በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴሸን—የክርስትና ተሟጋች ወይስ መናፍቅ?

ቴሸን—የክርስትና ተሟጋች ወይስ መናፍቅ?

ቴሸን​—⁠የክርስትና ተሟጋች ወይስ መናፍቅ?

ሐዋርያው ጳውሎስ በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው መገባደጃ ላይ የኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎችን ለስብሰባ ጠርቶ እንዲህ አላቸው:- “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኵላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።”​—⁠ሥራ 20:29, 30

በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ብዙ ለውጦች መታየታቸውና በትንቢት የተነገረለት ክህደት መከሰቱ የጳውሎስን ቃላት እውነተኝነት ያሳያል። የአንዳንድ አማኞችን እምነት የበከለው ግኖስቲሲዝም በመባል የሚታወቀው ሃይማኖትንና ፍልስፍናን አጣምሮ የያዘ እንቅስቃሴ እየገነነ መጥቶ ነበር። ግኖስቲኮች ቁስ አካል በሙሉ ክፉ ሲሆን መልካም የሆነው መንፈሳዊ ነገር ብቻ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ሥጋ ሁሉ ክፉ ነው ብለው ስለሚያምኑ መጋባትና መዋለድ ሰይጣን ያመጣቸው ነገሮች እንደሆኑ አድርገው በመቁጠር አይቀበሏቸውም ነበር። አንዳንዶቹ ግኖስቲኮች ደግሞ መልካም የሆነው መንፈሳዊው የአካል ክፍል ብቻ ስለሆነ አንድ ሰው በሥጋዊ አካሉ ያሻውን ቢያደርግ ምንም ችግር የለውም ብለው ያምኑ ነበር። እንዲህ ያሉት አመለካከቶች አንዳንዶች ዓለም በቃኝ ብለው በብህትውና እንዲኖሩና ሌሎች ደግሞ ሥጋዊ ፍላጎቶችን በማሳደድ እንዲጠመዱ አድርገዋል። ግኖስቲኮች መዳን የሚገኘው በምስጢራዊ ግኖስቲሲዝም ማለትም ራስን በማወቅ ነው የሚል እምነት ስለነበራቸው በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው እውነት ምንም ቦታ አይሰጡም ነበር።

በወቅቱ ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩት ሰዎች እንዲህ ላለው የግኖስቲካውያን አደገኛ እምነት ምን አመለካከት ነበራቸው? አንዳንዶቹ ይህን የተሳሳተ ትምህርት በግልጽ ሲቃወሙ ሌሎች ግን በተጽዕኖው ተሸንፈዋል። ለምሳሌ ኢራንየስ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ይህን የመናፍቃውያን ትምህርት ተቃውሟል። ይህ ሰው በሐዋርያት ዘመን ይኖር የነበረው የፖሊካርፕ ተማሪ ነበር። ፖሊካርፕ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ ያስተማሯቸውን ትምህርቶች በጥብቅ መከተልን ያበረታታ ነበር። የኢራንየስ ጓደኛ የነበረው ፍሎሪነስ በፖሊካርፕ እግር ሥር የተማረ ቢሆንም የግኖስቲኮች እንቅስቃሴ ዋነኛ መሪ በነበረው በቫሌንቲነስ ትምህርቶች ተስቦ ተወስዷል። በእርግጥም እነዚያ ጊዜያት አደገኛ ወቅቶች ነበሩ።

የሁለተኛው መቶ ዘመን ታዋቂ ጸሐፊ የሆነው የቴሸን የጽሑፍ ሥራዎች በወቅቱ ስለነበረው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ያለንን ግንዛቤ ያሰፉልናል። ቴሸን ምን ዓይነት ሰው ነበር? ወደ ክርስትና እምነት ሊለወጥ የቻለው እንዴት ነበር? ቴሸን በወቅቱ ገንኖ ስለነበረው የግኖስቲኮች መናፍቃዊ አስተሳሰብ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? ለእምነቱ ለመሟገት ሲል የሰነዘራቸው ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችና ከራሱ ሕይወት የምናገኘው ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው እውነት ፈላጊዎች ጠቃሚ ትምህርት ይሆነናል።

“አንዳንድ ባዕድ ጽሑፎችን” አገኘ

ቴሸን የሶርያ ተወላጅ ነበር። ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መጓዙና በርካታ መጻሕፍትን ማንበቡ በዘመኑ ስለነበረው የግሪክና የሮማውያን ባሕል የጠለቀ እውቀት እንዲኖረው አስችሎታል። ቴሸን ወደ ሮም የመጣው ተጓዥ የሕዝብ ተናጋሪ ሆኖ ነበር። በሮም ቆይታው ወቅት ግን ክርስትና ትኩረቱን ሳበው። ከሰማዕቱ ጀስቲን ጋር መቀራረብ የጀመረ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ የእርሱ ተማሪ የሆነ ይመስላል።

