በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቶስ ለጉባኤዎቹ የላከው መልእክት

ክርስቶስ ለጉባኤዎቹ የላከው መልእክት

ክርስቶስ ለጉባኤዎቹ የላከው መልእክት

“በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል።”​ራእይ 2:1

1, 2. ክርስቶስ በትንሿ እስያ ለነበሩ ሰባት ጉባኤዎች ለላከው መልእክት ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?

 የይሖዋ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ነው። ክርስቶስ የራስነት ሥልጣኑን በመጠቀም በመንፈስ የተቀቡ ተከታዮቹን ያቀፈው ጉባኤ ያለ ነቀፋ እንዲሆን ምስጋና እና እርማት ሰጥቷል። (ኤፌሶን 5:​21-27) ኢየሱስ በትንሿ እስያ ለነበሩ ሰባት ጉባኤዎች የላከው በራእይ ምዕራፍ 2 እና 3 ላይ የሚገኘው ኃይለኛ ሆኖም ፍቅር የተንጸባረቀበት መልእክት ለዚህ ምሳሌ ይሆናል።

2 ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የላከውን መልእክት ከመስማቱ በፊት “በጌታ ቀን” የሚፈጸመውን በራእይ እንዲያይ ተደርጎ ነበር። (ራእይ 1:​10) ይህ “ቀን” የጀመረው በ1914 መሲሐዊው መንግሥት ሲቋቋም ነው። በመሆኑም ክርስቶስ ለጉባኤዎቹ የላከው መልእክት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ የሰጠው ማበረታቻና ምክር በዚህ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች መወጣት እንድንችል ይረዳናል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5

3. ሐዋርያው ዮሐንስ የተመለከታቸው ምሳሌያዊዎቹ “ከዋክብት፣” “መላእክት” እና “የወርቅ መቅረዞች” ምን ትርጉም አላቸው?

3 ዮሐንስ ‘በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘውንና በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች (ጉባኤዎች) መካከል የሚሄደውን’ ክብር የተጎናጸፈውን ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልክቷል። ‘ከዋክብቱ’ “የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው።” (ራእይ 1:20፤ 2:1) ከዋክብት መንፈሳዊ ፍጡር የሆኑትን መላእክት የሚያመለክቱበት ጊዜ ቢኖርም ክርስቶስ ለመንፈሳዊ ፍጡራን መልእክት ለመላክ በሰው አይጠቀምም። በመሆኑም እነዚህ “ከዋክብት” በመንፈስ የተቀቡ የበላይ ተመልካቾችን ወይም የሽማግሌዎችን አካል እንደሚያመለክቱ መረዳት ይቻላል። “መላእክት” የሚለው ቃል መልእክተኞች መሆናቸውን ያሳያል። የአምላክ ድርጅት እየሰፋ በመሄዱ ‘ታማኙ መጋቢ’ ከኢየሱስ “ሌሎች በጎች” መካከል ብቃት ያላቸውን ወንዶችም የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ሾሟል።​—⁠ሉቃስ 12:​42-44፤ ዮሐንስ 10:​16

4. ሽማግሌዎች ክርስቶስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን በትኩረት በማዳመጣቸው የሚጠቀሙት እንዴት ነው?

4 ‘ከዋክብቱ’ በኢየሱስ ቀኝ እጅ ውስጥ ናቸው ሲባል በእርሱ ሥልጣን፣ ቁጥጥር፣ ሞገስና ጥበቃ ሥር መሆ​ናቸውን ያሳያል። በመሆኑም በእርሱ ዘንድ ተጠያቂ ናቸው። ለሰባቱ ጉባኤዎች የላከውን መልእክት በትኩረት በማዳመጥ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ ይችላሉ። ደግሞም ሁሉም ክርስቲያኖች የአምላክ ልጅ የሚናገረውን ማዳመጥ አለባቸው። (ማርቆስ 9:​7) ክርስቶስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን በትኩረት በማዳመጥ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

በኤፌሶን ወዳለው መልአክ

5. ኤፌሶን ምን ዓይነት ከተማ ነበረች?

