና አምላክ የሆነው ኤስክሊፒየስ በከተማዋ ከነበሩት ታላላቅ አማልክት መካከል አንዱ ነበር። ሎዶቅያ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩባት የነበረ ይመስላል፤ አንዳንዶቹም በጣም ሃብታም እንደነበሩ ይታሰባል።

17. የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ተግሣጽ የተሰጣቸው ለምን ነበር?

17 ኢየሱስ በሎዶቅያ ለሚገኘው ጉባኤ የላከውን መልእክት በጉባኤው “መልአክ” በኩል ሲያስተላልፍ “የታመነውና እውነተኛው ምስክር፣ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ” እንደ መሆኑ መጠን እንደ ባለሥልጣን ተናግሯል። (ቆላስይስ 1:13-16) የሎዶቅያ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሁኔታ “በራድ ወይም ትኵስ” ባለመሆናቸው ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል። ለብ ያሉ በመሆናቸው ክርስቶስ ከአፉ ሊተፋቸው ነው። የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ይህን ምሳሌ መረዳት አያቅታቸውም። በአቅራቢያዋ በምትገኘው በኢያራ ከተማ ፍል ውኃ ይመነጭ የነበረ ሲሆን በቆላስይስ ደግሞ ቀዝቃዛ ውኃ ይገኝ ነበር። ሎዶቅያ ውሃ የምታገኘው ራቅ ካለ ቦታ በቱቦ ሲሆን ውኃው ወደ ከተማዋ ሲደርስ ለብ ያለ ይሆናል። ውኃው የተወሰነ ርቀት በትልቅ ቧንቧ አልፎ ወደ ሎዶቅያ ሲቃረብ አንድ ላይ ከተለሰኑ ድንጋዮች በተሠራ ቱቦ አቋርጦ ወደ ከተማዋ ይገባል።

18, 19. ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በሎዶቅያ እንደነበሩት ክርስቲያኖች እርዳታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ዛሬም በሎዶቅያ የነበሩትን ክርስቲያኖች የሚመስሉ ግለሰቦች የሚያነቃቃ ግለትም ሆነ መንፈስ የሚያድስ ቅዝቃዜ የላቸውም። እነዚህ ግለሰቦች ለብ እንዳለ ውኃ ከአፍ ውስጥ ይተፋሉ! ኢየሱስ የተቀቡ ‘የክርስቶስ አምባሳደሮች’ በመሆን የእርሱ ቃል አቀባይ እንዲሆኑ አይፈልግም። (2 ቆሮንቶስ 5:20) ንስሐ ካልገቡ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ የመሆን መብታቸውን ያጣሉ። የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ዓለማዊ ሃብት በማሳደድ ተጠምደው የነበረ ሲሆን ‘ጐስቋላና ምስኪን ድሀም ዕውርም የተራቆቱ መሆናቸውንም አላወቁም።’ ዛሬም እነርሱ በነበሩበት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ መንፈሳዊ ድህነታቸውን፣ ዕውርነታቸውንና ራቁትነታቸውን ለማስወገድ የተፈተነ እምነትን የሚያሳየውን ‘የነጠረ ወርቅ፣’ የጽድቅ አቋምን የሚያመለክተውን ‘ነጭ ልብስ’ እንዲሁም መንፈሳዊ እይታቸውን የሚያጠራ “ኩል” ከክርስቶስ መግዛት ይኖርባቸዋል። ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች እነዚህ ግለሰቦች ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ በመሆን “በእምነት ባለ ጠጎች” እንዲሆኑ ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። (ያዕቆብ 2:5፤ ማቴዎስ 5:3) ከዚህም በተጨማሪ የበላይ ተመልካቾች እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ “ኩል” እንዲቀቡ በሌላ አባባል የኢየሱስን ትምህርት፣ ምክር፣ ምሳሌነትና አስተሳሰብ እንዲቀበሉና ከዚያም ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ሊረዷቸው ይገባል። ይህ ‘የሥጋ ምኞትን፣ የዓይን አምሮትንና ስለ ገንዘብ መመካትን’ ለመቋቋም የሚያስችል መድኃኒት ነው።​—⁠1 ዮሐንስ 2:15-17

19 ኢየሱስ ለሚወዳቸው ሁሉ ተግሣጽና እርማት ይሰጣቸዋል። በእርሱ ሥር የሚገኙ የበላይ ተመልካቾችም አዘኔታ በተሞላበት መንገድ እርማትና ተግሣጽ መስጠት ይኖርባቸዋል። (ሥራ 20:28, 29) የሎዶቅያ ክርስቲያኖች በአስተሳሰባቸውና በአኗኗራቸው ለውጥ በማድረግ ‘ቅንዓት ማሳየትና ንስሐ መግባት’ አስፈልጓቸው ነበር። ለአምላክ የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት በሕይወታችን ውስጥ ዝቅተኛ ቦታ እንድንሰጠው የሚያደርገን አኗኗር መከተል ጀምረን ይሆን? ከሆነ ቅንዓት በተሞላበት ሁኔታ መንግሥቱን የማስቀደሙን አስፈላጊነት ማየት እንድንችል ‘ከኢየሱስ ኩል እንግዛ።’​—⁠ማቴዎስ 6:33

20, 21. በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ ‘ሲያንኳኳ’ ምላሽ የሚሰጡት እነማን ናቸው? ምን ተስፋስ ተዘርግቶላቸዋል?

