በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኖኅ ካሰፈረው የግል ማስታወሻ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ኖኅ ካሰፈረው የግል ማስታወሻ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ኖኅ ካሰፈረው የግል ማስታወሻ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ኢየሱስ መገኘቱን ስለሚጠቁመው ምልክትና ስለምንኖርበት ሥርዓት መደምደሚያ ትንቢት ሲናገር “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:3, 37) ኢየሱስ በጊዜያችን የሚፈጸሙት ሁኔታዎች በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ተናግሯል። ስለ ኖኅ ዘመን የሚናገረው ትክክለኛ ዘገባ ለእኛ ጠቃሚ መልእክት ይዟል።

ኖኅ ያሰፈረው የግል ማስታወሻ ያን ያህል ጠቃሚ ነው? እንደ አንድ እውነተኛ ታሪክ አድርገን ልንቀበለው የምንችለው ነው? የጥፋት ውኃው መቼ እንደደረሰ በትክክል ማወቅ እንችላለን?

የጥፋት ውኃው የተከሰተው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ታሪክ የጀመረበትን ጊዜ ወደኋላ ተመልሰን ለማስላት የሚያስችል ትክክለኛ የዘመን ቀመር ይዟል። ዘፍጥረት 5:​1-29 የመጀመሪ​ያው ሰው አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ኖኅ ልደት የሚያደርሰውን የዘር ሐረግ ይዘረዝራል። የጥፋት ውኃው የጀመረው “በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት” ነው።​—⁠ዘፍጥረት 7:11

የጥፋት ውኃው የተከሰተበትን ጊዜ ለማስላት አንድ መነሻ ነጥብ ያስፈልገናል። ለዚህም በዓለም ታሪክ ተቀባይነት ያገኘን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መጠቀም አለብን ማለት ነው። ይህን ዘገባ እንደ መነሻ አድርገን በማስላት በአውሮፓውያን አቆጣጠር የጥፋቱ ውኃ መቼ እንደተከሰተ ማወቅ እንችላለን።

እንደ መነሻ አድርገን ልንጠቀምበት የምንችለው አንደኛው ዘገባ በ539 ከዘአበ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ባቢሎናውያንን ስለማጥፋቱ የሚገልጸው ታሪክ ነው። ዲዶረስ፣ ዩሲቢየስ እና ቶለሚ በጻፏቸው ጽሑፎች እንዲሁም በባቢሎናውያን ጽላት ላይ ቂሮስ የነገሠበት ዘመን ሰፍሮ ይገኛል። ቂሮስ ባወጣው ትእዛዝ መሠረት የአይሁድ ቀሪዎች ባቢሎንን ለቅቀው ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት በ537 ከዘአበ ነው። ይህ ጊዜ ይሁዳ ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና የቆየችበት ዘመን ያበቃበትን ጊዜ የሚጠቁም ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ደግሞ ይህ ዘመን የጀመረው በ607 ከዘአበ ነው። የመሳፍንትን ዘመንና የእስራኤል ነገሥታት የገዙበትን ጊዜ በማስላት እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበት ጊዜ 1513 ከዘአበ ነው ብለን መናገር እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ቀመር ላይ ተመሥርተን 430 ዓመት ወደኋላ ብንቆጥር 1943 ከዘአበ ማለትም አብርሃም ቃል የተገባለት ዘመን ላይ እንደርሳለን። ከዚህ በመቀጠል የታራን፣ የናኮርን፣ የሴሮሕን፣ የራግውን፣ የፋሌቅን፣ የዔቦርንና የሳላን እንዲሁም “ከጥፋት ውኃ በኋላ በሁለተኛው ዓመት” የተወለደውን የአርፋክስድን የትውልድ ዘመን እናሰላለን። (ዘፍጥረት 11:10-32) በዚህ መሠረት የጥፋት ውኃው የጀመረው በ2370 ከዘአበ ነው ማለት ይቻላል። a

የጥፋት ውኃው ጀመረ

በኖኅ ዘመን የተከሰቱትን ክንውኖች ከመመልከታችን በፊት ከዘፍጥረት ምዕራፍ 7 ቁጥር 11 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 8 ቁጥር 4 ድረስ ያለውን ታሪክ ማንበቡ ጥሩ ነው። የጎርፍ መጥለቅለቅ ያስከተለውን ዝናብ በተመለከተ እንዲህ እናነባለን:- “በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት [2370 ከዘአበ] በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፣ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፣ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ።”​—⁠ዘፍጥረት 7:11

ኖኅ አንዱን ዓመት እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ባሏቸው 12 ወራት ከፍሏል። በጥንት ዘመን የዓመቱ የመጀመሪያ ወር የሚጀምረው በአውሮፓውያን አቆጣጠር በመስከረም ወር አጋማሽ ገደማ ነው። ዝናቡ መዝነብ የጀመረው “በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት” ሲሆን ኅዳርና ታኅሣሥ 2370 ከዘአበ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት አለማቋረጥ ዘንቧል።