5 ኢየሱስ በኤፌሶን ለሚገኘው ጉባኤ ምስጋና ብቻ ሳይሆን ተግሣጽም ሰጥቷል። (ራእይ 2:​1-7ን አንብብ።) በትንሿ እስያ ምዕራባዊ ዳርቻ በምትገኘው የንግድና የሃይማኖት ማዕከል በሆነችው በዚህች የበለጸገች ከተማ አርጤምስ ለተባለች እንስት አምላክ የቆመ ግዙፍ ቤተ መቅደስ ይገኝ ነበር። በኤፌሶን የሥነ ምግባር ብልግና፣ የሐሰት ሃይማኖትና ጥንቆላ ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም አምላክ ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያኖች በዚህች ከተማ ያከናወኑትን አገልግሎት ባርኮታል።​—⁠ሥራ ምዕራፍ 19

6. ዛሬ ያሉ ታማኝ ክርስቲያኖች በጥንቷ ኤፌሶን ከነበሩት ክርስቲያኖች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

6 ክርስቶስ የኤፌሶንን ጉባኤ እንዲህ በማለት አመስግኗል:- “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፣ እንዲሁም ሳይሆኑ:- ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ።” በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ጉባኤዎችም በተመሳሳይ በመልካም ተግባራቸው፣ በትጋታቸውና በጽናታቸው ይታወቃሉ። እንደ ሐዋርያት መቆጠር የሚፈልጉ ውሸተኛ ወንድሞችን አይታገሡም። (2 ቆሮንቶስ 11:​13, 26) በኤፌሶን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉት ታማኝ ክርስቲያኖችም ‘ክፉዎችን አይታገሡም።’ በመሆኑም የይሖዋን አምልኮ ንጽሕና ለመጠበቅና ጉባኤውን ከአደጋ ለመከላከል ሲሉ ንስሐ ከማይገቡ ከሐዲዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖራቸውም።​—⁠ገላትያ 2:​4, 5፤ 2 ዮሐንስ 8-11

7, 8. በኤፌሶን የነበረው ጉባኤ ምን ከባድ ድክመት ነበረበት? እኛስ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ማድረግ እንችላለን?

7 ይሁንና በኤፌሶን የነበሩት ክርስቲያኖች አንድ ከባድ ድክመት ነበረባቸው። ኢየሱስ “የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና” ብሏቸዋል። የጉባኤው አባላት ለይሖዋ የነበራቸውን የቀደመውን ፍቅራቸውን እንደገና ማቀጣጠል አስፈልጓቸዋል። (ማርቆስ 12:​28-30፤ ኤፌሶን 2:​4፤ 5:​1, 2) እኛም ብንሆን ለአምላክ የነበረን የቀድሞ ፍቅራችን እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ይኖርብናል። (3 ዮሐንስ 3) ቁሳዊ ሃብት ወይም ተድላ የማሳደድ ምኞትን የመሳሰሉ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ መያዝ ቢጀምሩስ? (1 ጢሞቴዎስ 4:​8፤ 6:​9, 10) ከሆነ እንዲህ ያሉትን ዝንባሌዎች አስወግደን ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ለማዳበርና እርሱና ልጁ ላደረጉልን ነገሮች የአመስጋኝነት መንፈስ ለማሳየት የሚያስችለንን መለኮታዊ እርዳታ እንድናገኝ አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል።​—⁠1 ዮሐንስ 4:​10, 16

8 ክርስቶስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን “ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ” ሲል አሳስቧቸዋል። እንዲህ ሳያደርጉ ቢቀሩስ? ኢየሱስ “አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ” ብሏል። በጎቹ በሙሉ የመጀመሪያ ፍቅራቸው ከጠፋ ‘መቅረዙ’ ወይም ጉባኤው ሕልውናውን ያጣል። እንግዲያው እኛም ጉባኤው መንፈሳዊ ብርሃን መስጠቱን እንዲቀጥል ቀናተኛ ክርስቲያኖች በመሆን በትጋት እንሥራ።​—⁠ማቴዎስ 5:​14-16

9. ለኑፋቄ ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?