20 ክርስቶስ እንዲህ ይላል:- “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፣ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።” ኢየሱስ በምግብ ላይ እያለ መንፈሳዊ ትምህርት የሰጠባቸው ብዙ ወቅቶች አሉ። (ሉቃስ 5:29-39፤ 7:36-50፤ 14:1-24) ኢየሱስ እንደ ሎዶቅያ ባለ ጉባኤ በር ላይ ቆሞ እያንኳኳ ነው። የጉባኤው አባላት በሩን በመክፈት፣ ለእርሱ የነበራቸውን ፍቅር በማደስ፣ ከእነርሱ ጋር እንዲሆን በማስገባትና እንዲያስተምራቸው ፈቃደኛ በመሆን ይቀበሉት ይሆን? እንዲህ ካደረጉ ክርስቶስ አብሯቸው የሚመገብ ሲሆን ይህም ከፍተኛ መንፈሳዊ በረከት ያስገኝላቸዋል።

21 በዛሬው ጊዜ ያሉ “ሌሎች በጎች” በምሳሌያዊ አነጋገር ኢየሱስ እንዲገባ እየፈቀዱለት ሲሆን እንዲህ ማድረጋቸውም የዘላለም ሕይወት ያስገኝላቸዋል። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:34-40, 46) ክርስቶስ ድል ለነሣ ለእያንዳንዱ የተቀባ ክርስቲያን ‘እርሱ ድል ነሥቶ ከአባቱ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደ ተቀመጠ ሁሉ ከእርሱ ጋር በዙፋኑ ላይ የመቀመጥ’ መብት ይሰጠዋል። አዎን፣ ኢየሱስ ድል ለነሡ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአባቱ ቀኝ ከእርሱ ጋር በዙፋን ላይ የመቀመጥ ታላቅ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። ድል የነሡ ሌሎች በጎችም በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለመኖር በጉጉት ይጠባበቃሉ።

ለሁላችን የሚሆን ትምህርት

22, 23. (ሀ) ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች ከላከው መልእክት ሁሉም ክርስቲያኖች ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

22 ኢየሱስ በትንሿ እስያ ለነበሩት ሰባት ጉባኤዎች ከላከው መልእክት ሁሉም ክርስቲያኖች ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ክርስቶስ የሰጠውን ተገቢ ምስጋና በመመልከት ጥሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግለሰቦችንና ጉባኤዎችን ለማመስገን ይነሳሳሉ። ሽማግሌዎች አንዳንድ ድክመቶችን በሚያዩበት ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊ መድኃኒቶችን እንዲጠቀሙ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ይረዷቸዋል። ሁላችንም ክርስቶስ የተለያዩ ጉዳዮችን በተመለከተ ለሰባቱ ጉባኤዎች የላከውን ምክር ከልባዊ ጸሎት ጋር ሳንዘገይ በተግባር እስካዋልን ድረስ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። a

23 ያለንበት የመጨረሻ ቀን ቸልተኛ የምንሆንበት፣ ቁሳዊ ሃብት የምናሳድድበት ወይም ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ለይስሙላ እንዲሆን የሚያደርግብንን ማንኛውንም ነገር የምናስተናግድበት ጊዜ አይደለም። እንግዲያው ሁሉም ጉባኤዎች ኢየሱስ ባሉበት እንዲቀመጡ እንደሚፈቅድላቸው መቅረዞች ደማቅ ብርሃን መስጠታቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል። ታማኝ ክርስቲያኖች በመሆን ክርስቶስ ሲናገር በትኩረት መከታተልና መንፈስ የሚናገረውን ማዳመጥ ምንጊዜም ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን። እንዲህ ካደረግን ለይሖዋ ክብር ብርሃን አብሪዎች በመሆን ዘላቂ ደስታ እናገኛለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ራእይ 2:​1 እስከ 3:​22 ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 7 እስከ 13 ላይም ተብራርቷል። መጽሐፉ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ነው።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ‘ኤልዛቤል’ ተብላ የተጠራችው ማን ነበረች? ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች የእርሷን አካሄድ መከተል የሌለባቸው ለምንድን ነው?

• በሰርዴስ በሚገኘው ጉባኤ ምን ዓይነት ሁኔታ ተከስቶ ነበር? በዚያ ይኖሩ እንደነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ላለመሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

• ኢየሱስ ለፊልድልፍያ ጉባኤ ምን ተስፋ ሰጥቶ ነበር? ዛሬስ ተፈጻሚነት የሚኖረው እንዴት ነው?

• የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ተግሣጽ የተሰጣቸው ለምን ነበር? ይሁንና ቀናተኛ ክርስቲያኖች ምን ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘የኤልዛቤልን’ መጥፎ አካሄድ ማስወገድ ያስፈልጋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ከመንግሥቱ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የአገልግሎት መብቶች ለማግኘት የሚያስችል “ትልቅ በር” ለተከታዮቹ ከፍቶላቸዋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በሩን ሲያንኳኳ ትከፍትለታለህ? የሚናገረውንስ ታዳምጣለህ?