ቴሸን ወደ ክርስትና እምነት የተለወጠበትን ሁኔታ አስመልክቶ ባሰፈረው ዘገባ ላይ “እውነትን እንዴት ማግኘት እንደምችል ምርምር ሳደርግ ነበር” ብሏል። ቅዱሳን ጽሑፎችን የማንበብ አጋጣሚ ባገኘበት ወቅት የተሰማውን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከግሪካውያን ፍልስፍናዎች ጋር ሲወዳደሩ ረጅም ዘመናት ያስቆጠሩ አንዳንድ የባዕድ ጽሑፎችን አገኘሁ። ጽሑፎቹ ስህተት ከሞላባቸው የግሪካውያኑ ጽሑፎች አንጻር ሲታዩ እንከን የማይወጣላቸው ነበሩ። እንዲሁም በተራቀቁ ቃላት ያልተሽሞነሞኑ መሆናቸው፣ ወደፊት የሚሆነውን የማወቅ ችሎታ የተንጸባረቀባቸው መሆኑ፣ ግሩም ምክሮችን መያዛቸው ብሎም አንድ የአጽናፈ ዓለም የበላይ ገዢ እንዳለ መግለጻቸው ከጸሐፊዎቹ ቅንነት ጋር ተዳምሮ እምነት እንዳሳድርባቸው አድርጎኛል።”

ቴሸን በጊዜው ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ክርስትናን እንዲመረምሩና ይህ ሃይማኖት ግራ ከሚያጋቡት የአረማውያን ፍልስፍናዎች በተለየ ቀላልና ግልጽ መሆኑን እንዲገነዘቡ ከማበረታታት ወደ ኋላ አላለም። ከእርሱ ጽሑፎች ምን እንማራለን?

የጽሑፎቹ ይዘት ምን ይመስላል?

ጽሑፎቹ ቴሸን ለእምነቱ ሽንጡን ገትሮ የሚሟገት ጸሐፊ እንደነበረ ይጠቁማሉ። ለአረማውያን ፍልስፍና ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው። ቴሸን አድሬስ ቱ ዘ ግሪክስ በተሰኘው የጽሑፍ ሥራው ላይ አረማዊ አምልኮ ከንቱ መሆኑንና በወቅቱ የነበረው ክርስትና ትክክለኛ መሆኑን ጎላ አድርጎ ጽፏል። ለግሪካውያን አስተሳሰብ የነበረውን ጥላቻ ሲገልጽ በጣም ኃይለኛ ነበር። ለምሳሌ ያህል ፈላስፋውን ሄራክሊተስን በሚመለከት እንዲህ ብሎ ነበር:- “[የሄራክሊተስ] አሟሟት አላዋቂነቱን በግልጽ አሳይቷል፤ ምክንያቱም ፍልስፍናን ብቻ ሳይሆን ሕክምናንም አጥንቶ ስለነበር ሰውነትን በሚያሳብጥ በሽታ በታመመ ጊዜ መላ ሰውነቱን በእበት ለቀለቀው። እበቱ ሲደርቅ ገላውን አኮማትሮ ስለያዘው ቆዳው ተሰነጣጠቀና ሞተ።”

ቴሸን የሁሉም ነገር ፈጣሪ በሆነ አንድ አምላክ ማመንን አጥብቆ ይደግፍ ነበር። (ዕብራውያን 3:​4) አድሬስ ቱ ዘ ግሪክስ በተባለው የጽሑፍ ሥራው ላይ አምላክ “መንፈስ” መሆኑን ገልጾ “መጀመሪያ የሌለው እሱ ብቻ ነው፤ የሁሉ ነገር መጀመሪያ እርሱ ራሱ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17) ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ስህተት መሆኑን ለመግለጽ “እንጨትንና ድንጋይን እንዴት አምላክ ብዬ ልጠራቸው እችላለሁ?” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:14) ቃል ወይም ሎጎስ ወደ ሕልውና የመጣው የሰማዩ አባት የፍጥረት ሥራዎች የበኩር ሆኖ እንደሆነና ግዑዙን ጽንፈ ዓለም በመፍጠሩ ሥራ እንደተካፈለ ያምን ነበር። (ዮሐንስ 1:1-3፤ ቆላስይስ 1:13-17) ቴሸን አምላክ በቀጠረው ቀን የሚኖረውን ትንሣኤ አስመልክቶ “የሁሉም ነገሮች ፍጻሜ ከመጣ በኋላ ሙታን ትንሣኤ እንደሚያገኙ እናምናለን” በማለት ተናግሯል። የምንሞትበትን ምክንያት በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የተፈጠርነው ለመሞት አልነበረም፤ ሆኖም የምንሞተው በራሳችን ጥፋት ነው። የመምረጥ ነፃነታችን ለጥፋት ዳርጎናል፤ ነፃ የነበርነው ሰዎች ባሪያዎች ሆነናል፤ ለኃጢአት ተሸጠናል።”

ቴሸን ነፍስን በሚመለከት የሚሰጠው ማብራሪያ ግን ግራ የሚያጋባ ነው። እንዲህ ይላል:- “ግሪካውያን ሆይ፣ ነፍስ ሟች እንጂ ዘላለማዊ አይደለችም። ቢሆንም የማትሞትበት ሁኔታ አለ። እርግጥ፣ እውነትን የማታውቅ ነፍስ ከሆነች ትሞትና ከሥጋው ጋር ትበሰብሳለች፤ ከዚያም በዓለም መጨረሻ ላይ ከሥጋው ጋር ተነስታ በዘላለማዊ ቅጣት አማካኝነት የሞት ፍርድ ትቀበላለች።” ቴሸን እንዲህ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ምናልባት በወቅቱ የነበሩትን ሰዎች ለማስደሰት ሲል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ሳይለቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ከዓለማዊ ፍልስፍናዎች ጋር ለማጣጣም ፈልጎ ይሆን?