9 የኤፌሶን ክርስቲያኖች ‘የኒቆላውያንን ሥራ’ መጥላታቸው የሚያስመሰግን ነበር። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሰው ሌላ ስለዚህ ኑፋቄ አመሠራረት፣ ትምህርቶችና ልማዶች ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና ኢየሱስ የሰዎች ተከታይ መሆንን አጥብቆ ስላወገዘ እኛም በኤፌሶን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ኑፋቄን መጥላት ይኖርብናል።​—⁠ማቴዎስ 23:​10

10. መንፈስ የሚናገረውን በትኩረት የሚያዳምጡ ሰዎች ምን ያገኛሉ?

10 ክርስቶስ “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” ብሏል። ኢየሱስ ምድር ሳለ ያስተማረው በአምላክ መንፈስ እየተመራ ነበር። (ኢሳይያስ 61:​1፤ ሉቃስ 4:​16-21) በአሁኑ ጊዜ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት በልጁ አማካኝነት የሚናገረውን በትኩረት ማዳመጥ አለብን። ኢየሱስ “ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ” ሲል በመንፈስ ተመርቶ ቃል ገብቷል። ይህም መንፈሱ የሚናገረውን በትኩረት የሚከተሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ባለው “በእግዚአብሔር ገነት” ወይም ይሖዋ በሚገኝበት ቦታ የማይጠፋ ሕይወት ያገኛሉ ማለት ነው። መንፈሱ የሚናገረውን የሚሰሙ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ደግሞ በገነቲቱ ምድር የሚኖሩ ሲሆን በዚያም ‘ከሕይወት ውኃ ወንዝ’ መጠጣትና በወንዙ ዳርቻ ከበቀለው ‘ከዛፉ ቅጠሎች’ ፈውስ ማግኘት ይችላሉ።​—⁠ራእይ 7:9፤ 22:1, 2፤ ሉቃስ 23:43

11. ሌሎች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

11 የኤፌሶን ክርስቲያኖች የቀድሞ ፍቅራቸውን አጥተው ነበር። ዛሬም በአንድ ጉባኤ ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢፈጠርስ? የይሖዋ ፍቅር ስለተንጸባረቀባቸው መንገዶች በመናገር ሌሎች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ በግለሰብ ደረጃ አስተዋጽኦ ማበርከት ይቻላል። አምላክ በውድ ልጁ በኩል ቤዛዊ ዝግጅት በማድረግ ላሳየን ፍቅር አመስጋኝነታችንን መግለጽ እንችላለን። (ዮሐንስ 3:​16፤ ሮሜ 5:​8) በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስንሰጥና ክፍል ስናቀርብ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የሚስማማ ከሆነ ስለ ይሖዋ ፍቅር መጥቀሳችን ተገቢ ነው። በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስንካፈል የይሖዋን ስም በማወደስ ለእርሱ ያለንን ፍቅር እናሳያለን። (መዝሙር 145:​10-13) በእርግጥም አንድ ጉባኤ የቀድሞ ፍቅሩን መልሶ እንዲያቀጣጥል ወይም እንዲያጠናክር በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።

በሰምርኔስ ወዳለው መልአክ

12. ሰምርኔስንና በዚያ የሚካሄደውን የአምልኮ ልማድ በተመለከተ ታሪክ ምን ያሳያል?