የጥፋት ውኃውን በተመለከተ የሚከተለውን ዘገባም እናገኛለን:- “ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ አሸነፈ። . . . ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፣ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጐደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች።” (ዘፍጥረት 7:24-8:4) ስለዚህ ውኃው ምድርን ከሸፈነበት ጊዜ አንስቶ እያደር እስኪቀልል ድረስ 150 ቀናት ወይም አምስት ወራት ፈጅቷል። ከዚያም መርከቡ ሚያዝያ 2369 ከዘአበ በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠ።

አሁን ደግሞ ዘፍጥረት 8:​5-17ን እናንብብ። የተራሮቹ ራሶች ከሁለት ወር ተኩል (73 ቀናት) ገደማ በኋላ ማለትም “በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን” ተገለጡ። (ዘፍጥረት 8:5) b ከሦስት ወር (90 ቀናት) በኋላ ማለትም “በኖኅ ዕድሜ በስድስት መቶ አንድ ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን” ወይም መስከረም 2369 አጋማሽ ላይ ኖኅ የመርከቡን ክዳን አነሣ። “ውኃው ከምድር ፊት እንደ ደረቀ አየ።” (ዘፍጥረት 8:13) አንድ ወር ከ27 ቀን (57 ቀናት) በኋላ “በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን [ኅዳር 2369 ከዘአበ አጋማሽ ላይ] ምድር ደረቀች።” በዚህ ጊዜ ኖኅና ቤተሰቡ ከመርከቡ ወጡ። ስለዚህ ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡ ውስጥ የቆዩት አንድ የጨረቃ ዓመት ከአሥር ቀን (370 ቀናት) ነው።​—⁠ዘፍጥረት 8:14

ታሪካዊ ክንውኖችን፣ ዝርዝር ሁኔታዎችንና ጊዜን በተመለከተ ያገኘነው ይህ ትክክለኛ ዘገባ ምን ነገር ያረጋግጥልናል? ባገኛቸው የጽሑፍ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ የዘፍጥረት መጽሐፍን የጻፈው ዕብራዊው ነቢይ ሙሴ ያሰፈረልን ዘገባ አፈ ታሪክ ሳይሆን እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጥልናል። በዚህም የተነሳ የጥፋት ውኃው ለዘመናችን ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።

ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ጥፋት ውኃው ምን ብለዋል?

ከዘፍጥረት መጽሐፍ በተጨማሪ ስለ ኖኅ ወይም ስለ ጥፋት ውኃው የሚጠቅሱ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት:-

(1) የተለያዩ ጽሑፎችን አገላብጦ የእስራኤላውያንን የትውልድ ሐረግ የጻፈው ዕዝራ ኖኅንና ልጆቹን (ሴምን፣ ካምንና ያፌትን) ጠቅሷል።​—⁠1 ዜና መዋዕል 1:4-17

(2) ሐኪምና ወንጌላዊ የሆነው ሉቃስ የኢየሱስን የትውልድ ሐረግ ሲዘረዝር ኖኅን ጠቅሶታል።​—⁠ሉቃስ 3:36

(3) ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያን ባልደረቦቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የጥፋት ውኃን ደጋግሞ ጠቅሷል።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:5፤ 3:5, 6

(4) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኖኅ ቤተሰቡን ለማዳን የሚያስችለውን መርከብ በመገንባት ትልቅ እምነት እንዳሳየ ተናግሯል።​—⁠ዕብራውያን 11:7

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገረውን ዘገባ እውነተኛነት ስለመቀበላቸው እንድንጠራጠር የሚያደርግ ነገር ይኖራልን? እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ አድርገው እንደተቀበሉት ምንም ጥርጥር የለውም።

ኢየሱስ እና የጥፋት ውኃ

ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር ነበር። (ምሳሌ 8:30, 31) የጥፋት ውኃው ሲከሰት ተመልክቶ ስለነበር ስለ ኖኅና ስለ ጥፋት ውኃው ከሁሉ የላቀ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማረጋገጫ ይሰጠናል። እንዲህ አለ:- “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ወኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።”​—⁠ማቴዎስ 24:37-39

ኢየሱስ በዚህ ሥርዓት ላይ ስለሚመጣው ጥፋት እኛን ለማስጠንቀቅ አፈ ታሪክን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቅሳልን? በፍጹም! አምላክ ክፉዎችን እንዳጠፋ የሚገልጽ እውነተኛ ታሪክ እንደተናገረ እርግጠኞች ነን። አዎን፣ ብዙ ሰዎች በዚህ ጥፋት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሆኖም ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው በሕይወት መትረፋቸው ያጽናናናል።