ሌላው በስፋት የሚታወቀው የቴሸን ሥራ ዲያቴሳሮን ወይም ሃርመኒ ኦቭ ዘ ፎር ጎስፕልስ (የአራቱ ወንጌሎች ስምምነት) የተሰኘው ነው። ቴሸን በሶርያ ለሚገኙ ጉባኤዎች ወንጌሎችን በራሳቸው ቋንቋ ያዘጋጀ የመጀመሪያው ሰው ነበር። አራቱን የወንጌል ዘገባዎች በአንድ ትረካ አጣምሮ የያዘው ይህ ትርጉም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥራ ሲሆን የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት ነበር።

ክርስቲያን ወይስ መናፍቅ?

የቴሸንን ጽሑፎች ስንመረምር ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ጠለቅ ያለ እውቀትና አክብሮት እንደነበረው እንገነዘባለን። ቅዱሳን ጽሑፎች ስላሳደሩበት ተጽዕኖ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሃብታም ለመሆን አልጓጓም፤ ወታደራዊ ሥልጣን እንዲሰጠኝም አልሻም፤ ምንዝርን አጥብቄ እጠላለሁ፤ በገንዘብ ፍቅር ተገፋፍቼ መርከበኛ አልሆንም፤ ዝነኛ የመሆን ጥማትም የለኝም፤ . . . የምንኖረው በድሎትም ሆነ በድህነት ሁላችንም አንዲት ፀሐይ ትወጣልናለች፣ እንዲሁም ሁላችንም መሞታችን አይቀርም።” ቴሸን እንዲህ በማለት ይመክራል:- “በውስጡ ያለውን ሞኝነት በመካድ ለዓለም የሞታችሁ ሁኑ፤ ለአምላክ ኑሩ፣ እንዲሁም ማንነቱን በጥልቅ በመረዳት አሮጌውን ሰውነት ገፍፋችሁ ጣሉ።”​—⁠ማቴዎስ 5:45፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:10

ይሁን እንጂ ኦን ፐርፌክሽን አኮርዲንግ ቱ ዘ ዶክትሪን ኦቭ ዘ ሴቪየር የተሰኘውን የጽሑፍ ሥራውን ተመልከት። በዚህ ጽሑፍ ላይ መጋባትን ያመጣው ሰይጣን እንደሆነ ገልጿል። ሰዎች በጋብቻ አማካኝነት ራሳቸውን ለዚህ የሚጠፋ ዓለም ያስገዛሉ ብሎ ስለሚያምን ትዳርን አጥብቆ ያወግዝ ነበር።

በ166 እዘአ ገደማ ሰማዕቱ ጀስቲን ከሞተ በኋላ ቴሸን ኢንክራቲተስ የተባለ የባሕታውያን ኑፋቄ የመሠረተ ወይም ከዚህ ኑፋቄ ተከታዮች ጋር መቀራረብ የጀመረ ይመስላል። የዚህ ኑፋቄ ተከታዮች ራስን በመግዛትና ሰውነትን በመቆጣጠር አጥብቀው ያምኑ ነበር። ከወይን፣ ከመጋባትና ንብረት ከማፍራት በመታቀብ የመናኝ ኑሮ ይኖሩ ነበር።

ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ቴሸን ከቅዱሳን ጽሑፎች ይህን ያህል የራቀበት ምክንያት ምንድን ነው? “ሰምቶ የሚረሳ” በመሆኑ ምክንያት ይሆን? (ያዕቆብ 1:23-25) ለሐሰት ትምህርቶች ጆሮውን በመስጠቱ በሰዎች ፍልስፍና ተማርኮ ይሆን? (ቆላስይስ 2:8፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:7) ከባድ በሆኑ ነጥቦች ላይ ሊሳሳት የቻለው በጊዜያዊ የአእምሮ መቃወስ የተነሳ ይሆን?

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የቴሸን የጽሑፍ ሥራዎችና ያሳለፈው ሕይወት በዘመኑ ስለነበረው ሃይማኖታዊ አመለካከት የጠለቀ ግንዛቤ ያስጨብጠናል። የዓለም ፍልስፍና የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ያህል ጎጂ ሊሆን እንደሚችልም ያሳየናል። እንግዲያው ሐዋርያው ጳውሎስ “በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር” እንድንርቅ የሰጠንን ማስጠንቀቂያ ልብ ልንለው ይገባል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:20