12 “ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው” የተባለው ክርስቶስ በሰምርኔስ ለሚገኘው ጉባኤ ምስጋና ልኳል። (ራእይ 2:8-11ን አንብብ።) ሰምርኔስ (በቱርክ የምትገኘው የአሁኗ ኢዝሚር) በትንሿ እስያ ምዕራባዊ ዳርቻ የምትገኝ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች ግሪካውያን ነበሩ። ሆኖም በ580 ከዘአበ ገደማ ልድያውያን ከተማዋን ደመሰሷት። የታላቁ እስክንድር ተተኪዎች ሰምርኔስን በአዲስ ቦታ ላይ መልሰው ገነቧት፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሮማ ግዛት ክፍል ሆነች። በዚህ ጊዜ ድንቅ በሆኑ ሕንፃዎቿ የምትታወቅ ታላቅ የንግድ ማዕከል ነበረች። በጢባርዮስ ቄሳር ስም የተገነባው ቤተ መቅደስ የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ማዕከል አድርጓታል። በንጉሠ ነገሥቱ አምልኮ የሚካፈሉ ሰዎች ጥቂት እጣን እንዲያጤሱና “ቄሳር ጌታ ነው” እንዲሉ ይጠበቅባቸው ነበር። ክርስቲያኖች ‘ጌታቸው ኢየሱስ ስለነበር’ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም። በዚህም ምክንያት ለመከራ ተዳርገዋል።​—⁠ሮሜ 10:​9

13. በሰምርኔስ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሆች ቢሆኑም ባለ ጠጋ የነበሩት ከምን አንጻር ነው?

13 ከዚህም በላይ በሰምርኔስ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ድሆች ነበሩ። ለዚህም የተዳረጉት በንጉሠ ነገሥት አምልኮ ባለመካፈላቸው ምክንያት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ስለተጣለባቸው ሊሆን ይችላል። በዚህ ዘመን የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮችም ተመሳሳይ ፈተና ሊያጋጥማቸው ይችላል። (ራእይ 13:​16, 17) በቁሳዊ ሁኔታ ድሆች ቢሆኑም በሰምርኔስ የነበሩ ክርስቲያኖችን የሚመስሉ ከሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ባለ ጠጋ ናቸው፤ ደግሞም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ይኸው ነው።​—⁠ምሳሌ 10:​22፤ 3 ዮሐንስ 2

14, 15. በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከራእይ 2:​10 ምን ማጽናኛ ማግኘት ይችላሉ?

14 በሰምርኔስ የሚኖሩ አብዛኞቹ አይሁዶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶችን በመከተላቸው፣ የአምላክን ልጅ አንቀበልም በማለታቸውና በመንፈስ የተቀቡ ተከታዮቹን በመሳደባቸው ‘የሰይጣን ማኅበር’ ተብለው ተጠርተዋል። (ሮሜ 2:​28, 29) ሆኖም በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በራእይ 2:​10 ላይ ከሚገኙት የክርስቶስ ቃላት ከፍተኛ ማጽናኛ ማግኘት ይችላሉ! ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፣ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፣ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።”

15 ኢየሱስ ሞት ሊያስከትልበት ቢችልም የይሖዋን ሉዓላዊነት ከመደገፍ ወደ ኋላ አላለም። (ፊልጵስዩስ 2:​5-8) በዛሬው ጊዜ ሰይጣን በመንፈስ በተቀቡት ቀሪዎች ላይ ጦርነት ቢከፍትም በቡድን ደረጃ ሲታይ የሚደርስባቸውን መከራ፣ እስራት ወይም ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ፈርተው አያፈገፍጉም። (ራእይ 12:​17) እንዲያውም ዓለምን ያሸንፋሉ። በአረማውያን የስፖርት ውድድሮች ላይ አሸናፊ የሆኑት ከሚሰጣቸው ጠፊ የአበባ ጉንጉን በተለየ ክርስቶስ ከሞት ለተነሱት ቅቡዓን ‘የሕይወትን አክሊል’ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ይህም በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት ያገኛሉ ማለት ነው። ይህ እንዴት ያለ በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ ነው!

16. በጉባኤያችን ውስጥ በጥንቷ ሰምርኔስ በነበረው ጉባኤ የተከሰተው ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ የትኛው ነው?