“በኖኅ ዘመን” የተከሰተው ሁኔታ “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ በተገኘበት በአሁኑ ጊዜ ለሚኖሩ ሰዎች ጠቃሚ መልእክት ይዟል። ኖኅ ካሰፈረው የግል ማስታወሻ የተጠናቀረውን ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገረውን ዝርዝር ዘገባ ስናነብ እውነተኛነቱን እንድንጠራጠር የሚያደርገን ምንም ምክንያት አናገኝም። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው አምላክ ያስጻፈው ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገረው ዘገባ ለዘመናችን የሚሆን ትልቅ መልእክት ይዟል። ኖኅና ወንዶች ልጆቹ ከነሚስቶቻቸው አምላክ እነርሱን ለማዳን ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት እንዳሳዩ ሁሉ እኛም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ካሳደርን ይሖዋ ያድነናል። (ማቴዎስ 20:28) ከዚህም በላይ ኖኅ ያሰፈረው የግል ማስታወሻ እርሱና ቤተሰቡ በጊዜያቸው ከደረሰው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በሕይወት እንደተረፉ እንደሚገልጽ ሁሉ እኛም ይህ ሥርዓት ሲወድም በሕይወት ከሚተርፉ ሰዎች መካከል ለመገኘት ተስፋ ልናደርግ እንችላለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የጥፋት ውኃው የተከሰተበትን ጊዜ በተመለከተ ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 458-60 ተመልከት።

b ካይል ዴልች ኮሜንታሪ ኦን ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 148 እንዲህ ይላል:- “የተራሮቹ ራሶች ማለትም መርከቧ ያረፈችባቸው የአርሜንያ ተራራማ አካባቢዎች የተገለጡት ምናልባት መርከቧ ካረፈች ከ73 ቀናት በኋላ ሊሆን ይችላል።”

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ያን ያህል ረዥም ዕድሜ ኖረዋልን?

መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 9:29) የኖኅ ቅድመ አያት ማቱሳላ 969 ዓመት ኖሯል። ይህም በጽሑፍ ከሰፈሩት ሁሉ ረዥሙ የሰው ልጅ ዕድሜ ነው። ከአዳም እስከ ኖኅ ባለው አሥር ትውልድ ውስጥ የኖሩት ሰዎች አማካይ ዕድሜ 850 ነው። (ዘፍጥረት 5:5-31) በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች ይህን ያህል ረዥም ዕድሜ ኖረዋልን?

የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። የመጀመሪያው ሰው አዳም ለአምላክ ታዛዥ ቢሆን ኖሮ ሳይሞት ለዘላለም ይኖር ነበር። (ዘፍጥረት 2:15-17) ሆኖም አዳም በማመፁ ምክንያት ይህን መብት አጣ። አዳም 930 ዓመት ኖሮ ካረጀ በኋላ ወደተገኘበት አፈር ተመለሰ። (ዘፍጥረት 3:19፤ 5:5) የመጀመሪያው ሰው ለዘሮቹ ኃጢአትንና ሞትን አወረሰ።​—⁠ሮሜ 5:12

ቢሆንም በዚያን ዘመን የነበሩት ሰዎች ከእነርሱ በኋላ ከተወለዱት ሰዎች ይልቅ ረዥም ዕድሜ ሊኖሩ የቻሉት ለአዳም ፍጽምና ቅርብ ስለነበሩ ሊሆን ይችላል። ከጥፋት ውኃ በፊት ረዥም የነበረው የሰው ልጅ ዕድሜ ከጥፋት ውኃው በኋላ በፍጥነት ማሽቆልቆል ጀመረ። ለምሳሌ ያህል አብርሃም የኖረው 175 ዓመት ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 25:7) አብርሃም ከሞተ ከ400 ዓመታት ገደማ በኋላ ነቢዩ ሙሴ “የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፣ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 90:10) በአሁኑ ጊዜ ያለው የሰው ልጅ ዕድሜ በሙሴ ዘመን ከነበረው የተለየ አይደለም።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሥዕል]

ቂሮስ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ ካወጣበት ጊዜ አንስቶ በኖኅ ዘመን እስከደረሰው የጥፋት ውኃ ድረስ ወደኋላ ሲቆጠር

537 ቂሮስ ያወጣው ትእዛዝ c

539 ባቢሎን በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ መውደቋ

68 ዓመታት

607 ይሁዳ ባድማ ሆና የቆየችበት 70 ዓመት የጀመረበት ጊዜ

የእስራኤል አለቆች፣

መሳፍንትና ነገሥታት

የገዙባቸው

906 ዓመታት

1513 እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበት ዓመት

430 ዓመታት የእስራኤል ልጆች በግብፅ ምድርና

በከነዓን የቆዩባቸው 430 ዓመታት

(ዘጸአት 12:40, 41)

1943 ከአብርሃም ጋር የተገባው ቃል ኪዳን የጸደቀበት ዓመት

205 ዓመታት

2148 ታራ የተወለደበት ዓመት

222 ዓመታት

2370 የጥፋት ውኃው የጀመረበት ዓመት

[የግርጌ ማስታወሻ]

c ቂሮስ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ ያወጣው “በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት” ሲሆን ይህም በ538 ከዘአበ ወይም በ537 ከዘአበ መጀመሪያ ላይ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።