16 ተስፋችን በሰማይ መኖርም ሆነ በምድር በጉባኤያችን ውስጥ በጥንቷ ሰምርኔስ ከነበረው ጉባኤ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ቢፈጠርስ? ከሆነ የእምነት ጓደኞቻችን አምላክ መከራ እንዲኖር በፈቀደበት ዋነኛ ምክንያት ይኸውም አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትን በሚመለከተው አከራካሪ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንርዳቸው። ፍጹም አቋሙን ጠብቆ የሚመላለስ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ሰይጣን ውሸታም መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው ስደት ቢደርስበትም የአምላክን የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት በታማኝነት መደገፍ እንደሚችል ያሳያል። (ምሳሌ 27:​11) ሌሎች ክርስቲያኖችም ስደትን በጽናት በመወጣት ‘በዘመናቸው ሁሉ [እንዲሁም ለዘላለም ይሖዋን] ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ የማገልገል መብታቸውን’ ይዘው እንዲቀጥሉ እናበረታታቸው።​—⁠ሉቃስ 1:68, 69, 74, 75

በጴርጋሞን ወዳለው መልአክ

17, 18. በጴርጋሞን ምን ዓይነት አምልኮ ይካሄድ ነበር? በእንደዚህ ዓይነቱ የጣዖት አምልኮ ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆንስ ምን ሊያስከትል ይችላል?

17 በጴርጋሞን የነበረው ጉባኤ ምስጋና ብቻ ሳይሆን እርማትም ተሰጥቶታል። (ራእይ 2:​12-17ን አንብብ።) ከሰምርኔስ በስተ ሰሜን 80 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ጴርጋሞን ጣዖት አምልኮ የተስፋፋባት ከተማ ነበረች። ከለዳውያን አስማተኞች (ኮከብ ቆጣሪዎች) ከባቢሎን ሸሽተው በዚያ መኖር የጀመሩ ይመስላል። ሕመምተኞች የፈውስና የሕክምና የሐሰት አምላክ ወደሆነው በጴርጋሞን ወደሚገኘው ዝነኛው የኤስክሊፒየስ ቤተ መቅደስ ይጎርፉ ነበር። በጴርጋሞን ለአውግስጦስ ቄሣር አምልኮ የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ ይገኝ ስለነበር ከተማዋ “በጥንቷ የሮማ ግዛት የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ዋነኛ ማዕከል” ተብላ ተጠርታለች።​—⁠ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ 1959, ጥራዝ 17፣ ገጽ 507

18 በጴርጋሞን ዚየስ ለተባለው አምላክ የቆመ መሠዊያ ይገኝ ነበር። ከዚህም በላይ ከተማዋ ዲያብሎስ ያመነጨው የሰዎች አምልኮ የሚካሄድባት ቦታ ነበረች። በዚያ የሚገኘው ጉባኤ “የሰይጣን ዙፋን” ባለበት እንደሚገኝ መገለጹ ምንም አያስገርምም! የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚደግፍ ክርስቲያን በንጉሠ ነገሥት አምልኮ ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆኑ ሞት ሊያስከትልበት ይችል ነበር። ዛሬም ቢሆን ዓለም በዲያብሎስ የተያዘ በመሆኑ ብሔራዊ አርማዎች እንደ ጣዖት ይመለካሉ። (1 ዮሐንስ 5:​19) ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖች ኢየሱስ “በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ” ብሎ እንደጠራው ክርስቲያን ሰማዕት ሆነዋል። ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነዚህ ያሉትን ታማኝ አገልጋዮች ፈጽሞ አይረሷቸውም።​—⁠1 ዮሐንስ 5:​21

19. በለዓም ምን አድርጎ ነበር? ሁሉም ክርስቲያኖች በየትኞቹ ወጥመዶች እንዳይያዙ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል?

19 በተጨማሪም ክርስቶስ “የበለዓምን ትምህርት” በተመለከተ የተናገረው ሐሳብ አለ። ሐሰተኛ ነቢይ የነበረው በለዓም ቁሳዊ ሃብት ለማግኘት ከነበረው ጉጉት የተነሳ እስራኤላውያንን ለመርገም ጥረት አድርጓል። አምላክ እርግማኑን ወደ በረከት ሲቀይርበት በለዓም ከሞዓብ ንጉሥ ከባላቅ ጋር ተማክሮ በርካታ እስራኤላውያን በጣዖት አምልኮና በፆታ ብልግና የሚወድቁበትን ወጥመድ አዘጋጅቷል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች የበለዓምን ሴራ ለማክሸፍ እርምጃ እንደወሰደው እንደ ፊንሐስ ለጽድቅ ጥብቅ አቋም ሊኖራቸው ይገባል። (ዘኍልቍ 22:​1 እስከ 25:​15፤ 2 ጴጥሮስ 2:​15, 16፤ ይሁዳ 11) ደግሞም ሁሉም ክርስቲያኖች ጣዖት አምልኮና የፆታ ብልግና ወደ ጉባኤው ሰርጎ እንዳይገባ መከላከል አለባቸው።​—⁠ይሁዳ 3, 4

20. አንድ ክርስቲያን የክህደት አመለካከት ማስተናገድ ከጀመረ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

20 በጴርጋሞን የሚገኘው ጉባኤ በመካከሉ የሚገኙትን ‘የኒቆላውያንን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች’ በቸልታ በማለፉ ከባድ አደጋ ተደቅኖበት ነበር። ክርስቶስ ለጉባኤው “ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፣ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ” የሚል መልእክት ልኳል። መናፍቃን በክርስቲያኖች ላይ መንፈሳዊ ጉዳት ማድረስ ይፈልጋሉ። መከፋፈል የሚፈጥሩና ኑፋቄ የሚያስገቡ ሰዎች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም። (ሮሜ 16:​17, 18፤ 1 ቆሮንቶስ 1:​10፤ ገላትያ 5:​19-21) አንድ ክርስቲያን የክህደት አመለካከት ማስተናገድ ከጀመረና ይህንንም በጉባኤ ውስጥ የማስፋፋት አዝማሚያ ካለው ክርስቶስ ከሰጠው ማስጠንቀቂያ ትምህርት ማግኘት ይኖርበታል! ራሱን ከውድቀት ለመጠበቅ ንስሐ መግባትና በጉባኤ ውስጥ ካሉት ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል። (ያዕቆብ 5:​13-18) ኢየሱስ ፍርድ ለመስጠት በቶሎ ስለሚመጣ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ በጣም አስፈላጊ ነው።

21, 22. “ከተሰወረ መና” የሚበሉት እነማን ናቸው? ይህስ ምን ያመለክታል?

21 ታማኝ የሆኑ የተቀቡ ክርስቲያኖችና ከጎናቸው የሚቆሙት አጋሮቻቸው መጪውን የፍርድ ጊዜ መፍራት አይኖርባቸውም። ኢየሱስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አመራር የሚሰጠውን ምክር የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ በረከት ይጠብቃቸዋል። ለምሳሌ ያህል ዓለምን ያሸነፉ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ‘ከተሰወረው መና’ እንዲበሉ የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ “አዲስ ስም” የተጻፈበት ‘ነጭ ድንጋይ’ ይሰጣቸዋል።

22 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት በተጓዙበት ወቅት አምላክ መና መግቧቸዋል። ከዚህ “እንጀራ” ጥቂት ተወስዶ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ በወርቅ መሶብ የተደረገ ሲሆን ይህም የይሖዋን መገኘት የሚያመለክተው ተአምራዊ ብርሃን በሚታይበት በመገናኛው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ተሰውሮ ተቀምጦ ነበር። (ዘጸአት 16:​14, 15, 23, 26, 33፤ 26:​34፤ ዕብራውያን 9:​3, 4) በስውር ከተቀመጠው ከዚህ መና ማንም እንዲበላ አይፈቀድለትም። ይሁን እንጂ በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ተከታዮች ትንሣኤ በሚያገኙበት ጊዜ የማይጠፋ ሕይወት የሚላበሱ ሲሆን ይህም በምሳሌያዊ ሁኔታ “ከተሰወረ መና” እንደመብላት ተደርጎ ተገልጿል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​53-57

23. ‘ነጩ ድንጋይ’ እና ‘አዲሱ ስም’ ምን ትርጉም አላቸው?

23 በሮማ ፍርድ ቤቶች ጥቁር ድንጋይ የቅጣት ፍርድን የሚያመለክት ሲሆን ነጭ ድንጋይ ደግሞ በነፃ መለቀቅን ያመለክታል። ኢየሱስ ድል ላደረጉ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ‘ነጭ ድንጋይ’ መስጠቱ እነርሱን ቅን፣ እንከን የለሽና ንጹሕ አድርጎ እንደሚቆጥራቸው ያሳያል። በተጨማሪም ሮማውያን ድንጋዮችን ከፍተኛ ክንውኖች ወደሚካሄዱበት ቦታ እንደ መግቢያ አድርገው ይጠቀሙባቸው ስለነበር ‘ነጩ ድንጋይ’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ወደሚከናወነው የበጉ ሰርግ እንዲገቡ እንደተፈቀደላቸው ሊያመለክት ይችላል። (ራእይ 19:​7-9) ‘አዲሱ ስም’ በሰማይ በተቋቋመው መንግሥት ተባባሪ ገዥዎች በመሆን ከኢየሱስ ጋር የመኖር መብት ማግኘታቸውን እንደሚያመለክት መረዳት ይቻላል። ይህ ሁሉ በመንፈስ የተቀቡትንም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ በመያዝ በይሖዋ አገልግሎት አብረዋቸው የሚሳተፉትን ክርስቲያኖች በጣም ያበረታታቸዋል!

24. ክህደትን በተመለከተ ምን አቋም መያዝ ይገባናል?

24 የጴርጋሞን ጉባኤ በከሃዲዎች ትምህርት የመበከል አደጋ አንዣቦበት እንደነበር ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። የጉባኤያችንን መንፈሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ተመሳሳይ ሁኔታ ቢፈጠር ለክህደት ፈጽሞ ቦታ ባለመስጠት በእውነት ጎዳና መመላለሳችንን እንቀጥል። (ዮሐንስ 8:​32, 44፤ 3 ዮሐንስ 4) የሐሰት አስተማሪዎች ወይም የክህደት አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ጉባኤውን በአጠቃላይ ሊበክሉ ስለሚችሉ የኑፋቄ ትምህርት ለእውነት እንዳንታዘዝ እንዲያደርገን ፈጽሞ ባለመፍቀድ ክህደትን አጥብቀን መቃወም ይኖርብናል።​—⁠ገላትያ 5:​7-12፤ 2 ዮሐንስ 8-11

25. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ክርስቶስ ለየትኞቹ ጉባኤዎች የላከው መልእክት ይብራራል?

25 ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሿ እስያ ከሚገኙት ሰባት ጉባኤዎች መካከል ለሦስቱ የላከውን ልብ የሚነካ ምስጋናና ምክር ተመልክተናል። ሆኖም ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ለቀሩት አራት ጉባኤዎችም እንዲሁ መልእክት ልኳል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊልድልፍያና በሎዶቅያ ለሚገኙ ጉባኤዎች የላከው መልእክት ይብራራል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ክርስቶስ ለጉባኤዎቹ የላከውን መልእክት በትኩረት መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?

• አንድ ጉባኤ የቀድሞ ፍቅሩን መልሶ እንዲያቀጣጥል ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?

• በጥንቷ ሰምርኔስ የነበሩት ክርስቲያኖች በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሃ ቢሆኑም ባለ ጠጋ ናቸው ሊባሉ የሚችሉት ለምንድን ነው?

• የጴርጋሞን ጉባኤ የነበረበትን ሁኔታ በማስታወስ የክህደትን አስተሳሰብ እንዴት መመልከት ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ትንሿ እስያ

ግሪክ

ሰምርኔስ

ኤፌሶን

ጴርጋሞን

ትያጥሮን

ሰርዴስ

ፊልድልፍያ

ሎዶቅያ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እጅግ ብዙ ሰዎች” ገነት የምትሆነዋን ምድር ይወርሳሉ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ስደት ቢደርስባቸውም ዓለምን ያሸንፋሉ